እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

7. ክርስቲያናዊ ምነና

7. ክርስቲያናዊ ምነና

ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳልነው ምናኔና ብሕትውና የሚሉት ቃላት ከምንኩስና ሕይወት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ትርጉም ቢያስተላልፉም ቅሉ በጊዜ ሂደትም ሆነ በአናኗር ዘይቤ ይለያያሉ። ስለዚህም የክርስቲያናዊ ምንኩስናን አጀማመርና ታሪክ ለመረዳት የክርስቲያናዊ ምነናን ቀዳሚነትና አመጣጡን ማየቱ ጠቃሚ ነው።

የክርስቲያን ወንጌል የተሰበከበት ጥንታዊ ዓለም ወጥ የሆነ አንድ ዓይነት ባህል ብቻ የነበረበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦችና ባህሎች ተሰበጣጥረው በሚኖሩበት ዘመን ነው ክርስትና በአዲስ ኃይል መሰበክ የጀመረው። ክርስትና ከአይሁድ ምድር በወጣ መጠን ለግሪክ ባህልና አስተሳሰብ መጋለጥ እጣ ፈንታው ነበር፤ ይህንንም ግሪካዊ ጫና በወንጌሎችና በሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቶች በተለያዩ ቦታዎች እናገኛለን። የወንጌል መልእክትን እንደሚገባ አድርጎ ለማስተላለፍ የግሪክ ቃላትን፣ ፍልስፍናንና ሃሳባትን መዋስ ግድ ነበር። ከነዚህም ሃሳቦች መካከል የምነና ሕይወት ዘይቤ ዋነኛውና ተጠቃሽ ሃሳብ ነው።

ለጥንታውያን ግሪኮች የምነና ሃሳብ ዋና መሠረታዊ ቁርኝት ከሯጮችና መሰል የአካል እንቅስቃሴ ከሚያዘወትሩ ሰዎች (አትሌቶች) ልምምድ ጋር የተያያዘ ነበር። ቀስ በቀስ ከአካላዊ ልምምድ ወደ ሞራላዊ ልምምድና የሕይወት አናኗር ክፍል ተሸጋገረ። በዚህም መሠረት ከእንቅልፍ፣ ከተወሰኑ ዓይነት ምግብና መጠጥ፣ ከወሲባዊ ግንኙነት መቆጠብን፣ በድህነት መኖርንና መጾምን ማካተት ጀመረ። ከላይ በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው ክርስቲያን ባልሆኑ ሃይማኖቶች ቀደም ብለው በተለያዩ ዓላማዎች እነዚህ ነገሮች ነበሩ። በአዲስ ኪዳንም የዘመኑን ምናኔ ተፅእኖ ከሚገልጹ ጽሑፎች መካከል 1ቆሮ. 7:31፤ ማር.10:17-31፤ ማቴ.6:19-20፤ 10:16-23፤ 19:12፤ 19:16-22፤ ሉቃ.12:13-21 ን መጥቀስ ይቻላል።

ጥንታዊው ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ክርስቲያናዊ ካልሆነው ምናኔ የወረሳቸው ጥሩ ያልሆኑ ብለን ልንጠቅስ ከምንችለው ነገሮች ዋነኛው ነገሮችን ሁሉ በሁለት ነገሮች ማለትም ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ የመወገን ሂደት (Dualism) ነው። ይህ አስተሳሰብ ሥጋ መጥፎ ነገርና ክፉ ስለሆነ ነፍስ ከርሱ ነጻ መውጣት አለባት ይል ነበር። ስለዚህም የምናኔ ሕይወት ለዚህ ዓላማ የሚያግዝ አንድ መንገድ ሆኖ ተገኘ። በክርስቲያኖች መካከል ይህንን ሃሳብ የሚያራምዱ ግኖስቲክስ የሚባሉ ቡድኖች ተነሥተው በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ውዝግቦችን ፈጥረዋል።

ይህን ሃሳብ ማየታችን ምናኔን በድፍኑ ጥሩ ነው ወይም መጥፎ ነው ብለን ፈርጀን ከማለፍ ይልቅ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን የሚችልበትን ነገር አስበን ከታሪኩ ተምረን ለማለፍ እንዲጠቅመንና ክርስቲያናዊ ምናኔ ከኢክርስቲያናዊው ምናኔ በምን እንደሚለይ፤ እንዲሁም ከምንኩስና ሕይወት ጋር ምን ዓይነት ታሪካዊና ተግባራዊ ትስስር እንዳለው ለመገንዘብ እንዲያግዘን ነው።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው ክ.ዘ. የነበረ ፊሎ ዘአለክሳንደሪያ የሚባል አይሁዳዊ ፈላስፋ በ50 ዓ.ም. አካባቢ <<On the Contemplative Life>> በሚል መጽሐፉ አሴናውያንና ቴራፐውተ ስለሚባሉ አይሁዳውያን ቡድኖች ገዳማዊ (ማኅበራዊ) ሕይወት የጻፈው ጽሑፍ የኋላ ኋላ የክርስቲያናዊ ምናኔና ድንግልና ሃሳብን ያስፋፉ ታላላቅ ክርስቲያን ጸሐፊዎች እነ ቅዱስ ቀለሜንጦስ፣ ጤርጡላያኖስና ኦሪገን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም። በክርስቲያኖች መካከል የመጀመሪያዎቹ መናንያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ በመጾም፣ ከወሲብ በመራቅና በጸሎት ይኖሩ የነበሩ በአቅራቢያቸው ያለችውንም ቤተ ክርስቲያን ያገለግሉ የነበሩ ደናግልና መበለቶች ናቸው። ይህን መሰል ሕይወት የነበራቸው ሰዎች በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ይከበሩ ነበር፤ ቀደምት አበውም ስለዚህ ዓይነት አናኗር ጠቃሚነት ጽፈዋል።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት