ት/ርት ፳፱ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ዮናስ)
- Category: የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
- Published: Wednesday, 10 June 2015 07:18
- Written by Super User
- Hits: 17057
- 10 Jun
ክፍል ሦስት (ትምህርት ሃያ ዘጠኝ)
የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ዮናስ
- ዮናስ ተወልዶ ያደገውና የነቢይነት ተግባሩን የተወጣው መቼና የት ነው? የቤተሰብ ኑሮውስ ምን ይመስል ነበር?
ዮናስ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ “እርግብ” ማለት ነው፡፡ ዮናስ ከዐሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት አንዱ ሲሆን የኖረውም ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ክፍለ ዘመን ከ786-746 ዓ.ዓ አካባቢ እንደሆነ ከመጽሐፉ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ዮናስ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመን የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ዮናስም ኢዮርብአም ሶርያውያንን አባርሮ የእስራኤል ድንበር እንደሚመልስ ትንቢት ተናገረ፡፡ በዚህም ዮናስ ከቀደምት ወይም ከመጀመሪያዎቹ ነቢያቶች ከእነ አሞጽና ኢሳይያስ በተመሳሳይ ወቅት እንደኖረ ይታመናል(2 ነገ 14፡ 25)፡፡ ገና ከመጽሐፉ መግቢያ ዮናስ የአሚታይ ልጅ መሆኑንና መኖርያውም በገሊላ በጋትሔፌር ከተማ እንደነበር ቢገለጽም ስለሌላው ቤተሰባዊ ሕይወቱ ግን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም(ዮና 1፡ 1)፡፡ ዮናስ የነቢይነት ተግባሩን የሚጀምረው እስራኤል ውስጥ ሲሆን የሚያጠናቅቀው ብዙ ሕዝብ ይኖሩባት የነበረው ነነዌ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ነነዌ በጤግሮስ ወንዝ ዳር በናምሩድ የተመሠረተች ጥንታዊት ከተማ ስትሆን ለአሦር ደግሞ እንደ መናገሻ፣ ሰፊና ውብ የነበረች ከተማ ናት(ዘፍ 10፡ 11-12)፡፡ ለብዙ ዘመናት የአሦር ንጉሠ ነገሥት የእስራኤል ተቀናቃኝ ጠላት ሆኖ የኖረ መንግሥት ነው፡፡ የከተማው ቅጽር ርዝመት ዐሥራ ሁለት ኪ.ሜ እንደነበርና በውስጥዋም ብዙ ሕንጻዎች ተሠርተውባት ነበር(ዮና 4፡11)፡፡ የባቢሎን መንግሥት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ612 ዓ.ዓ ከተማዋን ይዞ አፈረሰው፡፡
- የትንቢተ ዮናስ ጥንቅሩና ይዘቱ እንዲሁም ጠቅላላው የመጽሐፉ አወቃቀር ምን ይመስላል?
ትንቢተ ዮናስ አራት ምዕራፎች ብቻ ያሉት፣ እጥር ምጥን ያለ መጽሐፍ ሆኖ ድርጊቱ ግን ልብ ሰቃይና አስገራሚ በሆኑ ትርኢቶች የተጠናቀረ ነው፡፡ የትንቢቱ ቃል ወይም መጽሐፉ የሚጀምረው ለነቢይነት አገልግሎት ተመርጦ የእግዚአብሔር መልእክት እንዲያደርስ የታጨውን የዮናስ አለመታዘዝናከእግዚአብሔርፊትኮብልሎ ለመሄድአስቦወደተርሴስየሚያደርገውን ሽሽት በማስቀደም ልብ ሰቃይነቱን በየብስ ይጀምራል(ዮና 1፡ 1-3)፡፡ ዮናስ ወደ አሦር ምድር እንዲላክ ሲጠራ በተቃራኒው አቅጣጫ ወደሚገኘው ወደ ተርሴስ ይሄዳል፡፡ ቀጥሎም ታሪኩ ከደረቅ ምድር ወደ ባሕር፣ ከአንድ ሰው ተዋናኝነት በዛ ወዳሉት የመርከብ ተሳፋሪዎችና ሠራተኞች፣ ሰላማዊ ጅማሬ ከነበረበት ወደ ፍርሃት፣ ጩኸትና የሞት አደጋ ወዳንዣበበት የመርከብ ጉዞ ይቀየራል፡፡ በምዕራፍ ሁለት ላይ ዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ እንደጸለየና በጸሎቱም መጨረሻ ላይ ዓሣው ወደ ምድር እንደተፋው ይናገራል፡፡ ዮናስ በጸሎቱ እግዚአብሔርን ከዚህ የዓሣ ሆድ ውስጥ አውጣኝ በማለት አይጠይቅም፤ ነገር ግን ተጨንቆ ሳለ ወደ እግዚአብሔር እንደተጣራና እግዚአብሔርም እንደሰማው ይናገራል፤ ወደፊትም የምስጋና መሥዋዕት እንደሚያቀርብም ቃል ይገባል(ዮና 2፡ 9)፡፡ በዚህም ምዕራፍ ሦስት የትንቢተ ዮናስ መልእክት የያዘ ዋናው ክፍል ሆኖ ይገኛል፡፡
በመጨረሻም በሚያስገርም ሁኔታ ዮናስ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ ይቅር ባይነትና መሐሪነት እንዲሁም ደግሞ ኃጢአተኞች ተጸጽተው ንስሓ በመግባታቸውና ምሕረት በማግኘታቸው ሲበሳጭና የገዛ ሞቱን ሲመኝ እናገኛለን(ዮና 4)፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር ለዮናስ በሚሰጠው ማብራሪያና አሳማኝ በሆነ ንግግር ታሪኩ ይቋጫል፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉ እንደ አንድ ልበ ወለድ የተጠናቀረ ሆኖ በውስጡ የእግዚአብሔር ፈላጊነት፣ የሰው እምቢተኛነትና ሽሽት በደንብ ይተነትናል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ሁሉም ገዢ መሆኑንና በሁሉም ቦታ እንደሚገኝ፣ የደስታና የሀዘን ተለዋዋጭነት፣ የጾምና የንስሓ አስፈላጊነት፣ የእግዚአብሔር መሐሪነት፣ የአንድ ነቢይ ብስጭትና ሌሎችንም አካቶ የያዘ ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት መጽሐፉ በአፈ ታሪክ የተሞላና ከእውነታ የራቀ እንዲሁም እጅግ በጣም ተጋኖ የተጠናቀረ አድርገው ይተቹታል፡፡ ይህ መጽሐፍ በእርግጥ በአጠነቃቀሩ ተጋኖ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ታሪኩ እውነተኛ መሠረት ባለው ነገር ላይ ተመርኩዞ የቀረበ፣ የራሱ የሆነ ለየት ያለ የአጻጻፍ ዘዴ የተጠቀመና በአቀራረቡም ለየት ያለ ነው እንጂ አንድ ሰው ከምንም ነገር በመነሣት ያቀነባበረው የፈጠራ ሥራ አይደለም፡፡
- ዮናስ ለነቢይነት አገልግሎት በተጠራ ጊዜ ጥሪውን ሳይቀበል ቀርቶ እንደኰበለለ ይታወቃል፤ ለመሆኑ ለምንድን ነው በባሕር ላይ ተጉዞ መኰብለል የመረጠው?
እግዚአብሔር መልእክቱን እንዲያደርስ ዮናስን ለነቢይነት ሲያጨው እንደነ ነቢዩ ኤርምያስ “ገና ልጅ ነኝ” ወይም እንደነ ነቢዩ ኢሳይያስ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ” ሳይሆን ምንም ዓይነት መልስ ሳይሰጥ መኮብለልን ወይም ከእግዚአብሔር መሰወርን መረጠ፡፡ ኩብለላውም ወይም ሽሽቱን በባሕር ላይ አደረገ፤ ባሕር ከእግዚአብሔር ግዛት ውጪ ይሆናል ብሎ በማሰብ ምርጫውን ከደረቁ ምድር መራቅ ሆነ፡፡ በዚህም ሰብአዊ ዕውቀቱን ውስን መሆኑን አሳወቀ፡፡ በእርግጥ በጥንት ዘመን እስራኤላውያን ለባሕር ጥሩ የሆነ አመለካከት አልነበራቸውም፡፡ ባሕር የክፉ መናፍስት ዋና መኖሪያ ቦታ እንደሆነ አድርገው ይቈጥሩት ስለነበር እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ አይገኝም፤ ባሕርም በእግዚአብሔር ግዛት ሥር አይደለም የሚል አመለካከት ነበራቸው፡፡ ይህንን አመለካከት በልቦናው ውስጥ የነበረው ዮናስ፤ ወዲያውኑ ያሰበው በባሕር ላይ በመጓዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወይም ዕይታ መሰወርን ነው(ዮና 1፡3)፡፡
- እግዚአብሔር ሰው እንዲታዘዝለት ያስገድዳልን? ዮናስ እምቢ ብሎ ከኰበለለ እግዚአብሔር ለምን ተከታተለው?
በእርግጥ ዮናስ እዚያው በነበረበት ቦታ ሆኖ አለመፈለጉን ቢገልጽ ይችል ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዮናስን መተውና ሌላ ፈቃደኛ የሆነ ነቢይ ማስነሣት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን በዮናስ ውስጥ የነበረውን አመለካከት በብዙዎች ዘንድ የሚንጸባረቅ አሳብ ስለነበር ሊያስተምረው ፈልጎ እልኸኛነት በተሞላበት መልኩ ተከታተለው፡፡ ይህም እግዚአብሔር የየብስ ብቻ ሳይሆን የባሕርና በውስጥዋም ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ ገዢና አዛዥ መሆኑን ማስተማር ስለፈለገ ተከታትሎ ይህንን መረዳት በሚችል መልኩ ቀረበው፡፡ ዮናስ እግዚአብሔር ወደላከው ሳይሆን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ መሄድ ፈለገ፤ እግዚአብሔር ግን ወደ ትክክለኛው ጐዳና ሊመልሰው ፈልጎ ተከታተለው፡፡ በሌላ መልኩ የዮናስ መርከብ ውስጥ ገብቶ መሸሽ ብዙዎቹ ለማዳንና ወደ እግዚአብሔር መንገድ ለመመለስ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ በእርግጥ በንፋሱ ምክንያት የተቀሰቀሰው ማዕበል በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ ስላስደነገጣቸው ወደ አማልክቶቻቸው መጮኽና መጸለይ ጀመሩ፤ ዮናስን ከመርከቡ ተወግዶ ባሕሩ ጸጥ ባለ ጊዜ ግን ሰዎቹ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እጅግ በጣም ተገርመው መሥዋዕት አቀረቡ፤ እርሱን ለማገልገል ቃል ገቡ(ዮና 1፡16)፡፡
እግዚአብሔር ልጆቹን የሚወድና የሚንከባከብ አምላክ ነውና ዮናስን ለማስተማር ባደረገው ክትትል ምንም ዓይነት የከፋ ነገር እንዲደርስበት አላደረገም፡፡ የመርከቡ ሠራተኞችና ተሳፋሪዎቹ ወደ ባሕር በጣሉት ጊዜ የእግዚአብሔር ጥበቃ በየብስም ይሁን በባሕር መሆኑን መረዳት ይችል ዘንድ የሚውጠውና በጥንቃቄ የሚያቆየው ዓሣ አዘጋጀለት፡፡ በዓሣውም ውስጥ ለሦስት ቀናት እየጾመ፣ እየጸለየና ስለ ሕይወቱ እያስተነተነ ቆየ፡፡ ብዙውን ጊዜ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሰዎች በሕይወታቸው ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎች ከመውሰዳቸው በፊት በገለልተኛ ቦታዎች በጽሞና በመሆን ያስተነትናሉ፤ ሱባኤ ይገባሉ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወታቸው ውስጥ ምን እንደሆነ መርምረው ለማወቅ ይጥራሉ፡፡ ዮናስም በእነዚህ የሦስት ቀንና የሦስት ሌሊት ቆይታው ለአገልግሎት የጠራውን የእግዚአብሔር ማንነትና የዓለም ገዢነቱ የበለጠ ተረዳ፤ እግዚአብሔር እንኳንስ ባሕር ላይ ይቅርና፤ ጥልቅ በሆነው በሙታን ዓለምም ሆነ በጥልቅ ባሕር ውስጥ ሊደርስና ሊያወጣው እንደሚችል ራሱ በጸሎቱ አረጋገጠ(ዮና 2፡1-6)፤ ውሳኔም አደረገ፡፡ ዓሣውም በደረቅ ምድር ላይ በተፋው ጊዜ ወዲያውኑ ምንም ሳያመነታ ወደ ተላከበት ወደ ነነዌ ለመሄድ ወስኖ ጉዞውን ጀመረ (ዮና 3፡3)፡፡ ስለዚህ ይህ ክስተት የዮናስ ሕይወት እንዲለወጥ አደረገው፡፡ ከእምቢተኛነት ወደ እሺታ ወደተሞላው ተላላኪነት፣ ከሽሽት ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ ማድመጥ፣ ጥርጣሬ ከተሞላበት ሕይወት እርግጠኛነት ወደተሞላ ሕይወት ተሸጋገረ፡፡
- ዮናስ የተላከው ወደ ነነዌ ከተማ ነው፡፡ በወቅቱ ነነዌ በምን ዓይነት የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ትገኝ ነበር ? ነነዌ የምትባለው ከተማ የት ነው የምትገኘው?
ነነዌ ከእስራኤል ውጭ በጥንታዊት ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳር የተመሠረተች ጥንታዊት ከተማ ስትሆን ዛሬ ደግሞ ኢራቅ በሚባለው አገር ውስጥ የምትገኝ መንደር ነች፡፡ በወቅቱ ሕዝቦችዋም ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፡፡ ነነዌ ትልቅ ከተማ እንደነበረች ለመግለጽ ሲፈልግ ጸሐፊው በተጋነነ መልኩ ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ተጉዞ ለመድረስ ሦስት ቀን ይፈጅ ነበር ይላል(ዮና 3፡ 3)፡፡ በእርግጥ ነነዌ ትልቅና ብዙ ሕዝቦች የሚኖሩባት ከተማ ነበረች፤ ነገር ግን ከታሪክ መረጃዎችና ከሥነ ቁፋሮ ጥናቶች እንደተረጋገጠው በወቅቱ ነነዌ ከነበራት ስፋት ጋር ሲነጻጸር በዮናስ ታሪክ ውስጥ ስፋትዋ እጅግ በጣም ተጋኖ ቀርቧል፡፡ ዋናው መታወቅ ያለበት ነገር ነነዌ ብዙ ሰዎች የሚኖሩባት ከተማ እንደነበረችና ነዋሪዎችዋም ከእግዚአብሔር መንገድ የራቁ እንደነበሩ ነው፡፡
- ዮናስ ወደ ነነዌ ሄዶ የትንቢት ቃሉ ሲናገር የነነዌ ሕዝቦች ምላሽና ለእርሱ መልእክት የሰጡት ትኩረት ምን ይመስል ነበር?
ዮናስም ወደዚያ እንደደረሰ መልእክቱን አደረሰ፤ ነነዌ በአርባ ቀናት ውስጥ እንደምትደመሰስ ዐወጀ(አንዳንድ ከዕብራይስጥ ቋንቋ የተተረጐሙት በሦስት ቀናት ውስጥ ትጠፋለች ይላሉ)፡፡ የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በዮናስ መልእክት እጅግ በጣም የተደናገጡና የፈሩ እንዲሁም እርምጃ ለመውስድ የፈጠኑ ነበሩ፡፡ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች ይህንን የጥሪ ቃል እንደ ተራ ነገር በመቁጠር በዮናስ ላይ ማፌዝና የተለመደው ኑሮአቸው መቀጠል አልፈለጉም፡፡ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር ምሕረት ለማግኘት፣ ራሳቸውንና ከተማቸውን ለማዳን ፈጣን የሆነ እርምጃ መውሰድ ፈለጉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አመኑ፤ ጾምም ዐወጁ፤ መጸጸታቸውንም ለመግለጽ ከታላላቅ ጀምሮ እስከ ታናናሽ ድረስ ሁሉም ማቅ ለበሱ(ዮና 3፡ 5)፡፡ ከሕዝቡም አልፎ የአገሪቱ ንጉሥ መጸጸቱንና ለራሱ፣ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ምሕረት መሻቱን ለመግለጽ ራሱን ዝቅ በማድረግ ከዙፋኑ ወርዶ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ፣ ማቅ ለብሶ ዐመድ ላይ ተቀመጠ(ዮና 3፡ 6)፡፡ ከዚህም በላይ ለሕዝቡ ዐዋጅ አስነገረ፤ በአዋጁም መሠረት እያንዳንዱ ሰው ወደ እግዚአብሔር በሙሉ ልቦናው እየጮኸ ምሕረት እንዲለምን አዘዘ፤ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ጭምር ምንም ሳይበሉና ሳይጠጡ ማቅ በመልበስ እውነተኛ በሆነ መንፈስ ተጸጽተው፣ መጥፎ ጠባያቸውንና የግፍ ሥራቸውን በመተው ምሕረትን ከእግዚአብሔር እንዲሹ አዘዘ(ዮና 3፡ 6-9)፡፡
ይህ የሕዝቡ ጸጸትና ምሕረት ፈላጊነት በእርግጥ በአቀራረቡ የተጋነነ ይመስላል፤ ምክንያቱም እንስሳት እንኳ ከምግባቸው ታግደው፣ ንጉሡም ከዙፋኑ ወርዶ፣ ማቅ ለብሶ ዐመድ ላይ መቀመጡን የድርጊቱ እውነታ ትንሽ አጋኖታል፡፡ ነገር ግን ንጉሡ በዐዋጁ ምናልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ቁጣውን ይመልስ ይሆናል፤ እኛም ከጥፋት እንድናለን በማለት በግልጽ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው የሕዝቡ ኃጢአት ግልጽ የነበረ በመሆኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ምሕረት ለማግኘት የነበረው ብቸኛው አማራጭ ሁሉንም ሰው ከሕፃን ጀምሮ እስከ ንጉሡ ድረስ እንስሳትም ጭምር የሚችሉትን ሁሉ ማለትም ከልብ መጸጸት፣ መጾምና ትሕትና በተሞላበት መንፈስ መጸለይ ብቸኛው አማራጭ ስለነበር እነርሱም ጥሪውን ችላ ሳይሉና ምንም ሳይዘገዩ ፈጣን እርምጃ ወሰዱ፡፡
- እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ስላደረጉት ነገር ምን ዓይነት ምላሽ ሰጣቸው?
የተጸጸቱትን የሚምር፣ የልጆቹን በጎነት ሁሌም የሚመኘው፣ ከጥፋት ይልቅ ምሕረትን የሚቀበለው እግዚአብሔርም ምሕረቱን አወረደላቸው፤ ሊያመጣ የነበረውንም መዓት መለሰ(ዮና 3፡ 10)፡፡ እነዚህ የነነዌ ነዋሪዎች ምንም እንኳ ከእስራኤልና ከይሁዳ ውጭ የሆኑ ባዕዳንና ለእስራኤል ሕዝብም እንደ ጠላት የነበሩ ቢሆኑም የጥሪውን ቃል አደመጡ፤ እውነተኛ ጸጸትም አደረጉ፤ ጥሪውን በማድመጣቸውና በመጸጸታቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ተቀዳጁ፡፡ ምሕረቱ ከሰው አልፎ ለእንስሳትም በሚተርፍ መልኩ ተትረፈረፈ፡፡ የእግዚአብሔር መሐሪነት ዮናስም ሲመሰክር አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፣ ከመዓትም ወደ ምሕረት የምትመልስ አምላክ መሆንህን ዐውቅ ነበር አለ (ዮና 4፡2)፡፡ እግዚአብሔርም አዛኝነቱና መሐሪነቱን ሲገልጽ ነነዌ አንድ መቶ ሃያ ሺ ሕዝብ የሚኖሩባት ግራና ቀኙም ለይተው የማያውቁ ሕፃናትና ብዙ እንስሳት የሚገኙባት ታላቅ ከተማ ናት፤ ታዲያ እኔ ለዚህች ከተማ ማዘን አይገባኝምን? ይላል፡፡
በዚህም የእግዚአብሔር ምሕረትና ርኅራኄ ወሰን የለሽ መሆኑን ታወቀ፡፡ ከትንቢተ ዮናስ ከምንማራቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት በአንድ ዘር ማለትም በእስራኤላውያን ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን ለዓለም ፍጥረታት ሁሉ የተገለጠና ሁሉንም የሚያካትት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህንንም የምንረዳው እግዚአብሔር ከእስራኤል ውጭ ለነበሩት የነነዌ ሕዝቦች እንዲጠፉ ስላልፈለገ ነቢይ መርጦ ወደእነርሱ ላከላቸው፡፡ ዮናስም ወደ ከተማቸው በመሄድ ከተማቸው እንደምትደመሰስ ዐወጀላቸው፤ እነርሱም ይህንን የእግዚአብሔር መልእክተኛ በማድመጥ ከልብ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ መጥፎ ጠባያቸውና የግፍ ሥራቸውን ተዉ፤ እግዚአብሔርም ታድያ እኔ ለዚህች ከተማ ማዘን አይገባኝምን በማለት ምሕረቱን አወረደላቸው(ዮና 3፡4፤ ዮና 4፡11)፡፡
- ዮናስ ከኩብለላው ተጸጽቶ እግዚአብሔርን መታዘዝና ወደ ተላከበት ለመሄድ ተስማማ፤ ለመሆኑ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ምን ይገኛል? መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት ይኖራዋልን?
ዮናስ ለነቢይነት አገልግሎት ሲጠራ ከመታዘዝ ይልቅ መኮብለልን መረጠ፡፡ ከመታዘዝ የሚገኘውን በረከት ከማግኘት ይልቅ የራሱን ፈቃድ ተከትሎ “በሰላም እኖርበት ይሆናል” ብሎ ወዳሰበው አገር ጉዞ ጀመረ፡፡ በጉዞውም ላይ ሳለ ባዕዳን ሕዝብ በሆኑት በመርከቡ ተሳፋሪዎች እጅ ወደቀ፤ መጨረሻውም በሚያሳዝን ሁኔታ በባሕር ላይ መጣል ሆነ፡፡ ገና ጥንት በነቢዩ ሳሙኤል አማካይነት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ምርጥ የበግ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል ብሎ ነበር(1 ሳሙ 15፡ 22)፡፡ እግዚአብሔር ቃሉን ሰምተው ለሚታዘዙለት በረከቱን ይለግሳል፡፡ እግዚአብሔር ለማይታዘዙት ወደ ታዝዞ መንገድ እንዲመለሱ መንገዱን ያመቻችላቸዋል፤ ማንነቱና መልእክቱን ላልተረዱትም የሚረዱበትን መንገድ ይጠርግላቸዋል፡፡ ዮናስም እግዚአብሔር በባሕር ላይ አይኖርም ወይንም ባሕርን አይገዛም በማለት ከመታዘዝ መኮብለል ስለመረጠ እግዚአብሔርም ይህንን የሆነውን ግንዛቤው እንዲሰፋና ወደ ተአዝዞ ሕይወት እንዲመለስ ተከታተለው፡፡ ከማዕበሉ መናወጥ በኋላ ዮናስም ማንነቱን በመርከቡ ተሳፋሪዎች ሲጠየቅ እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ የብስንና ባሕርን የፈጠረውን የሰማይ አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ በማለት ቀድሞ በየብስ ብቻ ተወስኖ የነበረው ዕይታው አሁን ወደ ባሕርም እንደሰፋ ይገልጻል(ዮና 1፡ 9)፡፡
- ትንቢተ ዮናስ ጠቅላላ ይዘቱና የሚጠቀመው አገላለጽ በማየት ሊቃውንት በመጽሐፉ ብዙ ጥያቄዎች ያነሣሉ፤ ሊቃውንት ለምንድን ነው በመጽሐፉ ዙሪያ ላይ እና በታሪኩ እውነታነት ጥርጣሬ የሚያሳዩት?
ትንቢተ ዮናስ ውስጥ በተወሰነ መልኩ የተጋነኑ ነገሮች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ምንም እንኳ በአቀራረቡ የተጋነኑ ነገሮች ያካተተ ቢሆንም ለአንባቢው ብዙ መልእክቶች የሚያስተላልፍ መጽሐፍ ነው፡፡ በእርግጥ ከመጽሐፉ በመጀመሪያ ዕይታ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ከበስተጀርባቸው ግን የራሳቸው የሆነ መልእክት ይዘው የሚገኙ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዮናስ የባሕር ኩብለላ፣ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ያደረገው የሦስት ቀን ቆይታ፣ የነነዌ ንጉሥ ከዙፋኑ ወርዶ ዐመድ ላይ መቀመጥ፣ የነነዌ ሕዝብና እንስሳት ማቅ በመልበስ መጾምና መጸለይ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ዮናስን ከፀሐይ ግለት እንዲድን እግዚአብሔር ያበቀለለትና በአንድ ሌሊት በትል የተበላችው የቅል ተክል፣ የነነዌ ከተማ ስፋትና የሕዝብዋ ብዛት፣ እግዚአብሔር ለነነዌ ሕዝቦች ምሕረት በማድረጉ የታየው የዮናስ መበሳጨትና ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል ብሎ ማማረሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች በማየት ነው ሊቃውንት ጥርጣሬአቸው የሚገልጹትና በታሪኩ እውነታነት የሚጠራጠሩት፡፡ የዛሬዎቹ ሊቃውንት ይጠራጠሩ እንጂ ይህ መልእክት በወቅቱ ለነበረው ሕዝብም ሆነ ዛሬ ላለነው ሁላችን ሰፋ ያለ ትምህርት የሚሰጥ መጽሐፍ ነው፡፡
- አሁን ባለንበት ዘመን ጾመ ነነዌ በመባል የሚታወቅ ጾም አለ፡፡ ይህ ጾም ትንቢተ ዮናስ ውስጥ ከተጠቀሰው የነነዌ ሕዝቦች ታሪክ ጋር የተገናኘ ነው ወይስ የስም መመሳሰል ስላለ ነው፡፡
ጾመ ነነዌ በመባል ለሦስት ቀናት ያህል የሚጾመው ጾም የነነዌ ሕዝቦች የጾሙትን በማሰብ የሚተገበር ጾም ነው፡፡ ይህም የነነዌ ሕዝቦች ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት ለማግኘት በማለት ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ እንስሳትም ሳይቀሩ ጾሙ፤ ተጸጸቱ፤ አዘኑ፤ ጸለዩ፤ በሙሉ ልባቸው ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ይህንን በማሰብ እኛም ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እንጾማለን፤ እንማጸናለን፤ ምሕረትን ለማግኘት በሙሉ ልቦና እግዚአብሔርን እንለምናለን፡፡ ስለዚህ ይህ ጾም በትንቢተ ዮናስ ውስጥ ከተነገረው የነነዌ ሕዘብ ድርጊት ጋር የተያያዘ መሆኑን እንረዳለን፡፡
- በክርስትና እምነት ውስጥ የዓመቱ አቆጣጠር ተከትሎ የሚታወጁ ስንት አጽዋማት አሉ? በካቶሊክ እምነት ውስጥ እንድንጾማቸው የምንገደድባቸው አጽዋማት የትኞቹ ናቸው?
በክርስትና እምነት ውስጥ በተለይም በካቶሊክና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ወይም በእነዚህ ቤተ ክርስቲያን የሚታወቁትና የሚታወጁት አጽዋማት የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ጾመ ድኅነት(ረቡዕና ዓርብ)፦ ይህ ጾም ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለው ጊዜ ግን አይጾምም፤ በተመሳሳይ መልኩ ልደትና ጥምቀት ረቡና ዓርብ ዕለት ከዋሉ ጾመ ገሃድ የተባለው በዋዜማው ቀን ስለሚጾም አይጾሙም፡፡ ረቡዕ አይሁዶች ተሰባስበው ኢየሱስን ለመያዝ የተማከሩበትና የወሰኑበት ቀን ነው፤ ዓርብ ደግሞ የተሰቀለበት ቀን ስለሆነ ረቡዕና ዓርብ ይጾማል፡፡
- ጾመ ጽጌ ወይም ጾመ ቁስቋም(ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ድረስ ይጾማል)፡፡
- ጾመ ነቢያት(ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 ድረስ ይጾማል)፤ ነቢያት የነቢይነት ተግባራቸው በተወጡበት ዘመናት ስለ ክርስቶስ መምጣት ይጾሙና ይጸልዩ ነበር፡፡ በመሆኑም የእነርሱ ምሳሌ በመከተል የክርስቶስ ልደት ከመድረሱ ቀደም ተብሎ ለዝግጅት የሚጾም ነው፡፡
- ጾመ ገሃድ ወይም የገና ጾም(ታኅሣሥ 28 ማለትም የልደት ዋዜማ ላይ ይጾማል)፤ ለጌታ ልደት ዝግጅት የሚጾም ነው፡፡
- ጾመ ገሃድ ወይም የጥምቀት ጾም(ጥር 10 ማለትም የጥምቀት ዋዜማ ላይ ይጾማል)፤ ለጥምቀት ዝግጅት የሚጾም ነው፡፡
- ጾመ ነነዌ፦ ለሦስት ቀናት(ከሰኞ እስከ ረቡዕ) የሚጾም ሲሆን የሚጾመውም ከዐቢይ ጾም ሁለት ሳምንታት በፊት ነው፡፡
- ጾመ ሕርቃል፦ የዐቢይ(ሁዳዴ ወይም አርብዓ) ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ላይ የሚጾመው ጾም ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከዐቢይ(ከሁዳዴ ወይም አርብዓ) ጾም ጋር አብሮ ይቈጠራል፡፡ ሕርቃል በ614 ዓ.ም አካባቢ የቤዛንታይን ንጉሥ ሆኖ የገዛ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት ከጌታ መስቀል ጋር የተያያዘ ትርጉም ስላለው ነው፡፡ ይህም በወቅቱ ፋርሶች(የዛሬ ኢራናውያን) ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወሰዱት፡፡ ሕርቃል ወደ ፋርስ በመሄድ ተዋግቶ መስቀሉን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በጦርነቱ ወቅት በፈጸመው ነገር ሁሉ ሕዝቡ ተደሰቱ፤ ነገር ግን በጦርነት ወቅት ስለፈሰሰው ደም ስለ ሕርቃን ኃጢአት እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግ ዘንድ ሕዝቡ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ተማጸኑ፡፡ በዚህ ምክንያት የጾሙ ሳምንት በእርሱ ስም ተሰየመ፡፡ ጾሙ ግን በፈቃደኝነት የሚጾም ጾም ነው፡፡
- ዐቢይ(ሁዳዴ ወይም አርብዓ) ጾም፦ ጌ.ኢ.ክ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የዓርባ ቀናት ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ስምንት ሳምንታት ወይም ስልሳ ቀናት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም የሚሆነው የመጀመሪያው ሳምንት ማለትም ጾመ ሕርቃል እና የመጨረሻው ሳምንት ጾመ ሕማማት ስለሚያካትት ነው፡፡ ዓርባ ጾም የሚባለው ሁለቱ ሳምንታት ሳያካትት ነው፡፡
- ጾመ ሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም፦ ይህ ጾም ከጰራቅሊጦስ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ በሰኔ ወር እና በሐምሌ ወር ውስጥ እስከ ሐምሌ 5 ድረስ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉ በኋላ ለስብከት ወንጌል ከመሄዳቸው በፊት ለዝግጅት የጾሙት ጾም ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በማሰብና የሐዋርያትን ምሳሌነት በመከተል የሚጾም ጾም ነው፡፡
- ጾመ ፍልሰታ ለማርያም፦ ይህ ጾም ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ድረስ የሚጾም ጾም ነው፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት አገላለጽ እመቤታችን ካረፈች በኋላ ሐዋርያት ሊቀብርዋት ሲሄዱ አይሁዶች በታተንዋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ መላእክት የእመቤታችን ሥጋ ወስደው በገነት አኖሩት፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ እመቤታችንን በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ሆና በራእይ እንደሚያያት ለሐዋርያት ነገራቸው፡፡ ሐዋርያቶችም እንዴት እመቤታችን ለዮሐንስ ብቻ ተገልጣ ለእኛ አትገለጥም በማለት ጾሙ፤ ጸለዩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸው ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ አርጋለች የሚል ትውፊት መሠረት ያደረገ ጾም ነው፡፡ ይህ ትንታኔ ተጽፎ የምናገኘው ነሐሴ 16 በሚነበበው በስንክሳርና በተአምረ ማርያም ውስጥ ነው፡፡ በ15 የጾም ቀናት የእመቤታችንን አማላጅነት ይዘን እግዚአብሔርን እንለምናለን፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ጾም በብዙ የአገራችን ክፍሎች ከሕጻን እስከ ሽማግሌ ያለው የማኅበረሰቡ ክፍል የሚተገብረው የጾም፣ የጸሎትና የሱባኤ ወቅት ነው፡፡
ከእነዚህ አጽዋማት መካከል በፈቃድ እና በግዴታ ማለትም በቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ መሠረት የሚጾሙ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለምዶ እና በቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ የሚጾሙት ጾመ ድኅነት(ረቡዕና ዓርብ)፣ ጾመ ገሃድ(ሁለቱም)፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም(ጾመ ሕርቃልን ጨምሮ) እና ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ናቸው፡፡ ሌሎቹ በፈቃደኝነት የሚተገበሩ ናቸው፡፡
የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ
መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ
የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ
ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች
- የዮናስ ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት እንዲሁም ለነቢይነት በተጠራ ጊዜ ያሳየው ታዛዥነት በተመለከተ ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?
ሀ) ዮናስ ከመጨረሻዎቹ ነቢያቶች ከተባሉት በተመሳሳይ ወቅት የኖረ ነቢይ ነው፡፡ ለ) በወቅቱ ባሕር የክፉ መናፍስት ዋና መኖሪያ ቦታ ሆኖ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር እንደነበር ያምኑ ነበር፡፡ ሐ)ዮናስ ወደ አሦር ምድር እንዲላክ ሲጠራ እርሱ ግን በተቃራኒው አቅጣጫ ወደሚገኘው ወደ ተርሴስ ኰበለለ፡፡ መ)ነነዌ ከእስራኤል ጥንታውያን ከተሞች አንድዋ ነች፡፡ ሠ) ዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት በጸጥታ ቆየ፡፡
- የዮናስ ኩብለላና የእግዚአብሔር ክትትል፣ የዮናስ የነቢይነት መልእክትና የነነዌ ሕዝቦች ምላሽ በተመለከተ ትክክለኛው የትኛውን ነው?
ሀ)ዮናስ ከመርከቡ ተወርውሮ ወደ ባሕር ከተጣለ በኋላ ተጓዦቹ ወደ አማልክቶቻቸው እየጸለዩ ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ለ)ዓሣው ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ ከተፋው በኋላ ዮናስ አሁንም ወደተላከበት ለመሄድና ላለመሄድ ብዙ አመነታ፡፡ ሐ) የአገሪቱ ንጉሥ የዮናስን የትንቢት ቃል ሲሰማ ተጸጸተ፤ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ጾመ፤ ጸለየ፡፡ መ)እግዚአብሔር የየብስ ብቻ ሳይሆን የባሕርና በውስጥዋም ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ ገዢና አዛዥ መሆኑን ማስተማር ስለፈለገ ዮናስን ተከታትሎ ይህንን መረዳት በሚችል መልኩ ቀረበው፡፡ ሠ)የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በዮናስ መልእክት እጅግ በጣም ተደናገጡ፤ ፈሩ እርምጃ ለመውስድ ግን አልፈጠኑም፡፡
- ዮናስ ለነቢይነት አገልግሎት ወደ ነነዌ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ተነገረው፤ ለመሆኑ እንደ ትንቢተ ዮናስ አገላለጽ በወቅቱ በነነዌ ከተማ ምን ያህል ሕዝብ ይኖር ነበር? (ይህንን ለመመለስ ትንቢተ ዮናስን ማንበብ ያስፈልጋል)
ሀ) አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሕዝብ ለ) አንድ መቶ ዐሥር ሺህ ሕዝብ ሐ) አንድ መቶ ሠላሳ ሺህ ሕዝብ መ) አንድ መቶ አርባ ሺህ ሕዝብ ሠ) አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ሕዝብ፡፡
- ዮናስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ነነዌ ከሄደ በኋላ ለነነዌ ሕዝብ በዐዋጅ መልክ የተናገራቸው አንድ ዓረፍተ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር ምን የሚል ነው? በየትኛው ምዕራፍና ቁጥር ላይ ይገኛል?
- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የነቢዩ ዮናስ ታሪክ የሚመሳሰሉበት ነገር አለ ብለው ያምናሉ? ምላሽዎ አዎን ከሆነ የሚመሳሰሉበትን ነጥብ ይግለጹ፡፡
- በክርስትና እምነት ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊትና በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ብዙ አጽዋማት እንዳሉ ከላይ ተዘርዝረዋል፡፡ ለመሆኑ ለእርስዎ ወይም በእርስዎ እይታ(ግንዛቤ)፦
- ጾም ማለት ምን ማለት ነው?
- ዋናውና ትልቁ ጾም መሆን ያለበት የትኛው ነው? ማለትም ዋናው መጾም ያለበት ምንድን ነው? ምግብ ወይስ……
- ከላይ ከተዘረዘሩት አጽዋማት መካከል ለእርስዎ የበለጠ ትርጉም የሚሰጥዎትና ለመጾምም የሚፈልጉት የትኛው ጾም ነው? ለምን?