እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

22.1 - የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት የሚባለው ነገር ምንድነው?

Baptism-of-Christ-II-Nicolas-Poussinታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት (mainline Churches) ተብለው በሚታወቁት፥ የካቶሊክ፥ ኦርቶዶክስ እና ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ፥ ይህ አባባል እንዳልተለመደና እንደ እንግዳ ነገር ሲታይ ቆይቶ፥ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ብቅ ማለት ከጀመረው ፔንቴኮስታሊዝም አንሥቶ በእነኚሁ ሜይን ላይን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ቀስ በቀስ እያደገና በጣም እየተስፋፋ በመጣው የካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ አማካይነት፥ አባባሉ ከእንግዳነት ወደ ኖርማልነት በመቀየር ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ለብዙ ዘመናት አባባሉ ከክርስቲያኖች መዝገበ ቃላት ተሰውሮ ቢኖርም፥ እውነታው ግን ከጌታ ኢየሱስ ምድራዊ ምልልስ አንሥቶ የነበረና ያለም ነው፡፡

‹ጥምቀት› ወይም ‹መጠመቅ› የሚሉትን ቃላት ስንሰማ፣ መጀመሪያ ወደ ሐሳባችን የሚመጣው ውኃ ወይም ምስጢረ ጥምቀት የሚለው ፅንሰ- ሐሳብ ነው፡፡ የውኃ ጥምቀት ወይም ምስጢረ ጥምቀት (sacramental baptism) ከጌታ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ጋር የጀመረም ቢሆን፥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እና የእሳት ጥምቀትም የዚያኑ ያህል ዕድሜ አላቸው፡፡ ለመሆኑ የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት የሚባለው ነገር ምንድነው? ይህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ለማንበብና ለማጥናት የሚሹ የብዙ ክርስቲያኖች ጥያቄ ነው፡፡ መልሱንም ማግኘት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ረጋ ብለን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚለውን በአጭሩም ቢሆን ለማየት እንሞክራለን፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ስለመንፈስ ቅዱስና እሳት ጥምቀት ሲናገር የምናገኘው፥ መጥምቁ ዮሐንስን ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እየሰበከ፣ የንስሐን ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በመስጠት ላይ የነበረው ዮሐንስ፥ ስለ ማንነቱ ጥያቄ በቀረበለት ወቅት የሰጠው መልስ፡-

"እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከመው ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል" የሚል ነበር (ማቴ. 3፡11-14፤ ሉቃ. 3፡15-17)፡፡ "በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል" ያለውም ስለ ኢየሱስ ሲናገር ነበር፡፡ አሁን ባየናቸው ሁለት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ "የመንፈስ ቅዱስ እና የእሳት ጥምቀት" የሚለው ሐረግ ተያይዞ ባንድነት ሲገኝ በአያሌ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ላይ ግን "የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት" የሚለው ሐረግ ለብቻው ሲጠቀስ ይገኛል፡፡ ማር. 1፡8፤ ዮሐ. 1፡33፤ የሐዋ.ሥራ 1፡5, 11፡16 ይህን አባባል ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን በሁለቱም አገላለጾች ላይ የሚንጸባረቀው አንድ ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህ በሁለቱም መካከል ምንም ልዩነት አናገኝም፡፡ ሁለቱም የሚያመለክቱም በበዓለ ሃምሣ ዕለት የተፈፀመውን አስደናቂ ሁኔታ ነው፡፡ በአራቱም ወንጌላውያን የተዘገበው [በመንፈስ ቅዱስ (እና በእሳት) ያጠምቃችኋል] የሚለው አገላለጽ ከመጥምቁ ዮሐንስ አንደበት የወጣ ሲሆን፥ በሐዋ.ሥራ 1፡5 ላይ ግን ራሱ ጌታ ኢየሱስ በዚህ አባባል ሲጠቀም እንሰማዋለን፡፡ "ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ፡፡" የሐዋርያት ሥራን ቀጥለን በምናነብበት ወቅት ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን አባባል እንደተጠቀመበት እናገኛለን፡፡ "ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ፡፡" (የሐዋ.ሥራ 11፡16) ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሊናገር የበቃው ወደ አሕዛብ (ወዳልተገረዙት ሰዎች - የሐዋ. 11፡3) ቤት ገብቶ ሲሰብክ መንፈስ ቅዱስ በነርሱ ላይ በመውረዱ ምክንያት ከአይሁዳውያን ወገኖቹ ለቀረበበት ተቃውሞ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ነበር፡፡ የጴጥሮስ ምስክርነት በሁለት መንገድ ጠቃሚነት አለው፡፡

1ኛ. ‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት› የሚለውን አባባል ጌታ ኢየሱስ ራሱ እንደተጠቀመበት ያረጋግጣል፡፡ ‹የጌታ ቃል ትዝ አለኝ› በማለት ትዝታውን ያወሳል፡፡

2ኛ. በቁ.15 ላይ እንዳለው "ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው" ከዚህም ጋር አያይዞ ስለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መናገሩ፥ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ (ርደተ- መንፈስ ቅዱስ) ከተጠቀሰው ጥምቀት ጋር አንድ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በዕለተ ጰራቅሊጦስም ሆነ በሌሎቹ አጋጣሚዎች ሁሉ ላይ፥ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ላይ መውረዱን እያስታወሰ፥ አሁን ከሚመሰክርለት ክስተት ጋር አንድ እንደሆነም ያረጋግጣል፡፡

በሌላ በኩልም የዮሐንስ የውኃ ጥምቀትና የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል፡፡ እዚህ ላይ የጠቀስናቸው ጥቅሶች በሙሉ ይስማማሉ፤ በሁለቱም ዓይነት ጥምቀቶች መካከል ያለውን ልዩነትም አጥርተው ያሳያሉ፡፡ በሐዋ.ሥራ 11፡1-18 ላይ የተዘገበውን የቅዱስ ጴጥሮስን ምስክርነት ነጠል አድርገን እንድንመለከተው የሚያደርገን አንድ ምክንያት አለ፡፡ ይኸውም፡- "የመንፈስ ቅዱስ (እና የእሳት) ጥምቀትን" በሚመለከት የሚናገሩት ሌሎቹ ጥቅሶች በሙሉ ወይ በትንቢት መልክ ወይም በተስፋ ቃልነት የተነገሩ ሲሆኑ፥ በዚህ ጥቅስ ላይ ግን ትንቢቱና የተስፋው ቃል ተፈፃሚነትን አግኝተው በመጀመሪያ ደረጃ የዓይን ምስክር በሆነው ጴጥሮስ አማካይነት ለምስክርነት መብቃታቸው ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር፥ ወደ ኢየሱስ እየመራን "እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል" (ማቴ. 3፡11፤ ሉቃ. 3፡16) የሚል ትንቢታዊ ቃል ነው የሰጠን፡፡ ጌታ ኢየሱስም "ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ" (የሐዋ. ሥራ 1፡5) ሲል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነትን ስለሚያገኝ ታላቅ ጉዳይ የማረጋገጫ ቃልና የተስፋ ቃል ነው የሚሰጠን፡፡ በእርግጥም ይህ የተስፋ ቃል በተሰጠ በ10 ቀናት ውስጥ የማይረሳው የበዓለ-ሃምሣው ተፈጻሚት ተፈፀመ፡፡

ጴጥሮስ፣ የመጥምቁ ዮሐንስንም ሆነ የጌታ ኢየሱስን ትንቢቶችና የተስፋ ቃሎች አስቀድሞ ሰምቷል፤ በገዛ ራሱ ላይና በጓደኞቹ ሐዋርያት ላይም ሲፈፀሙ አይቷል፡፡ በዳዊት መዝሙር እንደተባለው "እንደ ሰማን እንዲሁ አየን" (መዝ. 48፡8) ወይም ኢዮብ እንዳለው፡- (መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ) (ኢዮብ 42፡5) እንዲያውም ለጴጥሮስ እጅግ የቅርብ ጓደኛ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳረጋገጠው "ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፤ ከአብ ዘንድ የነበረውን ለእኛም የገለጠውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላችኋለን" (1ዮሐ. 1፡1-3) የሚሉት ከመስማት ወደ ማየት የተሸጋገረን የዓይን ምስክር ቃላት ከጴጥሮስ የበለጠ ሊጠቀምባቸው የሚችል ሰው አይኖርም፡፡ ስለ እሳቱ ጥምቀትና ስለ መንፈስ ቅዱስ-ርደት አስቀድሞ በጆሮው ትንቢትን ሰምቶ ነበር፤ የተስፋ ቃልንም ተቀብሎ ነበር፡፡ የበዓለ-ሃምሣ ዕለት ግና ይህ ቃል በእርሱ ውስጥ ሥጋ ሲለብስ ማየት ብቻ ሳይሆን ዮሐንስ (ሐዋርያው) እንዳለው በእጆቹም ዳስሶታል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የተሟላ እውቀት አግኝቷል፡፡ ስለዚህም ያለጥርጥር በድፍረት ስለተባለው ጉዳይ መናገር ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያትም ነው የእርሱን ምስክርነት ነጠል አድርገን ልንመለከተው የፈለግነው፡፡

(ይቀጥላል)

በኣባ ኤፍሬም ዓንዶም

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት