እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘአስተምሕሮ 4ኛ- ዘመፃጉዕ

ለሰው ልጅ ነፍስ የሚስማማ <የአየር ሁኔታ>ዮሐ.9:1-41 1ቆሮ.2:1-16 1ዮሐ.5:1-5 ሐዋ.5:34-42

Gesu guarisce ciecoባለንበት የአስተምሕሮ ዘመን በቀጣይ ሰንበቶች እግዚአብሔር በሰው ልጆች መካከል የገለጸውን ወሰን የለሽ ምሕረት በተለያዩ የወንጌል ንባባት እየተመለከትን ነው። በዚህ ቀን የሚነበበው ወንጌል በተለየ ድራማዊ ሁኔታ የአንድ ዓይነ ስውር በኢየሱስ የመፈወስን ታሪክና በዙሪያው የነበሩ ሰዎች አሉታዊ ድርጊቶች ይተርክልናል። (እንደ ሁልጊዜው መልእክቶቹንና ወንጌሉን በሙሉ ማንበብን አይዘንጉ)

ይህ ወንጌላዊ ታሪክ ግልጽ ከሚያደርግልን ነጥቦች መካከል ሰው ሕይወቱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ሲጀምር ከሌሎች ጥያቄ እንደሚበዛበትና ማንነቱም ሁሉ በሌሎች ዘንድ ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚገባ እናስተውላለን። "ይህ ሰው ያ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?...እርሱን ይመስላል እንጂ እርሱ አይደለም! አሉ" ቁ.8:9። በተጨማሪም እግዚአብሔር ያደረገለትን ያለመሰልቸት የሚመሰክር አንድ ሰውና እግዚአብሔር ያደረገውን ላለማየት ቁርጥ ውሳኔ ያደረጉ፤ በወንጌሉ አገላለጽ በፈቃደኝነት "የታወሩ" መሆንን የመረጡ ብዙ ሰዎችን እናነባለን። የቃሉ ዓላማ ራሳችንን እንድናይ ነውና ከየትኞቹ ጎራ እንደሆንን እስቲ እንመርምር። እሱ በሕይወታችን ያደረገልንን ነገር ማስተዋልና ያለፍርሃት መመስከሩ ይቀለናል ወይስ "ያልተደረጉልን" የምንላቸውን ደርድረን ያለፍርሃት ማማረሩ?

ዓይናችንን ድርግም አድርገን ከጨፈንነው መብራት ቢበራም ፀሐይም ቢሆን ማየት የምንችለው ነገር ጨለማ መሆኑ ግልጽ ነው። ብርሃን ስለሌለ ሳይሆን ብርሃኑን ላለማየት ያለንን ችሎታ ስለተጠቀምን ማለት ነው። በተለያየ መንገድ መናገር የማይታክተው እግዚአብሔር ሁሌ ሲናገር በገሃዱ ዓለምም ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወስዱ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ምናልባትም ሳት ብሎ የሚከሠት ነገር ሳይሆን የተለመደ ያለመስማት ልማድ አዳብረንም ሊሆን ይችላል።

በወንጌሉ ውስጥ ክርስቶስ ዓይነ ስውሩን የመፈወስ ሂደት ጀመረና የሰውየውን ትብብር ጠየቀው፤ "ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው። ስለዚህ ሰውየው ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ"ቁ.7። ክርስቶስ ጋበዘ ሰውየው ተቀበለና ተፈወሰ። ሰሊሆም ማለት የተላከ ማለት ነው ይላል እዚያው ላይ ቃሉን ሲተረጉመው፤ ይህ ለኛ ጥልቅ ትርጉም አለው። በዚህች ምድር ተልከናል እንጂ ለዘላለም እንኖርባት ዘንድ አልመጣንም። ሕይወታችን መልእክት አለው፤ ትርጉም ወይም መልእክት የሌለው ሕይወት ያለው ሰው የለም። ይህ መልእክት ደግሞ ልክ እንደ ሰሊሆሙ ዓይነ ስውር ሰውዬ ክርስቶስን የማወቅና የመፈወስ መልእክት ነው። ማናችንም ለዘላለማዊ ጥፋት፤ ለጊዜያዊ "ደስታ" አልተላክንም።

የእግዚአብሔር ምሕረት ከምንም በላይ የማይገመት ነውና ባለን ቃላትና ችሎታ ልናጋንነው ብንሞክር ማጋነኑ ፍጹም ሊሳካልን አይችልም። ሊገባንና ሊረዳንም ስለሚያዳግተን ሁልጊዜ በእርሱ ምሕረት ፊት የሰው ልጆች ሁሉ አንድ ዓይነት ምላሽ የለንም። ስለዚህም ክርስቶስ በአካል ተገልጾ በነበረበት ዘመን አንዳንዶች ተቀበሉት፣ ገሚሶቹም አሳደዱት፣ ሌሎች ጤነኛነቱን ተጠራጠሩት፣...ወዘተ። እውነቱን ስናየው ግን የእግዚአብሔር ምሕረት የማይስፈልጋት ዓይነት ነፍስ ባለቤት የሆነ ማንም ሰው የለም፤ የትኛውም ሰው የእግዚአብሔር ምሕረት ግብዣ ጥሪ ሲደርሰው "ይለፈኝ" ቢል የሚያስገርም ዓይነት መልስ ይሆናል። ለግብዣው ምላሻችን ምን ይሆን?

አንድ ሊቀ ጳጳሳት ለነፍስ ብቸኛ ተስማሚ መንገድ የእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ሲገልጹ: "የእግዚአብሔርን በምልአት መገለጽ የማይቀበሉ ሰዎች ርካታ ቢስ ሕይወትን ይገፋሉ። የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ እግዚአብሔርን ለማወቅ፣ ለመውደድና ለማገልገል ነው። እምነትን በማጥፋትም ሆነ በሌላ ምክንያት ይህን ማድረግ ካልቻሉ ከተፈጥሯቸው ሁኔታ የወጣ ሕይወት ውስጥ ይገባሉ፤ ለሰው ልጅ ነፍስ የሚስማማ <የአየር ሁኔታ> እግዚአብሔር ነውና ነፍስ ከእግዚአብሔር ውጪ ልታብብ አይቻላትም" ይላሉ።

ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት የማይፈልግ ሰው በውስጡ የሚፈጠረውን ጎዶሎነት በሌላ ተግባራት ለመተካት ይራሯጣል። ለሌሎች ፍትሕን (ሕግን) በማስከበር፣ ተቆርቋሪነትን በመገለጽ፣ በበጎ አድራጎትና በመሰል ሁኔታዎች እዚህጋ የካዱትን ነገር እዚያጋ ለመተካት ይሞክራሉ። ለእግዚአብሔር ጸጋ ባለመታዘዝ ትልቁን ምሕረትና ፍቅር የነፈግናትንና የጎዳናትን ነፍስ በአላፊ ፍቅርና በሰው ሙገሳ ውጌሻነት ልንፈውሳት እንጥራለን። ነገር ግን ለእውነተኛ የሕይወት ለውጥ የሚጠራንን ድምጽ እስካልታዘዝን ድረስና እሱን በተቃወምነው መጠን የእርሱ ድምጽ በውስጣችን ያይላል።

"ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ" በማለት ዓይነ ስውሩን ለፈውስ የላከ ጌታ ዛሬም ለእያንዳንዳችን ሰሊሆም ይሆነን ዘንድ በውስጣችን የሚነግረን ድምጽ አለና እንታዘዘው፤ ከሁሉ ዓይነት ኃጢአት ባርነት ነጻ ሊያወጣን የሚችል እሱ ወደ ምሕረቱ ይጠራናል።

እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? መዝ.4:2

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት