እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ትምህርት አምስት - ኦሪት ዘጸአት

የመጽሕፍ ቅዱስ ጥናት -  ትምህርት አምስት

የኦሪት ዘጸአት ጥናት

ዘጸአት ማለት ምን ማለት ነው?

            ሙሴ ባህርን እንደከፈላትዘጸአት ሁለተኛው የሙሴ መጽሐፍ ሲሆን “ጸአት” ማለት መውጣት ማለት ነው፡፡ መውጣት ሲባል አንድን ቦታ ለቆ መውጣት ወይም ከባርነት ነፃ መውጣት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለእግዚአብሔር የተለዩት እስራኤላውን ከግብጽ ባርነት ነፃ እንደወጡና ወደ ከነዓን ምድር እንደተጓዙ እናነባለን፡፡ በአጠቃላይ እስራኤላውያን ከግብጽ የባርነት ኑሮ ነፃ መውጣታቸውንና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ጉዞ መጀመራቸውን የሚተርክ መጽሐፍ ስለሆነ “ዘጸአት” ተባለ፡፡ 

መጽሐፉ እንዲህ ይከፈላል ፦

  1. ምዕራፍ 1 እስራኤላውያን በግብጽ ውስጥ የነበሩበት የጭንቀትና የባርነት ኑሮ
  2. ምዕራፍ 2 ስለ ሙሴ መወለድና አስተዳደግ
  3. ከምዕራፍ 3- 12, 36) እግዚአብሔር ለሙሴ መገለጥና እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ መውጣት (የእስራኤላውያን ጉዞ ወደ ሲና ተራራ)
  4. ከምዕራፍ 19- 40, 38 እስራኤላውያን በሲና ተራራ አካባቢ መሆናቸውን ይናገራል፡፡    

ዋናው የኦሪት ዘጸአት ታሪክ የሚጀምረው ከሙሴ ጋር መሆኑን ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ሙሴ ማን ነበር? የት ተወልዶ አደገ? ዋና ሥራውስ ምን ነበር?

            ሙሴ እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ለማድረስ የተጠቀመበት የእስራኤል መሪ የነበረ ነው፡፡ ሙሴ ከሌዊ ነገድ ግብጽ ውስጥ በተወለደ ጊዜ እስራኤላውያን በግብጽ ባርነት ነበሩ፡፡ የፈርዖን ሴት ልጅ “ከውሃ አውጥችሃለሁና” ስትል ሕፃኑን ሙሴ ብላ ሰየመችው (ዘጸ 2, 10) ፡፡ ሙሴ አስቀድሞ በእናቱ እጅ በኋላም እንደ ፈርዖን የልጅ ልጅ ተቆጥሮ ሲያድግ እግዚአብሔርን እየፈራ የግብጽንም ትምህርት እየተማረ “በቃልም በሥራውም የበረታ ሆነ” (ዘጸ 2)፡፡ 

አርባ ዓመትም ሲሞላው በግብጽ ውስጥ በባርነት የነበሩትን እስራኤላውያን ወንድሞቹን ለመርዳት አስቦ ወደ እነርሱ ወጣ፡፡ ነገር ግን አንዱን ግብጻዊ በቁጣ ተነሣሥቶ ከገደለ በኋላ ወደ ምድያም ሸሸ፡፡ ሴቶች ልጆቹንም ስለረዳቸው የምድያምን ካህን በቤቱ ተቀበለው ፤ ከልጆቹም አንዲትዋን ዳረለት፡፡ ሙሴም እስከ አርባ ዓመት ድረስ የአማቱን በጎች በምድረ በዳ ሲጠብቅ ቆየ (ዘጸ 2, 11-25 ፤ ዕብ 11, 24-26 ፤ ሐዋ 7, 23-29)፡፡  እንደ አንዳንድ ሊቃውንቶች አገላለጽ ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን አገባ ይላሉ ፤ አንዳንዶች ይህች የዮቴር ልጅ ሲፓራ ናት ፤ ሌሎች ከግብጽ አገር ከእስራኤል ጋር የመጣች ሌላ ሴት ናት ይላሉ፡፡

የሙሴና የእግዚአብሔር ወዳጅነት እንዴት ተጀመረ? ከእግዚአብሔር የተሰጠውስ ተልእኮ ምን ነበር?

            ሙሴ በጎች በኮሬብ አቅራቢያ ሲጠብቅ ሳለ እግዚአብሔር ተገለጠለት ፤ እስራኤልን ከባርነት እንዲያወጣ ወደ ፈርዖን ላከው ፤ ወንድሙ አሮን እንዲናገርለት ፈቀደ (ዘጸ 3-4)፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር ወዳጅነታቸው ተመሠረተ፡፡ የተሰጠው ተግባር እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ ማውጣት ነበር፡፡ ፈርዖንም ሕዝቡን አልለቅም ባለ ጊዜ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ዐሥር መቅሠፍት በግብጽ ላይ አወረደ (ዘጸ 5-10)፡፡ የግብጽ በኩር ልጆች ሁሉ በሞቱ ጊዜ የፋሲካን ደም በመርጨት ሙሴ ሕዝቡን በደህና ከግብጽ አወጣቸው (ዘጸ 12-13)፡፡ ፈርዖንም ተከተላቸው ፤ እግዚአብሔርም የሙሴን ጸሎት ሰምቶ የኤርትራን ባሕር በመክፈል ሕዝቡን አዳነ (ዘጸ 14, 1-15 ፣ ዕብ 11, 27)፡፡ በማራ ፣ በኤሊም በራፊዲምም በኩል ወደ ሲና ሲጓዝ ሙሴ የሕዝቡን ማንጐራጐር እየታገሠ በጸሎት የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰጣቸው ፤ እጆቹንም ዘርግቶ በሚጸልይበት ጊዜ ጠላቶቻቸው በውሃ ሰጥመው ተሸነፉ (ዘጸ 15, 22-18, 27)፡፡

እግዚአብሔር እንዴትና የት ቦታ ላይ ነው ለሙሴ ሕግን የሰጠውና ሙሴም ሕዝቡን ቃል ኪዳን ያስገባው?

            እስራኤላውያን ለአንድ ዓመት ያህል በሲና ሰፍረው ሳሉ በሙሴ አማካኝነት ሕግን ተቀብለው ቅዱስ ሕዝብ እንዲሆኑለት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገቡ (ዘጸ 19-24) ፡፡ ሙሴ 40 ቀን በሲና ላይ በመቆየቱ ሕዝቡ ዐምፀው ለወርቅ ጥጃ ሰገዱ ፡፡ ሙሴም ተቆጥቶ ጽላቱን መሬት ላይ ጣለው ፤ ጣዖቱን ሰባበረ ፤ ለሕዝቡ ግን ጸለየ ፡፡ እንደገና 40 ቀን በተራራው ላይ ቆየ ፤ እግዚአብሔርም ይቅር በማለት ቃል ኪዳኑን እንደገና አጸናለት (ዘጸ 32-34) ፡፡ ሙሴም የመገናኛውን የድንኳን መቅደስ አሠርቶ ተከለ (ዘጸ 35-40) ፡፡ ስለ መሥዋዕትና ስለ ክህነትም ስለሚያደርጉትም ጉባኤ ሁሉ ትእዛዛትን ተቀበለ ፤ ሕዝቡን ቈጠረ ፤ በየነገዳቸውም በመቅደሱ ዙርያ እንዲሰፍሩ አደረገ ፤ ለጉዞም አዘጋጃቸው (ዘኁ 1, 1-10) ፡፡ እስከ ከነዓን ዳርቻም አደረሳቸው ፤ ከአለማመን የተነሣ አንወጣም ካሉ በኋላ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እስከ 40 ዓመት ድረስ በምድረ በዳ ጠበቃቸው (ዘኁ 13, 1-19) ፡፡

ሙሴ በተቆጣ ጊዜ ግብጻዊውን እንደገደለና (ዘጸ 2) የተቀበለውንም ጽላት መሬት ላይ በመጣል እንደሰባበረው ተገልጿል (ዘጸ 32, 19) ፤ ይህም ቁጣው እጅግ በጣም ነዶ እንደ ነበር ያሳያል ፤ ሙሴ በባሕርዩ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

            ሙሴ በባሕርዩ እጅግ በጣም ትሑት ሰው ነበር ፤ ግብጻዊውን በንዴት የገደለው ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን እጅግ በጣም የከፋ የባርነት ኑሮ ይኖሩ ስለነበርና እርሱም በወገኖቹ የስቃይ ኑሮ ተበሳጭቶ ስለነበር ነው ፡፡ ሙሴ የእስራኤላውያን መቃወምና ማጉረምረም ብዙ ጊዜ የታገሠ ሰው ነው ፡፡ ራሱንም ለእነርሱ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን በጸሎቱ በመግለጽ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ለመነ (ዘጸ 32, 11-14 ፣ ዘኁ 11, 1-15 ፣ 12, 1-16 ፣ 14, 10-19 ፣ 21, 4-9) ፡፡ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚንከራተቱባቸው ዓመታት መጨረሻ ላይ ግን አንድ ጊዜ ሙሴ ተቈጥቶ እግዚአብሔርን አላከበረምና ወደ ከነዓን እንዳይገባ ተከለከለ (ዘኁ 20, 1-13 ፣ መዝ 106, 32-33) ፡፡

ሙሴ በእግዚአብሔር የተመረጠና የተጠራ ትሑትና ታማኝ አገልጋይ ከነበር የአገልግሎቱ ዋና ዋና ተግባራት የትኞቹ ነበሩ?

-    ሙሴ የህዝቡ መሪና ፈራጅ ነበር (ዘጸ 18, 13-26) ፡፡

-    እግዚአብሔር በሲና ሕግን ሰጥቶ ከእስራኤል ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ሙሴ መካከለኛ ነበር (ዘጸ 19, 7 ፣ ገላ 3, 19)፡፡

-    እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳን መቅደስ አሠራ (ዘጸ 25-31 እና ከ35-40)፡፡

-    በእጁም አሮንና ልጆቹን ለክህነት የለየ ለሕዝቡም የጸለየ ካህን ነበር (መዝ 99, 6 ፣ ዘሌ 8 እና 9 ዘጸ 32, 30-32)፡፡

-    እግዚአብሔር “አፍ ለአፍ በግልጥ” ያናገረው እግዚአብሔርንም “ፊት ለፊት” ያወቀ ነቢይ ነበር (ዘኁ 12, 6-8 ፣ ዘዳ 34, 10-12)፡፡

-    አብዛኛዎቹ በእጅ ስለ ተጻፉ አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት “የሙሴ” ተብለው ይጠራሉ (ሉቃ 24, 27)፡፡

በምን መልኩ ነው ሙሴ የክርስቶስ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ሙሴ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ከተገለጸባቸው ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ፦

 ነቢይ በመሆኑ (ዘዳ 18, 15-19 ፣ ሐዋ 3, 22) ፣ በታማኝነቱ (ዕብ 3, 1-6) ፣ የማደርያውን ድንኳን በመትከሉና በማገልገሉ (ዕብ 8-9) እንዲሁም በደረሰበት ተቃውሞ (ሐዋ 7, 35-40) ተደጋግሞ ተጠቅሷል ፡፡ በኮሬብ በተገለጠው ክብር ፊቱ የበራ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ በደብረ ታቦር የክርስቶስን የክብር መገለጥ አየ ፡፡ ሙሴ አስቀድሞ በትንቢትና በምሳሌ ስለ ክርስቶስና ስለ ሞቱ ጻፈ (ዮሐ 5, 46 ፣ 3, 15) ፤ ስለ ትንቢቱም መፈጸም በታቦር ከክርስቶስ ጋር እንዲነጋገር ዕድል አገኘ (ሉቃ 9, 30-31 ዘጸ 34, 29-35 ፣ 2 ቆሮ 3, 7-18) ፡፡

ሙሴ ታቦት የተባለውን ቅዱስ ነገር እንደሠራ ይታወቃል ፤ ለመሆኑ የዚህ ታቦት አሠራሩ እንዴትና ከምን ነበር? ዋና አገልግሎቱስ ምን ነበር?

      ሙሴ በእርግጥ ከግራር እንጨት ታቦትን እንዲሠራ ታዘዘ ፡፡ አሠራሩም ሣጥን ዓይነት ነበረ ፡፡ ርዝመቱ 125 ፣ ወርዱ 75 ፣ ቁመቱ 75 ሳንቲ ሜትር ያህል ነበረ ፡፡ ታቦቱ በወርቅ የተለበጠ መክደኛውም ከወርቅ የተሠራ ነበር ፤ በላዩም ሁለት ኪሩቤል ተቀርጸዋል ፡፡ የታቦቱ አገልግሎት የነበረው ፦

  1. ዐሠርቱ ቃላት የተጻፉባቸው የሁለቱ ጽላት ማኖርያ
  2. ከእስራኤል መሪዎች ጋር የእግዚአብሔር መገናኛ ነበር ፡፡ ስለዚህ ታቦቱ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የመኖሩ ምልክት ነበር (ዘጸ 25, 1-22 ፤ 40, 20) ፡፡

ሙሴ ታቦቱን አሠርቶ ሲያበቃ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አኖረው ፡፡ የእስራኤልም ሕዝብ ይዘውት ይጓዙ ነበር ፡፡ በተለይም ዮርዳኖስን ሲሻገሩና ኢያሪኮን ሲዞሩ ካህናት ተሸክመውት ፊት ፊት ይሄዱ ነበር (ኢያ 3, 16)፤ የእስራኤል ሕዝብ ከኃጢአታቸው ሳይመለሱ በጦርነት እንደ መከላከያ መሣርያ ሲሸከሙት ታቦቱ በመሳፍንት ዘመን በፍልስጤማውያን ተማረከ ፡፡ ታቦቱ በእግዚአብሔር ስም የተጠራ ስለነበር እግዚአብሔር በፍልስጤማውያን ላይ ብዙ ተአምር አደረገ ፤ ፍልስጤማውያንም መለሱት (1 ሳሙ 4-6) ፡፡ በኋላም ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው ፡፡ ሲያመጣውም ዖዛ የተባለው ሰው በድፍረት ስለነካው ተቀሠፈ (2ሳሙ 6) ፤ ሰሎሞንም ራሱ በሠራው ቤተ መቅደስ አኖረው (1ነገ 8) ፡፡ ታቦቱ በኢዮስያስ ዘመን በቤተ መቅደስ ነበረ (2 ዜና መ. 35, 3)፡፡ በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ወደፊት የእስራኤል ሕዝብ ስለ ታቦቱ ምንም እንደማያስብ ትንቢት ተናገረ (ኤር 3, 16)፡፡

ነቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ሲያፈርስ ታቦቱ የጠፋ ይመስላል ፡፡ ምክንያቱም ዘሩባቤል በሠራው ቤተ መቅደስ ታቦት አልነበረምና ፡፡ በአዲስ ኪዳን የቃል ኪዳኑ ታቦት በእግዚአብሔር ሰማያዊ መቅደስ እንደታየ ተጠቅሷል (ራእ 11, 19)፡፡

ሙሴ ከሲና ተራራና ከኮሬብ ጋር በተያያዘ መልኩ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል ፤ ሙሴና ሲና ተራራ ግኑኝነታቸው ምንድን ነው? 

      ሲና ብዙ ጊዜ ተራራ እንደሆነ ሲጠቀስ ይደመጣል ፤ ነገር ግን ሲና ተራራ ሳይሆን ብዙ ተራሮች በውስጡ የያዘ ወይም ያካተተ ከግብጽ አገር በስተምሥራቅና ከእስራኤል በስተደቡብ የሚገኝ አገር ነው ፡፡ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት 40 ዓመት እንደ ተጓዙ ይታወቃል (ዘጸ 19, 1) ፡፡ ሌላው ደብረ ሲና የሚባለው ሲና ውስጥ ከሚገኙት ተራሮች አንዱ ሲሆን ዐሠርቱ ቃላት የተሰጡበት ተራራ ነው (ዘጸ 19, 20) ፡፡ ይህ ደብረ ሲና ኮሬብም ተብሎ ይጠራል (ዘጸ 3, 1 ፣ ዘዳ 4, 9-10) ፡፡ ሙሴም ዐሠርቱ ቃላት በዚህ ተራራ ላይ ሆኖ ስለተቀበለ ስሙ በተደጋጋሚ ከዚህ ተራራ ጋር በተያያዘ መልኩ ይጠራል ፡፡

ሙሴ ከሕግ ጋር በተያያዘ መልኩ ለምን ይጠቀሳል?

      በመሠረቱ ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ በደብረ ሲና የተቀበላቸው ዐሠርቱ ቃላት ሕግ ስለነበሩ ከዚያ ጋር በተያያዘ መልኩ ሲጠቀስ ይታያል (ዘዳ 4, 13) ፡፡ ትእዛዛቱ በቃል ኪዳን መልክ ተሰጡ (ዘጸ 20, 1-17) ፡፡ ሕግ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍትን (ማቴ 5, 17 ፣ ሉቃ 16, 16) እና ብሉይ ኪዳን በሙሉ (ዮሐ 10, 34 ፣ 12, 34) ሊያመለክት ይችላል ፡፡ ለዚህ ነው ሙሴ ከሕግ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚጠቀሰው ፡፡

ዐሠርቱ ትእዛዛት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? ለምንስ ተሰጡ?

            ዐሠርቱ ትእዛዛት የሚባሉት እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት በደብረ ሲና ለእስራኤል የሰጣቸው የኪዳን ትእዛዛት ናቸው (ዘጸ 19, 5 - 20, 17) ፡፡ ትእዛዛቱ በሁለት ጽላት በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉ ናቸው (ዘጸ 31, 18) ፡፡ ጽላቱም በታቦቱ ውስጥ ተቀመጡ (1ነገ 8, 9)፡፡ ከዓርባ ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ሊገቡ ሲደርሱ ሙሴ ትእዛዛቱን በድጋሚ አስታወሳቸው ፡፡ ሆኖም የእስራኤል ሕዝብ ሁኔታ አዲስ ስለሆነ ሰንበትን የማክበር ምክንያት ተለወጠ ፤ የባልንጀራንም እርሻ ደግሞ እንዳይመኙ ታዘዙ (ዘዳ 5, 6-21) ፡፡ በዘጸ 20, 2 መሠረት ዐሠርቱ ትእዛዛት የተሰጡት ደኅንነትን ተቀብሎ በቃል ኪዳን ውስጥ ለሚገኘው የእስራኤል ሕዝብ ነው ፡፡ የተሰጡበትም ምክንያት ደኅንነት ባለው ሕይወት እግዚአብሔርን እንዴት መከተል እንዳለባቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለቃል ኪዳኑ ሕዝብ ለማስረዳት ነው ፡፡

ዐሠርቱ ትእዛዛት በመባል ለምን ተጠሩ? ትእዛዛቱስ የትኞቹ ናቸው?

ትእዛዛቱ ዐሥር በመሆናቸው ነው ዐሠርቱ ትእዛዛት በመባል ሊጠሩ የቻሉት ፡፡ ትእዛዛቱም የሚከተሉት ናቸው

  1. ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ ፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም ከምድር በታች ባለው ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች የማንኛውንም ምስል ጣዖት አድርገህ አታምልክ ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እጅግ ቀናተኛ ስለሆንሁ ተቀርጾ የተሠራውን ማንኛውንም ጣዖት አታምልክ ፤ አትስገድለትም ፤ እኔ የሚጠሉኝን ሁሉ እቀጣለሁ ፤ ዘራቸውንም እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ እበቀላለሁ ፡፡ ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺ ትውልድ ድረስ ዘላለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ ፡፡
  2. የእኔ የአምላክህ ስም በከንቱ አትጥራ ፤ ምክንያቱም እኔ ስሜን በከንቱ የሚጠራውን ሁሉ እቀጣዋለሁ ፡፡
  3. እኔ እግዚአብሔር ባዘዝሁህ መሠረት ሰንበትን አክብር ፤ ቀድሰውም ፡፡ ሥራን ሁሉ የምታከናውንባቸው ስድስት ቀኖች አሉልህ ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ ለአምላክህ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው ፤ በዚያን ቀን ምንም ዐይነት ሥራ አትሥራ ፤ አንተም ሆንህ ልጆችህ አገልጋዮችህም ሆኑ እንስሳትህ በአገር ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችም ቢሆኑ ምንም ሥራ አትሥሩበት ፤ አገልጋዮችህም ልክ እንደ አንተው ዕረፍት ያድርጉ ፡፡
  4. እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ባዘዝሁህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር ፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንልሃል ፤ እኔ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል ፡፡
  5. አትግደል
  6. አታመንዝር
  7. አትስረቅ
  8. በማንም ሰው ላይ በሐሰት አትመስክር
  9. የሌላውን ሰው ሚስቱን አትመኝ ፤
  10. የሌላውን ሰው ቤቱን ፣ ርስቱን ፣ አገልጋዮቹን ፣ ከብቱን ፣ አህዮቹንም ሆነ ማናቸውንም ንብረቱን ሁሉ አትመኝ

ሰንበትን አክብር ፤ ቀድሰውም ሲል የትኛውን ቀን ያመለክታል? ለምንስ መከበር ያስፈልገዋል? አለማክበርስ ምን ሊያስከትል ይችላል?

            ሰንበት በዕብራይስጥ “ማቆም” “መተው” ማለት ነው ፡፡ እስራኤላውያን ሰባተኛውን ቀን ለእግዚአብሔር እንዲቀድሱት ከላይ በተዘረዘሩት ዐሠርቱ ትእዛዛት ተነግረዋል (ዘጸ 20, 8-11) ፡፡ ከዚህም በላይ ሰንበት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል የቃል ኪዳን ምልክት ነው (ዘጸ 31, 17) ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰንበትን አለማክበር ከባድ ቅጣትን ያስከትል ነበር (ዘኁ 15, 32-36) ፡፡  

ሰንበት የእግዚአብሔር ሥራ እንዲታወስ ያደርጋል ፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ስድስት ቀን ሠርቶ እንዳረፈ ሁሉ ሰውም በዚህ ዓለም ሠርቶ ወደ ዘለዓለም ዕረፍት አገራቸው ሲደርሱ ዐሠርቱ ቃላት በድጋሚ ተነገራቸው ፡፡ ከዚህም ላይ ሰንበት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ባርነት እንዳወጣቸው ያመለክታል (ዘዳ 5, 12-16) ፡፡ እስራኤል ቀኑን በሚገባ ባለማክበራቸው በነቢያት ተወቅሰዋል (ሕዝ 20, 12-16 ፣ አሞ 8, 6) ፤ እንዲያከብሩትም ተስፋ ተሰጥቷቸዋል (ኢሳ 56, 2-4 ፣ 58, 13-14) ፡፡ ነህምያ ሰንበትን አስከብሯል (ነሀ 10, 31 ፣ 13, 15-22) ፡፡ ኢየሱስ ሰንበትን አክብሯል (ሉቃ 4, 16 ) ፤ የፈሪሳውያንን የሰንበት አከባበር ግን ተቃውሟል ፡፡ እነርሱ ቀኑ እንዲከብር ብቻ እሸት ከመቅጠፍ ፣ ድውይ ከመፈወስ እስኪከለክሉ ድረስ ብዙ ሕግና ወግ ደንግገው ነበር ፡፡ ክርስቶስ ግን ከሰው ወግና ሥርዓት ምህረት እንደሚበልጥ አስተማረ (ማቴ 12, 1-14)፡፡

በአዲስ ኪዳን ዘመንስ እነዚህ ትእዛዛት ተሽረዋልን?

            በአዲስ ኪዳን ዘመንም እነዚህ ትእዛዛት አልተሻሩም ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርንና የሕዝቡን ግኑኝነት በማናቸውም ዘመን በቋሚነት ያስረዳሉ ፡፡ በእነዚህ ትእዛዛት ውስጥ የሚታየው የእግዚአብሐየር መሠረታዊ ፈቃድ “ታላቂቱና ፊተኛይቱ…ሁለተኛይቱም” በተባሉት ትእዛዛት ተጠቃልሎ ይገኛል (ማቴ 22, 36-40 ፣ ሮሜ 13, 8-10) ፡፡ እነዚህም ፦ ከሁሉም የሚበልጠውና የመጀመርያው ትዕዛዝ የተባለው “እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ ፣ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም አሳብህ ውደድ” ሲሆን ይህንን የሚመስለው ሁለተኛው ትእዛዝ “ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለው ነው ፡፡

ስለዚህ ትእዛዛቱ በቃልም ሆነ በመንፈስ በአዲሰ ኪዳን ይገኛሉ ፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደታየው ሁሉ በአዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት መጠበቅ አለብን (ዮሐ 15, 14) ፡፡ አዲስ ኪዳን እነዚህን ትእዛዛት ሕይወታችንን ለመምራት የሚያገለግሉ ናቸው (ገላ 4, 4-5) ፡፡

እነዚህ ትእዛዛት መጠበቅ (አክብሮ መኖር) ምን ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል?

            እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ሁሌም በሕይወቱ ትዝዛዛቱን ጠብቆ ይኖራል ፡፡ ትእዛዛቱም መጠበቅ ብዙ በረከቶችን እንደሚያስገኝ ቃለ እግዚአብሔር ይነግረናል (ዘዳ 7, 12-26) ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ትእዛዛቱን ጠብቀው የሚኖሩትን እግዚአብሔር ይወዳቸዋል ፤ ይባርካቸዋልም (ዘዳ 7, 13) ፡፡ የእግዚአብሔር ትእዛዛት እያከበረ የሚኖር ሕዝብ ብዙ ልጆች ይወልዳል ፤ በቁጥርም እየበዛ ይሄዳል ፤ እርሻውም ይባረካል ፤ ስለዚህ ብዙ እህል ፣ ወይንና የወይራ ዘይት ያገኛል ፤ ከዚህም ጋር ብዙ የከብትና የበግ መንጋ በማግኘት ይባረካል ፤ በከብቶቹም ሆነ በወንድና በሴቶች ልጆቹም መካከል መኻን አይገኝም (ዘዳ 7, 13-14)፡፡

 

ምስጋናችንና ጸሎታችን ለትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

ለመሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

ለጸሐፊት ፦ ለምለም ክፍሌ

  ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

  1. ሙሴ እስራኤላዊ ወይም ከዕብራውያን ወገን ሆኖ እያለ በግብጻውያን ንጉሥ በፈርዖን ቤት ሊገኝና ሊያድግ እንደቻለ ከዘጸ 2 እንረዳለን ፡፡ ከሚከተሉት ውስጥ የትኛውን ነው ሙሴ በፈርዖን ቤት የመገኘቱና የማደጉ ምክንያቶች ውስጥ የማይካተተው? ሀ) “ከዕብራውያን አዲስ የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ እያነሣችሁ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉ ፤ ሴቶች ልጆች ግን በሕይወት ይኑሩ” የሚለው የንጉሡ ትእዛዝ ለ) ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑንና እናቱ እንዳይገደልባት በቅርጫት አድረጋ ወንዝ ዳር ማኖርዋን ሐ) የፈርዖን ሴት ልጅ ሕፃን ማሳደግ ትፈልግ ስለነበር ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ አምጡልኝ ብላ ማዘዝዋን መ) የሕፃኑ የሙሴ እኅት ወደ ፈርዖን ልጅ ወደ ልዕልቲቱ ሄዳ “ይህን ሕፃን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች አንዲት ሞግዚት ልጥራልሽን?” ብላ መጠየቋን ሠ) መልሱ የለም ፡፡ አስተውል ፦ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 1 እና 2 ቀድመው በደንብ ያንብቡ ፡፡
  2. ሙሴ መንጋውን በኮሬብ ተራራ ሲጠብቅ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ በቁጥቋጦ ውስጥ በተቀጣጠለ የእሳት ነበልባል መካከል ሆኖ እንደተገለጠለት ይታወቃል ፤ ከሚከተሉት ውስጥ የትኛውን ነው በዚያን ጊዜ ከተከናወኑት ነገሮች ውስጥ የማይካተተው ወይም ሐሰት የሆነው? ሀ) “የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” ተብሎ መታዘዙን ለ) ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየቱን ሐ) እግዚአብሔር ስሜ “ያለሁና የምኖር ነኝ” ስሜም ለዘላለም ይኸው ነው ፤ ወደፊት የሚነሣው ትውልድ ሁሉ የሚያውቀኝ በዚሁ ስም ነው ማለቱን መ) ሙሴ የእግዚአብሔርን ጥሪ “የመናገር ችሎታ የለኝም ፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ” ማለቱን ሠ) እግዚአብሐየር ሙሴን “ሌዋዊ የሆነው ወንድምህ አሮን አለ ፤ እርሱ ጥሩ ተናጋሪ ነውና ይረዳሃል ማለቱን፡፡ አስተውል ፦ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ዘጸ 4-5 በትኩረት ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልጋል ፡፡
  3. ሰንበት በዕብራይስጥ ቋንቋ “ማቆም” “መተው” ማለት እንደሆነ ከላይ ተገልጿል ፡፡  ከሚከተሉት ውስጥ የትኛውን ነው ሰንበትን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነው? ሀ) ሰንበት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል የቃል ኪዳን ምልክት ነው ለ) እንደ ብሉይ ኪዳን አገላለጽ ሰንበትን አለማክበር ከባድ ቅጣትን ያስከትላል ሐ) ኢየሱስ ሰንበትን አክብሯል ፤ የፈሪሳውያንን የሰንበት አከባበር ግን ተቃውሟል መ) ዛሬም ቢሆን ሰንበትን በሚገባ አለማክበር እንደ ኃጢአት ይቆጠራል ፤ ሰንበትን ያላከበረ ንስሓ መግባት ይኖርበታል ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው     

4. በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ሙሴ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ከተገለጸባቸው ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ግለጽ ፡፡

5. ዐሠርቱ ትእዛዛት የሚባሉት እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት በደብረ ሲና ለእስራኤል የሰጣቸው የኪዳን ትእዛዛት መሆናቸው ይታወቃል (ዘጸ 19, 5 - 20, 17) ፡፡ እነዚህ ዐሠርቱ ትእዛዛት በሁለት ይከፋላሉ ፤ የሚከፈሉትም የተወሰኑት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ሁኔታ ስለሚመለከቱና ቀሪዎቹ ደግሞ ሰውን ወይም ሰው ከሰው ጋር የሚኖርበት ሁኔታ (ማኅበራዊ ግኑኝነትን) የሚመለከቱ ናቸው ፡፡ ከእነዚህ ዐሠርቱ ትእዛዛት የትኞቹ ናቸው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን (እግዚአብሔርን የሚመለከት) እና ሰው ከሰው ጋር ያለውን ግኑኝነት (ሰውን የሚመለከት)? ዐሠርቱ ትእዛዛት በሁለት መከፈላቸውን ከፋፍለው ያሳዩ ፡፡

6. የፋሲካ በዓል እንዴት ተጀመረና እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካን በዓል መቼና እንዴት እንዳከበሩት ከላይ ከተገለጸው ከዚህ ጥናትና ከኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 12 እንረዳለን ፡፡ ከላይ የተገለጸውን ጥናትና ዘጸ 12 በደንብ ካነበቡ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ ፡፡

 -    ፋሲካ ሲጀመር የተከበረው በዓመቱ የመጀመሪያው ወር ነው ፤ በወሩ በስንተኛው ቀን ነበር የተከበረው?

 

-    በዚህ ዕለት ሰው በቤተሰቡ ደረጃ ምን እንዲመርጥ ታዘዘ?

 

-    ከታረደው በግ ደም ወስደው ምን እንዲያደርጉ ታዘዙ? የዚህ ድርጊት ምልክትነቱስ ምንድን ነበር?

 

-  ይህ ድርጊት ዛሬም በተለይም በአካባቢያችን የመስቀል በዓል በሚከበርበት ጊዜ በሬው ከታረደ በኋላ ሰዎች ጐጆ ቤታቸው በር ላይ ሲያከናውኑት ይታያል ፤ ታዲያ ይህ ድርጊት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ብለው ያምናሉን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይገናኝ ክንውን ከሆነ በአካባቢያችን ይህ ድርጊት ለምን እንደሚተገበር ጠይቀው ምላሹን ይስጡ፡፡ 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት