የምትሄድበትን ዕወቅ
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Monday, 21 February 2022 20:19
- Written by Super User
- Hits: 766
- 21 Feb
የምትሄድበትን ዕወቅ!
አንድ ሰው መንገድ ከመጀመሩ በፊት ስለ መዳረሻው በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ያስፈልጋል። መዳረሻን ማወቅ የዓላማ ጽናት ብቻ ሳይሆን የጉዞ አቅጣጫ እና ራዕይ ይሰጠናል። መዳረሻውን በግልጽ የማያውቅ እና ራእይ የሌለው ጉዞ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ያሰበበት ሳይደርስ ከመንገድ መቅረቱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ለጉዞ ከመነሳት በፊት ራዕይ ያስፈልጋል፤ የምሄድበትን መንገድ ነባራዊ ሁኔታ፣ በዚህ ጉዞ ላይ የሚያስፈልጉኝን ውስጣዊ እና ውጫዊ መሰናዶዎች በሚገባ ማጤን እና ዐቅምን መፈተሽ ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ጉዞ ውጫዊ እና ውስጣዊ ዝግጅት ያስፈልገዋል። ምናልባት ህይወታችን መዳረሻቸውን ባላወቅናቸው ጉዞዎች፣ የት እንደምንሄድ ሳናውቅ በጀመርናቸው መንገዶች፣ ትርጉማቸው ሳይገባን በገባናቸው ቃል ኪዳኖች እና የማንዘልቅበት እንደሆነ እያወቅንም ሆነ ሳናውቅ በሰዎች ውስጥ ባከሰምናቸው ተስፋዎች፣ ግንኙነቶች፣ የሥራ ዕድሎች ወ.ዘ.ተ የተሞላች ናት። እነዚህ ሁሉ መዳረሻን ሳያውቁ ጉዞን ከመጀመር የሚመነጩ ችግሮች ናቸው። ተስፋው በእኛ ውስጥ ምን ያህል እንደሆነ ሳናውቅ ካለን ተስፋ በላይ ለሌላው ተስፍ ቃል እንገባለን። የመንገዱን ጠምዝማዛነት እና ርቀት ከግምት ውስጥ ሳናስገባ የሌላውን መስቀል ካልተሸክምን እንላለን ነገር ግን ብዙ ርቀት ሳንጓዝ ማጉረምረም፣ ብዙ ርቀት ሳንሸከም መድከም፣ እንደሚገባን ሳናፈቅር የፍቅር መቀዝቀዝ ወ.ዘ.ተ የዕለት ተዕለት የህይወት ታሪካችን ነው።
በመንፈሳዊ ሕይወትም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ መጾም ጀምረን እናቋርጣለን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን ብለን እንጀምራለን ነገር ግን ከተወሰኑ ቀናት አይዘልም፣ ዘንደሮ በቃ ይህን አደርጋለው! ብልን እንነሳለን ነገር ግን ከአምና የተለየ የምናደርገው ነገር የለም። በስሜት የሚደረጉ መንፈሳዊ ውሳኔዎች የመንፈሳዊ ሕይወታችንን መቀንጨር የሚያሳብቁ ክስተቶች ናቸው። የምንሄድበትን መንገድ ሳናውቅ ጉዞ ስለምንጀምር እምብዛም ሳንጓዝ ይደክመናል፤ የመፈሳዊ ጉዞ መዳረሻችንን ስለማናውቅ ወደ ዓላማው የሚያደርሰን ራዕይ እና ከድካማችን ባሻገር የሚስበን ተስፋ የለንም። በመሆኑም በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምንፈልገው እርካታ እና ምላዓት “ላም አለኝ በሰማይ” ይሆንብናል።
የምንሄድበትን መንገድ እና የጉዟችንን ራዕይ በሚገባ አለመረዳት፣ ችግሩ ከቆምንበት ቦታ ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል። ስለዚህ ቦታ እንቀይራለን። በመንፈሳዊ ሕይወት ያለማደጋችን ቁም ነገር ካለንባት ቤተክርስትያን እምነት ይመስለናል።ስለዚህ ቤተክርስትያን እንቀይራለን። በቤተክርስትያን ከሞላው የክርስቶስ የጸጋ ስጦታ ይልቅ በእኛ የተንሸዋረረ ዕይታ የጎደለ ብለን ያመንነውን ነገር ለመንፈሳዊ ሕየወታችን አለማደግ ያንን ጉድለት ተጠያቂ እናደርጋለን፤ ስለዚህ ለራሳችን ቤተክርስትያን በመቀየር ከእሥራት የተፈታን፣ ወደ አርነት የወጣን አድርገን ራሳችንን እናቀርባለን፤ በአዲሱ ቤተክርስትያን ነገሮች የተሻሉ፣ የተስተካከሉ፣ ተስፋ የሚሰጡ ይመስለናል። በዚህም ተጽናንተን ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወታችን ስንመለስ በርግጥ እንደ ትናንቱ ነን። ጸጋ በሕይወታችን የጉዞ አቅጣጫ እና ራዕይ ሊሰጠን ስፍራ ባላገኘበት ሁኔታ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ፈቀቅ ማለት አይችልም። የምንሄድበትን ለማወቅ የእግዚአብሔር ብርሃን ያስፈልገናል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ይህንን ብርሃን የምናይበት ዐይኖች እንዲኩልልን በጸሎት መለመን እንጂ ቤተ ክርስትያን መቀየር ለመንፈሳዊ ዕድገት ዋስትና አይደለም።
በትዳሩ ደስተኛ ያልሆነ ሰው ከትዳር አጋሩ ጋር ባለው መስተጋብር ከትዳር አጋሩ በፊት የራሱን ሁለንተናዊ ዕድገት በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ቢመረምር ራሱን፣ ትዳሩን፣ የትዳር አጋሩን ሁሉ ለእግዚአብሔር መንግሥት ያተርፋል። ትዳሩን ፈትቶ በመሄድ የሚሰራው ኃጢአት በአዲሱ ትዳሩ ተስፋ ከሚያደርገው ደስታ፣ ምልዓትና ስኬት ጋር ሲገናዘብ ትዝብት ውስጥ የሚጥል በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፈሪ ተግባር ነው። ክርስትና መሰረቱ “በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” (ሉቃ 21፡19) የሚለው የጊታችን ትምህርት ነው። በትዕግሥት መጠበቅ የመንገደኛ፣ የነጋዲ ሁነኛ ባሕርይ ነው። በማወቅና ባለማውቅ፣ በተስፋ እና በድካም፣ በተለዋዋጭ አቋም እና ወሳኔ የሚደክም ክርስትያን መንፈሳዊ ሕይወቱን እንዴት ማቅናት ይችላል?
ከዚህ አይነት ድካም ለማረፍ የሚረዳ መንፈሳዊ ዕቅድ እንዲኖረን ጌታ በሉቃስ ወንጌል መሰረታዊ የሕይወት ፕሮግራም ያስተምራል፤ “ከእናንተ ግንብ ሊሰራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደሆነ አስቀደሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቆጥር ማነው?” (ሉቃ 14፡28)። ጌታ በዚህ ትምህርቱ ትርፍ እና ኪሳራን ስለማስላት፣ ዐቅምን ስለማወቅ እና ያለንን ይዘን ወደምንፈልገው ግብ ለመድረስ ስለማቀድ ይናገራል። ዐቢይ ጾም ወደ ትንሳኤ የምናደርገው ጉዞ ነው። ነገር ግን በፋሲካ ዕለት በኢየሩሳሌም መገኘት እና ትንሳኤን በኢየሩሳሌም ማክበር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የዐቢይ ጾም ዝግጅት የትንሳኤን በዓል እንዴት እንደምናከብር ይወስናል። እግዚአብሔር ጸጋውን የሚሰጠው እኛ ራሳችንን ለጸጋ ሥጦታ ክፍት ባደረግንበት ዝግጅት መጠን ነው። ስለዚህ መቀበል ስናስብ አስቀድመን የተቀበልነው ነገር የሚያርፍበት ሥፍራ ማዘጋጀት አለብን። የምንቀበለውን ነገር በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻልን ልክ እንደ ሐዋርያው ፊሊጶስ ከኢየሱስ ጋር ብንቆይም “ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል” (ዮሐ 14፡8) ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ስለዚህ በተሻለ መንፈሳዊ ተሐድሶ ወደ ትንሳኤ ለመጓዝ እንዴት እንዘጋጅ? ይቀጥላል...
ሴሞ