እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ፍልሰታ ማርያም 1ኛ

ፍልሰታ ማርያም 1ኛ

Filsete Mariamስለ እመቤታችን ክብርና በርሷ ስለ ተደረገው ታላቅ የእግዚአብሔር ሥራ ገናናነት ለማወደስና አማላጅነቷን ለመማጠን ከሚደረጉ ጥልቅ መንፈሳዊነት በብዙዎች የአገራችን ክርስቲያኖች ልብ ዘንድ ልዩ ቦታን የሚይዘው የፍልሰታ ዘመነ ምህለላ መጀመሪያ ሳምንት ላይ እንገኛለን። ይህ ወቅት ከሚያስተላልፍልን መልእክቶች አንዳንዶቹን እንመልከት።

የእመቤታችን ፍልሰታ ሰው ሙሉ ክብር የመጎናጸፍ ጥሪን ከእግዚአብሔር መቀበሉን ያሳስበናል። ሰው በፈጣሪው ፊት በሥጋው፣ በመንፈሳዊነቱ፣ በስሜቶቹ፣ በሃሳቡ... ባጠቃላይ ማንነቱ ዘላቂ ክብር ይኖረው ዘንድ መፈጠሩንና በጣም አላፊና ጊዜያዊ እንዲሁም ሽሚያና ሽኩቻ ለተሞላ ነገር ሳይሆን ለዘላለማዊ ክብር መታጨቱን ይነግረናል። በዘመናችን ሰው ሙሉነቱ ተዘንግቶ አንድም በሥጋው ብቻ ዘላለም ይኖር ይመስል ሌላ ማንነቱን ረስቶ ሲመለክ ሌላም ለስሜት ርካታ ብቻ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ ሁሉ ነገር ስሜትን ለማርካት የሚጋብዝ ሆኖ በሚሰበክበትና በምልአት ማደጉ ችላ በተባለበት በዚህ ወቅት ፍልሰታ ማርያም ንቃ! የተፈጠርከው ለምልአት ነው ይለናል

የእመቤታችን በሥጋዋ ወደ ሰማይ መፍለስ ማለት እያንዳንዱ ክርስቲያን ለተሰጠው ክርስቶሳዊ ጸጋ ታማኝ እስከሆነ ድረስ የማይቀር የወደፊት ክስተት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል።" ይላል (1ቆሮ.15:42)። እመቤታችንም በተራዋ "እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቷልና ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተመሰገንሽ ነሽ ይለኛል" አለች (ሉቃ.1:48)። የትውልድ ክፍል ሆኖ የሚሰማው ግለሰብ ሁሉ እሷን የተመሰገንሽ የሚላትም ይህ እውነት በርሷ ስለተፈጸመ ነው፤ ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል ጸንሳ ወልዳ ለዓለም (ለኛ) ስላበረከትችና እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ምን መሆኑን ስላሳየችን፤ የተዘጋጀልን ዘላለማዊ ክብርም ምን እንደሚመስል በፍልሰቷ እግዚአብሔር ስላሳየን በምህለላችን እሷን ብፅእት እያልን እግዚአብሔርንም ለታላቅ ሥራው በርሷ እናከብረዋለን።

እግዚአብሔር ይህን የሥጋ ፍልሰት አስቀድሞ ለእመቤታችን ለምን አደረገ ካልን፤ ምናልባት ከመጀመሪያውኑስ አንደኛ ልጁ ከርሷ እንዲወለድ ለምን መረጣት ወደሚል ተመሳሳይ ሀሳብ ሊያመራን ይችል ይሆናል። እውነቱ ግን አንድ ሰው ሕይወቱ በክርስቶስ ጸጋ የመስመጡን ያህል በክርስቶስም ክብር ከፍ ይላል፤ እንዲሁም ምድራዊ ሕይወቱ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ሥር የመስደዱን ያህል በሰማያዊው ክብርም የላቀ ስፍራን ይይዛል። ታዲያ ሕይወቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የሰመጠ፤ በአናኗሩም ከጽንሰት እስከ መስቀል ግርጌ፤ ብሎም የሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ እስከመሳተፍ ድረስ በክርስቶስ ሥር የሰደደ ከእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም የበለጠ ማን አለ? ቅዱስ ገብርኤል ከራሱም ያይደል ከእግዚአብሔር የሆነውን መልእክት ሲያበስራት "አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፤ ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ" እንዳላት ፍልስቷም ይህንኑ እውነት ያፈካልናል "ከሰዎች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ" እንላታለን። 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት