እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ድንቅ ልውውጥ! ራሳችንን ማዳን ስለማንችል እርሱ እንደኛ ሆነልን!

ድንቅ ልውውጥ! ራሳችንን ማዳን ስለማንችል እርሱ እንደኛ ሆነልን!

Henri Nየቤተ ክርስቲያን አበው ስለክርስቶስ ልደትና የእኛ ሁኔታ ሲያስቡ በሁለታችን መካከል የተከናወነውን እውነት የሚገልጹባቸው ድንቅ ቃላት “ድንቅ ልውውጥ” የሚሉ ናቸው። ያ በሰማየ ሰማያት የሚኖር የሚባለው፡ ማንነቱ ቀርቶ ስሙ እንኳ በሰውኛ ቋንቋ መጠራት  የማይታሰብ የነበረው አምላክ በመልአክ አብሳሪነት አምላክ ሰው መሆኑ ታወጅ “እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ሉቃስ ፪፡፲፩-፲፪

የሩቅ ተብሎ የሚታሰበው አምላክ በኢየሱስ ልደት የቅርብ፣ የሚታይ የሚዳሰስ ሆነ። ይህ የመልአክ እወጃ ከባድና ለማመኑም የሚከብድ ነበር፡ ሆኖም ፍቅር ተአምር ያደርጋልና የአምላካችን ፍቅር የማይታሰበውን አደረገው፡ ሰው ሆነልን። ይህ ገራሚ እውነታ በራሱ ብዙ ሊባልለት የሚያስችል ሆኖ ሳለ፡ “ግን ለምን ሰው ሆነ?” ብለን ስናስብ ደግሞ ሌላኛው አስደማሚ እውነት ይከተላል። መልአኩ ስለ ሕፃኑ ያለው ነገር ‘መድኃኒት’ የሚል ነው። መድኃኒትነቱ ደግሞ ለእኛ ነው፡ እርሱ በእኛ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እኛን ወደርሱ ከፍ ሊያደርገን ተወለደ፡ እርሱ በከብቶች ግርግም እኛ በሰማያት ክብር! የዓለም ፈጣሪ ሥጋን ለብሶ “በዚያ ታገኙታላችሁ” ተብሎ ተነገረለት፡ የሄዱትም ሁሉ እርኞቹም ነገሥታትም  እንደተባለው ሕፃኑን በከብቶች ግርግም ተኝቶ አገኙት። ያ እነሙሴ ፊቱን ማየት ያልደፈሩት አምላክ በልደቱ በብጣሽ ጨርቅ ተጠቅልሎ ታየ፡ ያ በሰማይ በደመና በምድር በእሳት ክብሩ ይገለጽ የነበረ ጌታ ሙሉ ለሙሉ የእናቱና የቅዱስ ዮሴፍ ጥገኛ ሕፃን ሆኖ ተወለደ። እርሱ የሰው ልጅ ሆኖ ለዓላማ ማለትም እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ ተወለደ! ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” እንዲሁም “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” ይለናል። እርሱ በእኛ መካከል ያደረ ሥጋ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ተሰጠን። ኦ ድንቅ ልውውጥ!

የቤ/ያን አበው የሚያጎሉት ሌላኛው የጌታ ልደት እውነታ የሰው ልጅ ራሱን ማዳን ስለማይችል አምላክ ሰው ሆነ የሚለው ነጥብ ነው። ይህም ጥልቅ የሆነ መልእክትን የያዘ ነው። ሰው በገዛ ራሱ እንኳን ሙሉ ማንነቱን ነፍሱንም አካቶ ሥጋውን በራሱ ማዳን የማይችል ፍጡር ነው፤ የግድ የሌላ ድጋፍ ያሻዋል፤ በተለይ ደግሞ ሙሉ ተፈጥሮውን ለማዳን ደግሞ የግድ ፈጣሪው ያሻዋል፤ ስለዚህም አምላክ ሰው ሆኖ ተወለደለት።

ስመ ጥሩው ፍሰ ኄር አባ ሄንሪ ኖውዌን ይህን እውነት ሲያጎሉት ብዙዎቻችን በስቃይ ሆኖም ግን አምላክን ለማስጠጋት ባለመፍቀዳችን በስቃይ ውስጥ እንደምንኖር ለማሳየት የሚከተለውን ይላሉ።

እግዚአብሔር ወደኛ የመጣው በጉዟችን አብሮ በመሆን ታሪካችንን ለመጋራትና መንገዳችን የዝም ብሎ እሽክርክሪት ሳይሆን ወደ ሰላምና ደስታ ቤት የሚደረግ ጉዞ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ፈልጎ ነው፡፡ በጉዟችን ብቻችንን ያለመሆናችንን ማወቁ የጌታችን ልደት ትልቁ ምስጢርና ሁልጊዜም ቢሆን ሊያስድስተንና ሊያጽናናን የሚገባ ጉዳይ ነው። በማንኛውም ጊዜና በሁሉም ቦታ ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ አንድያ ልጁን የሰጠን የፍቅር አምላክ በሕይወታችን የትግል ወቅት እርሱ ከኛ ጋር መሆኑን በመገንዘብ ጠፍተናል፤ ማንም የለንም ብለን እንዳናስብ ያስችለናል።

በሁሉ ነገራችን ከኛ ጋር ሊሆን የሚፈልገውን አምላክ ያለማስተናገድ ወይም ያለመፍቀዳችን ሁኔታ ተጋድሮት ወይም ፈተና የሚሆንብን ጉዳይ ነው። ስቃይ ባለው የሕይወታችን ጉዳይ ላይ ብቻችንን በመጣበቅ እግዚአብሔር እንዲነካን አንፈቅድለትም። ብዙ ጊዜም  ጥፋተኝነትን፡ ኀፍረትን፡ ግራ መጋባትንና ባዶነትን በኛ ውስጥ የሚፈጥሩብንን የሕይወታችን ቦታዎች ከእርሱ ለመሸሸግ እንሞክራለን። በዚህም መልኩ ብቸኝነት የሚሰማን ማንነታችን ጋር አምላካችን ከኛ ጋር እንዲሆን አንጋብዘውም።

ገና /የጌታ መወለድ/ የሚያስፈሩ የሚመስሉ የሕይወት ሁኔታዎቻችንን እንዳንፈራ፣ ፍቅሩ ከራሳችን ልብና አእምሮ በላይ የሆነውን አምላክ እንደ አዲስ የምንጋብዝበትና እርሱን ዳግም ወዳጃችን የምናደርግበት ወቅት ነው።”

አዎን ያለ አምላካችን በቅርብ መገኘት በራሳችን ራሳችንን ማዳን አይቻለንም፤ በርግጥ እርሱ አማኑኤል ነውና ከእኛ ጋር ነው፤ ልደቱም ሆነ ጥምቀቱ የሚያበሥሩን አምላክ ሰው ሆኖ በመካከላችን መመላለሱንና ይህም እኛን ሊያድነን መሆኑን ነው፤ ራሳችንን በራሳችን የማዳን ብቃት ቢኖረን ኖሮማ ይህ ሁሉ ስቃይ ባላስፈለገው ነበር። ስለዚህ ይህ የእርሱ ዝቅ ማለት እኛን ከፍ ለማድረግ መሆኑን አስተውለን በዚህ የገናና የጥምቀት ወቅት ራሳችንን በክርስቶሳዊ እምነታችን ቀና የምናደርግበትና ከጎተቱንና ከሚጎተጉቱን የእምነት አዳካሚ ጎዳናዎች በቃሉ፤ በንስሐና በቤ/ያን ምሥጢራት ወደ ጌታችን እንመለስ።

ቡሩክ በዓለ ጥምቀት!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት