እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

አዎን ለነፃነት ተጠርተናል! ዘመፃጒዕ

ገላ 5፡1-18፣ ያዕ 5 13-20፣ ሐዋ 3፡1-10፣ ዮሐ 51-18

አዎን ለነፃነት ተጠርተናል!

ZeMetsaguበዘመነ ዐቢይ ጾም የያዝነው ሰንበት “ዘመፃጒዕ” ይባላል፣ “የድውይ፣ የሕመምተኛ” ሰንበት ማለት ሲሆን የጾሙ አራተኛ ሳመንት ነው። በዚህ መንፈስ የዕለቱን ንባባት ስናስተውል ገና ከጅማሬው አንድ ነገር እናስተውላለን፤ ያም በጳውሎስ መልእክት በጣም ግልጽ ባይሆንም በተቀሩት በሁሉም ውስጥ በተለያየ መልኩ የበሽታና የፈዋሽ ታሪክ አለ። ለአንድ ክርስቲያን ፈዋሽ እግዚአብሔር መሆኑንና ፈውስ ፈላጊ ደግሞ የሰው ልጅ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህም በነዚህ ንባባት አምላካችን የሚጋብዘን  ምናልባትም ሌሎች ሰዎች ለማያውቁት ውስጣዊ ደዌያችን በግለሰብ ደረጃ ከእርሱ የሆነውን ፈውስ እንድንቀበል ነው።

ዮሐንስ ወንጌላዊው የዚህን ሽባ ሰው ፈውስ ሲጽፍልን እንደው የኢየሱስን ዝና ወይ ተአምር አድራጊነት ለማመላከት ወጥኖ አይደለም፤ ይልቅስ ራሱ እንደሚለን “ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ተአምር በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እነድታምኑና አምናችሁም በእርሱ ስም የዘላለም ሕይወት እንድታገኙ ይህ ተጽፏል” (20፡30 / 21፡25)። ስለዚህ የታደለ ሽባ ሰውዬ በኢየሱስ የተፈወሰ፣ …ወዘተ ለማለት ሳይሆን ሰምተን እናምን፣ አምነንም እንድን ዘንድ ተጽፏል።

ሐዋርያው ቅ. ጳውሎስም በገላትያ 5፡1 ላይ በግልጽ “ክርስቶስ ነፃ ያወጣን በነፃነት እንድንኖር ነው” ይለናል። ክርስቲያኖች ለባርነት፣ ለኀዘን፣ ለብስጭት፣ ለጭንቀት፣ ለፍርሃትና መሰል የአናኗር ዘዬዎች አልተጠራንም፤ አዎን ለነፃነት ተጠርተናል! ይህን ክርስቲያናዊ ነፃነት ማመን መነሻ ነጥቡ ቢሆንም ቅሉ ነፃ የሚያወጣን “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንተባበር በፍቅር አማካይነት በሥራ ላይ የሚውል እምነት” መሆኑ በአፅንኦት ተገልጿል (5፡6)። እውነተኛ ነፃነት ከክርስቶስ ነው ያም ደግሞ ለክርስቲያኖች የተሰጠ ነው፤ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ እምነታችንና ሥራችን ይናበቡ እንጂ ክርስቶስ ነፃ ሊያወጣን በፍቅሩና በምሕረቱ ዛሬም ጉልበታም ነው።

ወደ ወንጌሉ ስንመለስ ኢየሱስ “ቤተዛታ/ቤተሳይዳ” ወይም “የምሕረት ቤት” በሚባለው ምንጭ አጠገብ ያልፍ ነበር፤ በዚያም በምንጩ ለመፈወስ “ብዙ በሽተኞች፣ ዕውሮች፣ አንካሶች፣ ሽባዎች” ነበሩ ይለናል ቅ. ዮሐንስ ወንጌላዊው። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የራሳችንን ቦታ ማየት መጀመር ያለብን፤ መቼም በሰፊው ትርጉሙ ከወሰድነው ማንም ሰው በሽታ የለብኝም ካለ ቢያንስ ይህን ማለት በመቻሉ አንድ የበሽታ ምልክት ነው ማለት ይቻላል፤ የምናውቀው አካላዊ ደዌ ስለሌለን ብቻ ነፃ ነኝ ማለቱ ከባድ ነው።

ሰው በመሆናችን አንድም ከማኅበራዊ ሕይወት ወይም ከስሜታዊ አሊያም ከመንፈሳዊው አቅጣጫ ፈውስ ያሻናል። ፍቅር፣ ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ትእግሥትን ከእና የሚፈልግ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል፤ ወይም እግራችን ወደማይገባ ቦታ ይመራን ዘንድ የምንፈቅድ፣ ደጋግመንም ከክርስትናዊ ሕይወታችን ጋር የሚጻረር ሁኔታ ውስጥ የምንመላለስበት ከሆነ አንካሳና ሽባነቱ ከእምነት አንጻር ግልጽ ነው፤ ይህን በመሰለ መልክ ሰፋ አድርገን ካየነው በርግጥ በክርስቶስ ፊት የፈውስ ለማኝ ሆነን ራሳችንን እናገኘዋለን።

በሽተኛነታችንን ከታመንን ቀጣዩ ትልቅ ብሥራት በዚህ የፈውስ ታሪክ ውስጥ ሂደቱን ጀማሪ ኢየሱስ ራሱ ነው “ኢየሱስ ይህን ሰው እዚያ ተኝቶ አየውና ከብዙ ጊዜ ጀምሮ መታመሙን አውቆ «መዳን ትፈልጋለህን?» አለው” (5።6)። በዚህም መልኩ ኢየሱስ ዘወትር የደካሞች ደካማ፣ ሰው ከሌለውና ከተዘነጋው ጋር እንደሚወግን አሳየ። ይህን ሲመሰክርም ሰውየው ራሱ “ሰው የለኝም አለ” (ቁ. 7)። አሁንም እያንዳንዳችንን ክርስቶስ ገና ሳናየው ከኛ ጋር ሊወግን አስቀድሞ አይቶናል፤ በየትም ስፍራ፣ በማንኛውም ዓይነት የሕይወት ሁኔታ ምናልባትም እርሱንም በሚያሳዝን አረማመድ ላይ ብንሆን “መዳን ትፈልጋለህን/ትፈልጊያለሽን?” ይለናል። ልባዊ መልስን እንስጠው፤ ካለንበት ቦታ ሆነን ወደ አፍቃሪና ፈዋሽ ልቡ አዎንታችን ያስተጋባ ዘንድ እንጩህ።

ሌላኛው ብሥራት ደግሞ ክርስቶስ ይህን ሽባ ሰው ለመፈወስ የተጠቀመው በቀጥታ ቃሉን መሆኑ ነው፤ እንደ አንዳንድ የወንጌል ፈውስ ታሪኮች ጭቃን ለውሶ አልቀባም፣ እንትፍ አላለም፣ እዚያ ሄደህ ታጠብ…አላለም። ኢየሱስ “ተነሥ! አልጋህን ተሸከምና ሂድ” አለው (5፡8)። ይህን እውነታ ከአንባቢ እይታ መቀመጫ ሳይሆን ከሽባው ሰውዬ አልጋ ላይ ሆነን ለመስማት እንሞክር። ኢየሱስ አንድ 38 ዓመታት አልጋ ላይ የነበረን ሰው፣ ጅማቶቹ እንኳን አልጋ ተሸክሞ እንዲሁ ባዶውን መራመድ ያላስቻሉቱን፣ ተዘረጋግተው የማወያውቁ ምናልባትም ሲዘረጋጉ ሊንጫጩ የሚችል አጥንቶች ያሉት፣ ለዓመታት መራመድ የሚባል ነገር የእኔ ነው ብሎ የማያስብን ሰው “ተነሥ!” ብቻ ሳይሆን “ተሸከም!” ይለዋል። ምናልባት እምነት በልቡ ቀድሞ ተንሸራሽሯል እንጂ ይህ ሽባ ሰው “አዬ ታሾፍብኛለህ አይደል! የእጅህን ይስጥህ” ብሎ ተመልሶ ወደልማደኛው አልጋው ቢተኛ’ኳ ቅር የማያሰኘን በመሰለ ነበር። ነገር ግን ቃሉን አመነው ታዘዘውም። የኢየሱስ ቃል ለአመኑትና ለታዘዙት ጅማትን ይነካል፣ ደረቅ አጥንትን ያለመልማል።

ተነሥ ተብሎ ሰውዬው ከተነሣ በኋላ በል አሁን ደግሞ አልጋህን ተሸከም አይደለመ ትእዛዙ፤ በአንድ ላይ ተነሥ፣ ተሸከም ነው፤ ብዙ ጊዜ ከተኛንበትም ሆነ ከተቀመጥንበት ሳናስተውለው የመነሣት ልምድ ስላለን ብዙም ጠለቅ ብለን አናስበው ይሆናል እንጂ መነሣት በራሱ ቀላል ነገር አይደለም፤ ተአምር ነው። ለዚህ ለሽባ ሰው ደግሞ ልዩ ተአምር። ይህን ሰው ከአልጋው ያስነሣው የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ካልሆነ ሌላ ምንም ሊገባን አይችልም። ይህ ቃል ውስጥን ይነካል፣ እኛም እንደው ጆሯችንን ዳብሶ ዝም ብሎ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ቃል የለንም፤ ካመንነው ከማንኛውም ደዌያችን ያነሣናል። ውስጣችንን ከከፈትንለት ከወስጥ ይፈውሰናል። ሰላም፣ ፍቅር፣ እርቅ የእኔ አይደለም የሚል ሰው ካለ በእግዚአብሔር ቃል ይመን የእርሱ ነው።

ጴጥሮስና ዮሐንስ በሐዋርያት ሥራ ላይ ያደረጉትን ተመሳሳይ ታሪክ ስናነብ ከላይ ያልነውን እውነታ ሁሉ ያጠናክርልናል (3፡1-10)። እነርሱም ወደ ቤተ መቅደስ ለጸሎት ሲያቀኑ አንድ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረ ሰው ምጽዋት ሲለምን ያዩታል ግን ዝም ብሎ ማየት ሳይሆን “ትኩር ብለው አዩትና ወደ እኛ ተመልከት አሉት”። ትኩር ብለው አዩት ማለት በርግጥ ይህ ሰው የሚያስፈልገው እርሱ የሚፈልገው ነገር ማለትም ምጽዋት እንዳልሆነ የመረዳታቸው ኃይል ነው። ስለዚህም በዚያች ሰዓት ሰውየው የፈለገውን ሳይሆን የሚየስፈልገውን “ብርና ውርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እስጥሃለሁ፣ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተራመድ” ብሎ ጴጥሮስ አወጀለት። “ቀኝ እጁንም ይዞ አሥነሳው፣ ወዲያውኑ እግሩና ቁርጭምጭሚቱ በረታ”። ይህ ነው የእግዚአብሔር ሥራ!

በመጨረሻም በወንጌሉ የፈውስ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ሽባ ለነበረው ኋላ ግን ለተፈወሰው ሰውዬ አደራ የሚለው ነገር አለ፤ “እነሆ አሁን ድነሃል! ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ” (5፡14)። ክርስቶስ ማንንም ቢሆን ለመፈወስ ዝግጁ ነው ያደርገውማል፤ ግን ይህንን ፈውስ ሁሌ ተግቶ መጠበቅ የእያንዳንዱ ክርስቲያን የዘወትር የቤት ሥራው ነው። ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያንን በቃሉና በምሥጢራት፣ በዳበረ የቅዱሳን ታሪክና ትስስር የሰጠን። የምሕረት አምላክ በሥጋውና ደሙ ራሳችንን እየመገብንና በኑዛዜ እየጸዳን በጸሎት ድጋፍ በርትተን የባሰ ነገር እንዳይመጣብን የምንቆም ክርስቲያኖች ያድርገን። አሜን።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት