እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተፈጻሚነት ያገኙ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ት/ርት ፴፭ ክ ፪

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተፈጻሚነት ያገኙ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች

የክርስቶስ ልደት

New Testament 1ወንጌላውያን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድን በተመለከተ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እያጣቀሱ ቀድሞ በነቢያቶች ተተንብዮለት የነበረው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ እንደነበር ያረጋግጣሉ፡፡ በእርግጥ በወንጌላውያኑ መካከል የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖሩም ዋናው መልእክታቸው ግን በተለያየ መልኩ የነቢያቶች ቃል በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜ እንዳገኘ ብሉይ ኪዳንን እየጠቀሱ ማሳየት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ማቴዎስ ነቢዩ ኢሳይያስን እየጠቀሰ የማርያምን የድንግልና ሕይወትና የዐማኑኤል መወለድን ቀድሞውኑ በነቢያቶች በተነገረው መሠረት ተፈጻሚነት እንዳገኘ ያስገነዝባል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከድንግል ማርያም መፀነሱን እግዚአብሔር በነቢይ እንዲህ ሲል የተናገረው እንዲፈጸም ነው፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም ዐማኑኤል ተብሎ ይጠራል በማለት ያስገነዝባል(ማቴ 1፡23)፡፡ በመቀጠልም ጌ.ኢ.ክ በትንሿ መንደር በቤተልሔም መወለዱን ቀድሞ በነቢያቶች ተነግሮ የነበረና እግዚአብሔርም በነቢያቶች የተናረውን ቃሉን ጠብቆ ተፈጻሚነት እንዳገኘ ቅዱስ ማቴዎስ ይናገራል፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጥ በይሁዳ ክፍለ አገር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም ሆይ! ከይሁዳ አገር ዋና ዋና ከተሞች ከቶ አታንሺም፤ ምክንያቱም ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ይወጣል ተብሎ በነቢዩ ሚክያስ ቀድሞ የተነገረውን የትንቢት ቃል ይጠቅሳል (ማቴ 2፡6፤ ሚክ 5፡2)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደም በኋላ ስለተከናወኑት ክስተቶች ቅዱስ ማቴዎስ ከነቢያቶች ቃል ጋር በማገናዘብ ነገሮቹ ሁሉ ቀድሞውኑ በነቢያቶች በተነገረው መልኩ ተፈጻሚነት እንዳገኙ ያስገነዝባል፡፡ ዮሴፍ ሕፃኑ ኢየሱስን ከእናቱ ጋር በመያዝ ሸሽቶ ወደ ግብጽ መሰደዱን “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ተብሎ በነቢዩ ሆሴዕ የተጻፈውን ቃል ተፈጻሚነት እንዲያገኝ እንደሆነ ቅዱስ ማቴዎስ ይገልጻል(ማቴ 2፡15፤ ሆሴ 11፡1)፡፡ በተጨማሪም ሄሮድስ የከዋክብት ተመራማሪዎች እንዳታለሉት በተገነዘበ ጊዜ በጣም ተቈጥቶ ወደ ቤተልሔምና በዙሪያዋ ወዳሉት መንደሮች ሁሉ ወታደሮቹን ልኮ ዕድሜአቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን ወንዶች ሕፃናትን እንዳስገደለ ይታወቃል(ማቴ 2፡16)፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን አሳዛኝ የሆነውን የሄሮድስ የጭካኔ ተግባር በነቢዩ ኤርምያስ የለቅሶና የብዙ ዋይታ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ ልጆችዋ ስለ ሞቱባት መጽናናት እምቢ አለች ተብሎ የተነገረውን ፍጻሜ እንዳገኘ በማመሳከር ይጽፋል(ማቴ 2፡18፤ ኤር 31፡15)፡፡ ከግብጽ የስደት ኑሮ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከማርያምና ከአሳዳጊው ከዮሴፍ ጋር ናዝሬት ውስጥ መኖሩን “ናዝራዊ ተብሎ ይጠራል” ተብሎ በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረውን የትንቢት ቃል እንዲፈጸም እንደሆነ ቅዱስ ማቴዎስ ያስገነዝባል(ማቴ 2፡23፤ ኢሳ 11፡1)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በእርግጥ ከዳዊት ዝርያዎች መካከል አዲስ ንጉሥ እንደሚነሣ ይተነብያል እንጂ “ናዝራዊ ተብሎ ይጠራል” አይልም፤ ቅዱስ ማቴዎስ ግን ይህንን ጥቅስ በመውሰድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኑሮ በናዝሬት የመሆኑ ምክንያት ለማስረዳት ይጠቀምበታል፡፡

የክርስቶስ መከራ ፣ ሥቃይና ሞት
አይሁዳውያን ከጥንት ጀምሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን መሲሕ መጥቶ እንደሚያድናቸው አምነው ቢጠብቁም ይህ መሲሕ በመከራና በሥቃይ ያልፋል የሚል እምነት ግን ፈጽሞ አልነራቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሐዋርያቶችንም ጭምር የክርስቶስ መከራና ሥቃይ የመረዳትና እንደ መሲሕ የመቀበል ችግር ስለነበራቸው ወንጌላውያን ይህንን የመከራ ጉዞ ቀድሞውኑ ነቢያቶች በተናገሩት መሠረት የተከናወነና ፍጻሜ ያገኘ መሆኑን በመግለጽ የነቢያት መጻሕትን እያጣቀሱ ያስተምራሉ፡፡ ይህንን መረዳት ያቃታቸው ደቀ መዛሙርቱ እንኳ ትተውት ወይም ከድተውት የሚሄዱበት ጊዜ እንደሚመጣ ለማስገንዘብ እረኛውን እመታለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ በማለት ነቢዩ ዘካርያስ የተናገረውን የትንቢት ቃል በመጥቀስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራቸዋል(ማር 14፡27፤ ዘካ 13፡7)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የጌ.ኢ.ክ የመከራ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ መከራ ወደ ሚቀበልበትና ወደ ሚሰቅልበት ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን ቀድሞ በነቢያቶች በተነገረው መሠረት እንደተከናወነ(ዮሐ 12፡15፤ ዘካ 9፡9)፡፡ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ከካህናት አለቆች ጋር በተስማማ ጊዜ “ሠላሳ ጥሬ ብር” ሊሰጡት ቃል እንደገቡለት ይታወቃል(ማቴ 26፡15)፡፡ ይህንን የይሁዳ የክህደት ተግባር ቀድሞውኑ በነቢያቶች የተነገረና የኢየሱስም በገንዘብ ተላልፎ መሰጠት በዚሁ በትንቢት ቃል መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማስረዳት ቅዱስ ማቴዎስ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረውን ስለዚህም ለእኔ በቂ ደመወዝ ነው ብለው የሰጡኝን ሠላሳ ብር ወስጄ በቤተ መቅደሱ የገንዘብ መቀበያ ሳጥን ውስጥ ጣልሁት የሚለውን የትንቢት ቃል ይጠቅሳል(ዘካ 11፡12)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተቸነከረ ጊዜ ሁለት ወንበዴዎች አምጥተው አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው መስቀላቸው ይታወቃል(ማር 15፡28፤ ሉቃ 22፡37)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ወይም መሲሕ ሆኖ እያለ ታድያ እንዴት ከወንበዴዎች ጋር በደረቅ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት ይችላል የሚለውን የጥርጣሬ መንፈስ ከሕዝቡ ወይም ከአድማጮቻቸው ዘንድ ለማራቅ ቅዱስ ማርቆስና ሉቃስ የነቢዩ ኢሳይያስን “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ” የሚለውን በመጥቀስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገበትን አሳዛኝ ድርጊት ቀድሞውኑ በነቢያቶች ተነግሮ የነበረ እንደሆነ ያስረዳሉ(ኢሳ 53፡12)፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ከሞተ በኋላ ከወታደሮች አንዱ ጐኑን በጦር እንደወጋውና ደምና ውሃ እንደወጣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ይነግረናል(ዮሐ 19፡37)፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከፍ ብሎ ይታይ ስለነበር የተወጋውንም ጐኑ ለሁሉም ይታይ ነበር፡፡ ይህንንም ድርጊት በነቢያቶች የትንቢት ቃል መሠረት እንደተከናወነ ሲገልጽ “ያንን የወጉትን ያዩታል” የሚለውን የነቢዩ ዘካርያስ የትንቢት ቃል በመጥቀስ ያስገነዝባል(ዘካ 12፡20)፡፡
በአጠቃላይ ወንጌላውያን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ፣ ሥቃይና ሞት ቀድሞውኑ በነቢያት ተነግሮለት የነበረ መሆኑን በመግለጥ ክርስቶስ እውነተኛው መሲሕና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በተለያየ መልኩ ገልጸውታል፡፡ በተለይም በትንቢተ ኢሳይያስ 53 ላይ የተገለጸው “የሚሠቃየው አገልጋይ” እና በመዝሙረ ዳዊት 22 ላይ የሚገኘውን “የሐዘን ጩኸት” የሚያሰማውን “ሥቃይተኛው” ማንነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ቀድሞ የተነገረለት እንደነበር ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ የነቢያቶችም የትንቢት ቃል በክርስቶስ እንደፈጸመና ሕዝቡም ይህንን መሲሕ ተቀብለው እንዲያምኑ በተለያየ መልኩ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር ተግባሩን በሚወጣበት ጊዜም ቀድሞ በነቢያቶች የተነገሩትን የትንቢት ቃላት እየጠቀሰ በትምህርቱ ውስጥ እሱ ራሱ እንደ ነቢይ በቅርብ ወይም በወቅቱና ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮች እየተናገረ እንዳስተማረ ከወንጌላት እንረዳለን፡፡ በእርግጥ ቀድሞ ነቢያቶች ከተናገሩት የትንቢት ቃል ወይም ካስተማሩት ትምህርት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየጠቀሰ ወይም ቀድሞ በነቢያቶች እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? በማለት አስተምሯል ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል (ኢሳ 56፡7፤ ኤር 7፡11፤ ማር 11፡17)፤ እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም (ሆሴ 6፡6፤ ማቴ 9፡13)፣ ጌታ ሆይ ! ምስክርነታችንን ማን አመነ? የእግዚአብሔር ክንድ ለማን ተገለጠ የሚሉት ይገኙበታል(ኢሳ 53፡1፤ ዮሐ 12፡38)፡፡ እንደ ትንቢት ከተናገራቸው ውስጥ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በሙሴ ሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል፤ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ይታያል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በዓለም መጨረሻ ስለሚሆኑት ነገሮች የተነበየውንም ይጠቀሳል(ማቴ 25፡31-46)፡፡ ከእነዚህ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንቢት ቃላት ውስጥ ፍጻሜያቸውን ያገኙና ገና ወደ ፊት ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁ እንዳሉም ግልጽ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማየት ያለብን ዋናው ነገር ጌ.ኢ.ክ ነቢያቶች ቀድሞ የተናገሩትን መጥቀሱና ትንቢት መናገሩ ሳይሆን የነቢይነት ተግባር በብሉይ ኪዳን ያበቃለትና የተቋረጠ የአገልግሎት ተግባር ሳይሆን የነበረ፣ ያለና በዘመናችንም የሚቀጥል በእግዚአብሔር ጥሪ ለአገልግሎት በተሰማሩት ሁሉ የሚከናወን የተቀደሰ የአገልግሎት ተግባር ነው፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ
የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ
ትምህርት ሦስት በዚሁ ተጠናቀቀ፡፡ ቀጣይ ትምህርት ማለትም ክፍል አራት የሚሆነው በአዲስ ኪዳን ዙሪያ ላይ ነው፡፡ የሥራችን ሁሉ ባለቤት የሆነውንና ዘወትር በምናከናውነው ተግባር ሁሉ የሚረዳን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! አሜን፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት