እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

እሺታ! Fiat!

እሺታ! Fiat!

fiat-1በግንቦት ወር መክፈቻ የእመቤታችን ልደት አክብረን፣ በዚህ በእመቤታችን ወር በተለየ መንፈሳዊነት ከእመቤታችን ጋር ስንጓዝ ቆይተናል። በእርግጥ የእመቤታችንን መንፈሳዊ ሕይወት በሚገባ ለሚያስተነትን ክርስትያን እያንዳንዱ ቀን ከእርሷ መንፈሳዊነት የሚማርበት የጸጋ አጋጣሚ መሆኑን ለማስተዋል አይቸገርም። እመቤታችን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበራት ሕይወት፣ የእግዚአብሔርን ቃል የምታስተነትንበት ጥልቀት እና የመንፈሳዊ ሕይወቷ ትህትና የክርስትናን ምሥጢር ለመማር ለሚፈልግ ሁሉ ትልቅ የመንፈሳዊ ሕይወት ትምህርት ቤት ናት። ቤተ ክርስትያን የእመቤታችንን መንፈሳዊነት እንድንለማመድ ስትጋብዘን በሌላ አነጋገር ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ምን እንደሚመስል እንድናስተውል እና እንድንማር ለማድረግ በማሰብ ነው።

በእመቤታችን ውስጥ “ቃል ሥጋ” ሆኗል! ይህንን ማስተዋል ምን ያህል ዘመን ይፈጃል? በዚህ ላይ መጸለይ በዕድሜ ዘመን የሚደረስበት ምሥጢር አይደለም። ቃል በሕይወቱ ሥጋ የለበሰበት ፍጥረት በሰማይም በምድርም እመቤታችን ብቻ ናት፤ ቃል ሥጋ የሆነበት ሕይወት ምን አይነት ሕይወት ነው? የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት ባለ የእምነት መታዘዝ ብትቀበለው ነው በውስጧ ሥጋ ይሆን ዘንድ ሰማይ እና ምድር የማይሸከሙት ልዑል አምላክ በዚያች ወጣት ሴት ሕይወት ውስጥ የተገለጠው? መንፈስ ቅዱስ በእምነቷ እና በትህትናዋ እንዴት ተገርሞ ይሆን? እግዚአብሔር በትሕትናው የሚገረምበት ሰው እንዴት ያለ ሰው ነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” (ዮሐ 14፡23) እያለ የተናገረው ቃል በእመቤታችን ሕይወት ውስጥ ፍንትው ብሎ ይታያል። በእግዚአብሔር ቃል የሚያምን፣ በመንፈስ እና በእውነት እንደ እግዚአብሔር ቃል መኖር የሚፈልግ አማኝ ሁሉ የእመቤታችንን ሕይወት ማጥናት ይጠበቅበታል፤ ከእመቤታችን በስተቀር በክርስጽቶስ ኢየሱስ መኖር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ሊያሳየን የሚችል ሌላ ፍጥረት የለም። ቅዱሳን ከእርሷ ሕይወት በተማሩት መሰረት የሚፈልጉትን የሕይወትን ጌታ አግኝተውታል፤ በመሆኑም እነርሱ ያገኙትን ኢየሱስን እኛም በሕይወታችን እናገኘው ዘንድ ወደ መዳረሻችን የምትመራን የባህር ኮከብ እያሉ ይጠሯታል።

በእመቤታችን ውስጥ ፍጥረት ሁሉ እንደ አዲስ ያብባል፤ ፍጥረት ለተፈጠረበት የተቀደሰ ዓላማ እንዴት መኖር እንደሚችል ከእርሷ ሕይወት ይማራል፤ በእግዚአብሔር መኖር፣ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ እና በትንሳኤ ሕይወት መኖር እንዴት እንደሆነ ከእመቤታችን ሕይወት በግልጽ ይመለከታል። እመቤታችን አዲሱ ዘር የበቀለባት ለም መሬት፣ ለእግዚአብሔር ሥራ የተሰናዳች አረም የሌለባት ንጹህ ማሳ ናት፤ እርሷ እግዚአብሔር አዲሱን ዘር ወደ ዓለም ይልክ ዘንድ፣ ቃሉን በአደራ ይሰጥ ዘንድ ልቡ የታመነባት፣ ሕይወት የሚሆን በረከት የሞላባት ለም መሬት ናት። እርሷ በመልካም መሬት ላይ የወደቀውን የሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ የተቀበለችው፣ “የሰው ዘር ሁሉ ለእግዚአብሔር ሥራ እሺ ብሎ የታዘዘባት የፍጥረት ሁሉ እሺታ ናት!”።

በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር ውስጥ ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አስቀድሞ በተፈጠረበት ጸዳል አዲስ ፍጥረት ሆኖ ተገልጧል። በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር ውስጥ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ኃጢአት ተነስቷል፤ ሰው እና እግዚአብሔርን ለያይቶ የነበረው ኃጢአት ቃል ወደ ዓለም በመግባቱ ምሥጢር በኩል አሁን ስፍራ የለውም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በመገለጡ ምሥጢር በኩል መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጅ አዲስ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የመለኮታዊ ሕይወት ተካፋይ ይሆን ዘንድ በር ከፍቶለታል። መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የመልበስ ምሥጢር በኩል “የምድርን ገጽ አድሷል”! ይህ መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ሕይወት ሞልቶ እንደሚንቀሳቀስ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ሕይወት እንደ መለኮታዊ ፈቃዱ በጎነት እና ዓላማ ይንቀሳቀስ ዘንድ እመቤታችን “እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት ሙሉ ፈቃድዋን ሰጥታዋለች። በመሆኑም በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው አዲስ ፍጥረት ምን እንደሚመስል እና እንዴት እንደሚመላለስ ከእመቤታችን ሕይወት በሚገባ ማስተዋል እና ማድነቅ ይቻላል። በላቲን ሥርዐተ አምልኮ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዋዜማ የሰርክ ጸሎት ላይ ቤተክርስትያን እንዲህ እያለች ትዘምራለች፡-

“ክርስቶስ ሆይ አንተ በምድር ላይ እንደ ሰው ተገልጠሃልና ላንተ የሚሆን እጅ መንሻ ምን እናቀርብልህ ዘንድ ይገባናል? ካንተ ላንተ የሆነው ፍጥረት ሁሉ ምሥጋናውን ይዞ በፊትህ ይቆማል። መላእክት መዝሙራቸውን፣ ሰማይም ኮከቡን፣ ሰብዓ-ሰገል ሥጦታቸውን፣ እረኞችም ስግደታቸውን፣ ምድርም ያቺን ብቸኛ ግርግም፣ ዛፎችም የተኛህባትን የእንጨት ጣባ አቀረቡልህ፤ እኛ የሰው ልጆች ደግሞ ድንግልም እናትም የሆነችህን እመቤት ይዘን በፊትህ እንቀርባለን”

የእመቤታችንን ሕይወት በመመልከት እና ቃል ሥጋ በመልበሱ ምሥጢር ውስጥ ያላትን ሱታፌ በማሰላሰል እያንንዳንዱ አማኝ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ሕይወት የራሱን ኃላፊነት እንዲያስተውል ይጋበዛል፤ አማኝ ራሱን እና ፍጥረትን ሁሉ ለተፈጠረበት ዓላማ በሚቀድስ መታዘዝ ለመንፈስ ቅዱስ ስራ ሊሰጥ የሚገባውን “እሺታ” እና እሺታው የሚያስገኘውን በረከት ከእመቤታችን ሕይወት በልቅም ማስተዋል ይችላል። በጌታን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በኩል ክርስትያናዊ ሕይወት ከፍጥረት ሁሉ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ቁም ነገር ነው፤ እርሱ ሰው ሆኖ በመገለጡ የሰውን ልጆች ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ፍጥረትን በሙሉ ለተፈጠረበት ክቡር ዓላማ ቀድሶታል። በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ፍጥረት ሁሉ በቀደመው ውብ ማንነቱ በምልዓት ተገልጦ ይታያል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስያስ ክርስትያኖች ስለዚህ ምሥጢር ሲጽፍላቸው እንዲህ ይላል፡-

እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል (ቆላ 1፡16)።

በመሆኑም የጌታ ዕርገት ምንም እንኳን በዚህ ዓለም የነበረውን ግዙፋዊ መገለጥ የደመደመ ቢሆንም፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ፣ በጰራቅሊጦስ በኩል ጌታ በመካከላችን እንደ አዲስ ተልጧል። ይህ አዲስ መገለጥ ቤተ ክርስትያን የተወለደችበት መገለጥ ሲሆን በዚህም ቤተ ክርስትያን የእመቤታችንን መንፈሳዊ ሕይወት እና ጥሪ እየተመለከትች “የእግዚአብሔርን ቃል በልቧ ይዛ በማሰላሰል” (ሉቃ 2፡51) እውነተኛ የክርስቶስ አካል ሆና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ፍጻሜ ትጓዛለች። የእመቤታችን ሕይወት የሚመሰክረው ክርስቶሳዊ ሕይወት እና በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በእግዚአብሔር ቃል የመሞላት ቁም ነገር የሰው ልጅ ስለ እግዚአብሔር አዲስ መረዳት፣ አዲስ መገለጥ እና አዲስ ዕውቀት እንዲያገኝ ሳይሆን ይልቁንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በቅድስት ሥላሴ ምሥጢራዊ ሕይወት ውስጥ ሱታፌ እንዲኖረው እና ከእግዚአብሔር ማዕከል የተነሳ አዲስ ሕይወት እንዲኖረው የሚያደርግ ቁም ነገር ነው።

በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው አዲስ ፍጥረት ከቅድስት ሥላሴ ማዕከል በተነሳ ሕይወት ይመላለስ ዘንድ በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት ከዚህ ምሥጢር ጋር ተቆራኝቷል። እመቤታችን በመንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በታዘዘው እሺታዋ አማካይነት ፍጥረት ሁሉ ለእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ክፍት ሆኖ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስራ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝ ዘንድ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ እና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን ያድር ዘንድ ፍትረትን ሁሉ ወክላ በእግዚአብሔር ፊት “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ!” በማለት የእምነት ምሥክርነቷን ሰጥታለች።

በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ የሚያምን ክርስትያን ሁሉ ጥሪ እና መንፈሳዊ ሕይወት “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ!” የሚል የእምነት ምሥክርነት መስጠት እና ይህንኑ በተግባር መኖር ነው። በአጭሩ ክርስትያናዊ ሕይወት ማርያማዊ ሕይወት ነው። ክርስትያን ነኝ የሚል ቢኖር ከዚህ የተለየ ሌላ ሕይወት የለውም! እያንዳንዱ ክርስትያን ከእመቤታችን ጋር በአንድ ድምጽ “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ!” እያለ የሚዘመር የአዲስ ኪዳን አዲስ ፍጥረት ነው።

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት