እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጽሑፎቹና መልእክቶቹ

ሀ - ጽሑፎቹ

 

መቅድም ስለ መልእክት ትርጉም

ወደ ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች ከመግባታችን በፊት በዘመኑ የነበሩ የአጻጻፍ ዘይቤዎችን መመልከት ተገቢ ነው። ምክንያቱም ጳውሎስ የተመረጠ የአምላክ አገልጋይ፣ ሐዋርያ ይሁን እንጂ የጊዜው ሰው እንደመሆኑ መጠን የጊዜውን አደራረግ እንደሚያጸባርቅ ግልጽ ነው። ስለዚህ የጳውሎስን መልእክቶች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የአዲስ ኪዳን መልእክቶችን በደንብ ለመረዳት የጊዜውን የአጻጻፍ ዘይቤ ጠቅላላ እውቀት ሊኖረን ይገባል።

1.   መልእክት እንደ ሥነጽሑፍ - በጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ በመልእክት መልክ ሐሳብህን መግለጽ የተለመደ ነገር ነበር። በጥንታዊ ግሪክና ላቲን ጽሑፎች እንደ መልእክት የሚታወቁ እስከ 14,000 የሚደርሱ ጽሑፎች አሉ። ጥንታውያን ግብጻውያን ለመጻፍ የሚጠቀሙበት ‘ፓፓይረስ’ (እንደ ወረቀት ለጽሑፍ ያገለግል የነበረ ቄጤማ ከሚመስል ተክል የሚዘጋጅና በጥንታዊቷ ግብጽ ይዘወተር የነበረ ነው) ላይ የተጻፉ መልእክቶች አሉ። ትንሹ 18 ቃላቶች ሲሆን ረጅሙ ደግሞ 200 ቃላቶችን የያዘ ነው። የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ግን ከዚህ ሰፋና ረዘም ያሉ ናቸው።

በጥንት ጊዜ የሚጻፉ መልእክቶች ብዙውን ግዜ በትትልቅ ሰዎችና በባለስልጣኖች ስለሆነ ላኪው (ደራሲው) የሚጽፈው ሳይሆን ጸሐፊው ነው። እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጸሐፊው ቃል በቃል የተባለውን ነው የሚጽፈው ወይስ የላኪውን ሐሳብና ፍላጎት ካወቀ በኋላ ራሱ ነው አቀነባብሮ የሚጽፈው? የአዲስ ኪዳን መልእክቶችንም በሚመለከት እንደዚህ አይነት ጥያቄ እናገኛለን። ለምሳሌ፤ ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ራሱ በማቀናበር ነው ወይስ የተባለውን እንዳለ በመድገም ነው የጻፈው?

2.   የአጻጻፍን ሥርዓትና መዋቅር በሚመለከት መጀመርያ መግቢያ - ስላምታ፣ የላኪና የተቀባይ ማንነት፣ ስምና ሹመትን ያካትታል። በመጨረሻ ላይ ደግሞ እንደ መደምደሚያ (መዝጊያ) - ሰላምታ፣ በእውነት የላኪው መሆኑን የሚገልጹ ቃላት፣ አንዳንድ ሓሳቦችና ስሞች ይገኙበታል። በነዚህ መሐል ላይ የሚገኘው ደግሞ የመልእክቱ ዋና ሐሳብና ይዘቱ የሚዘረዘርበት ነው።

3.   እኛ በቋንቋችን ሁሉንም መልእክት ብለን ነው የምንጠራው። እኛ መልእክት ብለን የምንጠራው በእንግሊዘኛ “Letter” ወይም “Epistle” ተብሎ ይጠራል። የመጀመርያው በልዩ ጉዳይ፣ ለልዩ ሰው ወይም ማኅበር (ቡድን) ሲጻፍ፤ ሁለተኛው ግን ሰፋ ያለ ሆኖ ብዙ ሰዎችን ያቀፈ ወይም ማንኛውንም አንባቢ ግምት ውስጥ ያስገባ ሲሆን ይዘቱ እንዲሁ ሰፋ ያለ ነው።

4.   የጳውሎስ መልእክቶች ብዙውን ጊዜ “Letter” በሚለው ቃል ነው የሚታወቁት፤ ተገቢም ነው። ወደ ፊልሞና ከተጻፈው መልእክት በስተቀር ሁሉም መልእክቶች ናቸው። ወደ  ዕብራውያን የተጻፈው ትምህርተ መለኮትን የሚተረትንና ጠለቅና ረቀቅ ያለ ጽሑፍ ሲሆን፤ የያዕቆብ መልእክት የምክርና የተግሳጽ ዝንባሌ ያለው፣ 1ኛ ና 2ኛ ጴጥሮስ እንዲሁም 1ኛ ዮሐንስ የስብከት ዘይቤ የተከተሉ ናቸው።

 

የጳውሎስ መልእክቶች

 

መቅድም፣ የመልእክቶቹ ብዛትና የጠፉ መልእክቶች

 

ከአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ውስጥ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፤ ቤተክርስቲያን ያጋጠሟትን ሁኔታዎች ተከትሎ በሐዋርያው የተጻፉ ናቸው። እነዚህ መልእክቶች ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የጻፈው ስለሆነ፤ እንደ አንድ ፈላስፋ ወይም አስተማሪ ሊታይ አይችልም። ጳውሎስ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው፤ መልእክቱም የእግዚአብሔር ነው። ጳውሎስ ይህንን እውነታ ስለተረዳ የወንጌልን መልእክት ልክ እንደ አደራ ንብረት በታማኝነት ለማዳረስ የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል።

በተለምዶ እንደምናውቀው ጳውሎስ 14 መልእክቶችን ነው የጻፈው። በ1ቆሮ. 5፤9-11 ላይ ጳውሎስ ከዚህ በፊት ሌላ ምልእክት ጽፎ እንደነበር ያመለክታል። እንዲሁም በፊልጵስዩስ 3፤1 “ከዚህ በፊት የጻፍሁላችሁን ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አያሰለቸኝም” ሲል ከዚህ በፊት ጽፎ እንደነበርና፤ እንደገና ነገሩን እንደ አዲስ ሊያነሳው የፈለገ ይመስላል። በቆላ. 4፤16 ወደ ሎዶቂያ ሰዎች መልእክት ጽፎ እንደነበር፤ የቆላስያስ ሰዎችም ይህንኑ መልእክቱን ከነሱ ተቀብለው እንዲያነቡት፤ ለነርሱ የተጻፈውን መልእክት ደግሞ ወደ ሎዶቂያ እንዲልኩት አደራ ሲላቸው ይታያል።

እነዚህ መልእክቶች ምንም ሳያገለግሉ፤ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች በአንድ ላይ ሳይጠረዝ፣ ሳይነበብና ወደ ተቀባዮቹ ሳይደርስ የጠፉ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የጻፋቸው መልእክቶች ዛሬ ቢገኙ ምን ይሆናል? ቤተክርስትያን በቀኖናዊ መጻሕፍት ታስገባቸዋለች? እነዚህንስ ለማግኘት ምን የሚደረግ ጥረት አለ? የሚል በ “ቢገኝ፣ ቢ ፣ ቢ” ላይ የተመሰረተ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ወይም ቀኖና የተወሰነ ስለሆነ፤ አሁን በሚገኙ አዲስ ግኝቶች ይቀያየራል ማለት አይቻልም። እነዚህ ጽሑፎች ከመጀመርያውኑ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ እንደሆኑ የታወቀ ነው። ዓላማው ለ/ስለ መጻፍ ሳይሆን፤ ወደ ማኅበረ ክርስትያኑ ደርሶ፣ እምነታቸውን ሊያጠነክር፣ ተስፋንና ፍቅርን ሊያሳድግ፣ ማኅበረ ክርስቲያኑንና እያንዳንዱ አባሎቿን ሊያበረታታና እንዲያንጽ በማለት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሲመጣ እንደ ሰሚው ሲሆን፤ ሲጻፍ ደግም እንደ አንባቢው ነው። ስለዚህ እነዚህ መልእክቶች ግባቸውን ያልመቱ፣ ሳይሰሙና ሳይነበቡ መንገድ ላይ የጠፉ ናቸው። በተቃራኒው እነዚህ አሁን የምንጠቀምባቸው መልእክቶች ግን ግባቸውን መተው፤ በእነሱ በታነጹ በመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች እንደ ክቡር የእምነት ሃብት በጥንቃቄ ተጠብቀው የቆዩ ናቸው። ስለዚህ እዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልገቡ ጽሑፎች ዛሬ በአርኪዮሎጂ ጥናት ቢገኙ ለጥናት ለምርምር አይጠቅሙም አይባልም። እንደ ክርስቲያንዊ ሃብት ይያዛሉ፤ በቀኖናዊ መጻሕፍት ማለትም ዛሬ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ብላ ለይታና ወስና ከያዘቻቸው መጽሐፍት ውስጥ ግን አይገቡም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት