እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘአስተምሕሮ 5ኛ

ሦስተኛው የክርስቶስ ምጽአት! - ዘአስተምሕሮ 5ኛ

የእለቱ ንባባት - ዘአስተምሕሮ 5ኛ

1ቆሮ 15፡12-32 / 2ጴጥ 3፡10-18  / ሐዋ 20፡28-38

ሉቃስ 12፡ 32-40

zeAstemhro 5የዛሬው የወንጌል ምንባብ ውስጥ ባሉት ሁለት ክፍሎች ውስጥ (ሉቃስ ቁ.34፣35 እና 38) ሁለት ነጥቦች ጎልተው ይታያሉ:- የልባችን አድራሻና የመጠባበቅ ሀሳብ። አንዱ ሃሳብ ሌላውን ሊያካትት ይችላል። ማለትም ልባችን ባለበት ቦታ መጠበቅ አለ ወይም በምንጠብቅበት ቦታ ልባችን አለ።

አንዳንድ ጊዜ የብዙ ነገር አድራሻዎችን እናውቅና የልባችንን አድራሻ ማስተዋል ስንጀምር ማመላከቱ ይከብደናል። የልባችን አድራሻ በሕይወታችን ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ጋር ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ቅድሚያ ለማን/ለምን እንደምንሰጥ ይጠይቀናል። የልባችንን አድራሻ ካወቅን የምንጠብቀውም ነገር ከሱ ጋር የተያያዘ መሆኑን በግልጽ እናያለን። በሌላ አባባል በምንጣበቅበት ቦታ እንጠብቃለን፤ ከዚያም ሌላ ነገር እንዳንጠብቅ ኃይል ያሳጣናል። ምናልባት እኔ እስከዚህ ድረስ በነገሮችና ጊዜያዊ እቅዶች የተዋጥኩ ዓይነት ሰው አይደለሁም የምንል ከሆነ እንኳ ራሱን ሙሉ ለሙሉ እስኪረሳ ድረስ ለነገሮች የሚሮጥ ሰው ማየቱ የሚያስቸግር ሁኔታ አይደለም። ይህ ራስን የመርሳት ትልቁ መዘዝ እግዚአብሔርን መርሳት ማስከተሉ ነውና ከክርስቶስ ያስቀደምናቸው ነገሮች ካሉ ቆም ብለን የሕይወት እቅድ ቅደም ተከተሎችን እናስተካክል።

ሁለታኛው የዛሬ ወንጌል ክፍል ጌታን በትጋት ስለመጠበቅ ይናገራል። በዘወትር እይታ ሁለት የክርስቶስ ምጽአት እንዳሉ እናስባለን። የመጀመሪያው ክርስቶስ ሰው ሆኖ የተወለደበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ክርስቶስ በክብር ሊፈርድ የሚመጣበት ዳግም ምጽአት ነው። ቅዱስ በርናርዶስ ግን ስለ ሦስተኛ የክርስቶስ ምጽአት ይናገራል። ይህም ከላይ በጠቀስናቸው በሁለቱ ማለትም በክርስቶስ ልደትና የክብር ዳግም ምጽአት መካከል ያለውን ጊዜ ማለት ነው። ይህ ሦስተኛ ምጽአተ ክርስቶስ ማለት እያንዳንዷ የምናሳልፋት ቀን ናት:: ካስተዋልነው በክብርና በመላእክት እወጃ ባይሆንም በተለያየ መልክ ወደ እኛ ይመጣል። አንዳንዴ በሰው ንግግር፣ ሌላ ጊዜ በቀጥታ የቃሉ ንባብ፣ በባልንጀራችን በጎ ነገርን በማድረግ፣ ደግሞ ደጋግሞ ደግሞ በልባችን ውስጥ በሚያሰማን ድምጹ...ወዘተ ክርስቶስ ሁሌ ወደኛ ይመጣል። በዚህም መልኩ እያንዳንዱ ቀን ክርስቶስን ሊሰጠን ዝግጁ ስለሆነ የተስፋና የበረከት ቀን ነው።

ባሳለፍናቸው የዕድሜያችን ዓመታት ሳትንጠቀምበት ያሳለፍነውና ዛሬ ላይ ሆነን የሚቆጨን አጋጣሚ የትኛው ነው ተብለን ብንጠየቅ በአእምሯችን ምን እንደሚመጣ እናስብ። ወንጌላችንን ካስተነተንነው ያ የሚቆጨን የምንለው ነገር ዋነኛና ብቸኛ የሕይወታችን የመኖር ዓላማ ነበር እንዳንል ያግዘናል፤ ምክንያቱም የሕይወታችን ዓላማ ክርስቶስን መጠበቅ ነው፤ ያውም በትጋት። የክርስቶስ ሦስተኛ ምጽአት ያልነውን ችላ ካልን ማለትም በየቀኑ ሕይወታችን ውስጥ ክርስቶስን መስማትና ማስተናገድ ያልቻልንበት ወቅት ካለ ያን እንቆጭበት፤ ይህ ቁጭት ግን ዛሬ እሱን እንድንሰማና እንድንቀበል ኃይል የሚሰጥ እንጂ አለፈ በቃ አከተመ የምንልበት ቁጭት አይደለም። ባለፉት ጊዜያት ውስጥ ክርስቶስን በዕለታዊ ምጽአት እንዴት አስተናግጄዋለሁ? ዛሬና ከዚህ በኋላስ እሱን እንዴት ማስተናገድና ለእሱስ እንዴት መኖር አለብኝ? ብለን እናስብ።

"መጠበቅ" ቀላልና ደስ የሚል ወይም የሚመች ዓይነት ሀሳብ አይደለም። በተለይ ነገሮች ሁሉ <<ቶሎ፤ አሁንና እዚሁ በቀላሉ>> በሚባልበት በአሁኑ ዘመን መጠበቅ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ከትንሿ ቀጠሮ ጀምረን እስከ ትላልቅ የሕይወት አቅጣጫ ድረስ ጠባቂ መሆን ብዙም የሚመች ነገር አይደለም። የቀጠሮ ሰዓት ማለፍ ሲጀምር ባለንበት ሆነን መቁነጥነጥ እንጀምራለን። ትምህርት እስክትጨርሱ፣ ሥራ/ትዳር እስክትይዙ...ነሮችን ጠብቁ ብንባል ትዕግሥታችን ብዙም ላይሆን ይችላል። እንግዲህ እንደዚህ በጊዜ የተገደቡት ትናንሽ መጠበቆች እንዲህ የሚከብዱን ከሆነ ሙሉ ዕድሜያችንን ባጭሩ ታጥቀን ጌታን ተግቶ መጠበቅ የሚለው ወንጌላዊ ሃሳብ ምን ያህል ይከብደን ይሆን!

በርግጥ ሁለቱን ሀሳብ ስናያይዛቸው መጠበቅ ከባድ ቢሆንም የሚቻል ነገር መሆኑ ሊገባን ይችላል፤ ምክንያቱም ከጠባቂው በኩል ብቻ ካየን ተስፋ ስንቆርጥ የምንጠብቀው ማን መሆኑን ካሰብን ግን የምንጠብቅበት ጊዜን በተስፋና በትዕግሥት እናሳልፈዋለን። ወንጌላዊ መጠበቅ የእጅ ማጣመር፣ ጌታቸው እንደሚመጣ ስለሚያምኑ የማይሠራበት ዓይነት መጠበቅና ያለምንም ተግባር በ"እምነት" ብቻ ለመኖር ሳይሆን ባጭር መታጠቅን፣ መብራት ማብራትንና ጌታችው ሲመጣ በር ለመክፈት መጠበቅን የሚጋብዝ ነው። የሉቃስ "መጠበቅ" ትርጉም ዛሬን ለክርስቶስ መኖር ማለት ነው። ራቅ ያለ ትርጉምን በፊቱ አስቀምጦ ለዚያ ትርጉም የመኖር ችሎታውን በተለያየ ሁኔታ በመሰረቅ ላይ ያለው ትውልዳችን ክርስቶስን በትጋት መጠበቅ መለማመድ ይኖርበታል።

ስለዚህ ልባችንን ወደ እግዚአብሔር እናንሣ፤ ዛሬ የተቆጣጠሩን ነገሮች ካሉ የነሱም ሆነ የሁሉ ነገር ጌታ አለንና እሱን እንቅረበው። ዘወትር በቅዱስ ቁርባን እኛን ለሚጠባበቀንና በቅዱስ ቃሉ ሁሌም ለሚናገረን ጌታ ልባችንንና አእምሯችንን ብናስገዛለት የበለጠ ሙላትን የሚያጎናጽፈን አምላክ ነውና ከሌሎች ነገሮች በመላቀቅ ከርሱ ጋር ለመጣበቅ እሱን በየዕለት ሕይወታችን እንጠብቅ-እንኑረው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት