እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘክረምት 9ኛ

ዘክረምት 9ኛ - ዘዕጕለ ቋዓት

ዕብ. 3:1-19     ያዕ.5:1-11       ሐዋ.22:1-21         ዮሐ.6:41-71

ቅዱስ ቁርባንለዚህ ሰንበት አስተንትኖ ያግዘን ዘንድ በወንጌል ያሉትን አንዳንድ ነጥቦች እንውሰድ። የዛሬው ወንጌል ንባብ የዘወትር የክርስቶስ ትምህርት ባህርይንና የሰው ልጅም ለርሱ ትምህርት የሚሰጠውን ግብረ ምላሽ ያንጸባርቃል። መቼም ቢሆን የክርስቶስ ትምህርት ወይም መልእክት ቀላል ሆኖ አያውቅም፤ ከዚህም የተነሣ ዘወትር ብዙዎች ይከራከሩበታል ፦ “ይህ ሰው ሥጋውን እንበላ ዘንድ እንዴት ሊሰጠን ይችላል? በማለት አይሁዳውያን ተከራከሩ”(ዮሐ.6:52)፣ ሌሎች ብዙዎችም እሱን መከተል ጀምረው ወደ ኋላ ያፈገፍጉበታል ወይም ይደናቀፉበታል ፦ “…ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢየሱስን መከተል ተዉ”(6:66)፣ የተወሰኑ ወይም ጥቂቶች ደግሞ ንግግሩ ከባድና እንዴት ይሆናል የሚያስብል ቢሆንም ተናጋሪው እሱ ራሱ ክርስቶስ ነውና ከርሱ ጋር አብረው መሆንን ይመርጣሉ ፦ “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን፤ አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አምነናል፤ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ አንተ እንደሆንህም ዐውቀናል።”(6:68)።  ምናልባት እኛ ራሳችንን በቀጥታ ከነዚህ ጋር ማመሳሰሉ ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን በተግባራዊ መልኩ ይህን ሀሳብ ስናየው ልናያይዘው የምንችለው በቀጥታ ለቅዱስ ቁርባን ወይም ለቅዳሴ ካለን ግንዛቤ፣ እምነትና ልምምዳችን አንጻር ነው።

በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ማለትም ቅዱስ ቁርባንን በሚመለከት የሆነ ነጥብ ሲነሣ ባብዛኛው የተለመዱ አባባሎች አሉ ፦ "የተወሰነ ጊዜ አዘወትር ነበር፣ ማመንማ አምነዋለሁ ግን፤ እስቲ ወደፊት…ወዘተ" እና መሳይ አቋሞች ናቸው። ቅዱስ ቁርባን በምግብ መልክ ለዘላለማዊነት የተሰጠን ቅዱስ ማዕድ ስለሆነ እንደማንኛውም ምግብ ሁሉ የአሁን ጉዳይ ነው። አንድ ሰው ከምግብ አሁን ርቄያለሁ፣ ትቻለሁ፣ ድሮ እበላ ነበር...ቢለን ቆም ብለን ይህ ሰው ጤነኛ ነው እንደዚህ እንዴት ሊኖር ይችላል ብለን ሃሳቡን መቀበሉ ይከብደናል። ስለ ቅዱስ ቁርባንም በክርስቶስ ፊት እንደዚያ ስንል እሱ ነፍሳችን ያለርሱ ምንም መሆኗን ይውቃልና “ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” ይለናል።

እዚህ ላይ ለቅዳሴ ያለንን ግንዛቤና አቋም እናስተውል። ምን ያህልስ የሕይወታችን ተቀዳሚ ነገር አድርገን እናስበዋለን? ትርፍ ጊዜ ሲኖረን፣ የቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ ጉዳይ ብቻ ሆኖብን ሌላ ሌላ ሳይሆን ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም”  በማለት በፍቅር የመከረንን ግብዣ ለመሳተፍ መሆን አለበት።

ወንጌል ውስጥ ክርስቶስ መሠረታዊ የሆነ አዲስ ትምህርት ሲያስተላልፍ “እውነት እውነት እላቸኋለሁ” ብሎ ይጀምራል፤ ስለ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ይህንኑ ነው ያለው። ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ግብዣ እውን ለማድረግ ብዙም አንጥርም፤ በጊዜ ሰሌዳችን ወይም በቀናት ፕሮግራማችን ውስጥም ቦታ አንይዝለትም። እስቲ ቦታ ከሌለው ሌላ መሰረዝ የምንችለውን ነገር ሰርዘን ክርስቶስ “እውነት እውነት እላቸኋለሁ” ብሎ የመከረንን ነገር ለመተግበር እንወስን።

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው በራሱ የአነጋገር ዘይቤ በወንጌሉ መጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ ሲነግረን:- “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፤ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ይለናል። ይህ ንግግር በቀጥታ ከቅዱስ ቁርባን እውነታ ጋር ይያያዛል። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በቅዳሴ የምትደግመው የእግዚአብሔር ቃል በመካከላችን በጸጋውና በክብሩ በመካከላችን ክርስቶስ ያድራል። በሌላ አባባል የክርስቶስ መወለድና ሰው መሆንን ማመን በቅዱስ ቁርባን የእሱ መገኘትን ከማመን ጋር ይተሳሰራል ማለት ነው። እንደኛ ሥጋን የለበሰውና ሰው ሆኖ የተገለጠው ክርስቶስ እኛን መሰል ከሆነው ይታይና ይጨበጥ በነበረው ሰዋዊ አካሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እንዲሁም ዛሬ በኅብስትና ወይን መልክ የክርስቶስ ሥጋና ደም አለ። ይህ የቅመማ ውጤት የሳይንስ ክፍል ወይም ሌላ እውቀት ሳይሆን የእምነት ጉዳይ ነው። ያመኑ ተከተሉት፣ ጊዜም ሰጡት ያላመኑት ግን ተዉት ጊዜም  ነሡት።

ለቅዱስ ቁርባን መታደማችን ታዛቢ የክብር እንግዶች እንድንሆን ሳይሆን የፍቅር ተሳታፊዎች እንድንሆን ነው። ፍቅር የልብ ጉዳይ ነውና ልባችንን ለርሱ እናነሣሳ። ከልባችን ውስጥ ክርስቶስን ለማራቅ ከምንጥር ይልቅ እሱ እንዳይገባ የሚያደርጉ ነገሮችን እናርቅ። በዚህ ሃሳብ በጸሎት ደካማነታችንን ታምነን በቀረብነው መጠን ሊያበረታንና ሊያቆመን ዝግጁ ነው። ያለርሱ በድካም ላይ ድካምን እናበዛለን፤ ከርሱ ጋርም በድካም ላይ ኃይልን እንጨምራለን - እንምረጥ።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት