እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ክፍል ሁለት - ት/ርት ፲ - የታሪክ መጽሐፍት ጥናት

ክፍል ሁለት- ትምህርት ዐሥር

የታሪክ መጻሕፍት ጥናት

በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍፍል መሠረት የታሪክ መጻሕፍት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

writing-bible-scroll-1መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት ቅዱሳት መጻሕፍት በተለያዩ ክፍሎች እንደሚመደቡ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ከአምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ቀጥለው የሚገኙት የታሪክ መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ ፡፡ እነዚህም መጽሐፈ ኢያሱመጽሐፈ መሳፍንትመጽሐፈ ሩት ፣ 1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል ፣ 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል ፣ 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት ፣ 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት ፣ 1ኛ ዜና መዋዕል ፣ 2ኛ ዜናመዋዕልመጽሐፈ ዕዝራመጽሐፈ ነህምያ ፣ ጦቢት ፣ ዮዲት እና መጽሐፈ አስቴር ናቸው፡፡

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍፍል መሠረት ኢያሱ ፣ መሳፍንት ፣ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥት የቀድሞዎቹ ወይም ቀደምት ነቢያት በመባል ሲታወቁ ዐሥራ ስድስቱ ነቢያት (ከትንቢተ ኢሳይያስ ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ያሉት) ደግሞ የኋላኞቹ ነቢያቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡ መጽሐፈ ኢያሱ ፣ መጽሐፈ መሳፍንት ፣ መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥት የታሪክ መጽሐፍት ከሚባሉት ውስጥ ቀደምቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት የኦሪትን መጻሕፍት በመከተል እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምን ያህል ደግና ተንከባካቢ እንደሆነ ነገር ግን ሕዝቡ ወደ ተሳሳተ ሕይወት እየገባ እግዚአብሔርን እንደሚያሳዝንና ከእግዚአብሔርም የመራቅ ዝንባሌ እንዳለው ያስገነዝባሉ፡፡ ቀጥሎም ሰው ከእግዚአብሔር ርቆ ሲሄድ ብዙ ችግር ፣ ፈተናና መከራ እንደሚገጥመው ይገልጻሉ፡፡

እስራኤላውያንበምድረበዳበሚንከራተቱባቸውዓመታትመጨረሻላይአንድጊዜሙሴተቈጥቶእግዚአብሔርንባለማክበሩወደከነዓንእንዳይገባመከልከሉንይታወቃል (ዘኁ 20 1-13 መዝ 106 32-33)፡፡ታድያከሙሴበኋላእስራኤላውያንማንይመራቸውነበር? ወደከነዓንምድርየገቡትስእንዴትናበማንመሪነትነበር?

ከሙሴ ሞት በኋላ የነዌ ልጅ ኢያሱ የሕዝቡ መሪ ሆኖ ሕዝቡን ወደ ከነዓን አሻግሮ ምድሩን አወረሳቸው(ዘኁ 27፡ 15-23 ዘዳ 3፡ 28 ፣ ዘዳ 31፡ 23) ፡፡ ኢያሱ ማለት “እግዚአብሔር አዳኝ ነው” ማለት ነው ፡፡ ኢያሱ ሎሌ ሆኖ ከግብጽ ወጣ ፤ ሙሴም ከአማሌቅ ጋር እንዲዋጋ አዘዘው ፤ አሸነፈም ፤ ከዚያም የሙሴ ሎሌ ሆነ(ዘጸ 17፡ 8-13 ፣ ዘጸ 24፡ 13 ፣ 32 ፡ 17 ፣ 33፡ 11)፡፡ ከነዓንን ሊሰልሉ ከቃዴስ ከወጡት 12 ሰላዮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እርሱና ካሌብ በእምነት እንውጣ ስላሉ ወደ ከነዓን እንደሚገቡ ተስፋ ተሰጣቸው(ዘኁ 13-14)፡፡

          እግዚአብሔርም በቃልና በራእይ አደፋፈረው(ኢያ 1፡ 1-9 ፣ 5፡ 13-15)፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በኢያሱ መሪነት ዮርዳኖስን ተሻግረው ኢያሪኮን ያዙ ፤ ዋና ሰፈራቸውም ጌልጌላ ሆነ፡፡ ከዚያም እየዘመቱ የከነዓንን ነገሥታት አሸነፉ፡፡ እግዚአብሔር ቀኑን በማስረዘምና በረዶ በማዝነብ ረዳቸው (ኢያ 10፡ 11-14)፡፡ አገሩን ከያዙ በኋላ መሬቱን ለእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ፡፡ የመሞቱ ጊዜ ሲደርስ ሕዝቡን ሰብስቦ እግዚአብሔር ስላደረገላቸው ነገር ሁሉ አሳሰባቸው፡፡ ከሕዝቡም ጋር ቃል ኪዳን ተጋብቶ ለመታሰቢያ ታላቅ ድንጋይ በሴኬም አቆመ (ኢያ 24፡ 25-28)፡፡ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ ፤ በርስቱ በኤፍሬም አገር ተቀበረ (ኢያ 24፡ 29-31)፡፡

መጽሐፈኢያሱስለምንያስተምራል ? የመጽሐፉዋናትኩረትምንድንነው?

          መጽሐፈ ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ እግር ተተክቶ በተሾመው በኢያሱ መሪነትና በእግዚአብሔር ኃይል በጦርነት ድል ነሥተው ከነዓንን እንዴት እንደያዙ የሚተርክ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ ኢያሱ ራሱ የሙሴን መጽሐፍ አነበበ፤ የሙሴን ሕግ በድንጋይ ጻፈ ፤ በሕይወቱ መጨረሻም ከሕዝቡ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን በጽሑፍ አሰፈረ (ኢያ 1፡ 8 ፤ 8፡ 32)፡፡ ይህ መጽሐፍ ከሚተርካቸው ዋና ዋናዎቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ስለ መሻገር ፣ ስለ ኢያሪኮ ግንብ መፍረስ ፣ በዐይ ስለተደረገው ጦርነትና ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ስለገቡት ቃል ኪዳን ስለማደሳቸው የሚናገሩት ናቸው፡፡

መጽሐፉ እንዲህ ይከፈላል ፦

  1. 1)የከነዓን ምድር መወረር (ኢያ 1-12)

ሀ) የእስራኤል ሕዝብ ዝግጅትና ዮርዳኖስን መሻገር (ኢያ 1-4)

ለ) የኢያሪኮ መያዝና የአካን ኃጢአት (ኢያ 5-7)

ሐ) የእስራኤል መዝመትና የከነዓን ነገሥታት መሸነፍ (ኢያ 8-12)

  1. 2)የከነዓን ምድር አከፋፈል (ኢያ 13-22)
  2. 3)የኢያሱ ስንብት (ኢያ 23-24) ናቸው፡፡

ኢያሱሕዝብየመምራትተግባሩንሲጀምርሰላዮችወደኢያሪኮከተማእንደላከይታወቃል፡፡ኢያሱይህንያደረገውኢያሪኮለእስራኤላውያን  ምንዐይነትጠቀሜታስለነበራትነው?

          ኢያሪኮ ከጨው ባሕር ወይም ከሙት ባሕር በስተ ሰሜን 15 ኪ.ሜ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ 25 ኪ.ሜ ርቃ የምትገኝ ጥንታዊት ከተማ ናት፡፡ ኢያሪኮ ማለት “የጨረቃ ከተማ” ማለት ነው፡፡ በኢያሪኮ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች በጥንት ዘመን ጨረቃን ያመልኩ እንደነበር ከታሪክ መዛግብት እንረዳለን፡፡ ኢያሪኮ የተስፋዪቱን ምድር ለመውረስ ወሳኝና ማእከላዊ ቦታ ከመሆንዋም በላይ የተስፋዪቱ ምድር አካል ነበረች፡፡ ዮርዳኖስ ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ የምትገኝ የመጀመሪያዋ ከተማ ስለነበረች ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ሰፍረው ወደ ተስፋዪቱ ምድር አሻግረው ይመለከቱ ለነበሩት እስራኤላውያን ኢያሪኮ ወሳኝ ቦታ ነበረች፡፡ ኢያሱም የኢያሪኮ ሕዝብ ለጦርነት ያደረጉት ዝግጅትና የመቋቋም ኃይላቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ በማለት ሰላዮች በምስጢር ላከ፡፡ ኢያሪኮም በጀግኖች ወታደሮች የምትጠበቅና ዙሪያዋም በቅጽር የታጠረች ከተማ ነበረች (ኢያ 6፡ 2)፡፡ ሰላዮቹም በአመንዝራዪቱ በረዓብ ረዳትነት ሁሉንም ነገር አጥንተው ሲመለሱ “እግዚአብሔር አገሪቱን በሙሉ ለእኛ እንደሰጠን እርግጠኞች ነን ፤ ምክንያቱም በዚያ የሚኖሩት ሁሉ እኛን ከመፍራት የተነሣ በመሸበር ላይ ናቸው” በማለት ያዩትንና የሰሙትን ለኢያሱ አበሰሩት (ኢያ 2፡ 23-24)፡፡

          ኢያሱም ሰላዮቹን የነገሩትን ካደመጠ በኋላ ሕዝቡን የቃል ኪዳኑ በተሸከሙ ካህናቶች መሪነት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ አቅራቢያ ደረሱ፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦት የተሸከሙ ካህናቶች ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በገቡ ጊዜ ውሃው እንደቆመና ሕዝቦችም ሁሉ በደረቅ ምድር መሻገር እንደቻሉ ከመጽሐፉ እንረዳለን(ኢያ 3፡ 14-15)፡፡ የኢያሪኮ ከተማ ዙሪያዋ በቅጽሮች የታጠረችና በወታደሮች ጥበቃ የምትገኝ ስለነበር ኢያሱና ይመራው የነበረው ሕዝብ በቀላሉ ወደ ከተማዪቱ መግባት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ረዳትነት ኢያሱ ከተማዋን መውረር የሚያስችለው ዕቅድ ነደፈ፡፡ በዚህም መሠረት የቃል ኪዳኑ ታቦት የተሸከሙ ካህናት በቅጽር የታጠረችውን የኢያሪኮ ከተማ ለስድስት ቀናት በቀን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ፡፡ ሌሎች ሰባት ካህናቶች ታቦቱን የተሸከሙትን በመቅደም መለከት በመንፋት ይመሩ ነበር፡፡ በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፡፡ በዚህ ጊዜ የከተማዪቱ ቅጽሮች ፈረሱ፤ ሠራዊቱ ወደ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማዪቱ በመግባት በቁጥጥሩ ሥር አደረጋት (ኢያ 6፡ 20)፡፡  ከዚህ በኋላ ከተማዪቱን እስከ ሥር መሠረትዋ ድረስ አቃጠሉአት፤ እነርሱ ወስደው በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት ካስቀመጡአቸው ከወርቅ ከብር ከነሐስና ከብረት ከተሠሩ ነገሮች በቀር በከተማዪቱ የነበረው ነገር ሁሉ አብሮ ተደመሰሰ (ኢያ 7፡ 24)፡፡

ከኢያሪኮድልበኋላ“ዐይ”የተባለችውከተማለመያዝሲታገሉእስራኤላውያንለምንድንነውከባድሽንፈትየደረሰባቸው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔርን ይዞ የተጓዘ ጉዞውን በድል ሲያጠናቅቅ ከትእዛዛቱ ርቆ በራሱ ፈቃድ የሚመራና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጥስ ሕይወቱ በመከራና በጭንቀት ተውጦ ጉዞውን በሽንፈት ሲያጠናቅቅ ይታያል፡፡ የእስራኤላውያንም ሽንፈት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እስራኤላውያን ኢያሪኮ ከተማ ሲገቡ ያገኙትን ሁሉ እንዲደመስሱ ታዘው ነበር፡፡ ነገር ግን መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች አንዳንዶችን ወስደዋል ፤ እነርሱንም ከሰረቁ በኋላ ምንም ነገር እንዳልወሰዱ በመዋሸት ከራሳቸው ንብረት ጋር ደባልቀዋል፤ በተለይም ዓካን የተባለው እስራኤላዊ ካገኘው ዕቃ መካከል ውብ የሆነ የባቢሎናውያን ካባ ሁለት ኪሎ ያህል የሚመዝን ብርና ግማሽ ኪሎ ያህል የሚመዝን ምዝምዝ ወርቅ ወስዶ በድንኳኑ ውስጥ በመቅበሩ እግዚአብሔር አዘነበት፡፡ ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ዓካንና ቤተሰቡ እንስሳቶቹም ጭምር “የመከራ ሸለቆ” በተባለበት ቦታ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉአቸው ፤ ንብረቱንም ሁሉ አቃጠሉ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ብርቱ ቁጣውን እንዲገታ አደረገ (ኢያ 7)፡፡

ኢያሱለምንድንነውሙሴየጻፈውሕግበዔባልተራራላይለሕዝቡያነበበው?

          በመጀመሪያ ሕግ ማለት አንድን ነገር ለመፈጸም የሚያዝዝ ወይም ከማድረግ የሚከለክል ትምህርት ፣ መመሪያ ፣ ውሳኔና ሥርዓት ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስተዳድረው በቃል ኪዳን ሥርዓት ነው፡፡ ሕግ በቃል ኪዳን ውስጥ የሰውን ተግባር ወይም ድርሻ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ሰው በእግዚአብሔር ሕግ መደሰት እንደሚገባው ይናገራል (መዝ 1፡ 2 ፤ 19፡ 7-11 ፤ 119)፡፡ ዐሠርቱ ቃላት የሕይወት መመሪያ ሕግ ናቸው (ዘዳ 4፡ 13)፡፡ እነዚህ ትእዛዛት በቃል ኪዳን መልክ ተሰጡ (ዘጸ 20፡ 1-17) ፡፡ የብሉይ ኪዳን ሕግ በሦስት ክፍሎች ይመደባሉ፡፡ እነርሱም የግብረገብ መመሪያዎች (የሞራል ሕግ) ፣ የመንግሥት መተዳደሪያ ሕግጋትና የመሥዋዕት አገልግሎት መመሪያዎች ናቸው፡፡

          ኢያሱ እስራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ፣ ከጦር አለቆቻቸው ፣ ከዳኞቻቸው ፣ ከካህናቶቻቸውና በመካከላቸው ከሚኖሩ የውጭ ሀገር ስደተኞች ጋር በዔባል ተራራ እንዲሰባሰቡ ካደረገ በኋላ ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበላቸውን ዐሠርቱ ቃላት ወይም የሕይወት መመሪያ ደንቦች በድጋሚ አነበበላቸው፡፡ ይህም ያደረገበት ምክንያት እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ገብተው ፣ ከጥንት ጀምረው ሲመኙት የኖሩትን አግኝተው ፣ ኑሮአቸው ካመቻቹ በኋላ የረዳቸውን ፣ በምድረበዳ የመራቸውን ፣ እስከ ተስፋዪቱ ምድር የመራቸውን አምላክ እንዳይረሱና ወደ ጣዖታት እንዳይታለሉ ለማስጠንቀቅ ሕጉን ዘነበበላቸው(ኢያ 8፡ 30-35)፡፡

ኢያሱ“የምታመልኩትንዛሬውኑምረጡእኔናቤተሰቤግንእግዚአብሔርንእናመልካለን”በማለትየተናገረውለማንናለምንድንነው (ኢያ 24 15)?

          ኢያሱ በሴኬም የእስራኤል ነገዶች በሙሉ በሴኬም በአንድነት ሰበሰበ፤ ሽማግሌዎች ፣ መሪዎች ፣ ዳኞችንና የእስራኤል የጦር አዛዥዎች ሁሉ ጠርቶ ከሰበሰበ በኋላ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ እስከዚያች ቀን ድረስ ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ ተረከላቸው (ኢያ 24፡ 1)፡፡ በማረስ ያልደከሙበትን የለማ ምድር ፣ ያልሠሯቸውን ከተሞች ፣ ያልተከሏቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፍ ፍሬዎች በተለያዩ ጊዜያት እግዚአብሔር ለግሷቸዋል (24፡ 13)፡፡ ስለዚህ ይህ አምላክ ሁሌም መከበር ብቻ ሳይሆን በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት መገልገል አለበት፡፡ ኢያሱ ይህንን ለሕዝቡ ማሳሰብ የፈለገበት ዋናው ምክንያት አባቶቻቸው ግብጽ ውስጥ እያሉ በጣዖት አምልኮ እንዲሁም በምድረባዳ ጎዞአቸው ብዙ ጊዜ ወደ ጣኦታት ሲያዘነብሉ ስለነበር ዛሬም ይህንን ዝንባሌ በእነሱ ላይ እንዳያድርና ከእግዚአብሔር እንዳይርቁ ስለሰጋ ባዕዳን አማልክትን አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ ይላቸዋል (ኢያ 24፡ 14)፡፡ በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዛት ሁሉ ለመጠበቅ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ለአምላካቸሁ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ እያለ ኢያሱ ደጋግሞ ያስገነዝባቸዋል (ኢያ 23፡ 6-8)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ቅዱስና ቀናተኛ አምላክ ስለሆነ ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ለእናንተ መልካም ነገር ያደረገላችሁ ቢሆንም ተመልሶ ያጠፋችኋል፤ በቁጣ ተነሣሥቶ ይቀጣችኋል በማለትም ያስጠነቅቃቸዋል (ኢያ 24፡ 20)፡፡ በመጨረሻም እሱና ቤተሰቡ እግዚአብሔር መርጠው እንደሚያመልኩ የራሱን ምሳሌ በመጥቀስ ይነግራቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ኢያሱን “እኛ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመልካለን ፣ ትእዛዛቱም እንፈጽማለን አሉት (ኢያ 24፡ 24)፡፡ ኢያሱ በሕይወት እስከነበረበት ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን በእምነት አገለገሉ (መሳ 2፡ 7)፡፡

 ኢያሱ የገባዖን ሰዎችን እንጨት በመቁረጥና ውሃ በመቅዳት ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ይታወቃል፡፡ የገባዖን ሰዎች አገልጋይ እንዲሆኑ ወይም አገልጋይ ሆነው ተቀብለው ለመኖር ለምን ተገደዱ?

የሒታውያን ወገኖች የሆኑት የገባዖን ሰዎች ኢያሱ በኢያሪኮና በዐይ ከተማዎች ላይ ያደረገውን የድል ዜና ሁሉ ስለ ሰሙ እርሱን ለማታለል ወሰኑ፡፡ እነርሱም ስንቃቸውን አዘጋጅተው ፣ አሮጌ ስልቻና ቀዳዳው ተለጥፎ የተሰፋ የወይን ጠጅ አቁማዳ በአህዮች ጫኑ፤ ተቀዳዶ ያለቀ አሮጌ ልብስ ለብሰው የተጠጋገነ እላቂ ጫማ አደረጉ፤ ለስንቅ የያዙትም እንጀራ ደረቅና የሻገተ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጌልገላ ወደሚገኘው ሰፈር ሄደው ኢያሱንና እስራኤላውያንን “እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ የመጣነውም ከእናንተ ጋር በሰላም መኖር የሚያስችል ውል ለማድረግ ነው” አሉአቸው፡፡ የእስራኤል ሰዎች ግን “ከእናንተ ጋር እንዴት ውል እናደርጋለን? ምናልባትም እናንተ በቅርብ የምትኖሩ ልትሆኑ ትችላላችሁ” አሉአቸው፡፡ የገባኦን ሰዎች ግን ከሩቅ የመጡ በመምሰልና ኢያሱን በማታለል “እኛ አገልጋዮችህ ነን” አሉት፡፡ እስራኤላውያን ስለ ሁኔታው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይጠይቁ ከገባዖን ሕዝቦች ጋር የወዳጅነት ስምምነት አደረጉ፤ ስምምነቱም ለመጠበቅ ቃል ገቡላቸው፡፡

ስምምነቱ በተደረገ በሦስተኛውም ቀን እስራኤላውያን እነዚህ ሕዝብ ወደሚኖሩበት አገር ደረሱ ፤ እነዚህ ሰዎች በቅርብ የሚኖሩ መሆናቸውን እስራኤላውያን ዐወቁ፤ ነገር ግን እነርሱን መግደል አልቻሉም፤ ምክንያቱም መሪዎቻቸው የእስራኤል አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብተውላቸው ነበር ፤ ስለዚህም ጉዳይ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በመሪዎቻቸው ላይ አጉረመረሙ፤ መሪዎቹ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው “በእርግጥ ነው የእስራኤል አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብተንላቸዋል፤ ስለዚህም አሁን ጉዳት ልናደርስባቸው አንችልም፤ የገባነውን ቃል ለማክበር በሕይወት እንዲኖሩ እንፈቅድላቸዋለን፤ ይህን ባናደርግ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣናል፡፡ በመካከላችን ይኑሩ፤ ነገር ግን እንጨት እየቈረጡ ፣ ውሃ እየቀዱ ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች ይሁኑ ተባባሉ(ኢያ 9)፡፡ የገባዖን ሕዝቦችም በእስራኤላውያን ዘንድ ግድያና የመሬታቸው ማጣት እንዳይደርስባቸው በማለት ለእስራኤል ሕዝብና ለመሠዊያ(እግዚአብሔር ለሚመለክበት ቦታ) አገልግሎት እንዲሰጡ ተስማሙ፤ ተገደዱ፡፡

► እስራኤላውያን ግብጽ ውስጥ የባርነት ቀንበር ተሸክመው ሲንከራተቱ ኖረዋል፤ እግዚአብሔር ጩኸታቸው ሰምቶ ሙሴ አስነሣላቸው፡፡ በሙሴ መሪነት ከግብጻውያን እጅ ነፃ ወጥተው ፣ ቀይ ባሕርን ተሻግረው ፣ ምድረበዳን አቋርጠው ከብዙ ዓመታት የመንከራተት ጉዞ በኋላ ወደ ሞአብ ምድር ደረሱ(ዘዳ 34)፡፡ ሙሴ ሞአብ ምድር ነቦ ተራራ ላይ ከመሞቱ በፊት ኃላፊነቱን ለኢያሱ አስረከበው(ዘዳ 34)፡፡ ታዲያ ኢያሱ እንዴት ነው ሕዝቡን ወደ ተስፋዪቱ ምድር አድርሶ የከነአንን ምድር እንዲወርሱ ያደረጋቸው? ማርና ወተት የምታፈልቀው ምድር መውረሳቸው እንዴት ይገለጻል?

 የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ብዙ ከተሞች በጦርነት ድል አድርጎ ተቆጣጠረ፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ማረከ፤ ያገኘውንም ሁሉ በሞት ቀጣ(ኢያ 11፡ 12)፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ምድሩን ሁሉ በእጁ አደረገ፤ ለእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ድርሻ በመስጠት ለእስራኤላውያን በሙሉ አከፋፈለ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከጦርነት ዐረፉ(ኢያ 11፡ 23)፡፡

እስራኤላውያን ተስፋዪቱ ምድር መውረሳቸው ከሚገለጽባቸው ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦

-       የራሳቸው የሆነ አገር በተለይም ሊያርሱት ፣ ሊሸጡትና ሊለውጡት የሚችሉት የራሳቸው የሆነ የመሬት ባለቤት መሆናቸውን፤

-       ሕዝባቸው ተደራጅቶ ፣ የራሱ የሆነ ሕግና ሥርዓት ጠብቆ እንዲሁም የራሱ የሆነ መሪ መርጦ መኖር መቻሉን፤

-       ጣዖት አምላኪ ከሆነ ሕዝብ ነፃ ወጥተው የራሳቸው የሆነ አምላክ እያመለኩ ፣ ሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካይነት የተሰጣቸውን ዐሥርቱን ትእዛዛት እየጠበቁ ፣ የራሳቸው የሆነ የአምልኮ ቦታ ሠርተው መኖር መቻላቸውን፤

-       ከማንኛውም ዓይነት የውጭ ወይም የባዕዳን ተጽእኖ ነፃ ሆነው መሬታቸው እያረሱ ፣ ከብቶቻቸው እያረቡ ፣ ልጆቻቸውን በራሳቸው ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር እያነጹ ፣ ሀብት እያከማቹና አንድ ሕዝብ ሆነው በአንድነት መኖር መቻላቸውን፤

-       በሕይወታቸው መጨረሻ ማለትም በሞታቸው ጊዜ የራሳቸው የሆነ አገር ወይም መሬት ላይ ለመቀበር ዕድል ማግኘታቸውንና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በእርግጥ ይህች ተስፋዪቱ ምድር ማርና ወተት የምታፈልቅ ተብላ ብትገለጽም ማርና ወተት ከመሬት ውስጥ ይፈልቃል ማለት አይደለም፡፡ ማርና ወተት በጣፋጭነታቸውና ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ ኃይልና ሙቀት እየሰጡ ሰውነትን በመገንባታቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ማርና ወተት የምታፈልቅ አገር ማለት እስራኤላውያን ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በተለይም የራሳቸው የሆነ ለም መሬት ፣ ውሃ ፣ መጠለያና ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ያገኛሉ፤ ባለቤትም ይሆናሉ እንደማለት ነው፡፡ በእርግጥ ግብጽ ውስጥ በባርነት ሲኖሩ ምንም ነገር አልነበራቸውም፤ ሀብት ቢያፈሩም መውረስ አይችሉም ነበር፤ የመሬት ባለቤት መሆንም አይችሉም ነበር፡፡

በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ እግዚአብሔር ለኢያሱ “ሙሴ እንዲነግራችሁ ባዘዝሁት መሠረት የመማጸኛ ከተሞችን ምረጡ” በማለት እንዳዘዘው ይታወቃል(ኢያ 20)፡፡ የመማጸኛ ከተማ ማለት ምን ማለት ነው? ጠቀሜታውስ ምንድን ነው?

          “የመማጸኛ ከተማ” ማለት አንድ ሰው በድንገት ሰው ቢገድል ሸሽቶ ወደዚህች ከተማ በመሄድ የሚጠለልባት ወይም መጠጊያ የምትሆነው ከተማ ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው በድንገተኛ አጋጣሚ ሰው ቢገድል ከሚበቀሉት ሰዎች ለመዳን ወደ መማጸኛ ከተማ ይሸሻል፤ እዚያም በከተማዪቱ ፍርድ ሸንጎ ቀርቦ የሆነውን ነገር ሁሉ ለመሪዎቹ ይገልጣል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ከተማዪቱ እንዲገባ ይፈቀድለታል፤ የሚኖርበትም ቦታ ይሰጠውና በዚያ ይቆያል፡፡ ሊበቀሉት የሚፈልጉ ሰዎች ተከትለውት ቢመጡ የከተማዪቱ ሰዎች እርሱን አሳልፈው አይሰጡትም፤ ሰውን የገደለው በድንገተኛ አጋጣሚ እንጂ በቂም በቀል ተነሣሥቶ ስላይደለ ከአደጋ ይጠብቁታል፡፡ በሸንጎ ቀርቦ ፍርድ እስኪቀበልና በዘመኑ ያለው ሊቀ ካህናት እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በዚያች ከተማ ሊቆይ ይችላል፤ ከዚያም በኋላ ሸሽቶ ወደወጣበት ከተማ በመመለስ ወደቤቱ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ለኢያሱ ባዘዘው መሠረት የመማጸኛ ከተሞችን መረጡ፡፡ የተመረጡትም ከተሞች ቄዴሽ ፣ ሴኬም ፣ ኬብሮን ፣ ቤጼር ፣ ራሞትንና ጎላንን መረጡ(ኢያ 20)፡፡         

 የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ  ዋና አስተባባሪ ፦ ፀጋዬ ሀብቴ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. ከሚከተሉት ውስጥ ኢያሱንና የመሪነቱን ሥራ በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ፡፡

ሀ) ኢያሱ የሚለው ስም ትርጓሜ “እግዚአብሔር አዳኝ ነው” ማለት ነው፡፡

ለ) የእስራኤል ሕዝብ ዮርዳኖስን ተሻግረው ኢያሪኮን ሲይዙ የመሪነቱን ሚና የተጫወተው ኢያሱ ነበር፡፡

ሐ) ኢያሱ የተወለደው ግብጽ ውስጥ ነው ፤ ወጣት ሆኖ ከግብጽ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር ወጣ

መ) ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ፤ በኢየሩሳሌም ተቀበረ፡፡

ሠ) ኢያሱ በጦርነት ኃይለኛ ስለነበርና እግዚአብሔርም ስለረዳው ብዙ አገራትና ነገሥታቶቻቸው በማሸነፍ እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር አስገባቸው፡፡

2. የኢያሪኮ ከተማና አወዳደቅዋ በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ኢያሱ ምዕራፍ 6 በማስተዋል ያንብቡት)፡፡

ሀ) ኢያሪኮ ዙሪያዋ በቅጽር የታጠረ ፣ ንጉሥዋም እጅግ በጣም ብርቱ የሆነ ወታደሮችዋም ጀግኖች ነበሩ፡፡

ለ) የቃል ኪዳኑ ታቦት የተሸከሙ ካህናት እንዲሁም ኢያሱና ወታደሮቹ የኢያሪኮን ቅጽር (ከተማዪቱ ተከልላ የታጠረችበትን ግንብ) ለስድስት ቀናት በቀን ለአንድ ጊዜ ያህል ዞሩት፤ በሰባተኛው ቀን ግን ለሰባት ጊዜ ዞሩት፡፡

ሐ) ኢያሱ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ወታደሮች ኢያሪኮ ውስጥ የነበሩት ነዋሪዎች ሁሉ ገደሉ፡፡

መ) ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰች፤ ኢያሱም ከተማዪቱን እንደገና መልሶ የሚሠራት ሰው ቢኖር የእግዚአብሔር መርገም በእርሱ ላይ ይሁን አለ፡፡

ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው፡፡

3. “የመከራ ሸለቆ” ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ለምን በዚህ ስም ተሰየመ? ይህ ቦታ ለምን “የመከራ ሸለቆ” ተብሎ ተጠራ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ኢያሱ ምዕራፍ 7 በማስተዋል ያንብቡት)፡፡

ሀ) እስራኤላውያን የተሸነፉበት ቦታ ስለሆነ

ለ)ዓካን በተባለው እስራኤላዊ   በፈጸመው አሳፋሪ ሥራ ምክንያት እስራኤላውያን የተቸገሩበትና ዓካንንም የወገሩበት ቦታ ስለሆነ  

ሐ) እስራኤላውያን ብዙ ድል አድርገው ጠላቶቻቸውን የደመሰሱበት ቦታ ስለሆነ

መ) ኢያሱና ሠራዊቱ ብዙ የዐይ ነዋሪዎች የገደሉበትና ንብረታቸውን የደመሰሱበት ቦታ ስለሆነ

ሠ) እስራኤላውያን መከራ እንዲርቅላቸው እግዚአብሔር የተማጸኑበት ቦታ ስለሆነ ነው፡፡

4.ኢያሱ በሴኬም ለሕዝቡ ካደረገው ንግግር ውስጥ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ (ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ኢያሱ ምዕራፍ 24 በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡ 

ሀ) ኢያሱ የሕዝቡን የጣዖት አምልኮ ዝንባሌ ስለተረዳ “የምታመልኩትን አምላክ ዘሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” በማለት አስጠነቀቃቸው፡፡

ለ) ሕዝቡም ለኢያሱ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ ትእዛዛቱንም እንፈጽማለን” በማለት ቃል ገቡ፡፡

ሐ) ኢያሱም ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ ትእዛዛቱን ግን በሕግ መጽሐፍ ውስጥ መጻፍ አልፈለገም፡፡

መ) ምስክር ይሆን ዘንድ ትልቅ ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ በሚገኘው የወርካ ዛፍ ሥር አቆመው፡፡

ሠ) ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን አመለኩ፡፡

5. ኢያሱ “እንጨት በመቁረጥና ውሃ በመቅዳት” ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ሕዝቦች የትኞቹ ናቸው?

ሀ) የገባዖን ሕዝቦች፡፡ ለ) የዐይ ሕዝቦች፡፡ ሐ) የኢያሪኮ ሕዝቦች፡፡ መ) የዮርዳኖስ ሕዝቦች ሠ) የሴኬም ሕዝቦች ናቸው፡፡

6. በኢያሱ ምዕራፍ 10 ላይ “የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶቻቸውን እስኪመቱ ፀሐይ ቆመ፤ ጨረቃም ካለችበት ሳትንቀሳቀስ ቆየች፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጎን ተሰልፎ ይዋጋላቸው ነበር” ይላል(ኢያ 10፡ 13-14)፡፡

 -    ለመሆኑ ፀሐይና ጨረቃ መቆም ይችላሉን? ጸሐፊው ምን ለማለት ፈልጎ ይመስልሃል|ሻል ይህንን አባባል የተጠቀመው?

 

 - እግዚአብሔር ከእስራኤል ጎን ተሰልፎ ይዋጋላቸው ነበር ሲል እግዚአብሔር እንደ ሰዎች መሣርያ ይዞ ሰዎችን ሲገድል ነበር ማለት ነውን ወይስ ምን ለማለት ፈልጎ ይመስልሃል|ሻል ይህንን የተጠቀመው?   

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት