እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

20- የአምላክ እሳት በሁሉ ቦታ ይሰራጭ ዘንድ...

20- "... ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ፤ በከተማይቱም ላይ በትናት..." (ሕዝ. 10፡2)

መንፈስ ቅዱስ እሳትጌታ አምላካችን በማደሪያው ካለው ሙቀትና ኃይል ይሳተፉ ዘንድ ስለ ልጆቹ እጅግ ይመኛል፡፡ ስለዚህም መልእክተኞቹን በየጊዜው ሲልክ ይታያል፡፡ በዚህ ጥቅስም አማካይነት፥ መለኮታዊው እሳቱ ወደ ምድር ይወርድና ሁሉንም ያቀጣጥል ዘንድ ከመፍቀዱ የተነሣ፥ አንዱን አገልጋይ ወደ ኪሩቤል ገብቶ እጁን በእሳት ፍም ይሞላና በከተማይቱ ላይ እንዲበትን ሲልከው እናያለን፡፡ አስቀድመን እንዳየነው ጌታ መልእክተኞቹን የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እሳት የሆነ መልእክተኛ ከኪሩቤል ውስጥ እሳትን አፍሶ ወደ ከተማ መበተን ይችላል፤ ካልሆነ ግን እሳቱ እርሱን ይፈጀዋል፡፡

እሳት ከሆነው የአምላክ ፍቅር የቀመሰ ሰው ያን ፍቅር ውጦና አምቆ ጸጥ ብሎ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ያ ፍቅር ግድ እያለው፥ ያን ፍቅር በሄደበት ሁሉ ይዘራል፤ ይበትናል፡፡ የሚበተን ነገር በጥቂት ቦታ ብቻ ተወስኖ አይቀርም፤ ይሠራጫል፡፡

የአምላክ እሳትም በጥቂት ልቦች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ልቦች ውስጥ ይነድ ዘንድ ስለሚገባው በሁሉም ቦታ መበተን ያስፈልገዋል፡፡ ማንነው ያ በታኝ? ከእሳቱ እጁን የሞላ ሁሉ የዚያ እሳት በታኝ ነው፡፡ የእሳቱን ልዩ ጥምቀት የተቀበለ ሁሉ የዚህ መልእክተኛ ነው፡፡ ይህን እሳት በከተማ እንጂ በምድረ በዳ በትኑት አልተባልንም፡፡ ሰዎች በከተማ እንጂ በምድረ በዳ እንደማይኖሩት ሁሉ፥ የጌታ እሳትም በሰዎች መካከል እንጂ ሰው በሌለበት ስፍራ እንዲበተን ጌታ አይሻም፡፡ ብርሃኑን የለበስን ሁላችን የጌታ ሐዋርያት ነን፤ የእሳቱ አድራሾች ነን፡፡ በጥፋት እሳት ውስጥ ያሉትን አንዳንዶችን ማዳን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የመንፈስ ቅዱስ እሳታዊ ጥምቀት ይደርሳቸው ዘንድ መትጋት የማደሪያው አገልጋዮች ኃላፊነት ነው፡፡ የእሳቱ በምድር ላይ መንደድ ጌታ ኢየሱስን ምን ያህል ያሳስበው እንደነበር ከገዛራሱ ንግግር ስንሰማ፣ የኛን ከዚህ ጥሪ በማምለጥ መፍጨርጨር መሠረት አልባነት እንገነዘባለን፡፡ የመስቀል ሞቱን በማሰብ በናፍቆት ሲናገር፥ እሳቱ ይነድ ዘንድ ያለውን ታላቅ ጉጉት በግልጽ አሳይቷል፡፡ ይህ እሳት ግን የመለኮታዊው ፍቅር እሳት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

20.1- "በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ? ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?" (ሉቃ.12፡49-50)

እዚህ ላይ ጌታ ኢየሱስ ስለ እሳቱ በሚናገርበት ወቅት ሐሳቡ በሙሉ ያተኮረው ስለመስቀል ሞቱ ነበር፡፡ የመጨረሻ ትልቅ የፍቅር መግለጫ መሣሪያው ስለወዳጆቹ ነፍሱን በመስቀል ላይ አሳልፎ መስጠቱ ነበር፡፡ ከዚህ የበለጠ የፍቅር ግለትና ትኩሳት ሊገኝ አይችልም፡፡ የመጨረሻው የፍቅር እሳት ኃይል የተገለጸልን ቀራንዮ መስቀል ላይ ነበር፡፡ ግን ቀራንዮ የመጨረሻ የጉዞ መስመር አልነበረም፤ ትንሣኤና በዓለ-ሃምሣም ገና ይከተላሉ፡፡ ያለ መስቀል ሞት ትንሣኤ፥ ያለ ትንሣኤም በዓለ-ሃምሣ የለም፡፡ ጌታ ሊጥል የፈለገው እሳትም ይህን ሁሉ ጉዞ ያካተተና በበዓለ-ሃምሣ ዕለት አክሊልን የተቀዳጀ የድል ምዕራፍ ነበር፡፡ ጌታ እጅግ የተመኘውን ይህን ሂደት እኛም የግድ ልንመኘውና ልንጠባበቀው ይገባናል፡፡

በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ካነበብነው ጥቅስ፥ እሳቱን ለመበተን (ለመጣል) የተላከው አንድ አገልጋይ ሲሆን፥ አሁን ባየነው ክፍል ውስጥ ግን እሳቱን የሚጥለው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ምን ያህል ታላቅ ናፍቆት እንደነበረው ሲገልጽ የተጠቀመባቸው ቃላት ራሳቸውም ግለትን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ ያች ሰዓት እስክትመጣ ድረስ ብዙ ቃተተ፤ ሰዓቷም ደረሰችና እሳት የሆነ ፍቅሩን ያመቀውን ልቡን በሞት ለጥቂት ጊዜ ጸጥ ይል ዘንድ ፈቀደ፡፡ እንደ ስንዴ ወደቀ፤ ሞተ፡፡ ግን ሞቶ አልቀረም፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሞትን ማሰርያዎች ሁሉ በጣጠሰና ጣለ፡፡ ያን እርሱን ከሞት ያስነሣውን የእግዚአብሔር መንፈስ በእሳት መልክ ለደቀ መዛሙርቱ ላከላቸው፡፡ እሳቱን በምድር ጣለ፤ እሳቱም እጅግ ነደደ፤ ተቀጣጠለ፡፡ የብዙዎችን ደንዛዛ ልብ አጋለ፤ ለሞቱት ሕይወትን ሰጠ፡፡ ከበዓለ-ሃምሣ በፊትም እንኳ ቢሆን "አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ?" ያለው ቃል፥ ሙሉ ለሙሉ ከበዓለ-ሃምሣ ጀምሮ በየጊዜው በመደጋገም ተፈጻሚነቱ ይታይ ጀመር፡፡ በዚህም ጌታ ኢየሱስ እንደረካ ቃሎቹ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ እሳትና ጌታ ሊጠመቀው የፈለገው ጥምቀት፥ በሁሉም ሰዎች ዘንድ እኩል የሆነ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ጌታ አስቀድሞ አመልክቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ መለያየትና መከፋፈል እንደሚመጣ ጌታ ተናግሯል፡፡ ክፍፍሉ ጌታን በሚቀበሉትና በማይቀበሉት ሰዎች መካከል ሲሆን፥ ከመለኮታዊው እሳት ጋር አያይዘን ከተመለከትነውም፥ በመለኮታዊው እሳት ሥር እና፣ በፍጥረታዊው እሳት ሥር በሚገኙ ሰዎች መካከል የሚኖረውን ልዩነት ያሳየናል፡፡

በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙት አባላትም እንኳ ሳይቀሩ የዚህ ክፍፍል ሰለባዎች እንደሚሆኑ፥ ማለትም ሦስቱ በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ እንደሚነሡ በጌታ ተጠቁሟል፡፡ የጌታ እሳትና፥ የእርሱ ጥምቀት (የመስቀል ሞቱ) የብጥብጥ ምክንያት ሆነ ማለት ይሆን? ወይስ አጽናኝ፣ መምህርና አስታዋሽ ስለሆነው መንፈስ ቅዱስ በሙላት መሰጠት በሚናገርበት ወቅት "ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም" (ዮሐ. 14፡27) ያለው የጌታ ኢየሱስ ቃል፥ "በምድር ላይ ሰላምን ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ" (ሉቃ. 12፡51) ከሚለው፥ በሌላ ጊዜ ከተናገረው፥ የራሱ ቃል ጋር የማይስማማ፣ ተቃራኒ አባባል ይሆን? ኢየሱስ ራሱን በራሱ እየተቃረነ ይሆን እነኚህን የተናገረው? በሁለቱም መካከል ምንም የሚጋጭ አባባል አናገኝም፡፡ "የሰላም አለቃ" (ኢሳ. 9፡6) ተብሎ እንደሚጠራ የተነገረለት ጌታ ኢየሱስ፥ ለዘለዓለም የሰላም አለቃ እንጂ፣ የብጥብጥና የክፍፍል አለቃ አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ግን ታዲያ ሁለቱን ጥቅሶች እሺ እንዴት አድርገን እናስማማቸው? ማስማማቱ የኛ ተግባር ሳይሆን ድሮም የተስማሙ ቃላት ናቸው፡፡ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ከዮሐ. 14፡27 ጀምረን በጥንቃቄ ካነበብናቸው ምስጢራቸውን በቀላሉ ልንገነዘበው እንችላለንና ከዚህ ጥቅስ እንጀምር፡፡ እዚህ ላይ ጌታ ይናገር የነበረው ስለ እርሱ ሰላምና፥ በዓለም አስተሳሰብ ሰላም ተብሎ ስለሚታሰበው ምድራዊና ሥጋዊ ሰላም ልዩነት ሲሆን፥ እርሱ የሚሰጠው ዘለዓለማዊና ዘላቂ ሰላም እንደሆነ፥ ይህ ሰላምም ውስጣዊና መንፈሳዊ እንደሆነ፥ በሌላ ወገን ደግሞ ሥጋዊው ሰላም የታይታና አጭበርባሪ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

በዓለም አስተሳሰብ ሰላም አለ የሚባለው፥ ግዙፍ ጦርነት ወይም ፍልሚያ የማይታይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን በመንፈሳዊው ዓለም (ሕይወት) ሚዛን ሲመዘን ሰላም አይደለም፡፡ የጌታ ሰላም እርሱን በልብ ውስጥ በማንገሥ የሚገኝ የዘለዓለማዊ ሕይወትን ጣዕም ከወዲሁ አስቀድሞ መቅመስ ነው፡፡ ይህን ሰላም በግዙፍ ዓይን የሚታይ ረብሻም ይሁን ብጥብጥ፥ ጦርነትም ይሁን ውጊያ ሊያደፈርሰው አይችልም፡፡ "እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም" ሲል ጌታ፥ ይህን በማመልከት ነው፡፡ የጌታ ሰላም እንደሚፈስ ወንዝ እና እንደጐርፍ ነው (ኢሳ. 66፡12 እይ)፡፡ ሁልጊዜ አዲስ ነው፤ የዓለም ግን ዘላቂነት የሌለው፥ በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አመቺ ሁኔታዎች ሁሉ ሲደረማመሱ ያ ሰላም መስሎ ይታይ የነበረው ስሜትም አብሮ ይደረመሳል፤ የተመረኮዙበትንም አብሮ ይጥላቸዋል፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት