እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ፍልሰታ ለማርያም

Emebetachinእንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እንወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ወልደኪ ኄር መድኃኔ ዓለም” /ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን እንማጠናለን።
በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይ የምሥራቃዊ ሥርዓተ አምልኮ የሚከተሉ አገረ ስብከቶች ማለትም የአዲስ አበባ፣ የዓዲግራትና የእምድብር አገረ ስብከት ምእመናን በነዚህ ቀናት የሚደረገውን ጾምና ልዩ መንፈሳዊነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ምእመናን ጋር የሚጋሩ ሲሆን ከበስተጀርባ ያለውን የአገራችንን ትውፊት አውቀን ይህን ወቅት የመጠቀሙን አስፈላጊነት ስላመንበት ከ http://www.zeorthodox.org/ ድረ ገጽ ያገኘነውንና ከቃሉ ትርጉም በመነሣት ከትውፊትና ከቅዱስ መጽሐፍት በማጣቀስ የፍልሰታ ለማርያምን ትርጉምና መንፈሳዊነት የሚገልጸውን ጽሑፍ ቃል በቃል ከዚህ በታች አስፍረነዋል።
• ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገርነው፡፡
• እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡
• እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘች
ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡
• እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡
• ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር 136፡8 “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሎአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
• ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ… ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ መኃ 2፡1አ-13
• ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡
ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/
• የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ መዝ 14፡13 የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን አረፈች፡፡
• እመቤታችን ጥር 21 ቀን እረፍት በሆነበት እለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ እረፍት ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል" እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች አረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡእ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች (ስንክሳር ዘጥር፡፡)
• የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ መዝ 44፡9
• ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
• የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን - መግነዟን ሰጥታው አረገች፡፡
• ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን;” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን - መግነዟን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡
• ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ረዳት ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ ዋና ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን እርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡
• ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና እርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጻመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡
• የእመቤታችን ትንሣኤና እርገት መታሰቢያ - በጾመ ፍልሰታ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡
• ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡
• በዚሁ በነሐሴ 16 ቀን የሰማእቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሰቱ ነው፡፡ ሥጋው ከፋርስ ሀገር ወደ ሀገሩ ወደ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው፡፡ ፍልሰቴን ከፍልሰትሽ አድርጊልኝ፣ ብሎ ለምኗት ስለነበር ፍልሰቱ ከእመቤታችን ፍልሰት ጋር እንዳሰበው ሆኖለታል፡፡ ስለዚህም እርሷን መውደዱ የሚያውቁ ሥእሉን ከሥእሏ አጠገብ ይስላሉ፡፡ በስሙ ለሚማጸኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ፡፡
የእመቤታችን አማላጅነቷ አይለየን አሜን፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት