እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፯ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ኢዩኤል እና ትንቢተ አብድዩ)

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሃያ ሰባት) - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት

ትንቢተ ኢዩኤል እና ትንቢተ አብድዩ

  • ኢዩኤል ማለት ምን ማለት ነው? ኢዩኤል ተወልዶ ያደገውና የነቢይነት አገልግሎት ተግባሩን የተወጣው የት ነው?

Joel postኢዩኤል የሚለው ስም በዕብራይስጥጆኤል”ሲሆንጆ” ወይም “ኢዩ” የሚለውቃሉ የመጀመሪያ የእግዚአብሔርመጠርያ መለኮታዊ ስምሲሆንኤል”ደግሞ  አምላክማለትነው፡፡ ስለዚህኢዩኤልማለትእግዚአብሔርአምላክነው”ማለት ነው፡፡ነቢዩኢዩኤልመቼእንደኖረ፣ የትና ከየትኛው ቤተሰብ ተወልዶ እንዳደገ፣ ለነቢይነት እንዴት እንደተጠራና የነቢይነት ተግባሩ መቼ እንደተወጣ በአጠቃላይም ስለሕይወት ታሪኩ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በእርግጥ በመጽሐፉ መጀመሪያ የወላጅ አባቱ ስምፑ ቱኤል እንደሆነ ተገልጿል (ኢዩ 11)፡፡ ነገር ግን ከየት እንደሆነበማን ዘመነ መንግሥት ትንቢት መናገር እንደጀመረና እንዳስተማረ ምንም ዓይነት መረጃ አይሰጥም፡፡ በአጠቃላይ ነቢዩ ከመልእክቱ በስተጀርባ ተከልሎ ወይም በመልእክቱ ውስጥ ተሸፍኖ ይገኛል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ የነቢይነት ተግባሩን የተወጣበት ጊዜ ለመገመት የሚያስችል ምንም ዓይነት መረጃ ባይኖርም ከመልእክቱ ይዘት በመነሣት ሊቃውንቶች መጽሐፉ የተገኘው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ወይም በአምስተኛው መቶ ምዕተ ዓመት አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ኢዩኤል የነቢይነት አገልግሎቱን የተወጣው ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲሆን መልእክቱም በወቅቱ ወራሪዎችን በመፍራት በስጋት ይኖሩ ለነበሩት ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተላለፈ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፉ ከሚሰጠው እጅግ በጣም ውስን የሆነ መረጃ ምክንያት የኖረበትና ያስተማረበት ወቅት እንዲሁም መጽሐፉ የተጻፈበት ጊዜና ቦታ በትክክል ይህ ነው ብሎ መወሰን አልተቻለም፡፡

  • የትንቢተ ኢዩኤል መጽሐፍ ጥንቅሩና ይዘቱ ምን ይመስላል?

የመጽሐፉ ይዘትና ጥንቅር በምናይበት ጊዜ መጽሐፉ ሁለት የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት እንረዳለን፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ከምዕራፍ 1፡ 1 እስከ ምዕራፍ 2፡ 11 ያለው ክፍል የሚያካትት ነው፡፡ ይህ ክፍል በሰቆቃ ወይም በሙሾ መልክ የተገለጸ ነው፡፡ የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ 2፡ 12 እስከ ምዕራፍ 3፡ 31 የሚሸፍን ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የሚያተኩረው የሰቆቃ ጩኸት ላይ ነው፡፡ የሰቆቃ ጩኸት የሚያሰማው ወይም ሙሾ የሚወርደው የእህል ሰብል፣ የወይን ተክልና የበለስ ዛፎችን በሙሉ ለማጥፋት በተከሰተው በአንበጣ መንጋ ምክንያት ነው፡፡ የሰቆቃው መራራነት ለመግለጽ ጸሐፊው በማኅበራዊ ሕይወትና በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ክስተቶችና ድርጊቶች ተጠቅሟል፡፡ አንበጦቹ መልካቸው ፈረስ እንደሚመስልና የሩጫቸውንም ፍጥነት እንደ ጦር ፈረስ እንደሆነ በመግለጽ የሰቆቃው ብርታት በማጠናከር ማንም ከዚህ ጥፋት መዳን እንደማይችል ያስገነዝባል፡፡ ይህ ጥፋት ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለከብቶችና ለዱር አራዊትም ጭምር መሆኑን በመግለጽ ሁሉም በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ያሳያል፡፡

የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል ዋና ትኩረቱ የሆነው በመጀመሪያው ክፍል ለነበረው ችግር መፍትሔዎችን በመፈለግ ነው(ኢዩ 2፡ 12 - 3፡ 31)፡፡ የመጀመሪያው ትኩረቱ የሆነውም በንስሓ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ምሕረትንና ይቅርታን አግኝቶ እግዚአብሔር ምድርን እንደገና በበረከት እንዲሞላው መማጸን ነው፡፡ ስለዚህ “ጹሙ፣ አልቅሱ፣ እዘኑ”፤ በማለት ምሕረት ከእግዚአብሔር ለማግኘት የመለወጥ ሂደት መጀመር እንዳለባቸው ለሕዝቡ ይነግራል፡፡ እዚህ ላይ የእግዚአብሔርን ደግነት፣ ቸርነት፣ መሐሪነት፣ አፍቃሪነትና ለቁጣ የዘገየ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ በሙሉ ከሕፃናት እስከ ሽማግሌ ሙሽሮችም ጭምር በመንፈሳዊ ስብሰባ እያለቀሱ እንዲጸልዩ ይቀሰቅሳል፡፡

ሌላው ከመጽሐፉ ለየት ባለ መልኩ መልእክት ማስተላለፊያ መንገድ ሆኖ ተደጋግሞ የምናገኘው ነገሮችን በዐዋጅ መልክ የመነገራቸው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ ነቢዩ ዐውጁ፣ መለከትን ንፉ፣ የጥሪ ድምጽ አሰሙ፣ አልቅሱ፣ ለልጆቻችሁ ንገሩ፣ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው ይንገሩ፣ እነርሱ ደግሞ ለሚከተለው ትውልድ ይንገሩ፣ ሕዝቡን ጥሩ የሚሉትንና እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙት ሌሎች ነገሮችን በተለያየ ጊዜ ደጋግሞ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ነቢዩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለው የነቢይነት መልእክቱን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ይህ መልእክት በከፍተኛ ድምፅ እንዲነገርና ሁሉም ሰምቶ በንስሓ እንዲመለስ ለማስገንዘብም ጭምር የተጠቀመበት ይመስላል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ ሁለት ክፍል ቢኖሩትም በጥንቅሩ ወጥነት የሚታይበት፣ የተፈጥሮ ክስተቶችን ለሕዝቡ ትምህርት ሰጪ በሆነና ወደ ንስሓ ለመጥራት በሚያስችል መልኩ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለበት፣ የእግዚአብሔር መሐሪነት የተንጸባረቀበትና ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል የተካተተበት እጥር ምጥን ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ እግዚአብሔር ብዙ ሠራዊቶች ያሉት ብርቱ ተዋጊ እንደሆነ እንዲሁም የኤደን አትክልት ቦታ እጅግ በጣም የለመለመና ያማረ ሆኖ እንደሚገኝ ይገልጻል(ኢዩ 2፡ 3፤ 2፡ 1)፡፡

  • በሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ ውስጥ ስለተከሰተው የአንበጣ መንጋና ስላደረሰው ከባድ የንብረት ውድመት ነቢዩ ኢዩኤል ምን እንዲደረግ ለሕዝቡ ይመክራል? ይህንን ጥፋት ካየ በኋላ ነቢዩ ኢዩኤል ችግሩን እንዴት አድርጎ ገለጸው?

በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል የአንበጣ መንጋ ባስከተለው ጥፋት ምክንያት በአገሪቱና በነዋሪዎችዋ የደረሰውን ሁሉ ነቢዩ ከተመለከተ በኋላ ሕዝቡ ይህንን የደረሰውን ጥፋት በደንብ እንዲገነዘብና ጩኸቱን ወደ እግዚአብሔር እንዲያደርግ ይቀሰቅሳል፡፡ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ የሰብል ማውደም ጥፋት ምክንያት ሁሉም የኅብረተሰቡ ክፍል እንዲያዝንና ወደ እግዚአብሔር ምርር ብሎ በማልቀስ እንዲማጸን ጥሪ ያቀርባል፡፡ እንደ ነቢዩ አገላለጽ ስንዴውና ገብሱ ሌላውም መከር ሁሉ ስለጠፋ ገበሬዎች ማዘን አለባቸው፡፡ ለእግዚአብሔር አምላካቸው የሚያቀርቡት የእህልም ሆነ የወይን ጠጅ መባ ስለሌለና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ደስታ ፈጽሞ ስለጠፋ በመሠዊያው የሚያገለግሉ ካህናት ማቅ ለብሰው ማዘን አለባቸው፡፡ የእህልም ሆነ የወይን ጠጅ መባ ከቤተ መቅደስ የጠፋውም ሰዎች ምርታቸው በሙሉ በአንበጣው መንጋ ስለወደመባቸው ካህናቶችም ቤተ መቅደስ ውስጥ የአገልግሎት ተግባራቸው ለመወጣት አልቻሉም(ኢዩ 1፡13-16)፡፡ የወይን ተክል ሁሉ ስለጠፋ የወይን ጠጅ መጠጣት የሚያዘወትሩ ሰካራሞች እንኳ ሳይቀሩ ምርር ብለው ማልቀስ አለባቸው፡፡ ይህ ጥፋት ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም ጭምር ስለተረፈ ከብቶች በመጨነቅ ይጮኻሉ፤ የበጎች መንጋ ሳይቀሩ ተርበው በብርቱ ሥቃይ ላይ ይገኛሉ፤ ወንዝና ምንጭ ሁሉ ስለደረቀባቸው የሜዳው ሣር ሁሉ ስለተቃጠለባቸው የዱር አራዊት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ ነቢዩም በደረሰው ነገር ሁሉ አዝኖ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል(ኢዩ 1፡ 4-20)፡፡

በአጠቃላይ ሕዝቡ ሁሉ በደረሰው ድርቅና በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጥፋት ስለተጠቃ ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይሆን ስለደረሰው ነገር ምርር ብሎ ማዘንና ጩኸቱን ለእግዚአብሔር ማሰማት እንዳለበት ነቢዩ ደጋግሞ ያስገነዝባል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ሕዝቡ ዋና የሕይወቱ መተዳደሪያ ግብርናና ከብት እርባታ ስለነበርና እነዚህም በድርቁና በአንበጣው መንጋ ክፉኛ ስለተጎዱ የሰውም ሆነ የእንስሳቶች የመኖር ተስፋ እጅግ በጣም መንምኖ ነበር፡፡ ይህንን ከመድረሱ በፊት በድሎት ይኖር የነበረው ሕዝብ ዛሬ በመከራ ውስጥ ይገኛል፤ ይህ የመከራ ጊዜ ቶሎ እንዲያልፍ ሕዝቡ መፍትሔ ፍለጋ ቀንና ሌሊት መሯሯጥ አለበት፡፡ ይህ መፍትሔ የሚገኘው ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ምላሽ በአፋጣኝ እንዲሰጥ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ተግባር አሁኑኑ መወጣት ይኖርበታል፡፡

  • ይህ አስፈሪ የሆነውና ንብረት በሙሉ ያወደመው የአንበጣ መንጋ እውነትም የአንበጣ መንጋ ብቻ ነው ወይስ ምሳሌአዊ አነጋገር ሆኖ ከበስተ ጀርባው ሌላ የተደበቀና ተጨማሪ የሆነ ትንታኔ አለው? 

በእርግጥ ይህን የአንበጣ መንጋ ወደፊት በአይሁዳውያን ላይ ባዕዳን አገራት ስለሚፈጽሙት ወረራ አስቀድሞ የሚናገር ነው በማለት አንዳንድ ሊቃውንት መላ ምታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ የአንበጣ መንጋ፤ እንደ ወራሪ ጦር፣ ጥርሱም እንደ አንበሳ ጥርስ ስለታም የሆነና መንጋጋውም እንደ ሴት አንበሳ መንጋጋ እንደሆነ ይናገራል(ኢዩ 1፡ 6)፡፡ ይህ ወራሪ ጦር ምንአልባት ባቢሎናውያን ወይም አሦራውያን አሊያም ሌሎች የይሁዳና የእስራኤል አጎራባች አገራት ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊቃውንት ይተነትናሉ፡፡ በእርግጥ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እነዚህ ባዕዳን ወራሪዎች የይሁዳንና የኢየሩሳሌም ተወላጆችን ከአገራቸው አርቀው በመውሰድ እንደሸጡአቸው ይገልጽና በዚህ ክፉ ተግባራቸው ምክንያት እግዚአብሔር እንደሚበቀላቸው፣ ልጆቻቸውም ለይሁዳ ሕዝብ አሳልፎ እንደሚሰጥ እስራኤላውያንና አይሁዳውያን ግን ነፃ እንደሚያወጣቸው ይናገራል(ኢዩ 3፡ 4-8)፡፡ በአጠቃላይ ትክክለኛ የአንበጣ መንጋ ይሁን ወይም ወደፊት እስራኤላውያንና አይሁዳውያንን ለመውረር ሊመጣ የሚችል የባዕዳን ጦር ነው የተባለው እንደ ነቢዩ ኢዩኤል አገላለጽ መነሻቸው የሕዝቡ ከእግዚአብሔር መራቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስና መታረቅ ችግሩን የመፍቻው ዋናውና ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡

  • ለደረሰው ችግር ሁሉ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ በነቢዩ የተነገረው የመፍትሔ አሳብ ምንድን ነው?

በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ ለተከሰተው ችግርና ለተጋረጠው የመከራ ማዕበል ዋናው መፍትሔ የሕዝቡ መጸጸትና ንስሓ በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ እንደሆነ ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ ሕዝብ በሙሉ የመለከት ድምፅ በተለይም እንደ ጽዮን ተራራ ባሉት በከፍተኛ ቦታ ላይ እየተነፋ ለመንፈሳዊ ስብሰባ ተጠርቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣት አለበት፡፡ ለዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ልጆችና ጡት የሚያጠቡ ሕፃናት እንዲሁም ሙሽራዎች ሳይቀሩ ከጫጉላቸው ወጥተው መገኘት ይኖርባቸዋል(ኢዩ 2፡16)፡፡ ቀጥሎም የጸጸት ጉዞ ዋናውና መጀመሪያ የሆነውን ጾም መታወጅና መተግበር አለበት፡፡ ሕዝቡ በፍጹም ልቡ ወደ እግዚአብሔር መመለሱን ለመግለጽ ማዘን፣ ማልቀስ፣ መጾምና መጸለይ አለበት፡፡ ነቢዩ የሕዝቡ ጾምና ጸሎት እውነተኛና ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበት ሲያሳስብ ልባችሁ እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ ቸር፣ ምሕረቱ የበዛ ነው፤ ፍቅሩ ዘላለማዊ የሆነና ለቁጣም የዘገየ ነው፤ ከመቅጣት ይልቅ ይቅርታ ለማድረግ ዘወትር የተዘጋጀ ነው  ይላል(ኢዩ 2፡13)፡፡ ነቢዩ በአገሪቱ ላይ የደረሰው ድርቅና የአንበጣ መንጋ እንደ እግዚአብሔር ቁጣ አድርጎ ስለወሰደው ይህ ቁጣ ተወግዶ ዳግመኛ የበረከት ሕይወት እንዲመለስ ዋናው ነገር የሕዝቡ መመለስና ምሕረት ለእግዚአብሔር መለመን ስለሆነ ደጋግሞ ሕዝቡንና ካህናቶችን በቤተ መቅደሱ በር መካከል ሆነው ሌሊቱን በሙሉ እያለቀሱ እንዲማጸኑ ያሳስባቸዋል(ኢዩ 1፡13፤ 2፡17)፡፡

  • ነቢዩ ኢዩኤል እግዚአብሔርን እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል ? ለነቢዩ ኢዩኤል እግዚአብሔር ማን ነው?

በመጀመሪያ ለነቢዩ ኢዩኤል እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱ የበዛ፣ ብዙ በረከት የሚሰጥ፣ ፍቅሩ ዘላለማዊ የሆነና ለቁጣም የዘገየ  አምላክ ነው፡፡ ይህ አምላክ ከመቅጣት ይልቅ ይቅርታ ለማድረግ ዘወትር የተዘጋጀ፣ የሚታዘዙለት ብዙና ብርቱ ሠራዊቶች ያሉት፣ ድምፁ የሚያስፈራ፣ በሰማይና በምድር ድንቅ ነገሮች የሚያከናውን አምላክ ነው፡፡ በተጨማሪም ተራራዎች ሁሉ በወይን ተክል እንዲሸፈኑ የሚያደርግ፣ ኮረብታዎችም ላይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ከብቶች እንዲሠማሩ የሚፈቅድ አባት ነው፡፡ ከዚህም በላይ በምድር የሚገኙ ወንዞች ሁሉ በውሃ የተሞሉ የሚያደርግ፣ በቤተ መቅደስም ምንጭ የሚያፈልቅና በቁጣው እንደ ጦር ሠራዊት የበዙ የአንበጣ መንጋዎች የሚልክ አምላክ ነው(ኢዩ 1፡11 እና 2፡24-25)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ መሆኑን ነቢዩ ይናገራል(ኢዩ 2፡18)፡፡ ቀናተኛነቱም ስለምድሪቱና ስለ ሕዝቦችዋ ባለው ፍቅርና ወዳጅነት የተመሠረተ ነው፡፡

ስለዚህ ሕዝቦቹ ከፊቱ ሲሸሹና ወደ ሌላ ጎዳና ሲያመሩ ከተሳሳተው ጉዞአቸው ተመልሰው በጸጸትና በንስሓ ዳግመኛ ወደ ቤቱ ይመለሱ ዘንድ መንገዶችን ያመቻችላቸዋል፡፡ በሕዝቡም ላይ በደል ሲደርስ በፍጥነት ምላሽ በመስጠት ሕዝቡን ይታደጋል፡፡ ስለዚህ አሁንም የደረሰው ድርቅና የአንበጣ መንጋ ጥፋት አስወግዶ በድጋሚ እህል፣ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት እስኪጠግቡ ድረስ ይለግሳቸዋል፡፡ ከሰሜን የሚመጣውም የአንበጣ መንጋ አርቆ ወደ በረሓና ወደ ምድረ ባዳ ያባርራቸዋል፡፡ የምድር እንስሳት የሚሠማሩበት መስኮችም ያለመልማል፤ ዛፎችም ያፈራሉ፤ የበለሱና የወይኑ ፍሬ እጅግ የበዛ ይሆናል፡፡ በሕዝቡም የደረሰውን ጥፋት ለመካስ በበጋና በክረምት ወራት በቂ ዝናም ይሰጣል፡፡ ሕዝቡ እስከሚጠግቡ ድረስ የሚበሉትን ብዙ ምግብ ይለግሳቸዋል፤ ሕዝቡ ከእንግዲህ ወዲህ ሐፍረት አይደርስባቸውም፡፡ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ምርኮ ይመልሳል፤ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ አውርዶ ስላደረሱት በደል ሁሉ ይፈርድባቸዋል(ኢዩ 2፡19-27፤ 3፡1-2)፡፡

  • ነቢዩ ኢዩኤል ስለ ታላቁና አስፈሪው የጌታ ቀን ይናገራል፡፡ ለመሆኑ ይህ ቀን ምን ዓይነት ተግባር የሚከናወንበት ቀን ነው ? ቀኑስ ለምን አስፈሪ ተባለ?

ነቢዩ ኢዩኤል የጌታ ቀን እንደሚመጣ እንዲያውም እንደደረሰና ይህ ቀን ደግሞ የፍርድና እጅግ በጣም አስፈሪ ቀን እንደሚሆን ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በዚያች ቀን እግዚአብሔር  ሠራዊቱን በአስፈሪ ድምፅ እያዘዘ ወደ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ በአሕዛብ ላይ ለመፍረድ ይመጣል(ኢዩ 2፡11፤ 3፡12)፡፡ ኢዮሳፍጥ በዕብራይስጥእግዚአብሔር ይፈርዳልማለት ነው፡፡ይህ ሸለቆ የት እንደሚገኝ በትክክል ማወቅ ባይቻልም ብዙ ሊቃውንትና የሥነ ቁፋሮ አጥኚዎች ኢዮሳፍጥ ኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙት ሸለቆዎች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ከስሙ ትርጓሜ እንደምንረዳው እስራኤላውያን በተለምዶ እግዚአብሔር እዚያ ቦታ ላይ ይፈርዳል ብለው ያምኑ እንደነበር ነው፡፡ነገር ግን ይህ ቀን ከመምጣቱ በፊት ብዙ ድንቃ ድንቅ ነገሮች በሰማይና በምድር ላይ ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህም ነገሮች ውስጥ ደምና እሳት፣ የጢስ ዐምድም ይታያል፡፡ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች፤ ከዋክብትም ብርሃናቸው ያጣሉ(ኢዩ 2፡ 30-31፤ ኢዩ 3፡15)፡፡ ቀጥሎም በታላቁ የፍርድ ቀን ሕዝቦቹንና አሕዛብን በሙሉ ተሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፡፡ በዚህ የፍርድ ቀን አሕዛብ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በደል ስላደረሱ ይፈረድባቸዋል፡፡ አሕዛቦች ከሚፈረድባቸውም ምክንያቶች ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በአሕዛብ መካከል መበተናቸው፣ የእስራኤልን ምድር ተከፋፍለው ስለያዙ፣ የማረኩአቸውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለመከፋፈል ዕጣ መጣጣላቸው፣ አመንዝራ ሴቶች ለማግኘት ወንዶች ልጆች መስጠታቸውና ወይን ጠጅ ለመጠጣት ሴቶች ልጆችን ባሪያ አድርገው መሸጣቸውን ይገኙበታል(ኢዩ 3፡ 2-3)፡፡

በዚህች ታላቅ ቀን የሚከናወነው ፍርድ በእስራኤላውያን ላይ መደረግ አለመደረጉ ነቢዩ ምንም የገለጸው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም በዚህች ቀን ሰማይና ምድር ሲናወጡ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ ለእስራኤል መጠጊያ ምሽግ እንደሚሆን ያረጋግጣል(ኢዩ 3፡16)፡፡ በተጨማሪም በዚያች በጭንቅና በፍርድ ቀን የእግዚአብሔር ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ ጌታም የመረጣቸው ሁሉ ይድናሉ(ኢዩ 2፡ 32)፡፡ ይህች ቀን የእግዚአብሔር ሕዝቦች እግዚአብሔር በመካከላቸው እንዳለ፣ እርሱ ብቻ አምላካቸው እንደሆነና ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ዓይነት ሐፍረት የማይሰማቸው መሆኑን የሚያረጋግጡበት ቀን ይሆናል(ኢዩ 2፡ 27)፡፡ ከዚህም በላይ እግዚአብሔር መንፈሱን በሰው ሁሉ ላይ ያፈሳል፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትንቢት ይናገራሉ፣ ሽማግሌዎች ሕልም ያልማሉ፣ ወጣቶችም ራእይ ያያሉ፣ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቹ ላይ መንፈሱን ያፈሳል(ኢዩ 2፡ 28-29)፡፡ በአጠቃላይ ይህ ቀን ለአሕዛቦች የፍርድ ቀን ሲሆን እግዚአብሔርን አምነው ጉዞአቸውን ላደረጉት ደግሞ የነጻነትና የመዳን ቀን ይሆናል፡፡

  • ትንቢተ ኢዩኤል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተሰቅሶአልን? ከተጠቀሰ በየትኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ትንቢተ ኢዩኤል በተለያዩ ቦታዎች ቢጠቀስም ዋናው ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን ነው፤ ይህም እግዚአብሔር መንፈሱን በሰው ሁሉ ላይ ስለማፍሰሱን የተናገረውንና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚገኘውን ነው(ኢዩ 2፡28 ፤ ሐዋ 2፡17-21)፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሰው ሁሉ ላይ ወርዶ ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታው ታላቅ ሊሆን እንደሚችልና በአጽንኦትም ይመኝ እንደነበር ገና ድሮ ሙሴ ተናግሮ ነበር(ዘኁ 11፡29)፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ግን ይህንን በነቢዩ ኢዩኤል ተነግሮ የነበረውን የትንቢት ቃል በጰራቅሊጦስ ዕለት እንደተፈጸመ ይመሰክራል፡፡ በሌላ መልኩ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ደኅንነት ለሁሉም እንደሆነ ሲገልጽ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚለውን የትንቢተ ኢዩኤልን ቃል በመጥቀስ ያስተምራል(ኢዩ 2፡ 32፤ ሮሜ 10፡13)፡፡ በአጠቃላይ ትንቢተ ኢዩኤል በውስጡ ባካተታቸው ትምህርቶች በተለይም እግዚአብሔር መንፈሱን በሁሉም ሰው እንደሚያፈስ በመግለጹ ምክንያት በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችና አንባቢዎች ዘንድ ከታወቁት የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ሆኖ ይገኛል፡፡

    

ትንቢተ አብድዩ

  • ነቢዩ አብድዩ ማን ነው? የትና መቼ ተወለደ? የነቢይነት የአገልግሎት ተግባሩን የተወጣው የትና መቼ ነው?

አብድዩ የሚለው ስም በሰባ ሊቃውንት (ሴፕቱአጂንት) አማካኝነት ኦባድያ ከሚለው ከዕብራይስጥ ቃል የተተረጐመ ስም ነው፡፡ ኦባድያ “ኤቬድ” እና “ያህ” የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ነው፡፡ ይህም በዕብራይስጥ “ኤቬድ” አገልጋይ “ያህ” ወይም “ጃህ” የእግዚአብሔር መጠርያ ስሞች ከሆኑት አንዱ ሲሆን አብድዩ ማለት ደግሞ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ አብድዩ ከየትኛው አካባቢ፣ ከየትኛው ወገን፣ የማን ልጅ እንደሆነ፣ የግል ቤተሰባዊ ሕይወቱ ምን እንደሚመስል አይጠቀስም፡፡ መጽሐፉ ውስጥ የነቢይነት ተግባሩን መቼና በማን ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደተወጣም  የሚገልጽ ምንም ዓይነት መረጃ የለም፡፡

  • ትንቢተ አብድዩ ጥንቅሩና ይዘቱ ምን ይመስላል ? የመጽሐፉ ወይም የትንቢት ቃሉ ዋና ትኩረት ምን ላይ ያደረገ ነው?

ትንቢተ አብድዩ በአንድ ምዕራፍ ብቻ የተጠቃለለና ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በእጥረቱ የታወቀ ትንሽ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ትኩረት ሰጥቶ የሚናገረው ስለ አንድ ፍሬ ሀሳብ ብቻ ነው፤ ይህም በወቅቱ የይሁዳ ጠላት ስለነበረችው ስለ ኤዶም ነው፡፡ ኤዶም ዔሳው የተሰየመበት ስም ነው፡፡ይህንንም ሊያገኝ የቻለው ከአደን ደክሞ ሲመለስ ወንድሙ ያዕቆብ ያዘጋጀውን ቀይ ወጥ በመመኘቱና ብኩርናውን በመሸጥ ገዝቶ በመብላቱ ነው (ዘፍ 2530)፡፡ኤዶማውያንም ከዔሳው የተገኙ በኤዶም ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው (ዘዳ 237)፡፡በኤዶም ስለኖሩ ኤዶማውያን ተብለዋል፡፡ዔሳው ወደ ሴይር ከገባ በኋላ የዔሳው ዘር ዋና ሕዝብ ሆነ (ዘፍ 36ዘዳ 212)፡፡በያዕቆብና በወንድሙ በዔሳው መካከል የነበረውን የጥላቻ ወይም ያለመግባባት መንፈስ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ በይሁዳና በኤዶም ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የራሱ የሆነ የጥላቻ መንፈስ ሊፈጥር እንደቻለ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ በዚህ አጭር ምዕራፍ ውስጥ ዔሳውን በመጥፎ ዕይታ ደጋግሞ ይጠቅሰዋል(ቁ. 6፡8, 9፡18፡21)፡፡ ኤዶም በጠንካራ አለት በተመሸገ ከተማ ውስጥ የነበረና ቤቶቹም በከፍተኛ ተራራዎች ላይ የተሠሩ እንደነበር ከመጽሐፉ እንረዳለን(ቁ. 3-4)፡፡ ከነዋሪዎችዋም ውስጥ ጥበበኞችና ጀግኖችም እንደነበሩም ጭምር ተገልጿል(ቁ. 8-9)፡፡ 

ጸሐፊው ኤዶምን ለመውቀስና ውድቀቷን ለመግለጽ የተለያዩ ቃላትና አገላለጾች ተጠቅሟል፡፡ የኤዶምን ክፋት ሲገልጽ ትዕቢት፣ ሌቦችና ቀማኞች፣ የተጠሉ የዔሳው ዝርያዎች፣ ከዳተኞች፣ ዘራፊዎች፣ ደባ ፈጻሚዎች፣ አሳዳጆችና በሰው ውድቀት የሚደሰቱ ክፉዎች አድርጎ ይገልጻቸዋል፡፡ ይህንን ክፋታቸው ከገለጸ በኋላ የሚገባቸው ቅጣት ምን መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት ኤዶማውያን እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ታናሽ እንደሚያደርጋቸው፣ በጠላቶቻቸው እንደሚጠፉ፣ ሀብታቸው በሙሉ እንደሚዘረፍ፣ ቀድሞ የነበረው ዕውቀቱ እንደሚከዳው፣ ጥበበኞቹም እንደሚጠፉ፣ እንደሚዋረዱ፣ እንደ ገለባ በእሳት አንደሚቃጠሉና ብዙ መከራ እንደሚደርስባቸው ይገልጻል፡፡ በዚህም ጸሐፊው ለኤዶማውያን ምን ያህል ጥላቻ እንደነበረው በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ በኤዶም ላይ ስለሚደረገው ፍርድ(ቁ. 1-9)፣ የኤዶማውያን ቂምና ጭካኔ(ቁ. 10-14) እንዲሁም በኤዶማውያንና በአሕዛብ ላይ ስለሚደረገው ፍርድ በድጋሚ ያትታል(ቁ. 15-21)፡፡

  • ነቢዩ አብድዩ ለምን በኤዶማውያን ላይ ስለሚመጣው የቅጣት ትንቢት ተነበየ?

እንደ ነቢዩ አብድዩ አገላለጽ ኤዶማውያን በወንድሞቻቸው አይሁዳውያን መከራና ጉስቁልና መደሰት ብቻ ሳይሆን ከአሳዳጆቻቸውን በመሸሽ ሲደበቁ የነበሩትን አይሁዳውያንን አድብቶ በመያዝ፣ ሀብታቸው በመውረስና ከጠላቶቻቸው ጋር በመተባበር ግፍ ፈጽመውባቸዋል(ቁ.10-11)፡፡ ዔሳው ብኩርናውን ለያዕቆብ በምስር ወጥ የሸጠ ስለሆነ ዘሮቹም የያዕቆብ ዘሮች አገልጋይ መሆንና ዝቅ ማለት የሚገባቸው እንደሆኑ አብድዩ ያምናል(ዘፍ 25፡34)፡፡ በእርግጥ ዔሳውና ያዕቆብ ገና በእናታቸው በርብቃ ማሕፀን ውስጥ እያሉ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም ለርብቃ በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስበርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል ብሏት ነበር(ዘፍ 25፡23)፡፡ ይህንን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ጥንታዊ ትውፊት ወይም እምነት በነቢዩ አብድዩ ጊዜ በይሁዳና በኤዶም ላይ የነበረ ነው፡፡

እንደ አብድዩ የትንቢት ቃል የእስራኤል ብቻ ሳይሆን አሕዛብንም ጭምር የሚገዛውና የሚፈርደው እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ የሚፈርድበት ጊዜ ስለደረሰ ኤዶም በሌሎች ላይ ያደረገውንና የፈጸመውን ግፍ በእርሱም ላይ እንደሚፈጸምበት ይናገራል(ቁ.15-16)፡፡ የመከራ ጽዋ ሲጠጡ የነበሩት የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑት አይሁዳውያን ግን የራሳቸውን የሆነውን ርስት ይወርሳሉ፤ ከራሳቸውም አልፈው የኤዶምንም ርስት ይወርሳሉ፤ ኤዶምንም ይገዛሉ፤ የከነዓንን ምድር እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳሉ፤ ጽዮንም የተቀደሰች ትሆናለች(ቁ.15-21)፡፡ በዚያን ጊዜ የኤዶም ጥበበኞች ይጠፋሉ፤ ዕውቀታቸውም እንዳልነበረ ይሆናል፤ ጀግኖችዋም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ (ቁ. 8-9)፡፡ በአጠቃላይ ነቢዩ ለኤዶም ከባድ ጥላቻ እንደነበረውና እንድትጠፋም በጽኑ ምኞቱ እንደሆነ “ትዋረዳለህ፤ ለዘላለም ጠፍተህ ትቀራለህ” ከሚለው የትንቢት ቃሉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

  • ነቢዩ አብድዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደፊት ስለሚወርሱት በረከት ይናገራል፤ ለመሆኑ የሚወርሱት በረከት ምንድን ነው?

በመጽሐፉ ሁለተኛና የመጨረሻው ክፍል ውስጥ ነቢዩ አብድዩ ከጥፋት ስለሚያመልጡ ሕዝበ እግዚአብሔር በተለይም ስለ ያዕቆብና ዮሴፍ ሕዝቦች፣ ስለ ጽዮን፣ ስለ ኢየሩሳሌም ሰዎችና ስለ ንጉሣቸው ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት ጽዮን የተቀደሰች እንደምትሆን፣ በስደት ላይ የነበሩት የሰሜን እስራኤል ሕዝብ ተመልሰው የከነዓንን ምድር እስከ ሰራጵታ ድረስ እንደሚወርሱና እግዚአብሔር ራሱ ንጉሣቸው እንደሚሆን ይተነብያል፡፡ በተጨማሪም የያዕቆብ ሕዝብ እንደ እሳት፣ የዮሴፍ ሕዝብ እንደ ነበልባል ሆነው የዔሳው ዝርያ የሆኑትን ኤዶማውያንን ያጠፋሉ፤ የኢየሩሳሌም ሰዎች በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው ኤዶምን ይገዛሉ፤ እስራኤላውያን የኤፍሬምና የሰማርያን ግዛት ይወርሳሉ፤ የብንያም ሰዎችም የገለዓድን ምድር እንደሚወርሱ የትንቢት ቃሉ ይናገራል፡፡ 

ከነቢዩ አብድዩ መልእክት በእርግጥ ለመረዳት የሚያስቸግር ነገር እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ይህም በመጀመርያ የእስራኤልና የይሁዳ ጠላት፣ ወራሪና ዋና ዘራፊ የነበረው ኤዶም ሳይሆን ባቢሎን ነበር፡፡ የተግባሩ ዋና ተዋናይና የጥፋቱ ዋና ተጠያቂ የነበረው ባቢሎን መቀጣት ሲኖርበት ለምንድንነው ነቢዩ ዋናው ትኩረቱን ወደ ኤዶም ያዞረው? ኤዶም ተሳታፊነቱ በተወሰነ መልኩ ሆኖ እያለ ለምን በዋና ተጠያቂነት ተፈረጀ?

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1 - ከሚከተሉት ውስጥ የነቢዩ ኢዩኤል ማንነት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክል የሆነውን የትኛው ነው?

ሀ) መጽሐፉ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው ወይም በአምስተኛው ምእተ ዓመት ገደማ ሊጻፍ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለ) ነቢዩ ወደፊት ይመጣል ብሎ የተነበየው ጥፋት ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ነበር፡፡ ሐ) የነቢዩ ዋና ትኩረት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለው የነቢይነት መልእክቱን ማስተላለፍ ላይ ብቻ ነበር፡፡ መ) ኢዩኤል የነቢይነት አገልግሎቱን የተወጣው ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲሆን መልእክቱም በወቅቱ ወራሪዎችን በመፍራት በስጋት ይኖሩ ለነበሩት ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ነበር፡፡ ሠ)መጽሐፉ ሁለት ክፍል ያሉት ሲሆን በጥንቅሩ ወጥነት አይታይበትም፡፡

2 - ነቢዩ ኢዩኤል ከተናገረው ስለ አንበጣ መንጋ፣ ስለ ችግሩ አሳሳቢነታና ስለ መፍትሔው ትክክለኛው የትኛውን ነው?

ሀ)የአንበጣ መንጋ ጥፋት ቢያደርስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ደስታ ፈጽሞ አልጠፋም፡፡ ለ)እንደ ነቢዩ አገላለጽ በአገሪቱ ላይ የደረሰው ድርቅና የአንበጣ መንጋ የተፈጥሮ ክስተት ውጤት ነው፡፡ ሐ)ሕዝቡ ልብሳቸውን እየቀደዱ መጾምና መጸለይ አለባቸው፡፡ ሐ)ስለ ተከሰተው ድርቅና የአንበጣ መንጋ ዋና መፍትሔው መሬቱን ቶሎ ማረስና መዝራት ነው፡፡ መ)በአገሪቱ በተከሰተው የድርቅና የአንበጣ ወረራ ምንም ያልተጨነቁትና አሳብ ያልገባቸው ሰካራሞች ብቻ ነበሩ፡፡ ሠ) በአንበጣ መንጋ ምሳሌነት የተነገረው ምንአልባት ባቢሎናውያን ወይም አሦራውያን አሊያም ሌሎች የይሁዳና የእስራኤል ተቀናቃኝና ጠላት የሆኑ አጎራባች አገራት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

3 - የነቢዩ ኢዩኤል የትንቢት ቃል በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?(ይህንን ለመመለስ ሦስቱም ምዕራፎች በሚገባ ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ)እግዚአብሔር ስለምድሪቱ ባለው ቅንአት ለሕዝቡ ይራራል፡፡ ለ) አንበጦቹ ለጦርነት እንደተዘጋጀ ብርቱ ሠራዊት በሰልፍ ይተማሉ፡፡ ሐ)በመጨረሻም ይሁዳና ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር ሕዝብ መኖሪያ መሆናቸው ያበቃል፤ እግዚአብሔር ራሱ ከጽዮን ተራራ ይሰወራል፡፡ መ)እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱ የበዛ፣ ፍቅሩ ዘላለማዊ የሆነና ለቁጣም የዘገየ፣ ከመቅጣት ይልቅ ይቅርታ ለማድረግ ዘወትር የተዘጋጀ ነው፡፡ ሠ) በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር መንፈሱን በሰው ሁሉ ላይ ያፈስሳል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትንቢት ይናገራሉ፡፡

4 - የነቢዩ አብድዩ ማንነት፣ የነቢይነት አገልግሎቱ፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) ትንቢተ አብድዩ ኤዶምን ለማገስና በእግዚአብሔር የተወደደች ከተማ መሆንዋን ለመግለጽ የተጻፈ ነው፡፡ ለ)አብድዩ የሚለው ስም “የእግዚአብሔር ተወካይ” በሚል ይተረጐማል፡፡ ሐ)ወደፊት የኢየሩሳሌም ሰዎች በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው ኤዶምን ይገዛሉ፤ እግዚአብሔር ራሱ ንጉሥ ይሆናል፡፡ መ)ኤዶማውያን የያዕቆብ ዘሮች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ሠ)አይሁዳውያን በጠላት በተከበቡ ጊዜ ኤዶማውያን  ብዙ መልካም ነገሮች በማድረግ ሊረዱዋቸውና ሊተባበሩዋቸው ተነሳሡ፡፡

5 - ከትንቢተ አብድዩ ከቁ. 10 እስከ ቁ. 14 ባለው ክፍል ውስጥ የኤዶም ጥፋት ናቸው ተብሎ ከተጠቀሱት መካከል ሦስቱን ጥቀስ፡፡ (አስተውል፦ ትንተ አብድዩ አንድ ምዕራፍ ብቻ ስለሆነ ቁጥሩ ብቻ ነው የሚጠቀሰው)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከቁ. 17 እስከ ቁ. 21 ባለው ክፍል ውስጥ ጽዮን፣ የያዕቆብ ሕዝብና የኢየሩሳሌም ሰዎች ምን ይሆናሉ ተብሎ ተገልጿል?

-   

-   

-   

-   

-   

-   

6 - ትንቢተ ኢዩኤል 2፡ 28-32 እና ሐዋርያት ሥራ ውስጥ ሐዋ 2፡ 14-24 በሚገባ መነበብ ይኖርበታል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ትንቢተ ኢዩኤል ውስጥ የተነገረውን በመጥቀስ በጰራቅሊጦስ ወይም በጰንጤቆስጤ ዕለት ለተሰበሰበው ሕዝብ ይናገራል፡፡ የሚናገረውም የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰው ላይ እንደወረደ ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንዳደረባቸው ራእይ በማየት፣ ትንቢት በመናገር፣ በማስተማር በመመስከርና የተለያየ ተግባራት በማከናወን አሳይተዋል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ አንድ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ውስጥ አለ፤ ወይም የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ነኝ፤ ወይም ሕይወቴ የሚመራው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው ብሎ በድፍረት የሚናገር ከሆነ መገለጫው ምን መሆን አለበት? ማለትም የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ የሆነ ሰው መንፈሱ በውስጡ የሚሠራ መሆኑን እንዴት ሊታወቅ ይችላል? ወይም በቀላሉ ለመግለጽ ያህል፦ እያንዳንዳችን ሕይወታችን ቆም ብለን ስናየው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣዊ ሕይወት ካለ እንዴት ነው መኖሩንና መሥራቱን የሚታየው?      

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት