እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፰ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ አሞጽ)

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሃያ ስምንት) - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት

ትንቢተ አሞጽ

  • amos by NaomiFriend comአሞጽ ተወልዶ ያደገው፣ የነቢይነት አገልግቱ የተወጣውና መቼና የት ነው? ቤተሰባዊ ሕይወቱስ ምን ይመስል ነበር?

ነቢዩ አሞጽ ይሁዳ ውስጥ ከምትገኝ ተቆዓ በመባል ከምትጠራ አንዲት መንደር የተገኘ ነቢይ ነው፡፡ አሞጽ በይሁዳ ከምትገኝ መንደር ይገኝ እንጂ የነቢይነት መልእክቱን ያስተላለፈው ለሰሜናዊው ግዛት ወይም ለእስራኤል ነው፡፡ ይህንንም መረዳት የሚቻለው መጽሐፉ ውስጥ ከሚጠቅሳቸው ቦታዎች በተለይም እንደ ሰማሪያና ነዋሪዎችዋ ያሉትን በትንቢት ቃሉ ውስጥ በተደጋጋሚ ስለሚገኙ ነው፡፡ አሞጽ በነቢይነት ያገለገለው ለሁለት ዓመታት ያህል ሲሆን ይህም ዳግማዊ ኢዮርብዓም በንጉሥነት እስራኤልን ይመራ በነበረበት(783-746 ዓ.ዓ) ወቅት ነው(አሞ 1፡ 1)፡፡ አሞጽ እንደ ነቢያት ልጆች ወይም ወገኖች ቤተ መቅደስ ወይም ከነቢያቶች ጋር በቅርበት አላደገም፡፡ ለነቢይነት ከመጠራቱ በፊት የበግ መንጋ ጠባቂና የዋርካ ፍሬ ለቃሚ ነበር(አሞ 7፡ 14)፡፡ ይህም ቢሆን የነቢይነት መልእክቱን ለሕዝቡና ለመሪዎቻቸው በሚገባ ከማስተላለፉም በላይ ከዐሥራ ስድስቱ ነቢያቶች ሁሉ ቀደምት ነቢይ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡

አሞጽ በነቢይነት ያገለገለበት ወቅት ለእስራኤልና ለይሁዳ የብልጽግና ጊዜ፣ ጥቂት የሆኑ ነዋሪዎችም የፈለጉትን ነገር ሁሉ ከሚገባ በላይ በግፍና በብዝበዛ መልክ ሰብስበው በድሎትና በቅንጦት የሚኖሩበት ጊዜ ስለነበር በማኅበረሰቡ ውስጥ ኢፍትሐዊነት የሰፈነበት፣ ድኾች በሀብታሞች የተጨቈኑበትና በሃይማኖትም ግብዝነት የተሞላበት ጊዜ ነበር፡፡ በተጨማሪም ግብረገብነት ጠፍቶ አመንዝራነት፣ ሌብነት፣ የጣዖት አምልኮና የመሳሰሉትን የተስፋፋበት እንዲሁም ደካሞች በብርቱዎች የሚንገላቱበት ወቅት ነበር(አሞ 2፡ 7)፡፡ ሕዝቡ ምንም እንኳ ሃይማኖቱ ይተገብር የነበረ ቢሆንም በአኗኗሩ ግን ከእግዚአብሔር ትእዛዛት የራቀና በኃጢአት የተዘፈቀ ነበር(አሞ 2፡ 8፤ 5፡ 21-23)፡፡ አሞጽ ይህንን አውግዞ በመናገሩ ምክንያት እንደነ ቤቴል ያሉት የእስራኤል ከተሞችና የማምለኪያ ቦታዎች ውስጥ ትንቢት እንዳይናገር ከመታገዱም በላይ እስራኤልን ለቆ ወደ ትውልድ አገሩ ይሁዳ እንዲሄድ በካህኑ አማጽያና በንጉሥ ኢዮርብዓም ትእዛዝ ተሰጠው(አሞ 7፡ 10-17)፡፡ በዚህም ምክንያት በካህኑ አማጽያና በቤተሰቡ ላይ ወደፊት ውርደትና ሽንፈት እንደሚመጣ ተነበየ(አሞ 7፡ 16-17)፡፡ አሞጽ ስለ ራሱ ሕይወት “የመንጋዎች እረኛና የሾላ ፍሬ ለቃሚ” ከመሆኑ ውጪ ስለ ቤተሰቡ ሕይወት ምንም የሚናገረው ነገር ስለሌለ ከነቢይነት አገልግሎቱ ውጪ ስለ ግል ሕይወቱ ምንም ነገር አይታወቅም፡፡

  • የትንቢተ አሞጽ ጥንቅርና ይዘት ምን ይመስላል? የአጻጻፍ ዘይቤውና የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ምን ላይ ነው?

መጽሐፉ ገና ከመጀመሪያው ትኩረት ሰጥቶ ለመግለጽ የሚሞክረው በእስራኤል ዙሪያ ባሉት አገራት፣ በይሁዳ፣ እንዲሁም በእስራኤል ሕዝቦች ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ነው(አሞ 1-2)፡፡ ይህ ፍርድ ነቢዩ ሲያስተዋውቅ ወጥ በሆነ መልኩ በያንዳንዱ ክፍል መጀመሪያ ላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ብሎ ይጀምርና እያንዳንዱ አገር ቀድሞ ያደረጉት በደልና ዐመፅ ካስገነዘበ በኋላ ወደፊት በቅጣት መልክ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጥፋት ያስገነዝባቸዋል፡፡ ከእነዚህም አገራት ውስጥ ሶርያ፣ ፍልስጤም፣ ጢሮስ፣ ኤዶም፣ ዐሞን፣ ሞአብ፣ ይሁዳና እስራኤል ይገኙበታል፡፡ ይህንን ውድቀትና ፍርድ ላይ ያተኮረው የመጀመሪው ክፍል የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችውና በወቅቱ በቅንጦትና በድሎት በሚኖሩ ሰዎች የተሞላችውን ሰማርያ የመውደቂያዋ ጊዜ መዳረሱን በመተንበይ ነው(አሞ 3)፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሁለተኛ ክፍል ዋና ትኩረቱ ያደረገው የእስራኤል ሕዝብና መሪዎች ኃጢአት ላይ ነው(አሞ 4-6)፡፡ በዚህ ክፍል የተለያዩ ይዘት ያላቸው መልእክቶች ለእስራኤል ሕዝብና መሪዎች እያስተላለፈ ወደ ንስሓ የሚመለሱበትን መንገድ ያሳያቸዋል፡፡

ነቢዩ በሁለተኛው ክፍል የንስሓ ጥሪ ካሰማ በኋላ በሦስተኛውና በመጨረሻው ክፍል በእስራኤል ሕዝብ ስለሚመጣው ጥፋት ያትታል፡፡ ነቢዩ አሞጽ በቋንቋው ጥራት፣ ጥሩ የሆነ የአጻጻፍ ስልት በመጠቀም፣ በምሳሌዎችና በአነጋገር ዘይቤዎች አጠቃቀም ጥበብ እንዲሁም በነገሮች አገላለጽ ችሎታው በብዙዎቹ ይደነቃል፡፡ ሌላው አሞጽ ለየት የሚያደርገው የሚጠቀምበት የንግግር ዘይቤ ቀጥተኛ ወይም አድማጩን ፊት ለፊት እንደሚያነጋግር ተናጋሪ ነቢይ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ የሰማሪያ ሴቶችን ሲናገር እንደ ባሳን ቅልብ መሲናዎች ሰውነታችሁን ያወፈራችሁ የሰማርያ ሴቶች ሆይ በማለት በቀጥታ ይወቅሳቸዋል(አሞ 4፡ 1)፡፡ ሌላው መጽሐፉ ውስጥ በትእዛዛት መልክ በነቢዩ የሚነገሩ ወይም የሚሰጡ የሕይወት መመሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ነቢዩ ሕዝቡንና መሪዎቻቸውን በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉ ነገር አታድርጉ፤ ክፉውን ነገር ጥሉ፤ መልካም የሆነውን ነገር ውደዱ እያለ የሚያስተላልፈው ግብረ ገባዊነት ያለው መልእክት ነው፡፡

በአጠቃላይ መጽሐፉ በጥሩ ሁኔታ የተጠናቀረ፣ በወቅቱ የነበረውን ችግር የሚዳስስና ለመፍታት የሚሞክር ከመሆኑም በላይ የነቢይነት መልእክቱ ለማስተላለፍ ተፈጥሮንና በውስጥዋ ያሉት ፍጥረታትን በሚገባ ጥቅም ላይ ያዋለ መጽሐፍ ነው፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ ግልጽ የሆነ መልእክት የያዘ ሲሆን ስለ ጸሐፊው ማንነት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ያላስከተለ ነው፡፡ ይህም ማለት ይህ መጽሐፍ በትክክል በአሞጽ መጻፉን ሁሉም ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ በእርግጥ ይህ በምንልበት ጊዜ የመጨረሻው እንደ መደምደምያ ሆኖ የቀረበውን የእስራኤል ሕዝብ የመመለስ ተስፋ ሳያካትት ነው(አሞ 9፡ 13-15)፡፡

  • ነቢዩ አሞጽ ስለ ፍትሕ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ይታወቃል፤ ፍትሕ ለነቢዩ አሞጽ ምን ማለት ነው? ለምንስ ስለ ፍትሕ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይናገራል?

ነቢዩ አሞጽ በኖረበት ማኅበረሰብ ውስጥ ፍትሕ የተጓደለበት፣ በአገሪቱ ሀብት ክፍፍል አድሎአዊነት የነገሠበትና ጥቂት ሀብታሞች ብቻ ተንደላቀው የሚኖሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ነቢዩ አሞጽ ይህንን ጥቂቶቹን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገውን በመቃወም ፍትሕ እንደ ምንጭ ውሃ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ ይፍሰስ በማለት ደጋግሞ ይናገራል(አሞ 5፡ 24)፡፡ በእርግጥ ነቢዩ በኖረበት ወቅት ድኾች በሀብታሞች የሚበዘበዙበት፣ ምስኪኖች በባርነት ተሽጠው ሌሎችን ለማገልገል የሚገደዱበት፣ አራጣ አበዳሪዎች የተንሰራፉበት፣ በሐሰተኛ ሚዛን በመጠቀም ማታለል የበዛበት፣ በአጠቃላይ ጥቂቶች በምቾት በመኖር ብዙዎቹ ደግሞ በድኽነት የሚማቅቁበት ወቅት ነበር፡፡ በተጨማሪም ጉቦኝነት የተንሰራፋበት፣ ደጋግ ሰዎች የሚጨነቁበት፣ ሀብታሞች ጉቦ እየሰጡ ፍትሕን የሚያጣምሙበት እንደነበር ነቢዩ ይናገራል(አሞ 5፡ 12)፡፡ ነቢዩ አሞጽ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉት ጥቂቶች በብዙኃኑ ላይ ስሚፈጽሙት ግፍ ሲናገር የድኾችን መብት ረገጣችሁ፤ እህላቸውንም ቀምታችሁ ወሰዳችሁ፤ ከጥርብ ድንጋይ ቤቶች ሠርታችኋል፤ እናንተ ግን አትኖሩባቸውም፤ የሚያስደስት ወይን ተክላችኋል፤ ነገር ግን ከእርሱ የሚገኘውን የወይን ጠጅ እናንተ አትጠጡም በማለት ይወቅሳቸዋል (አሞ 5፡ 10-11)፡፡ ከዚህም አልፎ ነቢዩ በቀጥታ ሲናገራቸው እናንተ የድኾችን መብት የምትረግጡና ምስኪኖችን ከአገር ለማጥፋት የምትፈልጉ ሁሉ በማለት ያስጠነቅቃቸዋል(አሞ 8፡ 4)፡፡

በእርግጥ በጊዜው የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖሩ የነበሩት ጥቂት ሀብታሞች በወቅቱ ድኾችን የሚበዘብዙበት የተለያዩ መንገዶች ያመቻቹ ነበር፡፡ የአዝመራ ወቅት ሲደርስ ለገበሬው እህል በማበደርና በምርት ጊዜ ከመጠን ያለፈ ክፍያ ይጠይቁ ነበር፤ ገበሬው አምርቶ እህሉን በሚሸጥበት ወቅት የእህሉን መስፈሪያ በማሳነስና ሐሰተኛ ሚዛን በመጠቀም ራሳቸውን ተጠቃሚ ያደርጉ ነበር፤ በምርት ወቅት ዕዳውን መክፈል ካቃተው አገልጋይ አድርገው ለራሳቸው ያሳርሱት ነበር(አሞ 8፡ 5-6)፡፡ ይህንን የጥቂቶች ድርጊት ያንገሸገሸው ነቢዩ አሞጽ እነዚህ በደል ፈጻሚዎችን በቀጥታ እናንተ ፍርድን ወደ መርዝ ለወጣችሁ፤ እውነትንም እንደ ሬት መራራ አደረጋችሁ በማለት ይናገራቸዋል(አሞ 6፡ 12)፡፡ እነዚህ የድኾችን ጉልበት በመበዝበዝ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩ ጥቂት ሀብታሞች እግዚአብሔር ወደ ሚመለክበት ቦታ በመሄድ ይጸልዩ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል መባና የሰባ ፍሪዳ ያቀርቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህንን ሁሉ አልቀበላችሁም፤ የመሰንቆአችሁንም ዜማ መስማት አልፈልግም፤ ይልቅስ ፍትሕ እንደ ምንጭ ውሃ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ ይፍሰስ በማለት ያስገነዝባቸዋል(አሞ 6፡ 21-23)፡፡

በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ምስኪኖች በኃያላን የሚበዘበዙበት፣ የፍትሕ አተገባበር የተዛባበት፣ የድኾች ጭቆናና መንገላታት የተስፋፋበት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የራቀበትና ለንጹሓን ተቆርቋሪና ተናጋሪ የጠፋበት ወቅት ውስጥ ነው ነቢዩ ድምፁን ከፍ በማድረግ ስለ ፍትሕ የተናገረው፡፡

  • ነቢዩ አሞጽ ከተናገረው የትንቢት ቃል ውስጥ ሰፋ ያለ ቦታ የሚሸፍነው አንዱ የንስሓ ጥሪ ነው፡፡ ይህ የንስሓ ጥሪ በምን ዓይነት መልኩ ተገልጾ ይገኛል?

ነቢያት አብዛኛውን ጊዜ ሲያስተምሩ ሕዝቡ ከተሳሳተው የሕይወት ጉዞው ተመልሶ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቅና እውነተኛ የጽድቅ ሕይወት መኖር እንዲችል መንገዱን ያመቻቻሉ፡፡ ከእነዚህም መንገዶች አንዱ የንስሓ ጥሪ ነው፡፡ ነቢዩ አሞጽ ሕዝቡ ንስሓ እንዲገባ ግልጽ በሆነ መንገድ የሕዝቡን ኃጢአቶች እየዘረዘረ ይናገራቸዋል፡፡ ዋናው የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ኃጢአት የእግዚአብሔር ሕግ መጣስና ትእዛዙንም አለመጠበቅ ነው(አሞ 2፡ 4)፡፡ እንደ ነቢዩ አሞጽ አገላለጽ የሕዝቡ ኃጢአቶች ከተባሉት ውስጥ ፍርድን ማጣመም፣ እውነትን ወደ ሐሰት በመለወጥ፣ ፍትሕን ማጓደል፣ ጣዖታትን ማምለክ፣ ድኾችን መበዝበዝ፣ አራጣ ማበደርና በንግድ ሥራ ላይ ሐሰተኛ ሚዛን እየተጠቀሙ ማታለል ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ስለ ምስኪኖች ሳያስቡ ለራስ ብቻ በቅንጦትና በመንደላቀቅ መኖር፣ ከመጠን በላይ የሆነ ወይን ጠጅ ጠጥቶ መስከር፣ ደጋግ ሰዎችን ማስጨነቅና የመሳሰሉት ይገኙበታል(አሞ 5)፡፡ አሞጽ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉ ነገር አታድርጉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል በማለት ደጋግሞ ጥሪውን ያስተላልፋል(አሞ 4፡14፤ 5፡ 4-6)፡፡

ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሕዝቡ ተጸጽቶና ከስሕተቱ ተምሮ ንስሓ እንዲገባ ብዙ ነገሮች እንዲከሰቱ ፈቅዶ ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል እህል አጥቶ በችጋር መኖር፣ የዝናም መቋረጥ፣ ለመጠጥ የሚሆን በቂ ውሃ አለማግኘት፣ ሰብል የሚያደርቅ ብርቱ ነፋስ መከሰት፣ አትክልቶች፣ ወይኖችና የወይራ ዛፎች በአንበጣ መበላት፣ የመቅሠፍት መምጣት፣ ጐልማሶች እንዲሞቱ ፈረሶቻቸውም እንዲማረኩ መደረግና ሌሎችም ይገኙበታል(አሞ 4፡ 4-12) ፡፡ ሕዝቡ ይህንን ሁሉ ተረድተውና ከስሕተታቸው ተምረው ገና ድሮ ንስሓ መግባት ነበረባቸው፤ እነርሱ ግን በእልኸኝነታቸው በመጽናት መኖርን መረጡ፡፡ እነዚህ ሁሉ በሕዝቡ እንዲደርስ የፈቀደው እግዚአብሔርም ሕዝቡን እናንተ ግን በመጸጸት ወደ እኔ አልተመለሳችሁም በማለት ደጋግሞ ይወቅሳቸዋል(አሞ 4፡1-12)፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ስለሆነ አሁንም ተጸጽተው ፍትሕን የሚተገብሩና ወደ እውነተኛው መንገድ የሚመለሱትን ስለሚምር በድጋሚ ወደ ንስሓ ይጠራቸዋል፡፡ ይህንን ጥሪ ሰምተው አካሄዳቸውን ባያስተካክሉና ባይመለሱ ግን ይወድቃሉ፤ ከወደቁበትም መነሣት አይችሉም(አሞ 8፡14)፡፡

  • ነቢዩ አሞጽ የፍርድ ቀን እንደሚመጣና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድ ይናገራል፤ ለመሆኑ ይህ ፍርድ እንዴት ይከናወናል ? እግዚአብሔር ሕዝቡን ለምን ይፈርዳል? ፍርዱስ ምን ይሆናል?

ነቢዩ አሞጽ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ስለሚፈርድበት ቀን ከመናገሩ በፊት ስለ እግዚአብሔር ኃያልነት፣ ሁሉን ፈጣሪነቱ፣ ሁሉን አድራጊነቱ እና ከእርሱ ፈቃድ ውጪ ምንም የሚከናወን ነገር እንደሌለ በተለያየ ሁኔታ በተደጋጋሚ ያስገነዝባል፡፡ እግዚአብሔር ሲጠራው እንኳ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት ኃያልነቱን አጉልቶ እየገለጸ ነው(አሞ 3፡12)፡፡ እንደ ነቢዩ አሞጽ አገላለጽ እግዚአብሔር ቁጣው በነደደ ጊዜ የሚያጠፋ(አሞ 2፡ 3)፣ መቅሠፍት የሚልክ(አሞ 4፡ 10)፣ በሰይፍ የሚጨርስ(አሞ 9፡ 1)፣ ነቃቅሎ ከምድር ገጽ የሚያጠፋና (አሞ 2፡ 9፤ 9፡ 8)፣ በእሳት የሚያቃጥል(አሞ 2፡ 5) አምላክ እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ረሀብን የሚያመጣተማርከው ወደ ሩቅ አገር እንዲሰደዱ የሚያደርግ አምላክ እንደሆነ ደጋግሞ በተለያየ መልኩ ያስገነዝባል፡፡

ይህ አምላክ ሕዝቡን የሚፈርድበት ቀን እንደሚመጣ ነቢዩ ለሕዝቡ ያሳውቃል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡንየሚፈርድበት ቀን የጭንቀትና የመከራ ጊዜ እንደሚሆን ነቢዩ ለሕዝቡ በማስገንዘብ ይህ ቀን ከመድረሱ በፊት ሕዝቡ ንስሓ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስና በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ያስጠነቅቃል፡፡ እንደ ነቢዩ አገላለጽ ያ ቀን ምንም ብርሃን የማይታይበት የድቅድቅ ጨለማና የጭንቀት ቀን ይሆናል፡፡ ነቢዩ ስለዚያች ቀን ሲናገር በዚያን ቀን ከአንበሳ አምልጦ እንደገና ድብ እንደሚያጋጥመውና ከድብ ሸሽቶ ወደ ቤት በገባም ጊዜ እጁን በግድግዳ ላይ ሲያስደግፍ እባብ እንደሚነድፈው ሰው ትሆናለችሁ በማለት አስፈሪነቱን ይገልጻል(አሞ 5፡ 19)፡፡ በዚያች ቀን ሕዝቡ በፈጸሙት ክፉ ሥራ ምክንያት ምድር ትናወጣለች፤ በአገሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ገና በእኩለ ቀን ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ ይመጣል፤ በቀትርም ምድሪቱ ትጨልማለች፤ የሚሸሽ አያመልጥም፤ የሚያመልጥ የሚመስለውም አይድንም(አሞ 8፡7-9)፡፡

ከዚህም በላይ ስለዚያች የጭንቀት ቀን እግዚአብሔር ራሱ ሲገልጽ ምድርን ቈፍረው ወደ ሙታን ዓለም ቢወርዱ እንኳ እኔ መንጥቄ አወጣቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ወጥተው ቢሸሸጉም ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ ይላል፡፡ እንደ ነቢዩ አገላለጽ ወደ ጥልቅ ባሕር ገብተው ለመሰወር ቢሞክሩም በባሕር ዘንዶ ይነደፋሉ፤ በጠላቶቻቸው ቢማረኩም እንዲገድሉአቸው ማራኪዎቻቸውን አዛለሁ፤ በዚህ ዐይነት እኔ እነርሱን ለመርዳት ሳይሆን ለማጥፋት ተነሥቻለሁ ይላል(አሞ 9፡ 2-4)፡፡ በተጨማሪም በዚያች ቀን ማንም ይሁን ማንም ማምለጥ እንደማይችል ሲገልጽ ፈጣን ሯጮች እንኳ ሸሽተው አያመልጡም፤ ብርቱ ሰዎችንም ኃይላቸው ይከዳቸዋል፤ ጦረኞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም፡፡ ቀስት ወርዋሪዎችም ቆመው አይመክቱም፤ ፈረሰኞችም ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም፤ እጅግ ብርቱ የሆኑ ጦረኞች እንኳ የጦር መሣሪያቸውን እየጣሉ ይሸሻሉ ይላል(አሞ 2፡13-15)፡፡ ስለዚህ ይህ የጭንቅ ቀን ከመምጣቱ በፊት ሕዝቡ ከተሳሳተ የሕይወት ጐዳና ተመልሶ ንስሓ በመግባት እንዲዘጋጅ ነቢዩ ያስገነዝባል፡፡

  • እግዚአብሔር በእስራኤል አጐራባች አገራት ላይ ፍርድ እንደሚፈርድ ነቢዩ አሞጽ ይናገራል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ አገራት ለምን ይፈረድባቸዋል? ፍርዱስ ምንድን ነው?

አሞጽ በትንቢቱ መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር በእስራኤል ዙሪያ በሚገኙት አገራት ላይ እንደሚፈርድ በተለያየ መልኩ ይገልጻል፡፡ እነዚህም አገራት የሚፈረድባቸውም ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት መሆኑንን ይናገራል፡፡ ከእነዚህም ኃጢአት መካከል የጢሮስ ሕዝብ የገቡበትን የወንድምነት ቃል ኪዳን አፍርሰው የማረኩአቸውን ሕዝቦች ወደ ኤዶም እንዲሰደዱ በማድረጋቸው ምክንያት ይቀጣሉ፡፡ የኤዶም ሕዝቦች ደግሞ ወንድሞቻቸው የሆኑት እስራኤላውያንን እንደ አውሬ አድነው ስለያዙአቸው ይቀጣሉ፡፡ የዐሞን ሕዝቦች ግዛት ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ በገለዓድ የሚኖሩትን እርጉዞች ሴቶች ሆዳቸውን በመቅደዳቸው ምክንያት በብርቱ ይቀጣሉ፡፡ የሞአብ ሕዝቦች የኤዶምን ንጉሥ ዐፅም ዐመድ እስኪሆን በማቃጠላቸው ሲቀጡ የይሁዳ ሕዝቦችም የእግዚአብሔር ሕግ በመጣሳቸውና ትእዛዙም ባለመጠበቃቸው ምክንያት ይቀጣሉ(አሞ 1-2)፡፡ ነቢዩ አሞጽ እነዚህን አገራት ሁሉ በስማቸው እየጠቀሰ የእግዚአብሔር ፍርድ ለምን በእነሱ ላይ ሊመጣ እንደሚችል ያስገነዝባቸዋል፡፡ በዚህ የፍርድ ሂደት ውስጥ እነዚህ አገራት የሚናገሩትም ሆነ የሚያቀርቡት ምንም ዐይነት አቤቱታ የለም፡፡

እግዚአብሔር ፍርዱን በአይሁዳውያንም ሆነ በሌሎች ሕዝቦች ላይ እንደሚያከናውን ነቢዩ አሞጽ የሚያረጋግጠው እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ሥልጣን እንዳለውና የሁሉም ገዥ ጌታ መሆኑን ለማስገንዘብም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በራሱ ተነሳሽነት ፍርዱን በማይታዘዙት ሁሉ ላይ እንደሚያደርግ በራሱ አንደበት እንዲህ አደርጋቸዋለሁ እያለ ፍርዱን ያሳውቃል፡፡ ይህ ፍርድ እግዚአብሔር ቀጥታ በመገለጥ በሕዝቡ ላይ የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች ይከናወናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተፈጥሮ አስፈሪ የሆኑ ክስተቶች ሕዝቡን ያስጨንቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የምድር መናወጥ፣ በኩለ ቀን ፀሐይ መጥለቅ፣ በቀትር ምድሪቱ እንድትጨልም ማድረግ፣ በምድር ላይ ረሀብን ማምጣትና የመሳሰሉትን ይገኙበታል(አሞ 9፡ 4)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ወራሪ ጠላቶች ሕዝቡን እንዲያስጨንቁ በማዘዝ ሕዝቡ ስለ ፈጸሙት ኃጢአት እንዲቀጡ ያደርጋል(አሞ 5፡3፤ 6፡9-10፣ 6፡14)፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ትእዛዙን ጥሰው በራሳቸው ፈቃድ ሲኖሩና ምስኪኑን ሲጨቁኑ በነበሩት በእስራኤላውያን፣ በአይሁዳውያንና በሌሎችም ሕዝቦች ላይ በተለያየ መልኩ ፍርዱን ይተገብራል፡፡             

  • አሞጽ የተለያየ ራእዮች እንዳየ ይናገራል፤ እነዚህ ራእዮች ይዘታቸውንና መልእክታቸው ምን ይመስላል?

ነቢዩ አሞጽ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መልእክት የሚያስተላልፉ ነገር ግን ሁሉም የእስራኤል ሕዝብና መንግሥት ተደምስሰው የመጥፊያቸው ጊዜ መቃረቡን የሚያመለክቱ አምስት ራእዮች አይቷል፡፡ እነዚህም የአንበጣ መንጋ መፈልፈል፣ የቅጣት እሳት መምጣት፣ የውሃ ልክ ማስተካከያ ቱምቢ፣ ፍሬ የሞላበት ቅርጫትና እግዚአብሔር በመሠዊያው አጠገብ ሆኖ ስለ መጨረሻው ፍርድ የተናገረበት ራእይ ናቸው(አሞ 7-9)፡፡ አሞጽ በመጀመሪያ ያያቸው ሁለት የጥፋት ራእዮች ውስጥ ማለትም የአንበጣ መንጋ የምድርን ልምላሜ ሁሉ ግጠው እንዲበሉት ማድረጉንና የቅጣት እሳት መምጣቱን በሚያመለክቱት ላይ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ የሕዝብህን በደል ይቅር በል፤ ሕዝብህ እስራኤል ጥቂቶች ስለሆኑ እንዴት መትረፍ ይችላሉ በማለት እግዚአብሔርን ይማልዳል(አሞ 7፡2)፡፡ እግዚአብሔርም የነቢዩን ጸሎት ሰምቶ ይራራል፤ አሳቡንም ለውጦ ይህ ያየኸው ነገር አይፈጸምም በማለት ይመልስለታል(አሞ 7፡3 እና 6)፡፡

በሌሎች ሦስቱ ራእዮች ግን አሞጽ እግዚአብሔርን መማለዱን ይተዋል፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እንዲመጣ የሚፈቅደውን ጥፋትና ፍርድ ይተነትናል፡፡ በእርግጥ በሦስተኛው ራእይ ማለትም በውሃ ልክ ማስተካከያ ቱምቢ ላይ እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ላለመታገሥና ሕዝቡን ለመቅጣት የወሰነ መሆኑን እንግዲህ እነርሱን ከመቅጣት አልመለስም ምክንያቱም ሕዝቤ እስራኤል ውሃ ልኩ ተስተካክሎ እንዳልተሠራ ቅጽር ጠማሞች መሆናቸውን በዚህ ቱምቢ አሳይበታለሁ በማለት ውሳኔውን ያሳውቃል(አሞ 7፡ 8)፡፡ ከእነዚህ ራእዮች ውስጥ በተለይ የመጨረሻው እጅግ በጣም አስፈሪና ማንም ሰው በምድርም ይሁን ከምድር በታች፣ በተራራም ይሁን በባሕር ውስጥ ከእግዚአብሔር ፍርድ ፈጽሞ ሊሰወር እንደማይችል ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም ወይም አያገኘንም በማለት የሚመኩት እንኳ በወንፊት ተንገዋሎ እንደሚበጠር እህል ይሆናሉ ይላል(አሞ 9፡9-10)፡፡

  • ነቢዩ አሞጽ ስለ ወደፊቱ የእስራኤል ሕዝብ ተስፋ በምን ዓይነት መልኩ ይገልጸዋል?

በትንቢተ አሞጽ ውስጥ ስለ ወደፊቱ ተስፋ የሚናገረው ብዙም ነገር እንደሌለ ከትንቢት ቃሉ እንረዳለን፡፡ ነቢዩ አብዛኛውን ትኩረቱ የሚያደረገው በወቅቱ በነበረው የሕዝቡ ማኅበራዊ ኑሮና እየተከናወኑ በነበሩት የኢፍትሐዊነት የኑሮ ሂደቶች ላይ ነበር፡፡ በእርግጥ አሞጽ በነቢይነት ያገለገለው የእስራኤል ሕዝብ በድሎትና በብልጽግና ይኖርበት በነበረበት በስምንተኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነና የትንቢቱም ቃል የተጻፈው የእስራኤል ሕዝብ ወደ ስደት ከመሄዳቸው ቀደም ብሎ እንደሆነ ከላይ ተጠቅሷል፡፡

በመጽሐፉ መጨረሻ ክፍል ማለትም አሞ 9፡ 11-15 ስለ እስራኤል ሕዝብ ከስደት መመለስ ይተርካል፡፡ ነገር ግን ይህ ክፍል ከብዙ ዓመታት በኋላ በሌላ ሰው የተጻፈና ዘግይቶ መጽሐፉ ውስጥ የታከለ ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ይህ ዘግይቶ የተካተተ የመጨረሻው የመጽሐፉ ክፍል የሚያተኩረውም ፈራርሶ የነበረው የዳዊት መንግሥት በድጋሚ እንደሚቋቋምና ቅጽሮቹም እንደሚጠገኑ ነው፡፡ በተጨማሪም እስራኤላውያን ተመልሰው አገራቸውን በመውረስ በአዲስ መልክ ኑሮአቸው እንደሚመሠርቱ፣ ዳግመኛም ከዚያች ምድር እንደማይወጡ፣ ወይን ተክለው የወይን ጠጅ እንደሚጠጡና ልዩ ልዩ ተክሎችን ተክለው ፍሬውን እንደሚመገቡ ይናገራል፡፡ በመጨረሻም ተራራዎችና ኮረብታዎች ጣፋጭ የወይን ጠጅ የሚያፈልቁበት ጊዜ እንደሚመጣ፣ የፈረሱትንም የእስራኤል ከተሞች እንደገና እንደሚሠሩና ብዙ የሆኑ መልካም ነገሮችን እንደሚወርሱ ነው፡፡

  • ትንቢተ አሞጽ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በየትኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍና ከምን ጋር በተያያዘ ሁኔታ ተጠቅሶ ይገኛል?

ትንቢተ አሞጽ ያካተታቸው ትምህርቶች የየትኛውም ማኅበረሰብ ዕለታዊ ኑሮን የሚዳስሱ እንደሆኑ ከትንት ቃሉ እንረዳለን፡፡ በተለየም በኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆነ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች መብት እንዲከበር ትኩረት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በጥቂት ባለሥልጣኖችና ባለሀብቶች ለሚበዘበዙት የማኅበረሰብ ክፍሎችን ትኩረት የሚሰጥ ስለሆነ ይህ መጽሐፍ በአዲስ ኪዳንም በተለያየ መልኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ሐዋርያቶችም ሲያስተምሩ በተደጋጋሚ በሀብታምና በድኻ መካከል የመለያየትና የማንቋሸሽ መንፈስ በክርስቲያኖች ዘንድ በምንም ዓይነት መልኩ መንጸባረቅ እንደሌለበት ደጋግመው ያስገነዝባሉ(1 ቆሮ 11፡22፤ ያዕ 2፡1-10)፡፡ እንዲያውም እውነተኛ የሆነ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሰዎች ለምስኪኖች፣ ለድኾችና ረዳት ለሌላቸው መንከባከብና ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያሳስባሉ(ያዕ 1፡27፤ 5፡1-6) ፡፡ በአዲስ ኪዳን ከማንም በላይ ለደካሞች ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሁም ልዩ የሆነ ትኩረት በመስጠት ፍትሕ በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ በሁሉም ሰው መተግበር እንዳለበት ያስተማረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር የፈረሰውን የዳዊት ቤት በድጋሚ እንደሚሠራና መንግሥቱንም እንደሚያቋቁም ገልጿል፡፡ ይህ ቤት ለእስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሕዝቦች ክፍት የሆነና ብዙ አገራትም የሚያካትት እንደሚሆን ነቢዩ አሞጽ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር(አሞ 9፡11-12)፡፡ ሐዋርያቶችም ይህንን ሀሳብ በመውሰድ የአዲስ ኪዳን ዘመን አረማውያንና አይሁዳውያን በእግዚአብሔር የተጎበኙበትና የማዳን ኃይሉም ለሁሉም እኩል የተገለጠበት ጊዜ መሆኑን በማስገንዘብ ትንቢተ አሞጽን በመጥቀስ ተናግረዋል(ሐዋ 15፡16-17)፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ሲጽፍ ትንቢተ አሞጽን በመጥቀስ ግብዝነት የሌለበት እውነተኛ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ክፉውን ነገር ጥሉ፤ መልካሙን ነገር ተከተሉ እያለ ያስተምራቸዋል(አሞ 5፡15፤ ሮሜ 12፡9)፡፡         

በአጠቃላይ ነቢዩ አሞጽ ቀለል ባለና ቀጥተኛ በሆነ አነጋገር ከእግዚአብሔር የተቀበለውን የትንቢት ቃል ለሕዝቡና ለመሪዎቻቸው በሚገባ አስተላልፏል፡፡ በዚህም መልእክቱ እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው መሥዋዕት ሳይሆን ዋናው ፍትሕ የተሞላበት አስተዳደርና አኗኗር መሆኑን ለማሳወቅ ብዙ ምሳሌዎችና ራእዮች በመጠቀም ሕዝቡን ወደ ንስሓ ጠርቷል፤ ይህ ካልሆነ ግን የፍርድ ቀን እንደሚመጣና በዚህ ዕለት ደግሞ ማንም ማምለጥ እንደማይችል አሰገንዝቧል፡፡ ይህ ትምህርቱ በተለይም ስለ ፍትሕ የተናገረውን ዛሬም ቢሆን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ወቅታዊ የሆነ የቤተክርስቲያን፣ የሊቃውንትና የብዙ በጎ መንፈስ ያላቸው ሰዎች ዕለት በዕለት የሚናገሩለትና የሚዋጉለት አጀንዳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴጂ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1 -የነቢዩ አሞጽ ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) ትንቢተ አሞጽ ግልጽ የሆነ መልእክት የያዘ ሲሆን ስለ ጸሐፊው ማንነት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ያላስነሣ መጽሐፍ ነው፡፡ ለ)አሞጽ እንደ ነቢያት ልጆች ወይም ወገኖች በቤተ መቅደስ ያደገ ነቢይ ነው፡፡ ሐ)አሞጽ የሚጠቀምበት የንግግር ዘይቤ ቀጥተኛ የሆነ አይደለም፤ ከንግግሩ በስተጀርባ የተደበቀ ምስጢር አለ፡፡ መ)አሞጽ የኖረው እስራኤል ውስጥ እኩልነትና ፍትሕ በሰፈነበት ወቅት ውስጥ ነው፡፡ ሠ) አሞጽ በነቢይነት ለሃያ ዓመታት ያህል አገልግሎአል፡፡

2 -ነቢዩ አሞጽ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ንስሓና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንዲሁም በአጐራባች አገራት ላይ ስለሚያከናውነው ፍርድ በስፋት ተናግሮአል፡፡ እነዚህን ርዕሶች በተመለከተ ከሚከተሉት ውስጥ ትክክለኛውን የትኛውን ነው?

ሀ) የድኾችን ጉልበት በመበዝበዝ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩ ሀብታሞች እግዚአብሔር ወደ ሚመለክበት ቦታ በፍጹም አይሄዱም ነበር፡፡ ለ)እግዚአብሔር ወራሪ ጠላቶች ሕዝቡን እንዲያስጨንቁ በማዘዝ ሕዝቡ ስለ ፈጸሙት ኃጢአት እንዲቀጡ ያደርጋል፡፡ ሐ) ሀብታሞች የአዝመራ ወቅት ሲደርስ ለገበሬው እህል በማበደር በምርት ጊዜ ተገቢውን ክፍያ ይጠይቁ ነበር፡፡ መ)የዐሞን ሕዝቦች ግዛት ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ በገለዓድ የሚኖሩትን ሰዎች ገደሉ፤ እርጉዝ ለነበሩ ሴቶችን ግን ተንከባከቡአቸው፡፡ ሠ)እግዚአብሔር ሕዝቡንየሚፈርድበት ቀን ለብዙዎቹ የደስታና የሰላም ጊዜ ይሆናል፡፡

3 -ነቢዩ አሞጽ ካያቸው ራእይ መካከል እግዚአብሔር የሕዝቡ ፍጻሜ የተናገረበትና ሕዝቡን የሚቀጣበት እንዲሁም በቅጣቱ ምክንያት የብዙ ሰው ሬሳ በየቦታው ወድቆ እንደሚገኝ የሚገልጸው ራእይ የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ ከተሰጠው ትምህርት በተጨማሪ አሞ ከምዕራፍ 7 እስከ ምዕራፍ 9 መነበብ አለበት)

ሀ) የአንበጣ መምጣት የሚያመለክት ራእይ፤ ለ) የቅጣት እሳት መምጣት የሚያመለክት ራእይ፤ ሐ) ስለ ውሃ ልክ ቱምቢ የሚናገረው ራእይ፤ መ) ፍሬ ስለ ተሞላው ቅርጫት የሚናገረው ራእይ፤ ሠ) ስለ በጎች መንጋ ያየው ራእይ ነው፡፡

4 -ነቢዩ አሞጽ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር ከሕዝቡና ከሕዝብ መሪዎች ምን እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ከምንም በላይ በምዕራፍ አምስት(5) ውስጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ እግዚአብሔር ከሕዝቡና ከመሪዎቹ የሚፈልገው ነገር ተናግሮአል፡፡ እንደ ምዕራፍ አምስት(5) ገለጻ እግዚአብሔር የሚፈልገው ትልቁ ነገር ምንድን ነው?

ሀ) የምስጋና መሥዋዕትና መባ፤ ለ) በመሰንቆ የታጀበ ዝማሬና እልልታ፤ ሐ) ፍትሕ እንደ ምንጭ ውሃ እንዲፈስ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ እንዲፈስ፤ መ) ለገበሬዎችና ለድኾች በቂ የሆነ ምግብ እንዲሰጥ፤ ሠ) አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ድምፃቸው ከፍ አድርገው እንዲናገሩ፡፡

5 -ነቢዩ አሞጽ በምዕራፍ አንድ(1) እና ሁለት(2) ውስጥ ይሁዳን ጨምሮ የተለያዩ አጐራባች አገራት በሠሩት የተለያየ ኃጢአት ምክንያት እንደሚቀጣቸው ይናገራል፡፡ ከእነዚህ አገራት ውስጥ የእግዚአብሔር ሕግ በመጣሱ፣ ትእዛዙን ባለመጠበቁና የሐሰት አማልክት በማምለኩ ምክንያት እንደሚቀጣ የተነገረው አገር የትኛው ነው?

ሀ) ሶርያ ለ) ፍልስጤም ሐ) ጢሮስ መ) ኤዶም ሠ) ይሁዳ፡፡

6 -ትንቢተ አሞጽ 8፡ 4-6 ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢዩ አሞጽ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛውና በስምንተኛው ክፈለ ዘመን እንደኖረ ይታመናል፡፡ ይህም ማለት ከዛሬ 2700 እና 2800 ዓመታት በፊት እንደማለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ነጋዴዎች የእህል መስፈሪያ አሳንሰው ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቁ ነበር፤ በሐሰተኛ ሚዛን እየመዘኑ ሕዝቡን ያታልሉ ነበር፡፡ ይህም ማለት ከአንድ ገበሬ 100 ኪሎ ቦቆሎ ሲገዙ ሚዛናቸው 80 ኪ.ግ እንዲመዝን ያደርጉታል፤ 20 ኪ.ግ ይሰርቃሉ ማለት ነው፡፡ ሲሸጡ ደግሞ የሚዛናቸው አመዛዘን ይለውጡታል፤ ይህም 10 ኪ.ግ ቦቆሎ ሲሸጡ ሚዛናቸው 12 ኪ.ግ አስመስሎ እንዲያሳይ ያደርጉት ነበር፤ በዚህም ከ10 ኪ.ግ ቦቆሎ ሁለት ኪ.ግ ያህል ይሰርቁ ነበር፡፡ ነቢዩ አሞጽ ይህንን አይቶ ነጋዴዎችም ሆነ ሀብታሞች ወይም ነገሥታት ባለሥልጣናት ሳይፈራ ሥራቸው ወይም ሌብነታቸው በግልጽ ያወግዝ ነበር፡፡

ዛሬም በምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሥጋ ወይም ዘይት ወይም የእህልና የተለያዩ ለዕለታዊ ኑሮ የሚጠቅሙ ነገሮች ነጋዴዎች በተጭበረበረ ሚዛን ይሸጣሉ፡፡ እህል በሚመረትበት አካባቢ ደግሞ በርበሬም ይሁን ሌላ ጥራጥሬ ሚዛናቸው በተለያየ መልኩ በማጣመምና በማጭበርበር ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ፡፡ ይህ ነገር በእኛ ላይ ቢደረግብን ወይም በሌሎች ወንድሞቻችን ላይ ሲደረግ ብናይ “እኛ የዛሬዎቹ ነቢያት” የሆንን ምን እንዳረጋለን? ምን ዓይነት እርምጃ እንወስዳለን? ትቶ መሄድ ወይስ በቀጥታ ለሰውዬው መናገር ወይስ ለሚመለከተው ክፍል ሄዶ ማጋለጥ ወይስ ፈርቶ ምን አገባኝ ብሎ መሸሽ ወይስ የትንቢተ አሞጽ መጽሐፍ ይዞ በመሄድ ለዛ ሰው ማንበብ ወይስ ሰውዬውን ለብቻውን ጠርቶ የሚያደርገው ነገር ግፍ እንደሆነ መናገር ወይስ በሽማግሎዎች ማስመከር ወይስ….ምን እናድርጋለን? ምላሻችን በእውነቱም ልናደርገው የምንችለው ነገር በቅንነት መመለስ ነው እንጂ የማናደርገው ነገር መሆን የለበትም፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት