የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ የንባብ ፡ ቁልፎች
- Category: የዮሐንስ ወንጌል 6፡1-15 ጥናት
- Published: Friday, 29 July 2011 10:05
- Written by Super User
- Hits: 3470
- 29 Jul
የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ የንባብ ፡ ቁልፎች
ከዚህም ፡ በፊት ፡ በዚሁ ፡ ጋዜጣ ፡ ላይ ፡ ለመግለጽ ፡ እንደሞከርነው ፡ አንድን ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ በምናነብበት ፡ ጊዜ ፡ በመጀመርያ ፡ እይታ ፡ ወይም ፡ በምናደርገው ፡ የአንድ ፡ ዙር ፡ ተራ ፡ ንባብ ፡ ምሥጢሩን ፡ ወይም ፡ ማስተላለፍ ፡ የፈለገውን ፡ ትክክለኛውን ፡ መልእክቱን ፡ በሚገባ ፡ ለመረዳት ፡ ሊያዳግተን ፡ ስለሚችል ፡ የወንጌሉን ፡ መልእክት ፡ በሚገባ ፡ ለመረዳት ፡ ማስተዋልና ፡ ማድረግ ፡ ከሚያስፈልጉን ፡ ነገሮች ፡ ውስጥ ፡ ጥቂቶቹን ፡ በድጋሚ ፡ እናስታውስ ፡፡
- የወንጌሉን ፡ ክፍል (ዮሐ 6 ፡ 1-15) በማስተዋል ፡ ደጋግሞ ፡ በሚገባ ፡ ማንበብ ፡፡ ወንጌሉን ፡ በምናነብበት ፡ ጊዜ ፡ ስለምን ፡ እንደሚያወራና ፡ ትኩረቱ ፡ ምን ፡ ላይ ፡ እንደሆነ ፡ በጥንቃቄ ፡ መከታተል ፡፡ በተጨማሪም ፡ ወንጌሉን ፡ የሚያወራው ፡ ስለ ፡ አንድ ፡ አርእስት ፡ ብቻ ፡ ነው ፡ ወይስ ፡ ሌሎችም ፡ አሉ ፤ ካሉስ ፡ ከአንዱ ፡ አርእስት ፡ ወደ ፡ ሌላው ፡ እንዴት ፡ ነው ፡ የሚሸጋገረው ፤ እንዲሸጋገርስ ፡ ምክንያት ፡ የሆነው ፡ ምንድን ፡ ነው ፤ ለምሳሌ ፡ ስለ ፡ ፍቅር ፡ እያስተማረ ፡ እያለ ፡ እዛው ፡ ላይ ፡ ስለ ፡ እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ ማውራት ፡ ይጀምራል ፡፡ በዚህ ፡ ጊዜ ፡ ታድያ ፡ የንግግሩን ፡ አርእስት ፡ እንዲቀይር ፡ ምክንያት ፡ የሆነው ፡ የሕዝቡ ፡ ረሃብ ፡ ወይም ፡ ጥማት ፡ ሊሆን ፡ ይችላል ፡፡ ስለዚህ ፡ ይህንን ፡ በማስተዋል ፡ ማየት ፡፡
- ወንጌሉን ፡ በምናነብበት ፡ ጊዜ ፡ ታሪኩ ፡ ውስጥ ፡ የሚንጸባረቁት ፡ ዋና ፡ ዋና ፡ ገጸ ፡ ባሕርያት ፡ በማስተዋል ፡ መመልከት ፡ ወይም ፡ በደንብ ፡ ለይቶ ፡ ማወቅ ፡፡ ይህም ፡ ታሪኩ ፡ በማን ፡ ዙርያና ፡ ትኩረቱ ፡ ማንን ፡ ወይም ፡ ምን ፡ ላይ ፡ እንዳደረገ ፡ የበለጠ ፡ ለመረዳት ፡ ይጠቅማል ፡፡ ለምሳሌ ፡ በዮሐ 6 ፡ 1-15 ጌ. ኢ. ክ ፣ ሕዝቡና ፡ ሐዋርያቶች የድርጊቱ ፡ ዋና ፡ ዋና ፡ ገጸ ፡ ባሕርያቶች ፡ ሆነው ፡ ይገኛሉ ፡፡
- ታሪኩ ፡ ምን ፡ ጊዜና ፡ የት ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ እየተከናወነ ፡ መሆኑን ፡ በደንብ ፡ በማስተዋል ፡ መመልከት ፡፡ ድርጊቱ ፡ እየተከናወነ ፡ ያለው ፡ ጸሎት ፡ ቤት ፡ ውስጥ ፡ ነው ፣ ባሕር ፡ አጠገብ ፡ ነው ፣ ገለልተኛ ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ነው ፣ ተራራ ፡ ላይ ፡ ነው ፣ ኢየሩሳሌም ፡ ውስጥ ፡ ነው ፡ ወይስ ፡ ገሊላ ፡ አውራጃ ፣ ወይስ ፡ ጌ.ኢ.ክ ፡ ከገሊላ ፡ ወደ ፡ ኢየሩሳሌም ፡ ያደርገው ፡ በነበረው ፡ ጉዞ ፡ ላይ ፡ ነው ፡፡ ያንን ፡ ቦታ ፡ ላይ ፡ ከዚህ ፡ በፊት ፡ ለምሳሌ ፡ በብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ውስጥ ፡ አንድ ፡ ድርጊት ፡ የተከናወነበት ፡ ወይም ፡ ትንቢት ፡ የተነገረለት ፡ ወይም ፡ ከሕዝቡ ፡ ማህበራዊና ፡ ታሪካዊ ፡ አኗኗር ፡ ጋር ፡ በተያያዘ ፡ መልኩ ፡ የራሱ ፡ የሆነ ፡ ሌላ ፡ መልእክት ፡ ሊያስተላልፍ ፡ ስለሚችል ፡ በደንብ ፡ መታየት ፡ አለበት ፡፡ ጊዜውስ ፡ ጠዋት ፣ ቀትር ፣ ማታ ፣ ክረምት ፣ በጋ ወይስ ፡ በፋሲካ ፡ ወቅት ፡፡
- እነዚህን ፡ ነገሮች ፡ ግንዛቤ ፡ ውስጥ ፡ በማስገባት ፡ ካነበብነው ፡ ወይም ፡ ካጠናነው ፡ በኃላ ፡ ከታሪኩ ፡ በፊትና ፡ በሁዋላ ፡ ያለውን ፡ የንባብ ፡ ክፍል ፡ በማንበብ ፡ ከታሪኩ ፡ ጋር ፡ የተያያዙ ፡ ወይም ፡ ምንም ፡ ግኑኝነት ፡ የሌላቸው ፡ መሆኑን ፡ በደንብ ፡ መረዳት ፡፡ ለምሳሌ ፡ በምናጠናው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል (ዮሐ 6 ፡ 1-15) ከሆነ ፡ ዮሐ 5 የመጨረሻው ፡ ከፍል ፡ ምን ፡ ላይ ፡ እንደሚያተኩርና ፡ ከዮሐ 6 ፡ 15 ጀምሮ ፡ ያለው ፡ ስለምን ፡ እንደሚያወራ ፡ በማስተዋል ፡ መመርመርና ፡ የሚገናኙበት ፡ ነጥብ ፡ ካለ ፡ አስተውሎ ፡ በማየት ፡ የበለጠ ፡ ለመረዳት ፡ መሞከር ፡ የራሱ ፡ የሆነ ፡ ጠቀሜታ ፡ አለው ፡፡
- የምናነበው ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ በሌሎች ፡ ወንጌላውያን ፡ በድጋሚ ፡ ተጽፎ ፡ ከሆነ ፡ እነሱ ፡ ከጻፉት ፡ ታሪክ ፡ ጋር ፡ በምን ፡ እንደሚመሳሰልና ፡ ልዩነቱስ ፡ ምኑ ፡ ላይ ፡ እንደሆነ ፡ ለይቶ ፡ መረዳት ፡ ያስፈልጋል ፡፡ ለምሳሌ ፡ ዮሐ 6 ፡ 1-15 በማትዮስ ፣ በማርቆስና ፡ በሉቃስ ወንጌሎች ፡ ውስጥ ፡ ተጽፎ ፡ ስለሚገኝ ፡ አራቱም ፡ እያመሳከርን ፡ የእያንዳንዳቸው ፡ ትኩረት ፡ ምን ፡ ላይ ፡ እንደሆነና ፡ ለምንስ ፡ ትኩረታቸው ፡ እዚያ ፡ ነገር ፡ ላይ ፡ ማረግ ፡ እንደፈለጉ ፡ ለመረዳት ፡ መሞከር ፡፡ በዚህ ፡ ታሪክ ፡ ውስጥ ፡ ቅዱስ ፡ ዮሐንስ ፡ የሐዋርያቶች ፡ ሥም ፡ እየጠቀሰ ፡ ከኢየሱስ ፡ ሲወያዩ ፣ ወቅቱም ፡ የፋሲካ ፡ ጊዜ ፡ እንደነበር ፣ አምስት ፡ እንጀራና ፡ ሁለት ፡ ዓሣ ፡ የያዘ ፡ ልጅ ፡ እንደተገኘ ፣ ኢየሱስ ፡ እራሱ ፡ እንጀራውና ፡ ዓሣዎቹ ፡ እንዳከፋፈለና ፡ በመጨረሻም ፡ ሕዝቡ ፡ ኢየሱስን ፡ ሊያነግሡት ፡ እንደፈለጉ ፡ ትኩረት ፡ ሰጥቶ ፡ ይተነትነዋል ፡፡ ሌሎቹ ፡ ወንጌላውያን ፡ ግን ፡ ይህንን ፡ ዝርዝር ፡ ሁሉ ፡ አይጠቅሱትም ፡፡ ታድያ ፡ ቅ. ዮሐንስ ፡ ይህንን ፡ ሁሉ ፡ መዘርዘሩ ፡ ለምን ፡ አስፈለገው ፡፡
- በተጨማሪም ፡ ይህንን ፡ የወንጌል ፡ ክፍል ፡ ቀድሞውኑ ፡ በብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ውስጥ ፡ በተለያየ ፡ መልኩ ፡ ተገልጾ ፡ ከሆነ ፡ ከዚህ ፡ በፊት ፡ የሰማናቸውን ፡ የብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ታሪኮች ፡ በድጋሚ ፡ ማሰብና ፡ ማገናዘብ ፡ ያስፈልጋል ፡፡ ይህም ፡ ማለት ፡ ቀድሞ ፡ በብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ውስጥ ፡ ስለዚያ ፡ ታሪክ ፡ ተነግሮ ፡ ወይም ፡ ተተንብዮ ፡ ከሆነ ፡ ከዚህኛው ፡ ታሪክ ፡ ጋር ፡ ምን ፡ ግኑኝነት ፡ ሊኖረው ፡ እንደሚችል ፡ ማስተዋል ፡፡ ለምሳሌ ፡ ዮሐ 6 ፡ 1-15 በምናይበት ፡ ጊዜ ፡ የፋሲካ ፡ በዓል ፡ በደረሰ ፡ ጊዜ ፡ ኢየሱስ ፡ ወደ ፡ ተራራ ፡ ወጣ ፤ ከዚያም ፡ ሕዝቡ ፡ ያልነበራቸውን ፡ እንጀራና ፡ ዓሣ ፡ እንዲመገቡ ፡ አደረጋቸው ፡ ሲል ፡ በብሉይ ፡ ኪዳን ፡ ውስጥ ፡ ሙሴ ፡ ከፋሲካ ፡ በዓል ፡ በፊት ፡ ወደ ፡ ተራራ ፡ መውጣቱንና ፡ በምድረ ፡ በዳ ፡ ከእግዚአብሔር ፡ ዘንድ ፡ መና ፡ እንዲወርድላቸው ፡ ማድረጉን ፡ የሚገልጸውን ፡ ታሪክ ፡ ለማገናዘብ ፡ መሞከር (ዘጸ 16 ፡ 4) ፡፡ ወይም ፡ ነብዩ ፡ ኤልሳ ፡ በሃያ ፡ የገብስ ፡ ሙልሙልና ፡ በጥቂት ፡ የእ ሸት ፡ ዛላዎች ፡ ብዙዎችን ፡ ከመገበ ፡ በሁዋላ ፡ ብዙ ፡ የተረፈ ፡ ምግብ ፡ መሰብሰቡን ፡ የሚተርከው ፡ የመጽሐፍ ፡ ቅዱስ ፡ ክፍል ፡ ጋር ፡ በማዛመድ ፡ ለመረዳት ፡ መሞከር (2 ነገ 4 ፡ 42-44) ፡፡