ዘፍሬ - ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ወይባርከነ እግዚአብሔር አምላክነ፤ ወይባርከነ እግዚአብሔር። ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል፤ እግዚአብሔር ይባርከናል። መዝ. 66:6-7 - ንባባት፡- 2ቆሮ.9:1-15, ያዕ.5:1-9, ሐዋ. ሥራ 19:21-40, ማር. 4:24-3
ሕይወታችን የሁለት ገበሬዎች የእርሻ ማሳ ናት።
በአዲስ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ላይ እንደመገኘታችን መጠን ይህንን ሁለተኛ ሰንበት ቤተ ክርስቲያን <<ዘፍሬ>> ብላ ሠይማዋለች። በርግጥ ፍሬ መጨረሻ ላይ የሚታፈስ፣ የሚለቀምና የሚሰበሰብ ሲሆን መጀመሪያ ላይ ስለፍሬ ማውራቱ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? ብለን ካሰብን ለዚህ መልስ እንዲሆነንና ለአስተንትኗችን እንዲያግዘን በዕለቱ ወንጌል ውስጥ የተካተቱ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተናገራቸውን ሁለት ምሳሌዎች እንይ።
የመጀመሪያው ምሳሌ ምዕ.4:26-29 ሲሆን የሚዘራ ገበሬ ከዘራ በኋላ <<ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።>> ይለናል። ይህን ከክርስቲያናዊ ሕይወታችን አቅጣጫ ካየነው ክርስትና በሁለት ጽንፎች መካከል የሚገኝ መሆኑን ያሳየናል። ማድረግ የሚገባንን ማድረግና እግዚአብሔር ብቻ ሊሠራው በሚችለው ነገር ደግሞ ያለመጨነቅ ወይም ለርሱ መተው።
ገበሬው ሳይዘራ እንደማያጭድ ሁሉ በመመኘት ብቻ ፍሬ አይሰበሰብም፤ በተቃራኒውም ደግሞ በመጣጣርና ሁሉን እኔ አደርገዋለሁ በማለት ፍሬን ማሳደግና ማብቀል አንችልም - ምክንያቱም ገበሬው ከዘራ በኋላ ማለትም ለዘሩ ማድረግ የሚገባውን ካደረገ በኋላ ይተኛል ይነሣል እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል ይላል ወንጌል። በሌላ አባባል በእምነታችን የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደተቆጣጠርን ሆነን መመጻደቅ አንችልም ምክንያቱም ባለቤቱ ራሱ እግዚአብሔር ነውና፤ እንዲሁም እሱ የማድረግንና የመኖርን ኀላፊነት ሰጥቶናልና ክርስትናችንን በእምነትና በተግባር መካከል ሚዛን ጠብቀን መኖር አለብን። በልቤ አምናለሁ በቃ! ወይም መልካም ነገር አደርጋለሁ፣ ለሰው ክፉ አልሆንም ሌላ እምነት፣ ሃይማኖት…አያስፈልገኝም ማለት አንችልም። ሕይወታችን እኛና እግዚአብሔር ተጋግዘን የምንሠራባት የሁለት ገበሬዎች የእርሻ ማሳ ናት።
ሁለተኛው ምሳሌ በምዕ.4:30-32 ውስጥ ሲሆን የእግዚአብሔር መንግሥት በጣም ደቃቃ በሆነችው በሰናፍጭ ዘር ተመስላ ኋላም ይህች ሚጢጢ መስላ የምትታየው ነገር በጊዜዋ ትልቅ ዛፍ ሆና ለሌሎች ማረፊያና ከለላ እንደምትሆን ያስረዳናል። በትንሹ ታማኝ የሆነ በትልቁ ታምኝ ይሆናል እንደሚለው ሉቃ. 16:10 ክርስትና በትንሽ ነገር ነው የሚጀመረው።
በመጀመሪያው ምሳሌ ውስጥ እምነትን ስለመኖር አይተናል፤ ያ ማለት ግን ትላልቅ ጀብዱዎችን ወይም ተአምራትን መፈጸም ማለት አይደለም ይልቁንም የተናቁ የሚመስሉ ነገሮችን በየዕለታዊ ሕይወታችን መለማመዱ ነው ቁም ነገሩ። ይህ በየቀኑ ስለክርስትናችን ማለትም ስለክርስቶስ ብለን የምናደርገው ነገር ከክርስቶስ ጋር እያተሳሰረን ይሄዳል። በተቃራኒውም ክፉ ነገሮችን ብናይ ተመሳሳይ አካሄድ ነው ያላቸው። ማንም ሰው በአንድ ቀን የሱስ ባሪያ አይሆንም። ትንሽ በትንሽ በየጊዜው ያደርገዋል መጨረሻ ላይ መውጣት እስከማይችል ድረስ በሱስ ይጠመዳል።
ስለዚህ በውስጣችን እያደገ ያለውን ዘር ማየትና የኛንም ትብብር ማስተዋል አለብን። የጊዜ ሂደት በራሱ ወደ አንድ ፍጻሜ ያደርሰናል፤ ያ ፍጻሜያችን ግን የዛሬ አናኗራችን ድምር ነውና የተራ ነገሮች ባሪያ ከሚያደርጉን ነገሮች ርቀን የእግዚአብሔር ባሪያ ሊያደርጉን የሚችሉት ትናንሽ ተግባሮችን ለማድረግ በእምነት እንጣር።