እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የኦሪት ዘፍጥረት ጥናት - ክፍል ሁለት

የኦሪት ዘፍጥረት ጥናት - ክፍል ሁለት

እግዚአብሔር አብረሃምን ለምን ለይቶ ጠራው?

Abrhamይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ጥሪ ወይም መጠራት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እናስቀድም ፡፡

እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ወደ ልጁ የሠርግ ግብዣ ይጠራል (ማቴ 22, 3-9) ፤ ይህም ማለት እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በወንጌል በኩል ለደኅንነት ይጠራል (ኢሳ 55, 1 ፣ ዮሐ 3, 16 ፣ ሐዋ 12, 30) ፡፡ የወንጌሉን ጥሪ ግን ሁሉም አይቀበሉም ፤ የሚቀበሉት በልቡናቸው ልዩ የእግዚአብሔር ጥሪ ሲሰማቸው ብቻ ነው (ማቴ 13, 9 ፣ 22, 14 ፣ ዮሐ 6, 44) ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጥሪ የንስሓ ጥሪ በመባል ይታወቃል (ሉቃ 5, 32 ፣ ማር 2, 17, ማቴ 9, 13) ፡፡ ይህ ጥሪ ለነፃነትና ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖረን ነው (1 ቆሮ 1, 9 ፣ ገላ 5, 13) ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር አንድን ግለ ሰው ብቻ ለይቶ ለተለየ አገልግሎት ይጠራል ፡፡ ለምሳሌ አብርሃም ፣ ሙሴ እና ነቢያቶች መጥቀስ ይቻላል ፡፡ ይህ የተጠራው ሰው ሙሉ የሆነ ነፃነት ስላለው ጥሪውን የመቀበል ወይም ያለመቀበል መብት አለው ፡፡ ጥሪውን ከተቀበለ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው አንድ ልዩ የሆነ ተልእኮ ይሰጠዋል ፡፡ በዚህ በጎ ፈቃደኛ በሆነው ሰው አማካኝነትም እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲገለገል ያደርጋል ፡፡ የአብርሃምም ጥሪ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ ባጠቃላይ አብረሃም የተጠራበት ምክንያት ከዘሩ ክርስቶስ በሥጋ እንዲወለድ ነው ፡፡ “የምድር ነገዶች በአንተ ይባረካሉ” (ዘፍ 12, 2-3) የሚለው ተስፋ የተፈጸመው በክርስቶስ ነው ፡፡

አብረሃም ማለት ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር ምን ያህል ጊዜና በምን ምክንያትስ አነጋገረው?

አብረሃም የመጀመሪያ ስሙ አብራም ነበር ፤ አብራም ማለት ታላቅ አባት ማለት ነው ፡፡ በኋላ ግን እግዚአብሔር ለብዙ አሕዛብ አባት ትሆናለህ በማለት አብረሃም ብሎ ስሙን ለወጠ (ዘፍ 17, 1-5) ፡፡ አብረሃም የታራ ታላቅ ልጅ ነው ፡፡

እግዚአብሔር አብረሃምን ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ወይም ምክንያቶች አነጋገረው ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ፦

1) ለእስራኤል ሕዝብ አባቶች የመጀመሪያው ይሆን ዘንድ ከትውልድ አገሩ ከከለዳውያን ዑር እንዲወጣ በጠራው ጊዜ አነጋገረው (ዘፍ 12, 1-6 እና ሐዋ 7, 2-3) ፡፡

2) ከአባቱ ከታራና ከአጐቱ ልጅ ከሎጥ ጋር ሆኖ ከዑር ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ ፡፡ ከካራን ወጥቶ ወደ ከነዓን ምድር ሲገባ ያችን ምድር ለዘሩ እንደሚሰጥ በግልጥ አነጋገረው (ዘፍ 12, 7) ፡፡

3) ለጥቂት ጊዜ በሴኬም ፣ በቤቴልና በአዜብ ወይም በደቡብ አገር ቆይቶ በራብ ምክንያት ወደ ግብጽ ተጓዘ ፡፡ ከዚያም ተመልሶ በኬብሮን ከቆየ በኋላ ከሎጥ በተለያየ ጊዜ አነጋረው (ዘፍ 13) ፡፡

4) ወራሽ ልጅ እንደሌለው አይቶ ባዘነ ጊዜ በራእይ አነጋገረው (ዘፍ 15, 1-21) ፡፡

5) ስሙን አብረሃም ብሎ በለወጠ ጊዜ ተገልጦ አነጋገረው (ዘፍ 17) ፡፡

6) በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር ተገልጦ ካነጋገረው በኋላ ወደ ቤቱ ገብቶ ሚስቱ ሣራ ልጅ እንደምትወልድለት ተስፋውን ነገረው ፡፡ በኋላም ስለ ሰዶምና ገሞራ ብዙ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ተወያየ (ዘፍ 18) ፡፡

7) ልጁን ይስሐቅን እንዲሠዋ በፈተነው ጊዜ አነጋግሮታል (ዘፍ 22, 1-18) ፡፡

የአብረሃም የትዳር ሕይወት ምን ይመስል ነበር? ስንት ልጆችስ ነበሩት? የሕይወቱ መጨረሻስ እንዴት ተጠናቀቀ?

            አብረሃም እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ሳይጠብቅ አጋር ከተባለች ግብጻዊት ገረዱ እስማኤልን ወለደ (ዘፍ 16) ፤ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑንና ምልክት የሆነውን ግዝረት ከሰጠው በኋላ ግን የተስፋ ልጁ ይስሐቅ ከሚስቱ ከሣራ ተወለደለት (ዘፍ 17 እና 21, 1-3) ፡፡ ሚስቱ ሣራ ከሞተች በኋላ ቀጡራ የተባለችውን ሴት አግብቶ 6 ልጆች ወለደ (ዘፍ 25, 1-2) ፡፡

አብርሃም በከነዓን አገር በድንኳን ውስጥ ይኖር ነበር ፡፡ ባረፈበትም ሁሉ መሠዊያን ይሠራ ነበር ፡፡ ዘሩ አገሩን እንደሚወርስ ተተነበየለት ፡፡ ተስፋውም በምድራዊ ርስት ብቻ ሳይሆን በሰማያዊ አገርም እንደሚፈጸም ተረዳ (ዕብ 11, 8-16) ፡፡ በ175 ዓመቱ ሞተና በኬብሮን ተቀበረ (ዘፍ 25, 9-10) ፡፡

አብረሃም ስለ ሰዶምና ገሞራ  ሕዝቦች እግዚአብሔርን እንደማለደ (እንደለመነ) ይታወቃል ፤ የሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች ኃጢአት ምን ነበር? እግዚአብሔርስ ለምን ሊያጠፋቸው ወሰነ?

            ሰዶምና ገሞራ የሚባሉት መንደሮች በዮርዳኖስ ሸለቆ የተቈረቈሩ ከተሞች ነበሩ ፡፡ ኃጢአታቸው በተለይም የዝሙት ሥራቸው አስጸያፊ ስለነበር እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ወሰነ (ዘፍ 18, 20 ፣ 19, 5-9) ፡፡ ሁለት መላእክት ሎጥን ከከተማው ካወጡ በኃላ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን በእሳትና በዲን አጠፋ (ዘፍ 19, 10-26) ፡፡ ሰዶምና ገሞራ አሁን በጨው ባሕር እንደተሸፈኑ ይገመታል ፡፡ ሰዶም የክፋት ሁሉ የፍርድም ምሳሌ በመሆን ተጠቅሷል (ኢሳ 1, 9-10 ፣ ኤር 23, 14 ፣ ሕዝ 16, 46 ፣ ማቴ 10, 15 ፣ ራእ 11, 8) ፡፡

            ይህ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ግን አብረሃም ስለነዚህ ከተሞች እግዚአብሔርንን ተማጽኖታል ፡፡ የአብረሃም ጥያቄ ወይንም ጭንቀት የነበረው ከተማው ውስጥ የሚገኙትን ንጹሓን ሰዎች እንዴት ከኃጢአተኞች ጋር አብረው ይደመሰሳሉ የሚል ነበር ፡፡ እንዲህም አለው “በእርግጥ በደል የሌለባቸውን ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህን? በከተማዪቱ ውስጥ ኀምሳ ደጋግ ሰዎች ቢገኙ ከተማዪቱን በሙሉ ትደመስሳለህን? ስለ ኀምሳው ደጋግ ሰዎች ስትል ከተማዪቱ እንዳትጠፋ አታደርግምን? በደል ያልሠሩት ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህ ብዬ አላስብም ፤ ይህንን እንደማታደርገው አምናለሁ ፤ ይህንንማ ካደረግህ ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር መቀጣታቸው ነው ፤ ይህ ከቶ አይሆንም ! የዓለም ፈራጅ በትክክል መፍረድ ይገባዋው የለምን?” በማለት እግዚአብሔርን ጠየቀ ፡፡ እግዚአብሔርም ዐሥር ንጹሓን ሰዎች እንኳ ከተማዪቱ ውስጥ ቢገኙ ከተማዪቱን እንደማይደመስስ ቢነግረውም ከተማዪቱ ከመደምሰስ አላመለጠችም ፤ በእርግጥም ሁሉም በኃጢአት ተዘፍቀው ነበርና ፡፡

  ሰዶማውያን ማለት ምን ማለት ነው? ከሰዶም ከተማ ጋር ምን የሚያዛምደው ነገር አለን?

            ሰዶማውያን ማለት ግብረ ሰዶምን የሚፈጽሙ ማለት ነው ፡፡ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ማለት ደግሞ ወንድ ከወንድ ጋር ሴት ከሴት ጋር ዝሙት የሚያደርጉ ማለት ነው ፡፡ ይህ ኃጢአት በሰዶም ይበዛ ነበርና ግብረ ሰዶም ተባለ (ዘፍ 19, 5) ፡፡ በሙሴ ሕግ ይህን ኃጢአት የሚፈጽሙ ሁሉ ያለ ምሕረት ይገደሉ ነበር (ዘሌ 20, 13 ፣ ዘዳ 23, 17) ፡፡ ሆኖም ይህ ኃጢአት በእስራኤል የተለመደ ነበር (መሳ 19,22 ፣ 1ነገ 14, 24 ፣ 2ነገ 23, 7) ፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን መፍራትና ማምለክ ሲተዉ ለጣኦታትም ሲሰግዱ የዚህ ዓይነት መጥፎ መንፈስ ያድርባቸዋል ፤ በአሕዛብ መካከል ይህ ኃጢአት ይገኛል (ሮሜ 1, 22-27 ፣ 1ጢሞ 1, 9-11) ፡፡ ይህ ዓይነት መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች በወንጌል ኃይል ሊድኑ ይችላሉ (ማር 6, 11 ፣ 1ቆሮ 6, 9-11) ፡፡

የሰዶምና የገሞራ ሕዝቦች ብዙ ብዙ ኃጢአቶች በመፈጸማቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አሳዝነው እንደነበና እግዚአብሔርም እንደቀጣቸው ከላይ ተገልጿል ፤ እንደ ቅዱሳን  መጻሕፍት አገላለጽ ሌሎች ከባድ ቅጣት ሊያስከትሉ የሚችሉ ኃጢአቶች የትኞቹ ናቸው?

            በእስራኤል ሕግ ነፍስ የገደለ ፣ ወላጆቹን የመታ ወይም የሰደበ ፣ ሰንበትን የሻረ ፣ ባዕድ አምልኮትን የተከተለ ፣ ያመነዘረ ፣ ከተፈጥሮ ጋር የማይስማማ የጾታ ግኑኝነትን ያደረገ የሞት ቅጣት ይፈረድበት ነበር (ዘጸ 21, 12-17 ፣ 22, 18-20 ፣ ዘሌ 24, 14-16 ፣ ዘኁ 15, 32-36) ፡፡

            ሰው ሰውን ቢጎዳ እንደ ጉዳቱ መጠን ካሣ መክፈል ነበረበት (ዘጸ 21, 23 - 25,30) ፡፡ ሰው ሲያጠፋ ሊገረፍ ይችላል ፤ የግርፋቱ ቁጥር ግን እንደ ኃጢአቱ መጠን ሆኖ ግርፋቱ ግን በአርባ የተወሰነ ነበር (ዘዳ 25, 1-3) ፡፡ በእስራኤል ዘንድ የሞት ቅጣት በድንጋይ በመውገር ፣ በእንጨት ላይ በመስቀል (ዘዳ 21, 22-23 ፣ ዘዳ 22, 24) ፣ በሮማውያ ዘንድ ራስን በመቁረጥ (ማቴ 14, 10) ወይም በስቅላት ይፈጸም ነበር (ማር 15, 21-25) ፡፡

በአዲስ ኪዳን ስናይ ደግሞ ከቅጣት ጋር በተያያዘ መልኩ የተጠቀሱ ነገሮች አሉ ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንደ ሥራው ይቀጣል (ሉቃ 12, 46-48 ፣ ራእ 20, 11-15) ፡፡ በደለኛ ለዘለዓለም ይቀጣል (ዳን 12, 2 ፣ ማቴ 25, 46) ፡፡ እግዚአብሔር ልጆቹን ይቀጣል ፤ ይህ ለጥቅማቸው ስለሆነ በትዕግሥት ሊቀበሉት ይገባል (ዕብ 12, 5-11) ፡፡  

አብርሃም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታዎች በጥሩ ተምሳሌትነቱ ተጠቅሶ ይገኛል ፤ የእምነት አባት በመባልም ይታወቃል ፤ ይህ ሊያሰኘው የቻለው ምንድን ነው?

አብርሃም ጥሩ ተምሳሌትነቱና የእምነት አባትነቱ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱበት ምክንያቶቸ ውስጥ የሚከተሉትን ይገኙበታል

1) ለእግዚአብሔር ታዛዠ ሆኖ በመገኘቱ (ዮሐ 8, 39-40 ፣ ዕብ 11, 17-19 ፣ ያዕ 2, 21-24) ምሳሌነቱ በተደጋገሚ ይጠቀሳል ፡፡ የአብረሃም ታዛዠነት የሚወደውን አንድ ልጁን ይስሐቅን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ እስከማቅረብ ይደርሳል (ዘፍ 22) ፡፡

2) እምነቱ ጠንካራ ስለነበርና ጽድቅ ሆኖ ስለተቆጠረለት የምእመናን ሁሉ አባት ተብሎ ተጠራ ስለዚህ በእርሱ የማመን ምሳሌ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ በእምነት እንደሚጸድቁ ተደጋግሞ ተነግሯል (ሮሜ 4 እና ገላ 3, 6-7) ፡፡

3) በጠንካራው እምነቱ የዓለም ወገኖች ሁሉ በእምነት የአብረሃም እውነተኞች ልጆች የተስፋውም ወራሾች ተብለው በመጠራታቸው ምክንያት አብረሃም ተደጋግሞ ይጠቀሳል (ሮሜ 4, 11-12 ፣ ሮሜ 9, 7-8 ገላ 3, 7-9 እና ቁ. 29) ፡፡ 

አብረሃም ከልጆቹ መካከል ለየትኛው ነው እግዚአብሔር “የአብረሃምን ተስፋ” ያጸናለትና የባረከውም?

እግዚአብሔር የአብረሃምን ተስፋ ያጸናለትና የባረከውም ለልጁ ለይስሐቅ ነው (ዘፍ 26, 3-5 ፣ ዘፍ 26, 12-29) ፡፡ ይስሐቅ ማለት “ይስቃል” ማለት ነው ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የአብርሃምና የሣራ ልጅ ሲሆን የያዕቆብም አባት ነው ፡፡ ሣራ በስተእርጅናዋ ወለደችው (ዘፍ 17, 15-21 ፣ ዘፍ 18, 9-15 እና ዘፍ 21, 1-7) ፡፡ ከመወለዱ 25 ዓመት ቀደም ብሎ ለአብረሃም የተሰጠው የዘር ተስፋ በይስሐቅ ሊፈጸም ጀመረ (ዘፍ 12, 1-3 ፣ ማቴ 1, 2 ገላ 3, 16) ፡፡

ይስሐቅ ተገረዘ (ዘፍ 21, 4) ፡፡ “በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል” ስለተባለ እስማኤል ተሰደደ (ዘፍ 21, 8-14) ፡፡ አብረሃም ይስሐቅን ለመሥዋዕትነት አቀረበ (ዘፍ 22) ፡፡ ይስሐቅ ርብቃን አገባ (ዘፍ 24) ፡፡ ከጸለየም በኋላም ዔሳውንና ያዕቆብን ወለደችለት (ዘፍ 25, 19-26) ፡፡

በዘመኑ ራብ በሆነ ጊዜ ወደ ፍልስጤም ተሰደደ ፤ እግዚአብሔርም ወደ ግብጽ አትውረድ አለው (ዘፍ 26, 1-2) ፡፡ 180 ዓመት ሲሆነው ሞተ (ዘፍ 35, 28-29) ፡፡ ጳውሎስ በእምነት የተወለዱትን የእግዚአብሔር ልጆች “የተስፋ ቃል ልጅ” በሆነው በይስሐቅ መሰላቸው (ሮሜ 9, 6-9 ፣ ገላ 4, 21-31) ፡፡ ከዚህም በላይ የእምነት ሰው መሆኑን በዕብ 11, 9 እና ቁ. 20 ተጽፎ እናገኛለን ፡፡

ይስሐቅንና ሚስቱ ርብቃ በሕይወታቸው ሁሉ ሲያዝኑበት የኖረው ጉዳይ ምን ነበር?

            ከልጆቻቸው መካከል በኩር የነበረውና ብኩርናውን ለታናሽ ወንድሙ ለያዕቆብ በቀይ ምስር ወጥ የሸጠው ዔሳው ከወገኖቹ ውጭ ከሆኑት ሁለት ሴቶች ጋር ጋብቻ በመፈጸሙ ነው (ዘፍ 26, 34-35) ፡፡ ይስሐቅ ያዕቆብን እንደመረቀውና ሚስት እንዲፈልግ ወደ መስጴጦምያ እንደላከው ዔሳው ተረዳ ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ሲመርቀው “ከነዓናዊት ሴት እንዳታገባ” ብሎ ያዘዘው መሆኑን ሰማ ፤ በዚህም አባቱ ይስሐቅ የከነዓናውያንን ሴቶች እንደማይወድ ዔሳው ተገነዘበ ፤ ስለዚህ ከዚህ በፊት ካገባቸው ሌላ በተጨማሪ ወደ አብርሃም ልጅ ወደ እስማኤል ሄዶ ልጁን ማሕላትን አገባ ፤ እርስዋም የነባዮት እኅት ናት ፡፡

በተለምዶ በኩር የሆነ ልጅ የአባቱ ምርቃት እነደሚቀበል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳልን ፤ ታድያ ይስሐቅ የበኩር ልጁ ዔሳው እያለ ለምንድን ነው ለያዕቆብ የባረከው?

            በእርግጥ ይስሐቅ ባሕሉን ወይም የተለመደውን አደራረግ በመከተል የበኩር ልጁን ዔሳውን ሊመርቀው ይፈልግ ነበር ነገር ግን ያዕቆብ በእናቱ በርብቃ ምክር ታግዞ አርጅቶና ዐይኖቹ ታውሮ የነበረውን አባቱን በማታለል ምርቃቱን ተቀበለ ፡፡ አባቱም ያዕቆብን እንዲህ በማለት መረቀው ፦ “እግዚአብሔር ከሰማይ የሚያረሰርስ ጠል ይስጥህ ፤ ምድርህን ያለምልምልህ ፤ እህልህንና የወይን ጠጅህን ያብዛልህ ፤ መንግሥታት ይገዙልህ ፤ ሕዝቦችም ያገልግሉህ ፤ በወንድሞችህ ሁሉ ላይ አለቃ ሁን ፤ የእናትህንም ልጆች ይስገዱልህ ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ ፤ የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ” (ዘፍ 27, 28-29) ፡፡

አባቱን ይስሐቅን በማታለል ምርቃት(በረከትን) የተቀበለው ያዕቆብ የሕይወት ጉዞ ምን ይመስል ነበር?

-    ያዕቆብ ማለት “ተረከዝን ይይዛል” የሚለው ትርጉም ይሰጣል ፡፡ ይህም መንትያ ከነበረው ወንድሙ ከዔሳው ጋር ሲወለድ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ከእናቱ ማሕፀን በመውጣቱ ነው ያዕቆብ ሊባል የቻለው (ዘፍ 25, 19-26) ፡፡ ስለዚህ ያዕቆብ ርብቃ ለይስሐቅ ከወለደችለት መንታዎች ታናሹ የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች አባት ነው ፡፡

-    ያዕቆብ ከዔሳው ለማምለጥና ሚስት ለማግኘት ወደ እናቱ ወንድም ወደ ላባ ሄደ (ዘፍ 27, 42 - 28, 9) ፡፡ የመሰላልን ሕልም አየ ፤ የአብርሃምም ተስፋ ተሰጠው (ዘፍ 28, 10-22) ፡፡

-    ያዕቆብ ሃያ ዓመት ላባን አገልግሎ ልያንና ራሔልን አገባ ፤ ብዙ ልጆችም ወለደ ፤ ብዙ ከብትም አገኘ (ዘፍ 29-30) ፡፡ 

-    እግዚአብሔር ወደ ከነዓን እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ ከላባ ቁጣ (ዘፍ 32-33) ጠበቀው ፡፡ እግዚአብሔር በጵኒኤል (ዘፍ 32, 22-32) በቤቴልም (ዘፍ 35, 9-15) ተገለጠለት ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው ፡፡

-    ብዙ ዓመት በከነዓን ከኖረ በኋላ (ዘፍ 33, 18-45) በረሃብ ጊዜ ወደ ግብጽ ሄደ (ዘፍ 46-47) ፡፡ ትንቢት እየተናገረ የዮሴፍን ልጆች የራሱንም ዐሥራ ሁለት ልጆች ከባረከ በኋላ 147 ዓመት ሲሆነው ሞተ (ዘፍ 47, 27-49, 33) ፤ በአብርሃምም መቃብር ተቀበረ (ዘፍ 50) ፡፡ ከእርሱ የተገኘው ሕዝብ እስራኤል አንዳንዴም “ያዕቆብ” ይባለል (ዘኊ 23, 10 ኢሳ 41, 8-21) ፡፡

-    ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት ፤ እነዚህም የልያ ልጆች የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ ሮቤል ፣ ስምዖን ፣ ሌዊ ፣ ይሁዳ ፣ ይሳኮርና ዛብሎን ናቸው ፡፡ የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው ፡፡ የራሔል አገልጋይ የነበረቸው የባላ ልጆች ዳንና ንፍታሌም ናቸው ፡፡ የልያ አገልጋይ የነበረችው የዚልፋ ልጆች ጋድና አሴር ናቸው ፡፡

  ከያዕቆብ ዐሥራ ሁለቱ ልጆች ውስጥ የትኛውን ነው በአባቱ በጣም የተወደደውን የተባረከው?

-    በአባቱ የተወደደውና የተባረከው የያዕቆብ ዐሥራ አንደኛው ወንድ ልጅ የነበረውና የራሔልም በኩር ልጅ ዮሴፍ ነው ፡፡ ዮሴፍ ማለት “ይጨምር” የሚል ትርጉም ይሰጣል (ዘፍ 30, 22-24)፡፡ ከጸባዩ መልካምነትና ከዝናው ፣ ከፈጸመውም ታላቅ ሥራ የተነሣ ከያዕቆብ ልጆች ሁሉ የተከበረ ሆነ ፡፡ አባቱ በተለይ ወደደው ፡፡ ብዙ ሕልም ስላየና ስለ ወንድሞቹ መጥፎ ወሬ ለአባታቸው ስላወራ ጠልተው ሸጡት (ዘፍ 37) ፡፡

-    በግብጽ ባርያ ሆኖ ሳለ በጶጢፋር ቤት ለአስተዳዳሪነት ተሾመ ፡፡ የጶጢፋር ሚስት በሐሰት ስትከሰው ግን በግዞት ታሰረ ፡፡ እዚያም ሞገስን አግኝቶ ከግዞት ቤት አለቃ በታች ኀላፊ ሆነ (ዘፍ 39) ፡፡ ሕልሞችን ለመተርጐም ስለቻለ ፈርዖን ፈታው ፤ በአገሩም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገው (ዘፍ 40, 41) ፡፡ ሰባት ዓመት እህልን እየሰበሰበ በረሀብ ዘመን ብዙ ሰዎችን የገዛ ራሱን ቤተሰብ ጭምር ከሞት አዳነ (ዘፍ 42-45) ፡፡

-    ዮሴፍ ግብጻዊቷን አሰናትን አግብቶ ምናሴንና ኤፍሬምን ወለደ (ዘፍ 41, 50-52) ፡፡ አባቱንና ወንድሞቹን ወደ ግብጽ አስመጥቶ መገባቸው (ዘፍ 46, 1-47) ፡፡ አባቱ በከነዓን ቀበረው (ዘፍ 49, 29-50) ፡፡ ዮሴፍ በወንድሞቹ ቂም አልያዘም (ዘፍ 50, 15-21) ፡፡ ሳይሞት ዐፅሙን በከነዓን እንዲቀብሩት የእስራኤልን ልጆች በማማሉ እምነቱን ገለጠ (ዘፍ 50, 22-24 ፣ ኢያ 24, 32 ፣ ዕብ 11, 22) ፡፡

-    ዮሴፍ ከእስራኤል ነገዶች የሁለቱ አባት ሆነ ፡፡ ያዕቆብ ብኩርናው ለዮሴፍ ይሁን በማለት የዮሴፍን ልጆች ምናሴንና ኤፍሬምን ባረከ ፤ በስሞቻቸውም ነገደ ምናሴና ነገደ ኤፍሬም ተብለው ተጠሩ (1 ዜና መ. 5, 1 ዘፍ 48 ዘኁ 1, 4-10 ፣ ዘዳ 33, 13-17) ፡፡

እስራኤላውያን በግብጽ አገር በባርነት ለብዙ ዘመናት እንደኖሩ ይታወቃል ፤ ለመሆኑ እስራኤላውያን ከታሪኩ መጀመሪያ እንዴት ግብጽ ውስጥ ሊገኙ ቻሉ? የእስራኤላውያን የግብጽ ኑሮ አጀማመር እንዴት ነው?

-    ዮሴፍ በወንድሞቹ ተሸጦ ወደ ግብጽ ከወረደ በኋላ ግብጻዊቷን አስናትን አግብቶ ምናሴንና ኤፍሬምን እንደወለደና ዘሩም እዘው ግብጽ ውስጥ እንደበዛ ይታወቃል ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ዮሴፍ በግብጽ ውስጥ አስተዳዳሪ በሆነበት ዘመን በግብጽና በሌሎችም አገሮች ለሰባት ዓመታት ከባድ ረሃብ ሆነ ፤ ዮሴፍ ግን ቀድሞ በጐተራዎች እህል አከማችቶ ስለነበር ግብጻውያን አልተራቡም ፡፡ በግብጽ እህል መኖሩን የሰማው ያዕቆብ እሱና ልጆቹ በረሃብ ከመሞታቸው በፊት ልጆቹን ከነበሩበት ከከነዓን ወደ ግብጽ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል (ዘፍ 42, 1-2) ፡፡ በመጨረሻም ያዕቆብና ቤተሰቡ በግብጽ አገር በዮሴፍ ጥበቃ ሥር መኖር ጀመሩ ፤ እጅግም ተባዙ ፡፡ እያንዳንዱ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ወደ ግብጽ ምድር የገቡት እስራኤል ተብሎ የተጠራው የያዕቆብ ልጆች ብዛት ሰባ ነበሩ (ዘጸ 1, 1-6) ፡፡ እነዚህ እስራኤላውያን ተዋልደው ቁጥራቸው ከመብዛቱ የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሉአት ፤ እጅግም ብርቱዎች ሆኑ ፡፡

  እስራኤላውያን ግብጽ ውስጥ በዮሴፍ ጥበቃ ሥር በታላቅ እንክብካቤ ንብረት አፍርተው ፣ ቤተሰብ መሥርተውና ተደላድለው ይኖሩ ከነበረ ኑሮአቸው እንዴት ወደ ባርነት ሊለወጥ ቻለ? ግብጻውያን ለምን እስራኤላውያንን መጥላት ጀመሩ?

-    ዋናው የግብጻውያን ጥላቻ መነሻ የሆነው ዮሴፍ ስለሞተና እሱ ያደረገው መልካም ነገር ሁሉ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብጽ አገር ስለተነሣ ነው ፡፡ እርሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ “እነሆ እነዚህ እስራኤላውያን ቁጥራቸው በዝቶአል ፤ የኀይላቸውም ብርታት አስጊ ሆኖብናል ፤ ከዚህም የተነሣ ከጠላቶቻችን ጋር ተባብረው ከወጉን በኋላ ከአገሪቱ አምልጠው መሄድ ይችላሉ ፤ ስለዚህ ቁጥራቸው እየበዛ እንዳይሄድ ኑ አንድ ዘዴ እንፍጠርባቸው” (ዘጸ 1, 8-10) ፡፡ ስለዚህ ንጉሡ በሰላም ተፋቅረውና ተከባብረው ይኖሩ በነበሩት ሁለቱ ሕዝቦቸ መካከል የጥላቻ መንፈስ ዘራባቸው ፡፡

-    የግብጽ ንጉሥ ጨካኞች የሆኑ አሠሪዎች ሾመባቸው ፤ ርኅራኄ በጎደለውም ጭካኔ በባርነት ያሠሩአቸው ጀመር ፤ ጭቃ በማቡካት ፣ ጡብ በማዘጋጀትና በእርሻ ውስጥ በጭካኔ ከባድ ሥራ በማሠራት ሕይወታቸው መራራ እንዲሆን አደረጉ ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በተጨቈኑ መጠን ቁጥራቸው ይበልጥ እየበዛና በምድሪቱም ላይ እየተስፋፉ ሄዱ ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ፈሩአቸው (ዘጸ 1, 12-14) ፡፡

-    ከዚህም በላይ ንጉሡ ሁለት ግብጻውያን አዋላጆች ጠርቶ የዕብራውያን (የእስራኤላውያንን) ሴቶች ሲያዋልዱ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ወዲያውኑ እንዲገድሉት አዘዘ ፡፡ አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ የግብጽ ንጉሥ እንዳዘዛቸው አላደረጉም ፤ እንዲያውም ወንዶችም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ አደረጉ ፡፡ ከዚህ በኃላ ንጉሡ ከእስራኤላውያን አዲስ የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ እያነሣችሁ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉ ሲል ለሕዝቡ ጥብቅ ትእዛዝ በማስተላልፍ ሕዝቡ ለእስራኤላውያን ያላቸውን ጥላቻ የከፋ እንዲሆን አደረገው ፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

ጸሐፊ ፦ ለምለም ክፍሌ

 

 

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች 

1- እግዚአብሔር አብራምን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠራው “አገርህን ትተህ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤተ ሰብ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ” ብሎታል ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ብዙ ነገሮች ቃል ገብቶለታል (ዘፍ 12, 1-3) ፡፡ ከሚከተሉት ውስጥ አንዱ እግዚአብሔር ለአብራም ከገባለት ቃል ውስጥ የማይካተተው የትኛውን ነው? 

ሀ) ረዥም ዕድሜ እንድትኖር አደርግሃለሁ ፤ ሞትም አይነካህም 

ለ) ዘርህን አበዛዋለሁ ፤ ታላቅ ሕዝብም ይሆናል ፤ እባርክሃለሁ 

ሐ) ስምህን ገናና አደርገዋለሁ ፤ ለሌሎችም በረከት ትሆናለህ 

መ) የሚመርቁህን እመርቃለሁ የሚረግሙህን እረግማቸዋሁ 

ሠ) በአንተ አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ

2- አብራም ከዶርላዖሜርና ከእነርሱ ጋር አብረው የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም ለአብራም እንጀራና የወይን ጠጅ አመጣለት ፤ ባረከውም ፡፡ በዚህ ጊዜ አብራም ለመልከ ጼዴቅ ምን አደረገለት? (ዘፍ 14, 17-24)

ሀ) በምላሹ አብራም መልከ ጸዴቅን ባረከው

ለ) መልከ ጼዴቅ ስለ አብራም የወደፊት ኑሮ ትንቢት ተናገረው

ሐ) አብራም በምርኮ ካገኘው ሀብት ሁሉ አንድ ዐሥረኛውን ለመልከ ጼዴቅ ሰጠው

መ) መልከ ጼዴቅ ለአብራም ዐሥራት ሰጠው

3- አብራም ስሙ ከተቀየረ በኋላ አብረሃም ተብሎ መጠራቱን ይታወቃል ፡፡ ለመሆኑ አብረሃም ለምንድን ነው የእምነት አባት ተብሎ በክርስቲያኖች ዘንድ የሚታወቀው ወይም የሚጠራው?

ሀ) አገርህን ትተህ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤተ ሰብ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ ሲባል በመቀበሉና በተግባር በመፈጸሙ (ዘፍ 11)

ለ) ይስሐቅን እንዲሠዋለት ባዛዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላከናወነ (ዘፍ 22)

ሐ) አብረሃም ቢሸመግልም ልጅ እንደሚወልድ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የተስፋውን ቃል አምኖ በመቀበሉ (ዘፍ 18)

መ) ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ወዳጅነት ስለነበረውና በእምነቱም ብርቱና ጻድቅ ስለነበር (ዘፍ 18, 17)

ሠ) ሁሉም

4- ከሚከተሉት ውስጥ ሰዶማውያንን ወይም ከሰዶማውያን ከሚለው ቃልና ትርጓሜ ጋር የማይካተተው የትኛው ነው?

ሀ) ሰዶማውያን ማለት ግብረ ሰዶምን ማለትም ወንድ ከወንድ ጋር ፣ ሴት ከሴት ጋር ዝሙት የሚያደርጉ ማለት ነው

ለ) ግብረ ሰዶማዊነት በተፈጥሮ የሚመጣ በሽታ ወይም በተፈጥሮ የሚሰጥ ባሕሪይ ነው

ሐ) በሙሴ ሕግ ይህን ኃጢአት የሚፈጽሙ ሁሉ ያለ ምሕረት ይገደሉ ነበር

መ) ሰዎች እግዚአብሔርን መፍራትና ማምለክ ሲተዉ ለጣኦታትም ሲሰግዱ የዚህ ዓይነት መጥፎ መንፈስ ያድርባቸዋል

ሠ) ግብረ ሰዶማውያን ከተለወጡ በወንጌል ኃይል ሊድኑ ይችላሉ

4- ሰዎች ጋብቻ በሚፈጽሙበት ጊዜ ሙሽሮቹን “ጋብቻችሁን የአብረሃምና የሣራ ጋብቻ ይሁን ”  ወይም “ጋብቻችሁ እንደ አብረሃምና እንደ ሣራ የተባረከ ይሁን” እያሉ በተለያየ መልኩ ከአብረሃምና ከሣራ ጋር እያዛመዱ ሲመርቁ ይሰማል ፡፡ ለመሆኑ ለምንድን ነው “ጋብቻችሁ እንደ አብረሃምና እንደ ሣራ ይሁን” የሚባለው ፡፡

5- በከነዓን ምድር ረሀብ እየበረታ በሄደ ጊዜ አብራም ሚስቱን ሣራይን ይዞ ወደ ግብጽ አገር መሄዱን (መሸሹን) ይታወቃል (ዘፍ 12, 10-20) ፡፡ በዚህ ጊዜ አብራም ሣራይ ቆንጆ ሴት ስለነበረች ግብጻውያን ይገድሉኛል በማለት እጅግ በጣም ፈርቶ ነበር ፡፡ ታድያ አብራም ከግብጻውያን ግድያ ለማምለጥ ሚስቱ ሣራይ እንድታደርግ የመከራት ነገር ምን ነበር? የግብጻውያን ንጉሥ (ፈርዖን) አብራምን አስጠርቶ የተናገረው ምን ነበር?


የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት