ዘስብከት 1ኛ
- Category: በሰንበት ወንጌል ላይ አስተንትኖ
- Published: Saturday, 28 April 2012 08:45
- Written by Super User
- Hits: 4331
- 28 Apr
ሰው እግዚአብሔርን ሲንቅ እግዚአብሔር ሰውን ሲያከብር! - ዘስብከት 1ኛ - 1ዮሐ.:1-14/ዕብ.1:1-14/2ጴጥ.3:1-9/ሐዋ.3:17-26/ዮሐንስ 1፡ 43-51
በሥርዓተ አምልኳችን አካሄድ መጪዎቹ ሦስት ሰንበቶች ስብከተ ገና ማለትም የጌታችንን ሰው መሆን ለምናከብርበት ወቅት መዘጋጃ የሚሆን ወቅት ነው። ኃያል፣ ቅዱስ፣ ሰማያዊው አምላክ እኛን መምሰል ሳይሆን እኛን መሆኑን የምናስታውስበት ልዩ ወቅት ነው። ስብከተ ገና የእሱ በዓለም ታሪክ ውስጥ መግባት የዓለምን አቆጣጠር ወደ ዓመተ ምሕረት እንደቀየረው ሁሉ የእኛንም ሕይወት በምሕረቱ ሊሞላት በርሱ በኩል ሁሌም ዝግጁ መሆኑ የሚሰበክበት ወቅት ነውና የዛሬው ሰንበት "ዘስብከት" ይባላል።
ከዛሬው ወንጌል በፊልጶስ፣ በናትናኤልና በኢየሰኡስ መካከል የተደረገውን ንግግር እንውሰድ። ፊልጶስ በኢየሱስ ከተጠራ በኋላ ናትናኤልን ሲያገኘው፦ "ሙሴ በሕግ መጽሐፍ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው" አለው። ናትናኤል ግን "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?" አለው። ፊልጶስም "መጥተህ እይ" አለው። ኢየሱስ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጥ ኣአይቶ "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!" ሲል ስለ እርሱ ተናገረ(ቁ.44-47)። ጊዜ ሰጥቶ በማስተዋል ላሰበው ሰው በነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በተለያየ መልኩ ይሁን እንጂ ዘወትር የሚደጋገም እውነት አለ። እግዚአብሔር ደካማ ሆኖ፣ በሥጋ ሰው ሆኖ፣ በማይመስለን መልኩ ሲገለጽ ሰው ደግሞ ሲንቀውና ሲጠራጠረው ይታያል። "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገን ይችላልን?" - እግዚአብሔር ናዝሬትን መረጣት፤ በማይመስልና በሚናቅ ነገር መሥራት ልማዱ የሆነ አምላክ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬም ይህን እውነት ያደርጋል።
ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሰው መሆን ነበረበትና ይህን ለመተግበርም ከኃጢአት በስተቀር እንደሰው ተቆጠረ፣ ተወለደ፣ ተናቀ፣ ተንገላታ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ ተሰደደ፣ ታማ፣ ለሌባና ለነፍሰ ገዳይ የሚደረግ ፍትሕና እንክብካቤ ተነፍጎት ተሰቀለ - ሞተ። እሱ ፍጹም ሰው ነበርና እያንዳንዷ ስቃይ እኛን ከምታሰቃየን በላይ ብዙ እጥፍ እንደምታሰቃየው መገመቱ ከባድ አይደለም።
ይህ በክርስቶስ ላይ የተፈጸመው እውነታ "በአንድ ወቅት" የነበረ ክሥተት አይደለም። እግዚአብሔር ዛሬም ደካማ ነገሮችን የመምረጥ አሠራሩን አልቀየረም፤ የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ድካም በሆኑ ነገሮች ውስጥ የሚገኘውን ጸጋ መናቁን አላቋረጠም። የሚገርመው ነገር ደግሞ ደካማው ኃያሉን ሲንቅና ኃያሉ ግን ደካማውን ሲይከብረው ማስተዋሉ ነው። ናትናኤል ስለ ኢየሱስ "ከቶ ምን መልካም ነገር ይገኛል" ሲል ኢየሱስ ግን ስለ ናትናኤል "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው" አለው።
"ከኅብስትና ከወይን ከቶ የክርስቶስ ሥጋና ደም ሊገኝ ይችላልን?" የሚሉ ዛሬ ዛሬ ቁጥራቸው ጥቂት ላይሆን ይችላል። ምናልባትም በቃላት ባይሉትና ባይክዱትም በተግባር ግን በመራቅና ባለመሳተፍ ይህን ንቀት በአክብሮት ስም የሚያስተጋቡትን አካቶ ማለት ነው (የምናከብረውንና የምንወደውን ላለመራቅ የሚቻለልን እንጥራለንና ቅዱስ ቁርባንን ስለማከብርና ስለምወድ አልቀርበውም የሚል አባባል በራሱ የተጋጨና ትርጉም የለሽ አባባል ነው)። ክርስቶስ ግን "ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው" (ዮሐ.6:54) ይለናል። እንደ ወንጌሉ ዛሬም እኛ ስንንቀውና ስናርቀው እሱ ይጋብዘናል፣ ያከብረናል ይቀርበናልም። የእሱ አካል የሆነችውና እሱ ፈቅዶ በተለመደ አመራረጡ በደካማ ሰዎች ላይ የቆረቆራትን ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ መልኩ ለማናቅና ለማወረድ ጥረት ባደረግን ቁጥር ለንስሐና ለቅድስና ዘወትር በራሷ በኩል ይጋብዘናል።
ይህን ሀሳብ የእሱን መወለድ ለማክበር በምናደርገው ዝግጅት ሂደት ውስጥ በጸሎት እያሰላሰልን ዛሬም እግዚአብሔር ደካማ በሚመስሉ ነገሮች የሚያደግልንን ጥሪ ተቀብለን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ዳግም የምንወለድበትን ጸጋ አናሳልፍ።