እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

2ኛ ፍልሰታ

እናትና አባትህን አክብር!

Emebeteቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ ለእግዚአብሔር እናት (እመ አምላክ) የተሰጡትን ታላላቅ ክብሮችና አካላዊ ፍልሰቷን በማስመልከት ሲናገር "በድንግልናዋ ልጅ የወለደችው እርሷ ከሞትም በኋላ አካሏ ያለመፍረሱ ተገቢ ነው። ፈጣሪን የወለደችውና በደረቷ ያቀፈችው እርሷ ከእግዚአብሔር ዘንድ መኖሪያ ቦታ ማግኘቷ ተገቢ ነው። ለአብ የተዳረችው እርሷ በሰማይ የጫጉላ እልፍኝ ውስጥ መኖሯ ተገቢ ነው። በመስቀል ላይ ስታየው የኀዘን ሰይፍ በልቧ ውስጥ ያለፈው እርሷ ልጅዋን ከአብ ጋር በክብር ተቀምጦ ማየቱ ተገቢ ነው። የአምላክ እናት በፍጥረታት ሁሉ መከበሯ ተገቢ ነው።" ይላል።

እናትና አባትህን አክብር ብሎ ከአሥርቱ ትእዛዛት እንደ አንዱ ለኛ የሰጠን እግዚአብሔር እናቱን ያለማክበር አይቻለውም። በሥጋ ማደሪያው ሆናለችና የርሷን ሥጋ የርሱ ክብር ማደሪያ አደረገው። ልዑል የሆነው እሱ ከሰማየ ሰማያት በርሷ ሥጋ ለማደር ዝቅ እንዳለ ሁሉ ዝቅተኛ አገልጋይቱ እሷን በርሱ ክብር እንድትሆን ከፍ ከፍ አደረጋት።ክርስቶስ እናቱን እስከመጨረሻ ድረስ በማክበር ወላጅን፣ ቅዱሳንንና ሰውን ሁሉ እስከመጨረሻ ድረስ ማክብር ምን ማለት መሆኑን አሳየን።

የቁስጥንጥንያው (የዛሬዋ ቱርክ) ቅዱስ ጌርማኖስ "እንደተጻፈው ውብ ሆነሽ ተገልጠሻል፤ ድንግል አካልሽ ቅዱስ፣ ንጹሕና የእግዚአብሔር መኖሪያ ነው። ስለዚህም አፈር መሆን አይቻለውም፤ ወደማይበላሸው ሕይወት ክብር ተለውጧል። ሆኖም ይኸው አካልሽ ሕያውና ክብራዊ፤ ከችግር የተጠበቀና ፍጹም የሆነ ሕይወት የሚካፈል ነው" በማለት የእመቤታችን አካል ያለመበስበስ ከመለኮታዊ እናትነቷ ጋር ብቻ ሳይሆን በድንግልና ክርስቶስን ከመጸነሷ ጋር የሚገናኝ ልዩ ቅድስና ጋር እንደሚስማማ ያመለክተናል።

ይህንን በመሳሰሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታዎች የእመቤታችን መከበብ እሷን ምንም ሳታደርግና ሳትጥር እንድትኖር ወይም በእግዚአብሔር ስጦታ ፊት ባተሌ እንድትሆን አላደረጋትም። የእግዚአብሔርን ቃል (ክርስቶስን) በመሸከም ብቻ ሳይሆን በመስማትና በመከተል ኖራለች። የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን በገባ ቁጥር አካሄዳችን ከጸጋው ጋር እንዲስማማ ኃላፊነታችን እየበዛ ይሄዳል። የእመቤታችንና የቅዱሳን ብቃት እዚህ ላይ ነው፦ ጸጋውን ሲቀበሉ የበለጠ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የፈቃዱ ባርያ ይሆናሉ። በተቃራኒው እኛ ይህ ነገር ያዳክመናል፤ እግዚአብሔር ለማንም ጸጋውን ነፍጎ አያውቅም፤ ግን ለሰጠን ጸጋ የሚገባ የምስጋናና የምስክርነት ሕይወት ከመኖር ይልቅ ከርሱ የመራቅና እሱን የመርሳት አባዜ የተጠናወተው የሕይወት ዥዋዥዌ ውስጥ ገብተን ሕይወታችን ያልፋል። በዚህም ሁኔታ ብዙዎቻችን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሣሪያ እንዳንሆን በተለያየ መልኩና በቀጠሮ እንኖራለን።

ድንግል ማርያም ሕይወቷ በሙሉ ለርሱ ፈቃድ ክፍት ነበር። እርሷ የምታስተምረን ሕያው ቃል "እርሱ የሚላችሁንአድርጉ" (ዮሐ.2:4) የሚል ነው። እግዚአብሔር በዚህ ሰዓት ምን ይለናል፤ ወይም በሕይወታችን ምን እያለን ነው ማለት ደግ ነው። እርሱ የሚለንን ለማድረግ ዝግጁ መሆንን ደግሞ አሳምራ ልታስተምረን የምትችል እሷ ናት።ለመልአኩ ገብርኤል "እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" ብላ የመለሰችው ያ ሰማያዊ ቃል ሕይወት መሆኑን አምና ነው፤ ስለዚህም በሕይወቷ ሁሉ የርሱ ቃል ለሰው ልጅ ብቸኛ ጠቃሚ ነገር መሆኑን ራሷ ታውቃለችና ዛሬም እርሱ የሚላችሁን አድርጉ ትለናለች። እንግዲህ ለርሷ የምናደርገው መንፈሳዊነት ድምዳሜ ሁሉ እንደርሷ ለእግዚአብሔር ቃል ራሳችንን በየዕለቱክፍት ማድረጉን በመወሰን ነው።

ለእግዚአብሔር ቃል ክፍት የሆነ ሕይወት ማለት በእግዚአብሔር ቃል ይበጃጅ ዘንድ ሁል ቀን ራሱን የሚሰጥ ሰው ማለት ነው። እኔ ተፈጥሮዬ እንዲህ ነው፤ ቁጡ ነኝ፤ ቂመኛ ነኝ፤ የሥጋዬ ተገዢ፣ ሱሰኛ ...ወዘተ ነኝ ከማለት ይልቅ እስቲ ዛሬ እሱ የሚለኝን አደርጋለሁ በማለት በደካማነታችን እሱ እንዲሠራ አምነን ራሳችንን ማዘጋጀት ማለት ነው። ይህን ስናደርግም በርግጥ እመቤታችንን በሕይወታችን እንደ እናት ተቀበልናት ማለት ነው። ልጅ ወላጁን በሆነ ነገር ሊመስለው ግድ ነውና የኛ የርሷ ልጅነት ለእግዚአብሔር ቃልና ፈቃድ ዝግጁነትን በመለማመድ መሆን አለበት። ፍልሰት ለኛ ይህ ነው፦ ከነበርንበት ደካማና ጠፊ አናኗር እግዚአብሔርን ወደ ሚያስከብር ሕይወት መሻገር! እናታችንን እሷንና አባታችንን ማክበርያ ብቸኛ መንገድም እርሱ የሚለንን ማድረግ መጀመር ነው። ለዚህ ብቃት አማልጅነቷ ይብዛልን። አሜን።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት