እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ደሙን አሟጥጦ ሰጥቶ አድኖናል

je bloodስለ ኢቦላ በሽታ መቼም በተለያየ መጠን ቢሆንም ግንዛቤው አለን፤ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ የገዘፈ፤ ሰለባውን ደግሞ ለመግደል የፈጠነ ዘግናኝ በሽታ ነው። ዛሬ የሚሰሙት በሽታ ግን ከዚያም በላይ በፍጥነት በጥቂት ሰዓታታ የሚተላለፍና የሚገባበትን መንደርም ሆነ አገር በትንፋሽ ብቻ በደረሰበት ሁሉ ሰው የሌለበት ዖና መንደርና አገር ማስቀረት መገለጫው ነው።

ይህን በምናብዎ ያስቡ፡-

እርስዎ የቀኑ ውሎት አደካክሞት ቤት ገብተው የእለቱን ዜና ሲያዳምጡ በእስያና በአውሮፓ ይህ ከኢቦላ የከፋው በሽታ እጅጉን ተስፋፍቶ ብዙ ሰዎችን እየጨረሰ መሆኑንና በአንዳንድ አፍሪካ አገሮችም እንደተከሠተ፤ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱንና ኢትዮጵያም ከውጪ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሰዎች ላይ የሚቻላትን ጥንቃቄና ምርመራ እያደረገች መሆኗን አደመጡ። እርስዎም ውስጥዎ የሆነ ነገር ሹክ አለዎትና ሆ! ሆ! የእስራኤል አምላክ ያውቃል! አሉ።

የበሽታው ክፉነትና አስጊነት ወሬ በአገራችን ናኘ፤ ሰዉም አይምጣ እንጂ አገራችን ቢገባ....እያለ የየራሱን የውስጥ ጭንቀት መተንፈስ ጀምሯል። በየቤተ እምነቱም “የእግዚአብሔር መቅሰፍት ነው!”፣ “ስምንተኛው ሺህ ገባ! አከተመ!”...ወዘተ የሚሉም ይደመጣሉ።

ከአራት ቀናት በኋላ የጸሎተ ሐሙስ እለት የፋሲካ ዝግጅት ሱባኤ ለማድረግ በማለዳ ወደ ቤ/ያን ሲያቀኑ የማለዳ ዜና ያደመጡ ወዳጅዎ የሰሙትን በመድገም “ያ ርኩስ በሽታ አ.አ. መግባቱንና በርሱም የተወሰኑ ሰዎች መሞታቸውን አረዱዎት። በቃ ሰዉ ሁሉ አገር አቀፍ ስጋት ውስጥ ወደቀ። ሰዉም በየአቅሙ ለጥንቃቄ ይበጃል የሚለውን ማድረግ ጀመረ፤ በጥቂት ሰዓታትም በሽታው ከአ.አ. በመውጣት ወደ ክልሎች መዛመቱን ተያያዘው፤ በአገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንሰራፋ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የበሽታው ፈውስ በአንድ የጥናትና ምርምር ቡድን እንደተገኘና ይህም በክትባት መልክ ሊሆን እንደሚችል የነገረው ሰበር ዜና ተበሠረ፤ ይህንንም ለመተግበር በበሽታው ያልተያዘና ልዩ የደም ዓይነት ያለው አንድ ሰው ማግኘት ግድ ይላል ተባለ። የስቅለተ ዓርብ እለት ጠዋት እርስዎና እኔ፣ ሁላችንም በአቅራቢያ ወዳለው ሆስፒታል ሄደን ደማችንን እንድናስመረምር ተነገረን። እናም ወደ ሆስፒታሉ ስንደርስ ለዚሁ ጉዳይ የተሰበሰበ ያገር ሕዝብ አለ። ሐኪሞች የደም ናሙና እየወሰዱ የግለሰቡን ስም በመጻፍ እየለጠፉ ያስቀምጣሉ።

በመጨረሻም የእርስዎና የቤተሰብዎ ተራ ደረሰ፤ መጀመሪያ የርስዎና የባለቤትዎ፣ ቀጥሎም የልጅዎ ደም ተወሰደ፤ “ለውጤቱ ስምዎ እስኪጠራ ከደጅ ይጠብቁ!” አሉዎት ሐኪሞቹ። በተነገረዎት መሠረት ከባለቤትዎና ልጅዎ ጋር በደጅ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጉጉት ውጤቱን መጠበቅ ጀመሩ። ውጪ ከሚያዩት በላይ ብዙ ነገር በውስጥዎ እየተተረማመሰ “በእውነት የዓለም ፍጻሜ ደረሰ እንዴ? ሁሉም የሚያከትምለት በዚህ ሁኔታ ይሆን?...” እያሉ ከራስዎ ጋር ያወጋሉ።

እስካሁን የማንም ስም አልተጠራም፤ ሐኪሞች የደም ናሙና መውሰዱን ቀጥለዋል። በድንገት አንድ ወጣት ሐኪም አንድ ስም የተጻፈበት ትልቅ ወረቀት ከፍ አድርጎ ይዞ የሆነ ነገር ይላል፤ እርስዎ በራስዎ ዓለም ውስጥ ነዎትና ቀልብዎን አልሰጡትም። ወጣቱ ይጮሃል፤ ሌሎች ሐኪሞችም አጅበውት ወደርስዎ አቅጣጫ  እየመጡ ነው፤ አብርዎ ያለው ወንድ ልጅዎ “አባዬ! እኔን ነው! የሚጠሩት የኔን ስም ነው!” ብሎ በጃኬትዎ ሊሸሸግ ይሞክራል። ገና ሁኔታው ሳይገባዎት ሐኪሞቹ ልጁን ይዘው ወደ ውስጥ ወሰዱት፤ እርስዎም “አረ ቆዩ! አንዴ! ልጄ ነው እኮ!” እያሉ ከኋላቸው መሮጥ ጀመሩ። ሐኪሞቹም “እሺ! እሺ! ከዚህ ሁሉ ሰው የሚፈለገው ዓይነት ደም ያለው እርሱ ሳይሆን አይቀርም፤ ርግጠኛ ለመሆን ደግመን መመርመር ይኖርብናል” ብለው ነገሩዎት።

ከአምስት የጭንቀት ደቂቃዎች በኋላ ሐኪሞችና ነርሶች እርስ በእርስ በደስታ እየተላቀሱ መተቃቀፈ በፈገግታም መሞላት ጀመሩ፤ እርስዎ ፈገግታ የሚባል ነገር ካዩ ሳምንት ሆነዎታል። በእድሜው ጠና ያለ ሐኪም ወደርስዎና ወደ ባለቤትዎ መጥቶ “እናመሰግናችኋለን፤ የልጃችሁ ደም በጣም ጤናማና በሁለ ነገሩ ለዚህ ጉደኛ በሽታ ፈውስ ክትባት ሊሠራበት ብቁ ነው” በማለት ነገሯችሁ።

ይህ ዜና እንደተነገረ በዚያ የተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ በደስታ መጮኽ፣ በምስጋና መጸለይ፣ ደስታ በደስታ መሆን ጀመረ። ያው ሐኪም ወደናንተ ተመልሶ መጣና የልጃችሁን ደም መስጠት ፈቃዳችሁ መሆኑን በፊርማ እንድታረጋግጡ ገለል አድርጎ ጠየቃችሁ። እናንተም በሰጣችሁ ቅጽ ላይ ወዲያው ፊርማችሁን ማስፈር ጀመራችሁ። ነገር ግን ቅጹ ላይ ምን ያህል የደም መጠን እንደሚሰጥ የሚጠቅመው ቦታ ባዶ መሆኑን ድንገት ያስተውሉና ሐኪሙን “ልጃችን የሚሰጠው ደም መጠን ምን ያህል ነው?” ብለው ጠየቁት። በዚህ ጥያቄ የሐኪሙ ፈገግታ በፊቱ ላይ ሲደበዝዝ አስተዋሉ እንዲህም አለዎት “ቅጹን ስናዘጋጅ ሙሉ እውቀት አልነበረንም ለዚህም ነው ያላመለከትነው” አለዎት ሐኪሙ፤ እርስዎም በድጋሚ “እባክዎ መጠኑን ይንገሩኝ!” አሉ። ሐኪሙም ዝቅ ባለ ድምጽ “ያለው ደም በሙሉ ያስፈልገናል!” አሉ።

እርስዎ መልሱ ግራ ግብት አለዎና “በሙሉ ያስፈልገናል ማለት ምን ማለት ነው? አንድና ብቸኛ ልጄ ነው እኮ!” አሉት።

ሐኪሙም ትከሻዎን ያዝ አድርጎ ወደርሱ ጠጋ እያደረገዎ ዓይንዎን ትኩር ብሎ እየተመለከተ “አሁን የምናወራው ስለሙሉ ዓለም ነው፤ ገባዎት! የሙሉ ዓለም ሕዝብ መድኃኒት! እባክዎ መፍጠን ስላለብን ይፈርሙ!”። እርስዎም “መፈረሙን ልፈርም ግን ከሌላ ሰው ደም አትሰጡትም?” ብለው ጠየቁ በልመና ቅላፄ። “ጤናማና ንፁሕ ደም ብናገኝ እንሰጠው ነበር፤ ነገር ግን ያ አልተገኘም፤ እባክዎ ይፈርሙ!” አለዎት ሐኪሙ።

ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ይሰጣሉ?

ሌላ ምንም አማራጭ ያለመኖሩን ስለሚያውቁ በከባድ ዝምታ ቅጹ ላይ ፊርማዎን አኖሩ። ከዚህም በኋላ ሐኪሙ “ደሙን ከመውሰዳችን በፊት ከልጅዎ ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ይፈልጋሉ?” ብሎ ጋበዘዎ።

“አባዬ! እማዬ! ምንድነው ነገሩ?” የሚለውን ልጅዎን ለመሰማት ወደ ሆስፒታሉ እሱ ወዳለበት ክፍል ይሄዳሉ? ልጅዎን እንደሚወዱት የመንገር ብራታት አለዎት? ሐኪሞቹና ነርሶቹ መጥተው ከልጅዎ የነጠሉ ዘንድ “እናዝናለን አሁን ደሙን መውሰድና ሥራውን መቀጠል አለብን በመላው ዓለም ሰው በመሞት ላይ ነው” ሲሉዎት ትተው መሄድ ያስችልዎታል? ልጅዎ ግራ እየተጋባ በፍርሃት ስሜት ሆኖ “እማዬ! አባዬ! ምንድነው እሱ? የት ነው የምትሄዱት? ለምን ብቻዬን ትትዉኛላችሁ?” ሲል ጥሎ መሄድ ይችሉ ይሆን? የሆነ ሆኖ አደረጉት የተባለውም ተከናወነ፤ ልጅዎ ሙሉ ደሙን ሰጠ - ሞተ።

በቀጣዩ ሳምንት ላይ ለሰው ልጆች ሁሉ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓልና የርስዎን ልጅ ለማክበር ልዩ ዝግጅት አገሩ አዘጋጀ። ነገር ግን የአገሪቱ አንዳንድ ሰዎች ተኝተው ቀሩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሌላ የሚያስቀድሙት ነገር ስላለ ለመገኘት ጭራሽም  አላሰቡም...ጥቂት ሰዎች በለበጣ /በውሸት/ ፈገግታ ልዩ መስተንግዶን በመፈለግ ሲመጡ አንዳንዶቹ ደግሞ “ኡፍ አሰልቺ ዝግጅት” ሲሉ ተደመጡ። እርስዎ ይህን ሲታዘቡ “ይቅርታችሁን! እርግጠኛ አይደለሁም ግን የገባችሁ አይመስለኝም - ይህ የምትኖሩት ውድ ሕይወታችሁ በልጄ ደምና ሞት የተገኘ ነው፤ እናንተ ሕይወት ይኖራችሁ ዘንድ እርሱ ሞተ። ስለእናንተ ሞተ፤ ይህ ማለት ለእናንተ ምንም ትርጉም የለውም እንዴ?” ለማለት ውስጥዎ ይገፋፋዎታል።

ምናልባት አኛንም እግዚአብሔር እንዲሁ ሊለን ይፈልጋል።

ዮሐ 3፡16 “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ እንዲሁ ወዶአልና”

ሮሜ 8፡32 “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?”

1ጴጥ 1፡18-19 "እናንተ የተዋጃችሁት ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚጠፋ ነገር፤ በብር ወይም በወርቅ አይደለም፤ እናንተ የተዋጃችሁት ነውር እንደሌለው ንጹሕ በግ በሆነው በክርስቶስ ክቡር ደም ነው"

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት