እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፮ - የኦሪት ዘጸአት ጥናት - 2

ት/ርት ፮ - የኦሪት ዘጸአት ጥናት - 2

Mosesከሙሴ ዘመን በፊት ከአብረሃም ጊዜ ጀምሮ ዐሥራት መክፈል የተለመደ ተግባር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ፤ ለመሆኑ ዐሥራት ማለት ምን ማለት ነው? አጀማመሩስ እንዴት ነው?

            ዐሥራት ማለት አንድ ዐሥረኛ ማለት ነው ፡፡ ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ ከማንኛውም ገቢ ዐሥረኛው እጅ ለሃይማኖት መሪዎች ወይም ለመንግሥት ይሰጥ ነበር ፡፡ ነገር ግን እንዴት እንደተጀመረ አይታወቅም ፡፡ ከሙሴ ዘመን በፊትና እንዲሁም ከባቢሎን እስከ ሮም ድረስ ይሠራበት ነበር ፡፡ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ ዐሥራትን ሰጠው (ዘፍ 14, 20) ፡፡ ያዕቆብም ለእግዚአብሔር ዐሥራት ለመክፈል ተሳለ (ዘፍ 28, 22) ፡፡ ሌዋውያን ካህናት እንዲጠቀሙበት (ዘኁ 18, 21-32) ፣ ምድር ከምታፈራውና ከከብትም ወገን ዐሥራት እንዲሰጥ ታዘዘ (ዘሌ 27, 30-33) ፡፡ የሚከፈልበት ጊዜ ተወሰነ (ዘዳ 12, 5-18 ፤ 14, 22-29) ፡፡ ዐሥራትም ሲከፍሉ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይባርካል (ዘዳ 26, 13-15 ፣ ሚል 3, 10) ፡፡ ፈሪሳውያን ከቅመማ ቅመም ሳይቀር ዐሥራት ይከፍሉ ነበር (ማቴ 23, 23) ፡፡ ሐዋርያት ስለ ዐሥራት አልጻፉም ፤ ሆኖም እንደ እግዚአብሔር በረከት መጠን በልግስና በውዴታ ዐሥራት መስጠት ይገባል (1ቆሮ 16, 1-4 ፣ 2 ቆሮ 9, 6-12) ፡፡

► እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት ከወጡበት ጊዜ ጀመሮ ፋሲካ የሚለው በዓል መከበር እንደተጀመረ ይነገራል ፤ ለመሆኑ ፋሲካ ማለት ምን ማለት ነው? አጀማመሩስ እንዴት ነው?

            ፋሲካ በዕብራይስጥ “ፓሳሕ” ማለት ሲሆን ትርጓሜውም “አለፈ” “ተሻገረ” ማለት ነው ፡፡ የእስራኤል ልጆች በግብጽ አገር በግ አርደው ደሙን በደጃፋቸው በመርጨት ከእግዚአብሔር ቁጣ ዳኑ ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በዚያች ሌሊት ግብጻውያንን ሲቀሥፍ ደም በነበረበት ቤት አልፎ ስላልገደለ ወይም ደም የተረጨበትን ቤት ስላለፈ ቀኑ ፋሲካ ተባለ ፡፡ ለፋሲካ የሚታረደውም በግ ፋሲካ ይባላል (ዘጸ 12, 1-13) ፡፡ በየዓመቱ በግ እያረዱ የእስራኤል ልጆች በመጀመርያ ወራቸው በ14ኛው ቀን የፋሲካን በዓል ያከብራሉ ፡፡ ከዚያም ምሽት እስከ አንድ ሳምንት ድረስ የቦካውን ነገር ለመብላት ስላልተፈቀደላቸው የሙሉ ሳምንት በዓል “የቂጣ በዓል” ተባለ ፡፡ የቂጣ እንጀራ መብላት የእስራኤል ልጆች በችኰላ ከግብጽ መውጣታቸውን የሚያስታውስ የመታሰቢያ ምልክት ነው (ዘጸ 12, 18-20 ፣ ዘዳ 16, 1-3) ፡፡

 እግዚአብሔርም እንዲህ በማለት ትእዛዝ ሰጣቸው ፦

            “ለጉዞ እንደተዘጋጀ ሰው ሆናችሁ ልብሳችሁን በአጭር በመታጠቅ ጫማችሁን አድርጋችሁ ፣ በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ በችኮላ (የበግ ወይም የፍየል ጥቦት) ብሉት ፤ እርሱም እኔን እግዚአብሔርን የምታከብሩበት የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ” (ዘጸ 11, 11) ፡፡

► የመጀመሪያው ፋሲካ እንዴትና የት ተከበረ (ተደረገ)?

የመጀመሪያው ፋሲካ እዛው ግብጽ ውስጥ በችኮላ እንደተከበረ ከዘጸ 12, 1-20 እንረዳለን ነገር ግን ትክክለኛው ፋሲካ ወይም “ማለፍ” ወይ “መሻገረ” የሚለውን ትርጉም በሚያሳይ መልኩ የተከበረው ግን የግብጽን የባርነት ኑሮ አልፈው ከወጡ በኋላ እንደሆነ ከዘጸ 12, 43- 51 ላይ እንረዳለን ፡፡ በዘጸ 12, 21 በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደተከበረ እንረዳለን ፦

            ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ አለቆች ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “ቤተሰባችሁ ሁሉ የፋሲካን በዓል እንዲያከብር ከእናንተ እያንዳንዱ የበግ ወይም የፍየል ጥቦት መርጦ ይረድ ፤ ጭብጥ የሚሞላ የሂሶጵ ቅጠል ውሰዱ ፤ በሳሕን ያለውንም ደም በቅጠሉ እየነከራችሁ የቤታችሁን በር መቃኖችና በላይ በኩል ያለውን ጉበን ቀቡ ፤ እስከ ማግሥቱ ጠዋት ድረስ ማንም ሰው ከቤቱ አይውጣ ፡፡ እግዚአብሔር ግብጻውያንን በሞት ለመቅጣት በግብጽ ምድር ያልፋል ፤ በጉበንና በመቃኖች ላይ ያለውንም ደም በሚያይበት ጊዜ አልፎ ይሄዳል ፤ የሞት መልአክም ወደየቤታችሁ ገብቶ እናንተን እንዳይገድል ያደርጋል ፤ እናንተንና ልጆቻችሁ ይህን ሥርዓት ለዘላለም ትጠብቁታላችሁ ፤ እግዚአብሔር ሊያወርሳችሁ ተስፋ ወደ ሰጣችሁ ምድር ስትገቡም ይህን ሥርዓት ትፈጽማላችሁ” (ዘጸ 11, 21-25) ፡፡  

ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ሳምንት የፋሲካ ሳምንት ነበረ (ሉቃ 22, 14-16 ፣ ዮሐ 18, 38-40) ፡፡ እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን “ፋሲካችን ክርስቶስ” ተባለ (1ቆሮ 5, 7 ፣ 1ጴጥ 1, 18-19) ፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ በዓል ፋሲካ ተብሎ ይጠራል ፡፡

► የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን እስራኤላውያንን አለቅም በማለት እልከኛ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር መቅሠፍት እንዳመጣባቸው ተደጋግሞ ተገልጿል ፤ ለመሆኑ መቅሠፍት ማለት ምን ማለት ነው ? የመቅሠፍት ዋና ምክንያትስ ምንድን ነው?

           መቅሠፍት ማለት እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት በሰው ላይ የሚያመጣው ችግርና በሽታ ነው (ዘፍ 12, 17 ፣ ዘኁ 16, 46 1ነገ 8, 37-40 ፣ ራዕ 9, 20) ፡፡ ከብሉይ ኪዳን እንደምንረዳው ከሆነ የመቅሠፍት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚባሉት አለመታዘዝ ፣ እልከኛነት ፣ ዐመፅ ፣ ትእዛዛትን መተላለፍ ፣ ጣዖትን ማምለክ ፣ በሥጋ ፈቃድ መኖር በአጠቃላይ እግዚአብሔርና ትእዛዛቱን ረስቶ መኖር ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይባርካል እንጂ በመቅሠፍት የሚደሰት አምላክ አይደለም ነገር ግን ሕዝቡ ከእልከኝነታቸው እንዲመለሱ ፣ ንስሓ እንዲገቡና ትእዛዛቱን ጠብቀው በበረከት እንዲኖሩ ያስተምራቸዋል ፡፡ ለምሳሌ ግብጻውያን እልከኞች በመሆናቸው ፡ እግዚአብሔር በዐሥር መቅሠፍቶች መታቸው ፡፡ እነርሱም የውሃ ወደ ደም መለወጥ ፣ ጓጕንቸር ፣ ቅማል ፣ የዝንብ መንጋዎች ፣ ቸነፈር ፣ ሻህኝ የሚመጣ ቁስል ፣ ነጐድጓድና በረዶ ፣ አንበጣዎች ፣ ጨለማና የበኩር ልጅ ሞት ናቸው (ዘጸ 7-12) ፡፡

► ከእስራኤላውያን የግብጽ የባርነት ኑሮ አልፎ ወደ ተስፋይቱ ምድር ካረጉት ጉዞ (ከምድረ በዳው ጉዞ ጋር) በተያያዘ መልኩ “መና” ስለተባለው ምግብ ይነገራል ፡፡ ለመሆኑ መና ማለት ምን ማለት ነው? ከሰማይ የወረደ ነው ሲባል ምን ያመለክታል?

            በዕብራይስጥ ቋንቋ መና ማለት “ይህ ምንድን ነው?” ማለት ነው (ዘጸ 16, 15) ፡፡ እስራኤላውያን በተራቡ ጊዜ በምሽት ብዙ ድርጭቶች አየበረሩ መጥተው ሰፈሩን ሸፈኑት ፤ በማለዳ ደግሞ በሰፈሩ ዙርያ ጤዛ ነበር ፤ ጤዛውም ከተነነ በኋላ ደቃቃና ስስ የሆነ ነገር በበረሓማው ምድር ላይ ታየ ፤ እርሱም በምድር ላይ ያረፈ ዐመዳይ ይመስል ነበር ፡፡ እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ (ዘጸ 16, 13-16) ፡፡ ከዚህ በመነሣት ነው “መና” የሚለው ስም የተገኘው ፡፡ ስለዚህ መና ማለት “ይህ ነገር ምንድን ነው” ማለት ነው ፡፡

ስለዚህ መና ጠዋት ጠዋት ጠል ካለፍ በኋላ እንደ ደቃቅ ውርጭ ያለ በምድር ላይ ይታይ ነበር ፤ የእስራኤል ሕዝብም ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ተመገቡት (ዘጸ 16, 35) ፡፡ እስራኤላውያን ጠዋት ጠዋት ያንን እየለቀሙ ይመገቡ ነበር ፡፡ ለማሳደር በሞከሩ ጊዜ ገማ ፤ በስድስተኛው ቀን ግን የተረፈው መና አልገማምና ለሰባተኛው ቀን ምግብ ሆነ ፡፡ ለተተኪ ትውልድ ምስክር እንዲሆን አሮን ከመናው በጎሞር ውስጥ ከትቶ በቅድስተ ቅዱሳን አኖረው (ዘጸ 16, 13-36 ዕብ 9, 4) ፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ እስራኤል በኢያሪኮ ምሥራቅ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ ሌላ ምግብ ስላገኙ መናው ቀረ (ኢያ 50, 10-12) ፡፡ እግዚአብሔር መናን ሲሰጥ እንዴት ወይም ምን እንደሆነ አይታወቅም ፡፡ እግዚአብሔር መናን በመስጠቱ ሰው በዚህ ብቻ እንደማይኖር በእግዚአብሔር ቃልም እንደሚኖር (ዘዳ 8, 3-16) ፤ ሰባተኛው ቀን እንዲያከብር አስተማረ (ዘጸ 16, 19-30 ዘጸ 20, 8-10) ፡፡ ክርስቶስ የእስራኤል መና ከጠቀሰ በኋላ የሥጋው ሕይወትነት ከዚያ ይልቅ እጅግ የበለጠ መሆኑን አሳየ (ዮሐ 6, 26-71) ፡፡

► ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ማውጣት ጋር በተያያዘ መልኩ የአሮን ስም ሲጠራ ይሰማል ፤ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ በመውጣት ሂዳት ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ይታወቃል ፤ ለመሆኑ አሮን ማን ነው? 

            አሮን የሙሴና የማርያም ወንድም ነው (ዘኁ 26, 59 ፣ ዘጸ 6, 20) ፡፡ ስሙ ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሰው እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ በገለጠበት ጊዜ ነው ፤ በዚያን ጊዜ ሙሴ የእስራኤል መሪ እንዲሆን ተመርጦ ነበር ፤ ነገር ግን ሙሴ “አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ” በማለት ለመታዘዝ አለመውደዱን በገለጠ ጊዜ እግዚአብሔር “ወንድምህ አሮን አፍ ይሆንልሃል” ብሎ መለሰለት (ዘጸ 4, 14-16) ፡፡

የይሁዳ ነገድ አለቃ እኅት የሆነችውን ኤልሳቤጥ የተባለችውን ሴት አግብቶ ከእርስዋ ናዳብ ፣ አብዩድ ፣ አልዓዛርና ኢታምር የተባሉ አራት ልጆችን ወለደ (ዘጸ 6, 23) ፡፡ ሙሴ ወደ ፈርዖን በቀረበ ቁጥር ከዚያም በኋላ የአርባው ዓመት የምድረ በዳ ጉዞ እስኪያልፍ ድረስ ሙሴ በሚሰራው ሥራ ሁሉ አሮን የቅርብ ረዳቱ ነበረ ፡፡  የእስራኤል ልጆች ከአማሌቅ ጋር በተዋጉ ጊዜ አሮንና ሖር የሙሴን እጆች ይደግፉ ነበር (ዘጸ 17, 9-12) ፡፡ ሆኖም የእስራኤል ልጆች ይሰግዱለት ዘንድ የወርቅ ጥጃን በመሥራቱ እግዚአብሔርን ሳያስቈጣው አልቀረም (ዘጸ 32) ፡፡ አሮን ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር የተመረጠ ለመሆኑ በበትሩ ማቈጥቈጥ ታወቀለት (ዘኁ 17) ፡፡ ቢሆንም መሪባ በተባለው ስፍራ ከሙሴ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለማክበሩ ኃጢአት ሠራ (ዘኁ 20, 12) ፡፡ 

► አሮን ከክህነት ሕይወት ጋር ለምን ተያይዞ ይጠቀሳል? ክህነት ማለት ምን ማለት ነው? ከብሉይ ኪዳን አኳያ ሲታይ አመሠራረቱስ እንዴት ነው? 

በእርግጥ አሮን ሊቀ ካህናት እንዲሆን በመመረጡ ከሌዊ ወገን ካህናት የመጀመሪያው ሆነ (ዘጸ 28, 1) ፡፡ ልጆቹም ካህናት እንዲሆኑ ተቀደሱ (ዘሌ 8, 12- 13, 30) ፡፡ በ123 ዓመቱ ሲሞት ሊቀ ካህናትነቱ ለልጁ ለአልዓዛር ተሰጠ (ዘኁ 20, 22-29 ፣ 33, 38 ፣ ዘዳ 10, 6) ፡፡ ከዚህም በላይ በአዲስ ኪዳን አሮን የክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ ተቈጥሯል (ዕብ 5, 4-5) ፡፡

ክህነት (ካህን) በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ነው ፡፡ ካህን ማለት አገልጋይ እንደማለት ነው ፡፡ ከብሉይ ኪዳን አኳያ ስናይ አገልግሎቱ መሥዋዕትን በመሠዋትና ጸሎት በመጸለይ ይፈጸማል ፡፡ ካህን በማንኛውም ሃይማኖት አለ (ዘፍ 41, 45 ፣ 1ሳሙ 6, 2 ሐዋ 14, 13) ፤ በመጀመሪያ እንደ አቤልና ቃየል ሰው ለራሱ የራሱን መሥዋዕት አቅራቢና ሠዊ ነበር (ዘፍ 4, 3-4) ፤ በኋላም አንደ ኖኅና እንደ አብርሃም አባት ለቤተሰቡ ይሠዋ ነበር (ዘፍ 8, 20 ፣ 12, 7 ፣ 13, 18) ፡፡ ሕግ ሲሰጥ ግን አሮንና ልጆቹ ለእስራኤል ካህናት እንዲሆኑ ተመረጡ (ዘጸ 28, 1) ፡፡ ከአሮን ቤተሰብ ውጭ የሌዊ ዘሮች በመቅደስ ያገለግሉ ነበር እንጂ መሥዋዕትን አልሠዉም (ዘኁ 3, 5-10)፡፡

ሆኖም ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው ቢሆንም እግዚአብሔር ራሱን ከገለጠለት እንደ ጌዴዎን መሥዋዕት ይሠዋ ነበር (መሳፍ 6, 18-26 ፣ 13, 16) ፤ እንደዚሁም የእግዚአብሔር ካህናት ሲጠፉ ኤልያስ መሥዋዕት ሠዋ (1ነገ 18, 30) ፡፡ ከአሮን ልጆችም ነውር ያለበት ከተገኘ አይሾምም ነበር (ዘሌ 21, 16-24) ፡፡

አሮንና ልጆቹ ሲሾሙ ልዩ ልብስ ለብሰው በዘይት ይቀቡ ነበር (ዘጸ 28, 40 ዘሌ 8)  ፡፡ አገልግሎታቸውንም በብዙ ጥንቃቄ እንዲፈጽሙ ታዘዙ (ዘጸ 30, 17-21) ፡፡ በዚያን ጊዜ የካህናት ሥራ በመቅደስ ማገልገል (ዘኁ 16, 40 ፣ 18, 5) ሕግን ለአሕዛብ ማስተማር (2 ዜና መ. 15, 3 ሕዝ 7, 26) ፣ በኡሪምና ቱሚም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ (ዘጸ 28, 30 ዕዝ 2, 63) ፣ ተላላፊ በሽታ ያለባቸውን መለየት ነበር (ዘሌ 13, 1-3) ፡፡

በአጠቃላይ ካህናት በቤተ መቅደስ የሚፈጽሙትን አገልግሎት በሦስት (3) ይከፋላል ፦

1) ዕለታዊ አገልግሎት ፦ ይህ ጠዋትና ማታ የሚቃጠል መሥዋዕትን የመሠዋት ፣ በቅድስት መብራቶችን የማብራት ፣ ዕጣን የማጠን ፣ ሰው የሚያመጣውን መሥዋዕትም በያይነቱ የማቅረብ አገልግሎት ነበር (ዘጸ 29, 38-39 ፣ 30, 1-8) ፡፡

2) ሳምንታዊ አገልግሎት ፦ በየሰንበቱ ዐሥራ ሁለት የመገኘቱን ኅብስት በገበታው ላይ የማኖር አገልግሎት ነው (ዘሌ 24, 5-9) ፡፡

3) ዓመታዊ አገልግሎት ፦ በማስተሥረያ ቀን ልዩ ሥርዓትን የመፈጸም አገልግሎት ነው (ዘሌ 16) ፡፡

► ሊቀ ካህናት የሚባለውስ አመጣጡ ከየት ነው? የአገልግሎት ተግባሩስ ምንድን ነው? ከአሮን ጋር ለምን ታያይዞ ይጠቀሳል?

ሊቀ ካህናት ማለት ካህናትን የሚቆጣጠር የካህናት አለቃ ማለት ነው ፡፡ ይህ ማዕረግ በመጀመርያ ለአሮን በኋላም ከአሮን ቤተሰብ ለዋናው ስለተሰጠ ከአሮን ጋር በተያያዘ መልኩ ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ ይሰማል ፡፡ በመጀመርያ ጊዜ እልቅናው እስከ ሞት ድረስ ነበር ፤ በኋላ ግን ነገሥታት እንደፈለጉ ሊቃነ ካህናትን ይሾሙና ይሽሩ ነበር ፡፡ በክርስቶስ ጊዜም እንደነ ሐና ያሉ በሮም መንግሥት የተሾሙ ሊቃነ ካህናት ነበሩ (1ነገ 2, 26 ሉቃ 3, 2) ፡፡ የሊቃነ ካህናቱ ልብሶች በዕውቅ (በልዩ ዓይነት) የተሠሩ ነበሩ ፡፡ እነርሱም ኡሪምና ቱሚም የተቀመጡበት የደረት ኪስ ፣ ኤፉድ ፣ ቀሚስ ፣ ዝንጉርጉር ሸሚዝ ፣ መጠምጠሚያ “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል የተቀረጸበት የወርቅ አክሊልና መታጠቂያ ናቸው (ዘጸ 28, 1-39) ፡፡

አሮን ሲሾም ሙሴ እንዲያለብሰው በዘይትም እንዲቀባው ታዘዘ (ዘጸ 29, 1-9) ፡፡ ሊቀ ካህናት ቤተ መቅደስን ያስተዳድራል ፣ ካህናትንም ይቈጣጠራል (1 ሳሙ 3, 12-13 ፣ 2ነገ12, 7 ፣ 12, 7 ፣ 22, 4) ፡፡ በሸንጎም ላይ ሊቀመንበር ይሆን ነበር (ማቴ 26, 57-65) ፡፡ ሊቀ ካህናት በማስተሰረያ ቀን ልዩ መሥዋዕት ለሕዝብ ያቀርባል ፤ በዚያን ቀን ብቻ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ በታቦቱ ላይ ደም ይረጫል (ዘሌ 16) ፡፡

► ኡሪምና ቱሚም ምንድን ናቸው? ከሊቀ ካህናቱ ጋር ምን ግኑኝነት አላቸው?

ኡሪምና ቱሚም ሊቀ ካህናት በሚለብሰው በኤፉዱ ላይ ባለው የደረት ኪስ ውስጥ የሚከተቱ ሁለት ዕቃዎች ናቸው (ዘጸ 28, 30 ዘዳ 33, 8)፡፡ ኡሪምና ቱሚም ከምን እንደተሠሩ ወይም እንዴት ያሉ እንደነበሩ አልተገለጠም ፤ በኡሪምና በቱሚም ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ይጠየቅ እንደነበረ ተገልጿል (ዘኁ 27, 21 ፣ ዕዝ 2, 63) ፡፡ ዳዊት በኡሪም (በኤፉድ) እግዚአብሔርን በጠየቀ ጊዜ መልስ አገኘ (1ሳሙ 23, 6-12) ፡፡ ሳኦል ግን ቢጠይቅ መልስ አጣ (1 ሳሙ 28, 6) ፡፡

► መልከ ጼዴቅ ከሙሴና ከአሮን በፊት እንደነበረና ከክህነታዊም አገልግሎት ጋር በተደጋጋሚ ይጠቀሳል ፤ የመልከ ጼዴቅ ክህነት ከአሮን ክህነት ይበልጣል ወይስ ያንሳል?

            መልከ ጼዴቅ ማለት የጽድቅ ንጉሥ ማለት ነው፡፡ የሳሌም ንጉሥ ነበር ፡፡ ይህም የሰላም ንጉሥ ማለት ነው ፡፡ ምናልባትም “ሳሌም” ኢየሩሳሌም ይሆናል ፡፡ የእግዚአብሔርም ካህን ነበር (ዕብ 7, 1-3) ፡፡ አብርሃም ከጦርነት በተመለሰ ጊዜ መልከ ጼዴቅ ባረከው ፤ አብርሃምም ከሀብቱ ሁሉ ዐሥራትን ሰጠው (ዘፍ 14, 18-20) ፡፡

ክህነቱ በእርግጥም ከአሮን ክህነት እንደሚበልጥ ተጽፎለታል ፡፡ ይህም አንደኛ በሥጋዊ ትውልድ ሳይሆን በእግዚአብሔር መሐላ በመሾሙ (ዕብ 5, 5-6 ፣ 7, 13-17) ፡፡ ሁለተኛ በሞት ሳይወሰን ለዘለዓለም በማገልገሉ ነው (ዕብ 6, 20 ፣ 7, 3 እና ከ23-25 ፡፡ ክርስቶስ እንደ መልከ ጼዴቅ በእግዚአብሔር ሊቀ ካህናት በመባሉ የአሮንን ክህነት አስቀርቷል (ዕብ 5, 7-10 ፣ 7, 11-19) ፡፡ 

►የክርስቶስ ክህነት ከመልከ ጼዴቅና ከአሮን ክህነት(ሊቃነ ክህነት) ጋር በተያያዘ መልኩ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?      

    ክርስቶስ  እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን ሆኖ ለኃጢአት ሁሉ የሚበቃውን መሥዋዕት አቅርቧልና የአሮን ክህነት አስቀርቷል (ዕብ 7, 11-28) ፡፡ የክህነቱን ሥራ የፈጸመው በምድራዊ መቅደስ ሳይሆን በሰማያዊ መቅደስ ፣ በእንስሳት ደም ሳይሆን በራሱ ደም ነው (ዕብ 9, 11-12) ፡፡ አሁን ለኃጢአት ሌላ የደም መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልግም ፤ ሆኖም ምእመናን ሁሉ በክርስቶስ ሥራ መሠረት መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ስለሚያቀርቡ የሚሰጡትን ምስክርነትም ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ስለሚያደርሱ ካህናት ተብለዋል (ሮሜ 12, 1 ፣ ዕብ 10, 19-25 ፣ 13, 15 ፣ 1ጴጥ 2, 5-9 ራዕ 1, 5-6) ፡፡

            ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት በመሆን ራሱን አንድ ጊዜ ሠውቶ ወደ ሰማያዊ መቅደስ ገብቷልና የሊቀ ካህናት ሥራ በአዲስ ኪዳን ቀርቷል (ዕብ 9, 1-28 ፣ 10, 12-21) ፡፡ 

► በብሉይ ኪዳን ሊቀ ክህናትና መሥዋዕት በተያያዘ መልኩ ሲገለጹ ይሰማል ፤ ለመሆኑ መሥዋዕት ማለት ምን ማለት ነው? አመጣጡና አደራረጉስ በምን ዓይነት መልኩ ይከናወን ነበር?

            እንደ ብሉይ አገላለጽ (የኦሪት መጻሕፍቶች) ሰው ለአምላኩ አንዳች ነገር ቢሰጥ ወይም ቢያቃጥል ያ ነገር መሥዋዕት ወይም ቁርባን ይባላል ፡፡ መሥዋዕቱም እንደ ሥርዓቱ ዓይነት ሲሠዋ መሠዋቱ ልዩ ልዩ አሳብ ሊገልጥ ይችላል ፡፡ ለምሳሌ በአምላክ ፊት ተቀባይነትን ለማግኘት ወይም ለማጠንከር ይሆናል ፤ እንዲሁም የሰጪውም እምነት ወይም ንስሓ ምስጋና ወይም ፍቅር ያሳያል ፡፡ መሥዋዕትን ያቀርቡ የነበሩ ሰዎች አንድ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እስራኤላውያን ብቻ ሳይሆኑ አረማውያንም ደግሞ ለጣዖቶቻቸው ያቀርቡ ነበር ፡፡

            በብሉይ ኪዳን ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘፍ 4, 4 ላይ ይገኛል ፡፡ እንዲሁም መሠረተ አሳቡ በዘፍ 3, 21 ላይ ተገልጿል ፡፡ ከሙሴ በፊት የጥንት አባቶች ለእግዚአብሔር ይሠዉ ነበር (ዘፍ 4, 4፣ 8, 20 ፣ 12, 7) ፡፡ በኦሪት ሕግ ግን የካህናት ወገኖች ብቻ እንዲሠዉ ተፈቅዶላቸዋል (ዘኁ 3, 10) ፡፡ የኦሪትም መሥዋእቶች ከሥጋ ከእህልና ከመጠጥ ነበሩ ፡፡ ከሥጋም ሲሆን ነውር ከሌላቸው ንጹሓን ከተባሉ እንስሶችና ወፎች መሆን ነበረበት (ዘፍ 8, 20 ፣ ዘሌ 22, 17-25) ፡፡

            እግዚአብሔር ከእስራኤል ያዘዛቸው መሥዋዕቶች አምስት ዓይነት ናቸው ፤ እነዚህም የሚቃጠል መሥዋዕት ፣ የእህል ቁርባን ፣ የደኅንነት መሥዋዕት ፣ የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ናቸው (ዘሌ 1-5) ፡፡

የመሥዋዕት አቀራረብ ሥነ ሥርዓት በእንስሳት ሲፈጸም ፦

1) እንስሳው ንጹሕ የሆነና እንከን የሌለበት ነበር (ዘጸ 12, 5 ፣ ዘሌ 22, 24-25 1ጴጥ 1, 18-19) ፡፡

2) አቅራቢው እጁን በእንስሳው ራስ ላይ ይጭናል (ዘሌ 1, 4) ፡፡ ይህን በማድረጉ በምሳሌነት ራሱን ከእንስሳው ጋር አንድ ያደርጋል ፤ ኃጢአቱንም ያሸክመዋል (ዘሌ 16, 21፣ ኢሳ 53, 6 ፣ 1ጴጥ 2, 24) ፡፡

3) አቅራቢው ያርደዋል ፤ የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና (ሮሜ 6, 23 ዕብ 9, 28) ፡፡

4) ካህን የመሥዋዕቱን ደም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል (ዘሌ 1, 5 ፣ 17, 11 ፣ ዕብ 9, 12) ፡፡

5) ካህን ከእንስሳው እንደ መሥዋዕቱ ዓይነት ልዩ ልዩ ክፍልና ብልት ያቃጥላል ፡፡ ይህ በምሳሌነት አቅራቢው ራሱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት እንደሚያቀርብ ይገልጣል (ዘፍ 8, 21 ፣ ሮሜ 12, 1 ፣ 2ቆሮ 2, 14-16 ፣ ኤፌ 5, 2) ፡፡

6) ካህን አንዳንድ ጊዜም አቅራቢው ከእንስሳ ያልተቃጠለውን በመሠዊያ አጠገብ ይበላል (ዘሌ 6, 26) ፡፡ ይህም በመሥዋዕቱ መሠረት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዳለው ያሳያል (1ቆሮ 10, 14-22 የይሁዳ መልእክት ቁ.12) ፡፡

 የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ  ዋና አስተባባሪ ፦ ፀጋዬ ሀብቴ

 

ለጥናት የሚያግዙ ጥያቄዎች

1) ዐሥራትን በተመለከተ ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ  ሀ) እግዚአብሔር ምድር ከምታፈራውና ከከብትም ወገን ሁሉ ዐሥራት እንዲሰጥ አዘዘ  ለ) እንደ ኦሪት ዘፍጥረት አገላለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ዐሥራት የከፈለው መልከ ጼዴቅ ነው ሐ) በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ገቢ ያለው እያንዳንዱ ግለ ሰው ዛሬም ቢሆን ዐሥራት የመክፈል ግዴታ አለበት መ) ዛሬም ቢሆን ዐሥራት የማይከፍል ገቢ ያለው ማንኛውም ሰው የእግዚአብሐየር ባለ እዳ ይሆናል ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው

2) የእስራኤላውያን የመጀመሪያው የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዓት በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ ዘጸ 12 በማስተዋል ደጋግሞ ማንበብ ያስፈልጋል) ፡፡ ሀ) እስራኤላውያን እንዲያገለግሉዋቸው ከሌላ ቦታ በግዢም ሆነ በሌላ መልኩ ከእነሱ ጋር ይኖሩ የነበሩ ወንዶች አገልጋዮች (ባዕዳን የነበሩ) የፋሲካን በዓል ከእስራኤላውያን ጋር ማክበር እንዲችሉ ግዴታ መገረዝ ነበረባቸው ለ) በታረደው የፋሲካ በግ ደም የቤታቸው መቃ እንዲቀቡ የታዘዙት የሞት መልአክ ወደየቤታቸው ገብቶ እንዳይገድላቸው የሚጠቅም የመለያ ምልክት እንዲሆን ነበር ሐ) የፋሲካው በግ ሥጋ በዚያኑ ሌሊት እየጠበሱ ከመራር ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር እንዲበሉት ታዘዙ መ) እስራኤላውያን ግብጽ ውስጥ በባርነት አራት መቶ ስልሳ ዓመት ከኖሩ በኋላ ነው ግብጽን ለቀው የወጡት ሠ) የአይሁዳ የፋሲካ በዓል በሚከበርበትና ጠቦታቸው በሚታረድበት ሰዓት ክርስቶስ ደሙን አፍሶ ዓለምን በማዳኑ ምክንያት ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን የፋሲካ በግ ተባለ ፡፡

3) እስራኤላውያን በምድረ በዳ ጉዞአቸው ውስጥ እያሉ በረሀብ ልናልቅ ነው ብለው ሲጮኹ መና ተጠማን ብለው ሲጮኹ ደግሞ ውሃ አዘነመላቸው ፡፡ ከሚከተሉት ውስጥ ከሰማይ ስለወረደው መና እና ከአለት ስለፈለቀው ውሃ ትክክለኛ ያልሆነው የትኛውን ነው? (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ዘጸ ምዕራፍ 16 እና 17 ደጋግሞ በማስተዋል ማንበብ ያስፈልጋል) ሀ) ሙሴ ለእስራኤላውያን ለሰባት ቀን በተከታታይ ከሰማይ የወረደውን መና ለምግብነት ይውል ዘንድ እንዲሰበስቡ አዘዛቸው ለ) ሕዝቡ ውሃ በተጠሙ ጊዜ ሙሴን በድንጋይ የመውገር ያህል ተዘጋጅተው ነበር ሐ) ሙሴ የአባይን ወንዝ የመታበትን በትር በመጠቀም በሲና ተራራ የነበረው አለት ሲመታው ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ከውስጡ ፈለቀ  መ) መና በወረደ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ለዕለት ምግቡ የሚያስፈልገውን ብቻ እንዲሰበስብ ተፈቀደለት ሠ) ሁሉም ልክ ናቸው

4) እንደ ኦሪት መጻሕፍት ስለ አሮን ወገኖችና ስለ ካህናት ዋና ዋና ተግባራት ከሚባሉት ውስጥ የማይመደበው የትኛውን ነው? ሀ) መቅደስ ላይሆኖ የራሱንና የሕዝቡን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ለ) ሕግን ማስተማር  ሐ) ዕለታዊ ፣ ሳምንታዊና ዓመታዊ አገልግሎቶችን ማከናወን መ) አሮንና ልጆቹ ለእስራኤል ካህናት እንዲሆኑ ተመረጡ ነገር ግን የሌዊ ዘሮች በመቅደሱ እንዲያገለግሉ ተፈቀደላቸው ሠ) ካህናት የሕዝቡን ንስሓ ይሰሙ ነበር (ንስሓ ያስገቡ ነበር) ፡፡ 

5) በሙሴ አማካኝነት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ውሃ ያፈለቀበት የሲና ተራራ አለት ስሙ ከዚህ ታላቅ ተአምራዊ ክንውን በኋላ የቦታው ስም ምን ተብሎ ተጠራ? በዚህ ስም የተጠራበት ምክንያቱስ ምንድን ነው (ወይም የቦታው ስም ትረጓሜ ምንድን ነው?)

6) በዘጸ 32, 32-35 ላይ ሙሴ ለእግዚአብሔር እንዲህ አለው “እባክህን ኃጢአታቸውን ይቅር በል ፤ ይቅር የማትላቸው ከሆነ ግን የሕዝብህ ስሞች ከተጻፉበት መዝገብ የእኔን ስም ደምስስ” ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት “ስሞቻቸውን ከመዝገቤ የምደመስሰው ኃጢአት በመሥራታቸው ያሳዘኑኝን ሰዎች ነው ፤ አሁንም ሂድ ፤ ወደነገርሁህ ስፍራ ሕዝቡን ምራ ፤ መልአኬም እየመራህ በፊትህ እንደሚሄድ አስታውስ ፤ ነገር ግን ይህን ሕዝብ ስለ ኃጢአቱ የምቀጣበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም” ፡፡

ለመሆኑ ይህ “የሕዝቦች ስሞች የተጻፉበት መዝገብ” ወይም “የእግዚአብሔር መዝገብ” የተባለው ምንድን ነው? ወይም ምንን ያመለክታል?    

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት