እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ልደት ሠርክ-አዲስ ነው!

ልደት ሠርክ-አዲስ ነው!

Christmas 2014 ecየጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እያንዳንዳችን በቅድስት ሥላሴ አርአያ እና አምሳል የመፈጠራችን ምስክርነት መገለጥ ነው። በዘላለማዊ አርምሞ ውስጥ የሚኖር አምላክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሁሉም በሁሉምየተናገረው፣ጸጋእና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን ያደረው ቃል "ሰው" የሆነበት ምሥጢር ቅድስት ሥላሴን የምንመስልበት እውነተኛው መልካችን መገለጥ ነው ።

እግዚአብሔር አምላክ እጅግ ስላፈቀረን ያደረገልን መልካም ነገር ሁሉ፣ ያለበሰን ክብር ሁሉ፣ የሰጠን ሕይወትም ሁሉ እርሱ ስለእኛ ያለውን ፍቅር እንደ ልቡ መሻት ጥሙን ሊቆርጥለት ስላልቻለ ከነገር ሁሉ በላይ በቃላትም ሊገለጽ በማይችል ፍቅርና ትህትና ከኃጢአት በስተቀር በሁሉ ነገር እንደ እኛ ሰው ሆነ።

የፍጥረት ሁሉ ባለቤት በተፈጥሮ ውስጥ፣ ጊዜ የማይገድበው የዘመናት ሁሉ ባለቤት እርሱ እንደ እኛ ለመሆን በወደደበት ትህትና ዘመን ተቆጠረለት። እርሱ ሰው የሆነው ከእርሱ ጋር እንዲሁም ከራሳችን ጋር ፍጹም በሠመረ ተግባቦት ኅብረት እንዳናደርግ የሚለየንን ነገር ሁሉ ከእኛ ለማስወገድ እና ከእኛ ጋር በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ገበታ ለመቅረብ ነው። አምላክ ሰው ሆኖ እንደ እኛ በምድር ላይ በመመላለሱ እኛም ደግሞ ሰው ሆኖ ከተገለጠው ከእርሱ "ሰው" መሆን ምን ማለት እንደሆነ እንማር ዘንድ እነሆ ጌታ ሰው የመሆን ምሥጢር ምልዓትና አብነት ሆኖ ተገልጧል።

እርሱ ከኃጢአት በስተቀር በሁሉ ነገር እንደ እኛ ሰው የሆነበትን የቃልን ሥጋ መሆን ምስጢር ስናከብር እኛም በሁለንተናችን ለእግዚአብሔር እንሆን ዘንድ መለየታችንን እያከበርን ነው። ሰው ሆነን በመፈጠራችን ቁምነገር ውስጥ የእግዚአብሔር ያልሆነ ምንም የእኔነት ጥግ የለንም። ሁለንተናችን የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና ለእግዚአብሔር ያልተፈቀደ የእኔ ብቻ የሆነ "ሰው" ነት የለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ቁምነገር ሲመሰክር "...ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?"
(1ኛ ቆሮ 4:7) ይላል። 

ሰው የመሆን ምስጢር የእግዚአብሔር በመሆንና የእግዚአብሔር እንደሆነ ሰው በመመላለስ ወደ ምልዓት የሚደርስ ጉዞ ነው። ፍጻሜውም ሰው ሆኖ የተገለጠው ጌታ በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው በአብ ቀኝ የሆነበት ክብር፤ የድል አድራጊዎች ሰማዕታት የቡሩካን ጻድቃን የክብር ሥፍራ ነው።

በዚህ ሥፍራ ከእርሱ ጋር በአባቱ መንግሥት ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ ጌታ "እኔን ምሰሉ" (ዮሐ 13: 15) እያለ የእርሱን አብነት እንድንከተል ይጋብዘናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበኩሉ በአዲስ ሕይወት መመለስ ባገኘው ጸጋ በሁሉ ነገር ለጌታ ከሆነ በኋላ "እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንም እኔን ምሰሉ" (1ኛ ቆሮ 11:1) እያለ ያበረታታናል። ደግሞሙ ወደ ተሰሎንቄ ክርስትያኖች በላካት የመጀመርያይቱ መልእክቱ 1ተሰ 1:6 ላይ "እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤" እያለ ልንከተለው የሚገባንን መንፈሳዊ አብነት ይጠቁመናል። በእርግጥም እያንዳንዱ ክርስትያን በምስጢረ ጥምቀት አማካኝነት ''ክርስትያን" ተብሎ ከክርስቶስ ስም ጋር እንዲሁም ከክርስቶስ ሕይወት ጋር የተሳሰረ ማንነት አለው። በመሆኑም ስሙ በነፍሳችን ላይ የተጻፈብን፤ ሕማሙ፣ ሞቱ እና ትንሳኤው በነፍሳችን ላይ የታተመብን በመሆኑ ለሌላ ለማንም ሳይሆን ለእርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ተቀድሰናል።

ነገር ግን ክርስቶስን መከተል ወይም ክርስቶስን መምሰል ማለት ምን ማለት ነው? ክርስቶስን መከተል ወይም ክርስቶስን መምሰል ማለት እርሱ በዚህ ምድር ሲመላለስ ያደረገውን ነገር ማድረግ ማለት አይደለም! ይልቁንም እርሱ በእውነት የሆነውን መሆን ማለት ነው፤ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! በዚህ ምድር በሥጋ ተገልጦ በተመላለሰበት ጊዜ የፈጸመዉ ነገር ሁሉ ከማንነቱ ማለትም የእግዚአብሔር ልጅ ከመሆኑ ቁምነገር የሚመነጭ ነው።  በመሆኑም የእርሱ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን እርሱ ያደረገውን ነገር በሚገባ እና እርሱ በተገለጠበት ግብረገብ ልክ ለመመላለስ እርሱ የሆነውን ለእኛም በስሙ ለምናምን እንሆነው ዘንድ ባለመብት ያደረገንን (ዮሐ 1:12) ይኸውም የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን መገኘት ይኖርብናል። በምስጢረ ጥምቀት አማካኝነት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እርሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባዘዘንና ባስተማረን መሠረት (ዮሐ 3: 3-5) በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው ተካፋዮች ሆነን፤ ሙሽራዬ እያለ ከሚጠራት ራሱንም ስለእርሷ አሳልፎ ከሰጣት (ኤፌ 5: 25-26) ከቤተክርስትያን ማኅጸን ዳግም በመወለዳችን የጌታ ወንድሞችና እኅቶች፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሶች፣ የእግዚአብሔር አብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሆነናል! የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘነው የአብ አንድ ልጅ ከሆነው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት በኩል ነው። ስለዚህም እንደ ባርያ ሳይሆን እንደ ልጅ በመኖር ክርስቶስ ያደረገውን ሳይሆን ክርስቶስ የሆነውን በመሆን ያደረገውን እንድናደርግ ተጠርተናል። ይህም ጥሪ የጌታን ልደት ለምናከብር ለእኛ በየዕለቱ ከአሮጌው ሰው መላቀቅና በየዕለቱ ከአዲሱ ሰው ጋር የመጣበቅ ጥሪ ነው (ኤፌ 4:22-25)።  ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ነጻነት ቀድሞ ለታሰርንበት ሕግ ስለሞትን ከሕግ ተፈትተናል። በመሆኑም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ ተመልሰን አንጠመድም (ሮሜ 7:6)።

እያንዳንዱ ክርስትያን በሥርዐተ አምልኮ ውስጥ ባለው ቅዱስ ቁርባናዊ ሱታፌ አሁን እንኳን በዚህ ምድር ሳለ በምስጢረ ጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በመቀደሱ ምክኒያት ተስፋ ከሚያደርገው ከቅድስት ሥላሴ ሕይወት ይካፈላል። በዚህም በመለኮታዊ መልክ እያደገና እየበሰለ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እየመሰለ ያድጋል። ኢየሱስን በድርጊቱ ብቻ ሳይሆን ሥራውንና አገልግሎቱን ሁሉ ፍጹም በሚያደርግበት በማንነቱ ያውም በአምላክ ልጅነቱ እንመስለው ዘንድ በቅዱስ ሥጋው እና በክቡር ደሙ ነፍሱንና መለኮቱን ጭምር አስተባብሮ ሰጥቶናል!።

ቤተክርስቲያን በምስጢራት በኩል የምትከፍትልን በር እና የምታሳየን መንገድ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለን ቁርባናዊ ትሥሥር እና ወዳጅነት ወደ ቅድስት ሥላሴ ልብ የምናድግበት የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው። በዚህም ጉዞ ከመላይቱ ቤተክርስትያን ጋር በጋራ እየተጓዝን በቅዱሳን አብነት እና አማላጅነት ከክብር ወደ ክብር እንገለጣለን። ስለዚህም የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ እንዲህ ይላል:-
" እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።" (ዕበ12:1-2)።

በመሆኑም በእነዚህ ሁሉ ምስክሮች በታጀበ የእውነት እና የመንፈስ በሆነ ሥርዐተ አምልኮ ውስጥ ባለን ቅዱስ ቁርባናዊ ሱታፌ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንደ ልጆች እንመላለስ ዘንድ ሕጻን ተወልዶልናል። ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ "ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም" (ኤፌ 2:19)።  ስለዚህ ክርስትያን በእግዚአብሔር መንግሥት መኖር የሚጀምረው በሚመጣው ዓለም ሳይሆን በዚህ ዓለም ሳለ የሚመጣው ዓለም የክብር ነጸብራቅ በሆነችው ቤተክርስትያን ውስጥ ዛሬ በሚፈጸመው የበጉ ሠርግ አማካይነት ነው። ክርስትያን በመንግሥተ ሰማያት የሚቀጥለው የክብር ሕይወት እንጂ ከዜሮ ሀ ብሎ የሚጀምረው ሕይወት የለውም።

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የምሥራቹን ቃል ለእረኞቹ ባበሠራቸው ጊዜ "ዛሬ" እያለ ይነግራቸዋል። የመልአኩ ቃል ያቺን ምሽት የሚመለከት የጊዜ ገላጭ ሳይሆን ዘላለማዊ ዛሬ፣ አሁናዊ ዛሬ፣ ሥርዐተ አምልኳዊ ዛሬ፣ የጌታ ሥጋ በመካከላችን የሚቆረስበት ዛሬ ነው። ስለዚህ ልደት ዛሬ ነው! ልደት አሁን ነው! ልደት ዘላለማዊ ነው! ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን በላካት መልእክቱ ኤፌ 5:1 " እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥"
እያለ የሚጋብዘን የልደት ጥሪ ነው። የጌታ ልደት ሠርክ-አዲስ ነው!

የሰው ልጅ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን እውነተኛውን የ"ሰው"ነት ትርጉምና ውኃ ልክ አግኝቷል። ይህም "ሰው"ነት ከእግዚአብሔር ጋር በመኖር የሚረጋገጥ እውነታ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከእያንዳንዳችን ጋር አብሮ ለመኖር ሰው ለመሆን ወዷልና ዛሬም በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ይህንኑ ፍላጎቱን ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ኢየሱስም ይህንኑ ሲመሰክር "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" (ዮሐ 14:23) እያለ ያረጋግጥልናል።

ልደት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ለመኖር በመካከላችን የሚገለጥበት ብሎም ወደ እያንዳንዳችን የሚመጣበት ፍቅር ነው! ከእኔ ጋር ሊኖር የሚወድ ጌታ ዛሬ ወደ እኔ፣ ዛሬ ወደ አንተ፣ ዛሬ ወደ አንቺ፣ ዛሬ ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል። እርሱም እንዲህ ይላል " እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።"
(ራእይ 3:20) አሜን ማራናታ! ጌታ ሆይ ቶሎ ና!
መልካም የገና በዓል ያድርግልን!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት