22.2 - የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት የሚባለው ነገር ምንድነው?
- Category: ትልቁ ወይስ ትንሹ እሳት
- Published: Monday, 13 May 2013 07:44
- Written by Super User
- Hits: 6612
- 13 May
(ካለፈው የቀጠለ)
እስካሁን እንዳየነው "የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት" የሚለው አባባል በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ (biblical) አባባል ነው፡፡ የሚያመለክተውም የመንፈስ ቅዱስን በምእመናን ላይ መውረድ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ እና በእሳት የሚያጠምቀው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ይህ ዓይነቱ ጥምቀት ሲፈፀም የምናየው በበዓለ-ሃምሣ ዕለት ነው፡፡ የሐዋ.ሥራ 2፡1-4 ላይ የተገለጸው የበዓለ-ሃምሣው ድራማ (ተፈጻሚት) የቃሉን ትክክለኛነት በተጨባጭ ያረጋግጥልናል፡፡ "... እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው..." (ቁ.3-4)
የኢየሱስ እናት ማርያምና ሐዋርያት ሌሎች አማንያንም ባንድ ልብ ተሰበብስበው በጸሎት ላይ እንዳሉ በመንፈስ ቅዱስ ድንገት ይሞላሉ፤ መንፈስ ቅዱስ በያንዳንዳቸው ላይ ያረፈው በእሳት ነበልባል (እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች) አምሳያነት ነበር፡፡ "የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት" የሚለው አገላለጽ ቃል ለቃሉ ሲፈጸም የምናገኘውም በዚሁ ጥቅስ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን "በመንፈስ ቅዱስ" መጠመቅ የሚል አገላለጽ ብቻ በሐዋርያት ሥራ ላይ ሲዘወተር እናያለን፡፡ እንዲሁም ይህን አገላለጽ "በመንፈስ ቅዱስ መሞላት" (የሐዋ.ሥራ 4፡31) "መንፈስ ቅዱስን መቀበል (የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት)" (የሐዋ. 8፡15) "የመንፈስ ቅዱስ መውረድ" (የሐዋ.ሥራ 8፡16፤ 10፡44፤ 11፡15) በሚሉ ተመሳሳይ አገላለጾች በተወራራሽነት ሲተካ እናገኛለን፡፡ ይህም የሚያረጋግጥልን፥ "በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ" ወይም "በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ" የሚባለው ነገር "በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን" የሚገልጽ አባባል እንደሆነ ነው፡፡
ያነበብናቸው ጥቅሶች እንደሚያሳዩት፥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከዮሐንስ ጥምቀት የተለየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በጌታ ኢየሱስ የተመሠረተው ምስጢረ ጥምቀት (ወይም አስቀድመን እንዳየነው ሳክራሜንታል ባፕቲዝም)፥ ከመንፈስ ቅዱስና እሳት ጥምቀት ጋር የሚጋጭ ነገር አይደለም፡፡ አብረው የሚመጡ አንዳንዴም አንዱ ከሌላው ቀድሞ የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው፡፡ በሁለቱም አማካይነት መንፈስ ቅዱስ ይወርዳል፤ ምእመናንን ይሞላል፣ ይቀድሳል፣ ኃይልም ይሰጣቸዋል፡፡ በመሠረቱ ሁለቱም አብረው የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጌታ ኢየሱስ እንደተጠመቀ ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በርሱ ላይ መውረዱ ይህን ያረጋግጣል፡፡ እዚህ ላይ ግን ማስታወስ የሚገባን የኛንና ጌታ ኢየሱስ የተጠመቀው ጥምቀትን ልዩነት ነው፡፡ እኛ ኃጢአታችን (ከአዳም የወረስነውን ይሁን ራሳችን የሠራነውን) እንዲደመሰስልን እንጠመቃለን፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ኃጢአት ስላልሠራ ይህ አያስፈልገውም ነበር፡፡ አጥማቂው ዮሐንስም ሌሎችን ሲያጠምቅ፥ አስቀድሞ ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ ያደርጋቸው ነበር፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ግን ይህን ሊጠይቅ ስላልቻለ፥ ሊያጠምቀው እንደማይችል፣ እንዲያውም በኢየሱስ መጠመቅ የሚገባው እርሱ እንደሆነ በማመልከት ሲከለክለው ይታያል፡፡
በኢየሱስ ሐሳብ ተስማምቶ ሊያጠምቀው የፈቀደው፥ ኢየሱስ "አሁንስ ፍቀድልኝ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና" ያለው ጊዜ ነው (ማቴ. 3፡15) ኢየሱስ የተጠመቀው ለእኛ ምሳሌን (አብነትን) በገዛ ራሱ ሕይወት በማሳየት ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም ነበር፤ እኛ ግን ከኃጢአት ነፃ በመውጣት ይህን የጌታን ጽድቅ ለመቀበል ነው የምንጠመቀው፡፡ ልዩነቱ ይህ ነበር፡፡ በርግጥ ጌታ ኢየሱስ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አብሮ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ በሥጋ ባሕርይ እንደኛ ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል የምናየው ግን ከጥምቀቱ ጋር ነው፡፡
የቅዱስ ጳውሎስን የለውጥ ታሪክ በምናነብበት ጊዜም ምስጢራዊ ጥምቀቱና የመንፈስ ቅዱስ ሙላቱ በአንድ ላይ እንደተፈጸመ (ወይም በአጭር ጊዜ ልዩነት ውስጥ እንደተከናወነ) እናያለን (የሐዋ.ሥራ 9፡17-19)
በሌላ በኩል ደግሞ ምስጢራዊ ጥምቀት ቀድሞ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ኋላ ሲከሰት የሚያመለክቱን ጥቅሶችም አሉ፡፡ በሐዋ. ሥራ 21፡8 ላይ ወንጌላዊ እንደነበረ የተነገረለት ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የነበረው ፊልጶስ ለሰማርያ ነዋሪዎች ወንጌልን ከሰበከላቸው በኋላ፥ በጌታ በማመናቸው አጠመቃቸው (ከተጠመቁ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል ማለት ነው)፡፡ ነገር ግን በጰራቅሊጦስ ዕለት በሐዋርያት ላይ የወረደውን የእሳት ጥምቀት ገና በሕይወታቸው አልተለማመዱትም ነበር፡፡ ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ ከኢየሩሳሌም ወደ ሰማርያ ወርደው ይህ እንዲፈጸም ጸለዩላቸው፡፡ ሰዎችም ይህን ተለማመዱ፡፡ "በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ" (የሐዋ.ሥራ 18፡17)፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ያደረጉት አሁን ጳጳሳት ሲያደርጉት የምናየውን ነው፡፡ ምስጢረ ሜሮንን የሚፈጽሙት ጳጳሳት ናቸው፡፡ በምእመናኑ ላይ እጃቸውን ጭነው ይጸልያሉ፤ ምእምናኑም በመንፈስ ቅዱስ ይሞላሉ፡፡ ከዚያ በፊት ግን መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉም ማለት አይደለም፤ ሲጠመቁ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተዋል፡፡
ፊልጶስ ዲያቆን ነበር፤ ስለዚህ ምስጢረ ሜሮንን ለማደል የግድ ጳጳስ መጥራት ነበረበት፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያዎቹን ጳጳሳት ጴጥሮስንና ዮሐንስን በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላከችለት፤ እነርሱም ይህን ተልእኮ ተወጡ፡፡ እዚህ ላይ እንደሚታየው፥ በነጴጥሮስ እጅ መጫን ምእመናኑ በመንፈስ ቅዱስ መሞላታቸው ምስጢረ ሜሮን ከመጀመሪያው ዘመነ ክርስትና ጀምሮ በተግባር ላይ የዋለ ምስጢር መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት፥ ይህን ሁኔታ፥ "የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት" ከሚለው አባባል ይልቅ "የምስጢረ ሜሮን አፈጻጸም" የሚለው አገላለጽ የበለጠ ያብራራዋል፡፡
(ይቀጥላል)
በኣባ ኤፍሬም ዓንዶም