ዐቢይ ጾም
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Tuesday, 22 February 2022 20:24
- Written by Super User
- Hits: 1023
- 22 Feb
ዐቢይ ጾም
ባለፈው ጽሑፋችን “የምትሄድበትን ዕወቅ” በሚል ርዕስ ለዐቢይ ጾም መንደርደርያ የሚሆን ንባብ አቅርበንላችሁ እንደነበር የሚታወስ ነው። (የክፍል አንድን ጽሑፍ ይህንን ማስፈንጠርያ በመጫን ማንበብ ይችላሉ የምትሄድበትን ዕወቅ (ethiocist.org) ) በዛሬው ጽሑፋችን ከክፍል አንድ የቀጠለውን እና ወደ ክፍል ሦስት መንደርደርያ የሆነውን ክፍል ትኩረታችንን የዐቢይ ጾም ምንነት ላይ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ!
ስለ ዐቢይ ጾም ስናስብ ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ከምግብ መከልከል እና ከእርሱ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ነጥቦች ናቸው፤ ነገር ግን በመከልከል ውስጥ ያለን መታመን እምብዛም አናስበውም። ጾም እንደ ቀሬናዊው ስምኦን የኢየሱስን መስቀል ለመሸክም መታምን እና ከኢየሱስ ጋር ወደ ጎሎጎታ፣ ወደ መስቀሉ ምሥጢር፣ በአትክልቱ ሥፍራ ወደሚገኘው እኛም ከእርሱ ጋር በጥምቀታችን ቃልኪዳን ወደተቀበርንበት መቃብር ወርደን ከጌታ ጋር ትንሳኤን ተስፋ ማድረግ ነው።
ዐቢይ ጾም በየዓመቱ የሚመላለስ ተራ ድግግሞሽ እና ያለፈን ነገር የምንዘክርበት የቤተክርስትያን ሥርዐት ሳይሆን ዐቢይ ጾም የጸጋ ጊዜ ነው። ዐቢይ ጾም ከቅዱስ ዳዊት ጋር “በሂሶጵ እርጨኝ እነጻለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶ ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” (መዝ 51፡7) እያለ የሚዘምር ክርስትያን እግዚአብሔር በእርሱ የጀመረውን መልካም ነገር ሁሉ ወደ ተወደደ ፍጻሜ እንዲያደርስ የሚታገስበት፣ የሚጠብቅበት የጸጋ ወቅት ነው። የክርስትና ሕይወት ከዐቢይ ጾም የተለየ አይደለም፤ የትንሳኤ እምነት የተቀበለ ክርስትያን ከኢየሱስ ጋር በአንድነት እግዚአብሔር አብን በመንፈስ ቅዱስ በሰማያዊ ዙፋኑ ፊት እስኪያመሰግነው ድረስ በዐቢይ ጾም ላይ ነው። ክርስትና በ “ተወረሰ ተስፋ እና ተስፋ በሚደረግ ፍጻሜ” (christianity between „already“ but „not yet“)[1] መካከል የሚኖር እምነት እንደመሆኑ መጠን ዘወትር ከትንሳኤ በተወረሰ ተስፋ ወደ ተስፋ ፍጻሜ በጉዞ ላይ ነን። ዐቢይ ጾም የጉዟችን አንደኛው ገጽታ እንጂ በጊዜ ቀመር ዑደት በየዓመቱ የሚደጋገም ዝክር አይደለም።
በዐቢይ ጾም የምናደርገው ነገር ሁሉ በጥምቀታችን የተቀበልነው ክርስትያናዊ ተልዕኮ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያስተምረው “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ገላ 6፡4)። የዐቢይ ጾም ጉዞ በሞቱ በኩል ወደ ትንሳኤው የሚደረግ የእምነት ጉዞ ነው። በጥምቀታችን የተቀበልነው አዲስ ሕይወት ከሞቱ ጋር ባለን ኅብረት የተገኘ ጸጋ እንደመሆኑ መጠን የዐቢይ ጾም ወቅት ሞቱን በሥጋዬ የምካፈልበት የምስክርነት ዘመን ነው።
የዐቢይ ጾም ጊዜ በላባችን ወደ መዳን ለመድረስ የምናከናወነው መንፈሳዊ የአቋም መለኪያ ውድድር አይደለም ነገር ግን በጸጋ ሁሉ ሥጦታ ለማደግ በጌታ እግሮች ስር ተቀምጠን የሚሻለውን የምንመርጥበት (ሉቃ 10፡42)፣ በተሻለው ለመኖር የምንሰለጥንበት መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ነው። ዐቢይ ጾም ምድርና ሰማይ የሚቀራረቡበት፣ ድካም በጸጋ የሚታደስበት የአማኞች ጊዜ ነው። በዚህ የጸጋ ጊዜ ነፍስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃይሏን እንደ ንስር የምታድስበት፣ ስብራቶቿን በፊቱ ግልጽ የምታደርግበት፣ ካልባረከኝ አልለቅህም የምትልበት ጊዜ ነው። ነፍስ ከእግዚአብሔር የቃሉን ጥበብ በመሻት “በአፉ መሳም ይሳመኝ” (መኃ 1፡2) እያለች ትዘምራለች! የዐቢይ ጾም ጊዜ የክርስቶስ ወታደር ነኝ የሚል አማኝ በነገር ሁሉ ላይ የሠራዊት ሁሉ ጌታ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ስም የአሸናፊነት ክንዱን ያነሳ ዘንድ ጌታ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት የጾመበትን እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ገንዘቡ ለማድረግ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኢየሱስን የሚጠራበትን እምነት የሚማርበት የጸጋ ትምህርት ቤት ነው።
ዐቢይ ጾም ወደ ትንሳኤ የሚደረግ ጉዞ እንደመሆኑ መጠን ወደ ትንሳኤ በሚያደርሰኝ መንገድ እና ውስጣዊ ፍጽምና መጓዝ ይገባኛል። ነገር ግን ወደ ትንሳኤ የሚያደርሰኝ መንገድ የቱ ነው? የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ለዚህ ጥያቄ መልስ ፍንጭ ሊሰጠን በሚችል መልኩ “እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ምስክሮች በዙርያችን እንደ ደመና ካሉልን” (12፡1) እያለ ክርስትና ለብቻ የሚኖር ሳይሆን ወደፊት ሞትን ድል አድርጎ ወደተነሳው ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ወደ ኋላ ወደ ክርስትናችን ታሪክና ወደ እምነት አባቶቻችን ምስክርነት እየተመለከትን ደግሞም ዛሬ ላይ በተሰጠን የቤተክርስትያን እምነት እንደ ቤተ ክርስትያን የምንኖረው ቁም ነገር ነው። ስለዚህ ወደ ትንሳኤ የሚያደርሰኝን መንገድ ለማወቅ ከፈለኩኝ መንፈስ ወደ በረሃ የወሰደውን እርሱን ማስተዋል ይገባኛል። ኢየሱስ እነዚህን ጊዜያት እንዴት ነበር የተመላለሰው? ይቀጥላል...
ሴሞ
[1] J. Ratzinger, the spirit of the liturgy, Ignatius, (2000), 92-112