እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

እግዚአብሔር በልጁ ልደት ሳመን! - ዘልደት

ዘልደት

ZeLidetቅዱስ በርናርዶስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር ጠለቅ ያለ ምስጢር መሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመበት አጭር ስእላዊ መግለጫ መሳምን ነው፤ ለዚህም ገለጻ መሠረት ያደረገው የመኀልየ መኀልይ መጽሐፍን ነው፤ “በአፉ መሳም ይሳመኝ” 1፡2 የሚለውን። የክርስቶስን ሰው መሆን /ተሠግዎቱ/ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ጥምረቱን ያተመበት ቀጣይ መሳም እንደሆነ በርናርዶስ በሚያምር ሁኔታ ይናገራል። ቃል /ክርስቶስ/ በሥጋ በመገለጹ የእግዚአብሔር ከንፈር አምሳል ሆኖ የክርስቶስ ሰው የመሆን ባህርይ ደግሞ ሰውነትን የሚገልጽ ሌላኛው ከንፈር በመሆን መለኮት ስብእናን በልደቱ እንደሳመ በሚረዳ መልኩ ያስረዳል። ይህ እውነታ እንደው ዝም ብሎ በድፍኑ የሰው ዘርን ሳይሆን እግዚአብሔር በልጁ ልደት እኔን ሳመኝ ብለን እንድናስብ፣ እንድናስተነትንና ፍቅሩ ጠለቅ ብሎ ከውስጥ እንዲነካን ይጋብዘናል።

ከላይ ከጠቀስነው ሃሳብ ተነሥተን የገና በዓል ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ብዙ ትርጉምን ሊሰጥና መወለዳችንን ባጠቃላይም ሰው መሆናችንን ይበልጥ እንድንወደው የሚያደርገን ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አንዴ ፈጥሮ በሥራችንና በድካማችን ብቻ እድሜያችን እስክታልቅ ባለበት ቦታ ሆኖ የሚጠብቀን ሳይሆን ዝቅ ብሎ ከፍ ሊያደርገን የሚጥር አባት ስለሆነ ነው።

በአዲስ ኪዳን ይህ እውነት፣ ማለትም የእግዚአብሔር ቅርብነት በግልጽ ተገልጾ የክርስቶስ ልደት ከመታወጁ በፊት በብሉይ ኪዳን ብዙ ታሪኮች ይህን ቅርበት የሚያሳዩ ሂደቶች ነበሩ። አዲስ ኪዳን ለክርስቶስ ልደት መንገድ ሲከፍትም የእግዚአብሔር ግለጸት በምልአት በክርስቶስ ሰው መሆን ሊገለጽ ሲቃረብ የተከሰቱት ሁኔታዎች የእግዚአብሔርን ዝቅ ማለት ያመለክታሉ። ክርስቶስ ሊወለድ ሲል በቅርብ ሆነው መንገድ የጠረጉለትን ሰዎች ስም ካስተዋልን ይህን እውነት ያንጸባርቃሉ፤ ዘካርያስ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የስሙ ትርጉም “ጌታ አስታወሰ” ሲሆን፣ የሚስቱ ኤልሳቤጥ ስምም “የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን” ማለት ነው፤ እንዲሁም የልጃቸው ስም ዮሐንስ ማለትም “የእግዚአብሔር ጸጋ” ነው። ስለዚህ እነዚህ ሦስት ሰዎች የተሰጣቸው ስም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ቅርብ መሆኑን ሲያመለክቱ የበለጠ ግን ሙሉ የሆነው በ”አማኑኤል” ነው፤ ይህም በክርስቶስ ልደት ኢየሱስ ቅርብ ብቻ ሳይሆን ከኛ ጋር ለመሆን አምላክ ጎንበስ ብሎ በበረት መወለዱን የሚያሳይ ስም ነው፤ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነውና።

የጌታ ልደት የእግዚአብሔርን ጎንበስ ማለት የምናከብርበት በዓል ነው፤ ይህ ማለትም እግዚአብሔር ያፈቀረንና ያዳነን በኃይል፣ በብርታት፣ በጉልበት፣ በአመፅ ሳይሆን በፍቅር፣ ዝቅ በማለት፣ በትሕትና መሆኑን ነው። ስለዚህም በጌታ ልደት ፍቅርንና ትሕትናን እናከብራለን፤ በእለታዊ ሕይወታችንም ውስጥ እንደርሱ አፍቃሪና ትሑት ለመሆን ቃል እንገባለን። በዚህ መልኩ የክርስቶስ ልደት በዓል ከሕይወታችን ጋር ይተሳሰራል፤ በዓመት አንዴ ክርስቶስን “መልካም ልደት” ወይም “እንኳን ተወለድክ” ለማለት ገናን እንደማናከብር የሚያደርጉን ነጥቦች ብዙ አሉ። የሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 2፡1-20 የክርስቶስ የልደት ትረካ ብቻ ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ ከስቅላቱና ትንሣኤው ጋር የሚተሳሰሩ እውነታዎች መኖራቸውም የልደት በዓል የትንሣኤ ማለትም የሕይወት በዓል መሆኑን ያሳየናል።

እመቤታችን ድንግል ማርያም ልጇን ክርስቶስን በጉዞ ሳለች ስትወልደው “በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቅልላ በከብቶች በረት ግርግም መመገቢያ” ውስጥ እንዳስተኛችው ይነግረናል፤ ይህ ደግሞ በዛው ወንጌል ውስጥ በምእራፍ 23፡52-53 ላይ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስክሬን ከጲላጦስ ጠይቆ በቀጭን ሐር ከጠቀለለው - ከከፈነው - በኋላ ማንም ሰው ባልተቀበረበት በአዲስ መቃብር እንዳሳረፈው እናነባለን። በልደቱና በሞቱ መካከል ይህ ትስስር ለልደት ለየት ያለ ትርጉም እንድንሰጠው ያግዘናል። በተመሳሳይ ሁኔታም በልደቱ ወቅት እረኞቹ በመላእክት በተነገራቸው መሠረት ወደ ቤተልሔሙ በረት ሄደው ክርስቶስን አግኝተው እንዳዩ ሁሉ፤ በትንሣኤው ጊዜ ሴቶቹ ሽቷቸውን ይዘው ወደ ኢየሱስ አስክሬን ቢሄዱም ከሐዋርያትም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩም ቢሮጡ የጌታን አስክሬን አላገኙትም፣ አላዩትም /24፡3/። እረኞቹ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በግርግም አገኙ፤ ጴጥሮስም በጌታ መቃብር ጋር በደረሰ ጊዜ አስክሬኑ የተከፈነበትን ቀጭን የሐር ልብስ ብቻ አየ /24፡12/é እንዲሁም “እነሆ ዛሬ አዳኝ ተወልዶላችኋል” የተባለለት ጌታ ዳግም በትንሣኤው “እርሱ እዚህ የለም፤ ተነሥቷል” /24:6/ ተብሎ በመላእክት ተነግሮለታል። ዛሬም ቢሆን መላእክት ክረስቶስ ተወልዷል፤ ይህ የተወለደውም አዳኙ ጌታ መነሣቱን ዛሬም ያውጁልናል፤ ይህን ለኔ ብለን ስንወስደው በርግጥ ልደተ ክርስቶስ የእኛ ልደት ይሆናል።

በመግቢያችን እግዚአብሔር በልጁ ልደት ሳመን ስንል፤ ከነበርንበት የሕይወት ዘዬ ወደርሱ ጥልቅ ፍቅር ሊያነሳን መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። በተጨማሪም ይህ እውነተ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ በእግዚአብሔር ቃልና በምሥጢራቱ መመገብ ግድ ይላል፤ እግዚአብሔር ዛሬም በምሥጢራቱ ይስመናል። ቅዱስ ሉቃስ የጌታ ልደት ለሁልጊዜ የሆነ እውነታ መሆኑን ሲያመለክት፤ ክርስቶስ በቤተልሔም ከተማ መወለዱን ይተርክልናል፤ ቤተልሔም ማለት የቃሉ ትርጉም የእንጀራ፣ የኅብስት ቤት መሆኑ እንዲሁም ደግሞ በቤተልሔም ከተማ ውስጥ በከብቶች በረት ግርግም መመገቢያ ውስጥ መወለዱ፤ ጌታ ለሁላችን ምግብ ሊሆን በዚህም እርሱን ተመግበን እንበረታና እናድግ ዘንድ ትርጉማዊ በሆኑ የልደቱ ቦታዎች ምልክትነት ያስረዳናል።

በክርስቶስ ልደት ዓለም ሊጎበኛትና ሊያድናት የመጣውን አምላክ ለመቀበል “ለእርሱ የሚሆን ቦታ” አልነበራትም። ይህም ነጥብ ዛሬ ልባችንን እንድንፈተሽ ግድ ይላል፤ ክርስቶስ በተለያዩ የሕይወታችን አጋጣሚዎች ወደ ልባችን ልግባ ክፈቱልኝ ሲለን፤ አሁን ላንተ የሚሆን ቦታ፣ ጊዜ፣ ቀልብ የለኝም እለፈኝ እንል ይሆናል በሌላ አባባል እግዚአብሔር ደጅ ሲጠና፤ የሰው ልጅ ደጅ ሲዘጋ እናስተውላለን። ስለዚህ የጌታ ልደት ትልቁ በዓል ሊሆንልን የሚችለው የልባችን በሮች ያለቀጠሮና ያለሰበብ ለርሱ ፍቅርና ትሕትና ሲከፈቱና ይህንንም ለሌሎች ስናካፍል ነው። በርግጥ ይህ ሲሆን የእግዚአብሔርን መሳም እንደሚገባ ሆነን እንቀበላለን፤ እናጣጥመዋለን።

የክርስቶስ መወለድ ታሪክ ገና ከጠዋቱ መሰደድ ያጀበው ነበር፤ እመቤታችን ከቅ. ዮሴፍ ጋር በመሆን ወልዳ እንዳልወለደች መሆን አልነበረባትምና፣ ልጇም ለዓለም ሁሉ /ለእኛ/ አዳኝ መሆኑን ታውቅ ነበርና እርሱን ለማዳን ተሰደደች። በሕይወታችን ተመሳሳይ ስደት በክርስቶስ ላይ የሚፈጥሩ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ሰዎች፣ ነገሮች፣ እቅዶች ካሉ ሄሮድስና ወታደሮቹን እየሆኑብን ነውና ቦታ እንዲለቁ እንጸልይ። ዛሬም እመቤታችን ማርያም እኛ እንጠፋ ዘንድ ስለማትፈልግ፤ ልጆቿ ነንና ወልዳ እንዳልወለደች መሆንን ስለማትሻ ስለኛ ትጸልያለች፣ ታማልዳለች። የልጇ ክርስቶስ ወንድምና እህቶቹ ሆነን እንኖር ዘንድ፤ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የተገዛ እለታዊ ሕይወትን ከርሷ እንድንማር ትፈልጋለች። ስለዚህ በዚህ የጌታ ልደት ዘመን እግዚአብሔር ውድ የማርያም ልጆችና የክርስቶስ ወንድምና እህቶቹ ሆነን እንኖር ዘንድ ጸጋውን ያብዛልን።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት