እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

21. ክርስትናችንና ግላዊ ውሳኔያችን

Christandtherichyoungmanጌታ ኢየሱስ ሊጥለው እጅግ ስለሚመኘው እሳትና ሊጠመቀው ስለሚሻው ጥምቀቱ ሲናገር ቆይቶ፥ ወዲያውኑ ሰላምን ለማምጣት ሳይሆን መለያየትን ለማምጣት እንደመጣ በሚናገርበት ወቅት (ሉቃ. 12፡49-53)፥ እርሱን በመቀበልና ባለመቀበል ምክንያት የሚከሰተውን ውጤት ያሳያል፡፡ እርሱን እና ትምህርቱን (እዚህ ላይ ስለ እሳቱ የሚያስተምረውን ሳንረሳ)፥ መቀበልና አለመቀበል የተራ ምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዮሐ. 1፡9-13 ላይ የተገለፀው ሐቅም ይህንኑ ነው የሚያሳየው፡፡ "ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው" (ቁ.12) ያልተቀበሉትስ? እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን የላቸውም፤ ውልደታቸውም ሥጋዊ ብቻ እንጂ መለኮታዊነት የለበትም፥ ዳግም በመወለድ የሚገኘውን የደኅንነት ጽዋንም ከመጎንጨት የራቁ ናቸው፡፡ ክፍፍሉና መለያየቱ እንግዲህ ይህ ነው፡፡

ጌታ የሚጥለው እሳት፥ ፈረንጆች የሚሉትን "ፐርሚሲቭነትን (Permissive) ማለትም የኃላፊነትና ሞራላዊ ግዴታዎችን ሁሉ አሽቀንጥሮ የጣለ ዓለማዊ (ሥጋዊ) ኅብረተሰብ፥ ብዙዎች የሚያደርጉትን ኃጢአትም ይሁን ዘግናኝ ተግባር በማጽደቅ፥ "ሁሉም እንዲህ ነው የሚያደርጉት፥ ስለዚህ መልካም ነው" የሚል መመሪያ የሚቃረን ነው፡፡ የጌታ እሳት ግን ከጽድቅና ከቅድስና ጋር እንጂ "ብዙዎች አደረጉት አላደረጉት" ከሚል ስሌታዊ አሠራርና አስተሳሰብ ጋር ጉዳይ የለውም፡፡ በጌታ እሳት ፊት ጽድቅና ቅድስና እንጂ፥ ድምፅ ብልጫ ዋጋ የለውም፡፡ በዓለም አስተያየት በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ቁጥር እስታቲስቲክስ፣ ስሌት እጅግ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ስሕተትም ይሁን ትክክል፥ አንድ እውነታ የሚለካው በገዛ ራሱ ትክክለኛነት ሳይሆን "ምን ያህል ሰዎች ይህን ሐሳብ ደገፉት?" በሚል የሰዎች ፍርድ ሆኗል፡፡ ለድምፅ ብልጫና ለእስታቲስቲክስ የእግዚአብሔር ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ጽድቅና ኃጢአትን ለመመደብ ሰዎች ከእግዚአብሔር እጅ ኃላፊነትን የተቀበሉ ይመስል፥ የሚስማማቸውን ነገር ሁሉ ክፉም ቢሆን እንደጽድቅ፥ የማይስማማቸውን ነገር ደግሞ፣ ግልጽ ለግልጽ በጌታ ቃል እንኳ ጽድቅ እንደሆነ ቢገለጽም፣ እንደ ኃጢአትና ስሕተት መቁጠር፥ በዚህ እምነትም እንደፈለጉ መሄድ ከጀመሩ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ እንደ ዘመናችን ግን፣ ሰው የራሱ እግዚአብሔር የሆነበት ዘመን ከዚህ በፊት የታየ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ የዚህ ዓይነቱ ትውልድ "ሰላም" የሚለው፥ ከሞራላዊ ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርገው ኃይል ያለ ይመስል፥ እንደፈለገ መሆን የሚያስችለውን አስተሳሰብና አስተዳደር ነው፡፡ ፈረንጆች ይህን ፐርሚሲቭ ሶሳይቲ (Permissive society) ይሉታል፡፡ ለሁሉም የሚስማማ መስሎ ከታየ እግዚአብሔርን ዞር ብሎ እንኳ ማየት የለ፡፡ መቀጠል ነው፤ ልክ መጨረሻ የሌለ ይመስል!

ጌታ ኢየሱስ በሥጋ ተገልጾ በምድር በተመላለሰበት ዘመንም ቢሆን፥ መቼም እንደ እኛ ጊዜ የከፋና የበረታም እንኳ ባይሆን፥ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነበር፡፡ በማቴ. 15፡1-9 እና ማር. 7፡1-13 ላይ እንደምናነበው፥ ፈሪሳውያንና ጸሐፊዎች (የሙሴ ሕግ መምህራን) የራሳቸውን ወግ ለማክበር ሲሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያፈርሱ እንደነበርና፥ በዚህ ምክንያትም ጌታ ኢየሱስ ፊት ለፊት እንደተቃወማቸው እናያለን፡፡ የነቢዩ ኢሳይያስን ቃል በመጥቀስም፡- "እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፤ ‹ይህ ሕዝብ በአፉ ብቻ ያከብረኛል እንጂ ልቡ ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውንም ሥርዓት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል› ሲል የተናገረው ቃል እውነት ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ" በማለት አክርሮ ይገስጻቸዋል (ማር. 7፡6-8)፡፡ ይህ ተግሣጽ ዛሬም ቢሆን እኛን ሁላችን፤ እያንዳንዳችንን ይመለከተናል፡፡ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ብንሆን በኃላፊነታችን፥ ከኃላፊነት ራቅ ያልንም ብንሆን፥ ግላዊና ልባዊ እምነታችንን በሚመለከት፥ ቃሉ ውስጣችንን ይመረምራል፡፡

የራሱ ሕግ አውጪ፥ የራሱን አስተሳሰብ ከአምላክ ሕግ በላይ የሚያከብርና፥ ከአምላክ ይልቅ ሥጋውን የሚያመልክ፥ ኅብረተሰብም ይሁን ቤተሰብ፣ ወይም ደግሞ ግለሰብ፣ ውጫዊ ግጭቶች እስካላጋጠሙት ድረስ በሰላም የሚኖር መስሎ ይሰማዋል፡፡ በምን ያህል የከፋ ባርነት ውስጥ እንዳለ ግን አይመለከትም፡፡ ጌታ ግን ይህን እውር የሆነ ግለሰብም ሆነ ማኅበረ-ሰብ፣ እጅግ ስለሚያፈቅረው፣ ሊያድነው ወደደ፡፡ ለማዳን ሊጠቀምበት ይችል የነበረው አንድ መንገድ ብቻ ነበር፤ ይኸውም ስለርሱ መሞት፡፡ ከሁሉም ነገር ይልቅ የሰዎች መዳንን እጅግ ከመፈለጉ የተነሣ፥ እርሱን ለማዳን መቀበል የነበረበትን ጥምቀት (የመስቀል ሞት) እጅግ ናፈቀው፤ ቶሎ ይፈፀምለት ዘንድም በእጅጉ ተመኘ፡፡ ሰውን ለማዳን የነበረው አንድ አማራጭ መሞት ብቻ ስለነበር ነው እንጂ ሞትንስ ማን ይመኘዋል? እርሱ በበኩሉ እንደተመኘው አደረገ፤ "ተፈፀመ" ብሎም ማድረግ የሻውን አደረገ፡፡ አሳዛኙ ታሪክ ግን ከዚህ ሁሉ በኋላም እንኳ ሊቀበሉት የማይፈልጉ መኖራቸው ነው፡፡ እዚህ ላይ ድምፅ ብልጫ አይሠራም፡፡ ሁሉም ለየግሉ መወሰንና መምረጥ አለበት፡፡ ስለዚህም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ ምርጫዎች ይለያዩ ጀመር፡፡ ሦስቱ ሲቀበሉ ሁለቱ አንቀበልም ሲሉ፤ አባት ሲድን ልጅ ሲጠፋ፤ አማት አልቀበል ስትል ምራት ስትቀበል፥ ልዩነቶች ጎልተው ይታዩ ጀመር፡፡ የልዩነቱ ኃላፊነት በየሰው ግላዊ ምርጫ ላይ የተጫነ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ እሳቱን ጣለ፤ በዚህም ተደሰተ፡፡ በሰዎች በኩል ግን ልዩነትን አመጣ የሚድኑና የማይድኑ፤ ትልቁ እሳት የነደደባቸውና ትንሹ እሳት ያጋያቸው ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡ ያ በሰላም ይኖር የነበረ ይመስለው የነበረው ኅብረተሰብ ሰላም እንዳልነበረው አሁን አየ፡፡ ሰላም ያለው ትልቁን እሳት በተቀበሉት አማኞች ወገን ብቻ ነው፡፡ የሌሎቹ ግን አታላይ ሰላም እንጂ የእውነት ሰላም አይደለም፡፡

ያ እሳት ወይም ያ "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው" (1ቆሮ. 1፡18)፡፡ ያ አንድ የመስቀል ቃል ተቀባዮቹን ለሁለት ከፈላቸው፡፡ ጌታ መለያየትን አመጣለሁ ያለውም ተፈፀመ፡፡ የመስቀሉ ቃል በሰዎች ድምፅ ብልጫ አይቀየርም፡፡ እልፍ ሂትለሮች ተነሥተው ነፍስ ግድያን ቢያጸድቁ፥ አእላፋት አርዮሶች ተሰብስበው ኢየሱስ ሰው ብቻ እንጂ አምላክ አይደለም ብለው በአንድ ድምፅ ውሳኔ ቢያስተላልፉ የሥላሴ ምስጢር ከብዷቸው እጅግ በጣም ብዙ ብዙ ግዙፋውያን ተሰብስበው፣ "ሥላሴ የለም" ቢሉ ወይም የሥላሴን ቁጥር ለምሳሌ አራት ናቸው ብለው ቢወስኑ፥ የመስቀሉን ቃል እንኳን ሊለውጡት አንዲት ነጥብም ሊፍቁበት አይችሉም፡፡ ግን ጌታ ከጣለው እሳት የተነሣ ተሰናክለው፥ ያን እሳት በተቀበሉት ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፡፡ የገዛ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ወይም ወላጆቻቸውንም እንኳ ሳይቀር ያሳድዳሉ፤ ይገድላሉም፡፡ እንደ እሳት ብርቱ የሆነው የመስቀሉ ቃል ከእንደነዚህ ዓይነቶች ጋር እንኳን ሊስማማ፥ እርሱ ባለበት እነርሱ ሊቆሙ እንደማይችሉት ሁሉ፥ በመስቀሉ ቃል ሙቀት የተጎበኙትም አማንያን ከነዚህ ሥጋውያን ጋር በምንም ዓይነት መንገድ ሊጋጠሙ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ብርሃን ከጨለማ ጋር ምንም ኅብረት የለውምና! (2ቆሮ. 6፡14 እይ) የጌታ ፍላጎትም ወገኖቹ የፈለገውንም ያህል መሥዋዕት የሚያስከፍላቸው እንኳ ቢሆን የእርሱን ፈለግ በመከተል የፍቅር ወንጌልን ችቦ አንድደው ያለመናወጥ እንዲጓዙ ነው፡፡ ዓለም በሙሉ እነዚህን አማንያን እንደ መናፍቃን፣ ስሕተተኞች፣ ደንቆሮዎችና ኋላ ቀሮች አድርጎም ቢያስባቸው፥ የተቃራኒዎቻቸውን ብዛት ሳይሆን የቆሙለትን ዓላማ ብቻ ሊመለከቱ ይገባቸዋል፡፡

ምናልባት በቤተሰብህ ውስጥ የጌታን እሳትና ብርሃን በመቀበልህ ምክንያት እንደ እብድ የተቆጠርከው አንተ ብቻ ነህ? ወይስ ስለጌታ እንደ ሞኝ የምትታየው የመንደርህ፥ የቀበሌህ ወይም የከተማህ ብቸኛ ሰው አንተ ትሆን? አይዞህ የመስቀሉ ቃል በድምፅ ብልጫ የሚጸድቅና የሚኮነን አይደለም፤ አትፍራ! ይልቅስ የጠራህ ጌታ የገባልህን ቃልና አደራ አዳምጥና ወገብህን ጠበቅ አድርገህ እሰር፡፡ "እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ" (ራዕይ 3፡11)፡፡

ኃጢአትህና ትዕቢትህ ከሆኑ፥ የመለያየት ምክንያቶቹ፥ ዛሬውኑ ንስሐ አድርግ፡፡ ዓለም እንደ ኃጢአት የቆጠረብህ ጌታ ኢየሱስን መውደድህ (ምናልባት በፍቅሩ ማበድህን) ከሆነ ግን ከዓለም ጽድቅ የአንተ ኃጢአት (ጌታን ከልብህ መውደድህ) በእጅጉ ይሻላልና አትጨነቅ፡፡ ለዓለም በደለኛና ጉድፍ ጥራጊም ብትሆን አይክፋህ፤ ብቻ ጽድቅህና ኃይልህ ጌታ ኢየሱስ ይሁን፡፡ አንተም ወገኔ ሆይ ከመንፈስ ቅዱስና ከሙሽራይቱ (ቤተ ክርስቲያን) ጋር ሆነህ ጌታ ኢየሱስን "ና" በለው፤ ይመጣል (ራዕይ 22፡17 እይ) በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው ጌታህም በፍጥነት ከተፍ ይላል፤ አሜን ይሁን፡፡

አባ ኤፍሬም ዓንዶም

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት