Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ር.ሊ.ጳ. የታገቱት ካቶሊኮች ይለቀቁ ዘንድ ድምፃቸውን አሰሙ !

ር.ሊ.ጳ. የታገቱት ካቶሊኮች ይለቀቁ ዘንድ ድምፃቸውን አሰሙ !

pope cameር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በደቡብ ምዕራብ ካሜሩን የታገቱት ካቶሊኮች ይለቀቁ ዘንድ ድምፃቸውን አሰምተዋል።“በማምፈ ሀገረ ስብከት አምስት ካህናትንና መነኩሲት እህት እንዲሁም ሌሎች የታገቱ ሰዎች ይለቀቁ ዘንድ አቤት ከሚሉት የካሜሩን ጳጳሳት ጋር አብሮነቴን እገልጻለሁ” ብለዋል። መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በእለተ ሰንበት “የብሥራተ ገብርኤል” የቀትር ጸሎት በደቡብ ጣልያን ከምትገኘው ማቴራ ከተማ ሆነው መልእክታቸውን ሲያስተላልፉ ላለፉት አምስት ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ካሜሩን ጌታ ሰላሙን እንዲሰጣትም መጸለያቸው ታውቋል።

መስከረም 6 ቀን ምሽት ላይ ካሜሩን ውስጥ ንቻንግ በሚባል ቦታ በምትገኘው የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ታጣቂ ሰዎች ጥቃት አድርሰው አምስት ካህናትን፣ መነኩሲት እህትን፣ በደብሩ የሚኖሩ አንዲት የግቢው ሠራተኛን፣ ትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪንና አንዲት የ15 ዓመት ታዳጊን ማገታቸውን የቫቲካን ዜና ዘገባ ገልጿል።

የካሜሩን ጳጳሳት ባወጡት መግለጫ ይህን ጥቃት በጥብቅ ያወገዙ ሲሆን፣ በፍጥነትም የታገቱትን ሁሉ እንዲለቀቁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፤ “ይህን ሀሳብ በአጽንዖት በቀጣይነት የምናስተላልፍበት ምክንያት አሁን ላይ ድርጊቱ ገደቡን ያለፈ ስለሆነ ነው፣ እናም በቃ ማለት በቃ ነው!” ብለዋል።

በቅርብ ጊዜያት በካሜሩን ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠሩ፣ እንደ ቦታው ጳጳሳት ገለጻም “መዋቅሯ ላይ ተድጋጋሚ የማሳደድ ማዕበሎች” እየደረሱ መሆኑ ተዘግቧል። አያይዘውም ጳጳሳቱ ራሳቸውን ለሕዝብ አገልግሎት የሰጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችን የሚቃወሙና ሁሉንም ዓይነት የሆኑ የዛቻ መልእክቶች እየተላኩባቸው መሆኑን በመግለጫቸው አሳውቀዋል።

የማምፈ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ አሎይሲየስ ፎንደግ አባጋሎ በእሳት ቃጠሎ በወደመችው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በፍርስራሹ መካከል መንበረ ቁርባኑ ሳይሰበር ማግኘታቸውንና ከዚያም ቅዱስ ቁርባንን አውጥተው ወደ ሌላ ቦታ ራሳቸው ማሻገራቸው በጊዜው የተቀረጸው ቪዲዮ ያስረዳል። እሳቸውም “በአገልጋዮቹ ላይ የደረሰው እገታና ቤተ ክርስቲያንን የማራከስ ሂደት እንደ ቤተ ክርስቲያን ከባድ ሁኔታን ፈጥሮብናል” በማለት ገልጸዋል። ሆኖም ይላሉ ሲቀጥሉ “ይህን መሰል ስቃይን የተስፋችንና የድላችን ምንጭ ከሆነው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ጋር ማስተሳሰራችንን አንዘነጋም” ብለዋል።

በተያያዘ ዜና እነዚህን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ያገቱ ታጣቂዎች አንድ መቶ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ካልተከፈላቸው ታጋቾችን እንደማይለቁ የካሜሩን ሊቀ ጳጳሳት አንድሪው ንኪያ ፉዋንያ መግለጻቸው ታውቋል።

ምንጭ፦ Catholic News Agency

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።