ት/ርት ፴፫ - የትንቢተ ዘካርያስ ጥናት
- Category: የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
- Published: Monday, 19 October 2015 10:26
- Written by Super User
- Hits: 11527
- 19 Oct
ክፍል ሦስት (ትምህርት ሠላሳ ሦስት) - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት
ትንቢተ ዘካርያስ
>> ዘካርያስ ተወልዶ ያደገው፣ ለነቢይነት የተጠራውና የነቢይነት አገልግሎቱን የተወጣው የትና መቼ ነበር?
ዘካርያስ የሚለው ስም “ዛካር” (ማስታወስ፣ መዘከር) እና “ያህ” (ከእግዚአብሔር መጠሪያ ስሞች አንዱ) የሚሉትን የሁለት ቃላቶች ጥምር ሲሆን ትርጓሜውም “እግዚአብሔር አስታወሰ” ወይም “እግዚአብሔር አሰበ” ማለት ነው፡፡ ምንአልባት ዘካርያስ የባቢሎን የስደት ኑሮ መጨረሻ አካባቢ (539) ተወልዶ ወላጆቹ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር እኛን ሕዝቦቹ ከስደትና ከጉስቁልና ኑሮአችን ነፃ ሊያወጣን አሰበን፤ እኛን ሕዝቦቹ አስታወሰን ከሚለው ጋር በተያያዘ መልኩ የተሰየመ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ዘካርያስ የዒዶ ልጅ መሆኑን ቢገለጽም በሌላ መልኩ ደግሞ የቤሬክያ ልጅ እንደሆነም ተነግሯል(ዘካ 1፡1)፡፡ ስለዚህ ወላጅ አባቱ ዒዶ ወይም ቤሬክያ መሆኑን በትክክል ባይታወቅም አንዳንድ ሊቃውንት ግን ቤሬክያ የዘካርያስ ወላጅ አባቱ፤ ዒዶ ግን መንፈሳዊ አባቱ ሊሆን እንደሚችል መላ ይመታሉ፡፡ ሌሎች ሊቃውንቶች ደግሞ የመጽሐፉ የመጀመርያው ክፍል(ዘካ 1-8) በዒዶ ልጅ ዘካርያስ የተጻፈ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል(ዘካ 8-14) ደግሞ በቤሬክያ ልጅ ዘካርያስ የተጻፈ ነው፤ በኋላ ግን መጽሐፉ ወደ አንድ ጥንቅር ወይም በአንድ መልክ በተዋቀረ ጊዜ ዒዶና ቤሬክያ እንደ አባት በአንድነት ተጠቅሰዋል በማለት መላ ምታቸውን ያቀርባሉ፡፡
ነቢዩ ዘካርያስ የኖረውና የነቢይነት ተግባሩን የተወጣው ነቢዩ ሐጌ በኖረበትና የነቢይነት ተግባሩን ባከናወነበት ተመሳሳይ ወቅት ነው፡፡ ዘካርያስ ለነቢይነት አገልግሎት እንዴት እንደተጠራ፣ የቤተሰባዊ ኑሮው ምን እንደሚመስል፣ የት እንደኖረና የነቢይነት አገልግሎቱ የት እንደተወጣ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በመጽሐፉ ስለ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ እንዲሁም በውስጥዋም ስለሚኖሩ እቃዎች፣ ስለ ሕገ እግዚአብሔር፣ ስለ ይሁዳ ሕዝቦች፣ በቤተ መቅደስ ስለሚያገለግሉት ሊቀ ካህናቶችና የአገልግሎት ልብሶቻቸው ብዙ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚናገር የነቢይነት ተግባሩን የተወጣው በኢየሩሳሌም አካባቢ እንደሆነና እሱም ከወገነ ክህነት በኩል ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በእርግጥ ዘካርያስ ኢየሩሳሌምንና አካባቢዋ በደንብ እንደሚያውቀው ከመጽሐፉ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ መጽሐፈ ነህምያ አገላለጽ ደግሞ ዘካርያስ ከይሁዳ ዘርና ከሌዋውያን ወገን እንደነበረ እንረዳለን (ነህ 11)፡፡
>> የትንቢተ ዘካርያስ ጥንቅር፣ ይዘትና የትንቢት ቃሉ ትኩረት ምን ይመስላል?
ትንቢተ ዘካርያስ ከዐሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት መጻሕፍቶች በስፋቱ ወይም ብዙ ምዕራፎች በማከተቱ ትልቁና የመጀመሪያ ያደርገዋል፡፡ ጸሐፊው፣ የተጻፈበት ትክክለኛ ጊዜ፣ የመጽሐፉ ወጥነትና የመጽሐፉ ይዘት በተመለከተ ግን ከሁሉም የነቢያት መጻሕፍቶች በላይ የተወሳሰበ መሆኑን በመጽሐፉ ዙሪያ ጥናታቸው ያደርጉ ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ ከመጽሐፉ ይዘት በደንብ መረዳት እንደሚቻለው ትንቢተ ዘካርያስ ግልጽ የሆኑ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም ከምዕራፍ 1-8 እና ከ9-14 ናቸው፡፡ የመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል ከባቢሎን ስደት በኋላ ኢየሩሳሌም በድጋሚ ትታደስበት ወይም ትገነባበት በነበረበት ወቅት በራሱ በዘካርያስ የተጻፈ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ ሌሎች አጠናቅረው መጽሐፉ ውስጥ ያካተቱት እንደሆነ ከይዘቱና ከአጻጻፍ ስልቱ መረዳት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው የባቢሎናውያን አገዛዝ ወደ መውደቂያው አካባቢና በእነዘሩባቤል አማካይነት የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የመታደስ ሥራ መጀመሪያው አካባቢ ነው፡፡ ይህም ማለት ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስት መቶ ሃያ እስከ አምስት መቶ ዐሥራ ስምንት አካባቢ እንደሆነ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል(4፡6-10፤ 6፡12-13)፡፡
የመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል (ዘካ 1-8) በራእይ የተሞላ ሆኖ ስለ ኢየሩሳሌም መታደስ፣ ስለ ቤተ መቅደሱ በድጋሚ መሠራት፣ ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ መንጻት፣ እግዚአብሔር ስለሚቀበለው ትክክለኛ ጾምና ወደፊት ስለሚመጣው የመሲሑ ዘመን የሚናገር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይህ የመጀመሪያው ክፍል ስምንት ራእዮች ያሉት ሲሆን ከራእዮቹ ውጪ ከስደት በሚመለሱትና በሚኖሩት የወደፊት ሕይወት ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ትምህርቶች ተካተዋል፡፡ እነዚህ ራእዮች አብዛኛው ትኩረታቸው በስደተኛው ሕዝብና በኢየሩሳሌም የወደፊቱ ብልጽግናና ክብር ላይ ያተኮሩ ሆነው አንዱ ከሌላው ተከታትለው የተገለጹ ናቸው፡፡
የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል (ዘካ 9-14) አብዛኛውን ትኩረት ግን ስለሚመጣው መሲሕና ስለመጨረሻው ፍርድ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የዘካርያስ ስም ምንም አልተጠቀሰም፤ ተግባራቱ የተከናወኑበት ጊዜም ከመጀመርያው ክፍል ፈጽሞ የተለየ ወቅት ነው፤ ምንም ዓይነት የተጠቀሱ ቀናትም ይሁን የመሪዎች ስም የለም፤ ቤተ መቅደስም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ ሆኖ በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል(ዘካ 9፡8 ፤ 11፡13-14)፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ነቢዩ ራሱን እንደ ተመታና እንደ ተነቀፈ እረኛ ሆኖ ያቀርባል፤ ጸሐፊው የተጠቀማቸው ቃላትና ገለጻዎች ከመጀመርያው ክፍል የተለዩ ናቸው፡፡
ምንም እንኳ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ክፍል መካከል በቃላት አጠቃቀም፣ በአነጋገር ዘይቤአቸው፣ ባካተቷቸው ዋና ዋና የትንቢት ቃላት፣ ትንቢቱ በተነገሩበት የጊዜ ሁኔታ፣ በተካተቱት ገጸ ባሕርያቶች፣ በሚጠቅሷቸው ቦታዎች፣ በሚሰጡት ታሪካዊ መረጃዎችና በሌሎችም ተጨማሪ በሆኑ ነገሮች ላይ ግልጽ የሆነ ልዩነት ቢኖርም የሚገናኙበት የጋራ የሆኑ ብዙ ፍሬ አሳቦች እንዳሉም ግልጽ ነው፡፡
>> ነቢዩ ዘካርያስ ከተናገራቸው የትንቢት ቃል ውስጥ የንስሓ ጥሪ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የንስሓ ጥሪ እንዴት ይገልጸዋል?
መጽሐፉ ገና ከጅማሬው አሁን ግን እናንተን የምላችሁ ይህ ነው ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳሁ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁን ዱካ አትከተሉ በማለት ከእግዚአብሔር ለሕዝቡ የተደረገውን የንስሓ ጥሪ በማሰማት ይጀምራል (1፡3-5)፡፡ ይህን የጥሪ ቃል ነቢዩ ገና ከነቢይነት አገልግሎት ጅማሬው በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚያሰማው የቀድሞ አባቶቻቸው የተሳሳተ አካሄድ እንዳይከተሉና እነርሱም አሰቃቂ መከራ እንዳይደርስባቸው ያስጠነቅቃቸዋል(ዘካ 1፡5)፡፡ በዚህ የመጀመሪያ የነቢይነት ተግባሩ የቀድሞ አባቶቻቸው ነቢያቶች ደጋግመው “ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ” ተመለሱ ብለው ቢያስጠነቅቋቸውም ሊመለሱ አልቻሉም፤ አሁንም በእኔ በመልእክተኛው አማካይነት የሚያስተላልፍላችሁ ጥሪ ይህ ነው፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንደ አካሄዳቸውና እንደ ሥራቸው ተገቢ ቅጣት ወስኖ እንደሰጣቸው እናንተንም እንዳይሰጣችሁ ይህንን ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ ሰምታችሁ ተመለሱ ይላቸዋል(ዘካ 1፡5)፡፡
ይህንን የንስሓ ጥሪ ነቢዩ ዘካርያስ በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ካሰማው በኋላ በመጽሐፉ መጨረሻ ክፍል በድጋሚ በተመሳሳይ መልኩ ያቀርበዋል (ዘካ 7፡8-14 እና ዘካ 8፡13-17)፡፡ በመጨረሻው ክፍል ለሁለተኛ ጊዜ ሕዝቤ ግን በእልኸኛነት አናዳምጥም ብለው አእምሮአቸው አጨለሙ፤ ልባቸውንም እንደ አለት ድንጋይ አጠነከሩ፤ ጥንት በነበሩበት ነቢያት አማካይነት በመንፈሴ የሰጠኋቸውን ትእዛዝ ሁሉ በእልኸኛነት አናዳምጥም በማለታቸው ምክንያት እኔ በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጣሁ በማለት የቀድሞ አባቶቻቸውን ድርጊት ዛሬም በእነርሱ ላይ እንዳይደገም ያስጠነቅቃቸዋል (ዘካ 7፡11)፡፡ በቀድሞ አባቶቻቸው የደረሰውን እየተናገረ ማስጠንቀቅና ወደ ንስሓ መጥራት ብቻ ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮአቸው እንዴት ፈሪሃ እግዚአብሔር በሕይወታቸው አድሮ መኖር እንዳለባቸው ያስገነዝባቸዋል፡፡ ስለዚህ የቀድሞ አባቶቻቸውን ሕይወት መማሪያ አድርገው በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርጉትን የሕይወት ጉዞአቸውን አስተካክለው እንዲኖሩ እያሳሰባቸው ይህ ሳያደርጉ ቀርተው በእልኸኛነት አናዳምጥም የሚሉ ከሆነ ግን እግዚአብሔርም የእነርሱ ጸሎት አያዳምጥም፤ የቀድሞ አባቶቻቸው አገራቸውና ለም መሬታቸው አጥተው እንደተሰደዱ እነርሱም ዳግመኛ ይህንን ዕድል ሊገጥማቸው እንደሚችል ያስገነዝባቸዋል (ዘካ 7፡13-14)፡፡
>> በትንቢተ ሐጌ እና በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥ ስለ ዘሩባቤል ተነግሮአል፡፡ ለመሆኑ ዘሩባቤል ማን ነው?
ዘሩባቤል “ዛር” እና “ባቤል” የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ትርጓሜውም “የባቢሎን” ዘር ማለት ነው፡፡ ዘሩባቤል ከዳዊት ትውልድ ሆኖ የምርኮኛው የዮአኪን የልጅ ልጅ የይሁዳ ገዥ የነበረው የሻልቱኤል ልጅ የነበረና ባቢሎን ውስጥ የተወለደ ነበር (1 ዜ.መ 3፡16-19)፡፡ ከታሪክ አኳያ ዘሩባቤል ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ የይሁዳ አለቃ በመሆን ቤተ መቅደስ በድጋሚ ያሠራ ንጉሥ እንደሆነ ይታወቃል (ዕዝ 3፡2፤ ሐጌ 1፡1 እና 14)፡፡ በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥም ዘሩባቤል ከኢየሩሳሌም፣ ከቤተ መቅደስዋና ከሕዝብዋም ዳግመኛ ግንባታና ማንሰራራት ጋር በተያያዘ መልኩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ ይህንን ተግባሩ ግን ገና ቀድሞውኑ በትንቢት መልክ ቅርንጫፍ ተብሎ የሚጠራው ሰው ባለበት ስፍራ በቅሎ ገናና ይሆናል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራል፡፡ በተጨማሪም ቤተ መቅደሱን አድሶ የሚሠራና ለንጉሥነት የሚገባውን ክብር የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተዳድራል፤ አንድ ካህን በዙፋኑ አጠገብ ይቆማል፤ ሁለቱም አብረው በስምምነትና በሰላም ይሠራሉ ተብሎ ተነግሮለት ነበር (ዘካ 6፡12-13)፡፡
ይህ ወደፊት እንደሚመጣ ወይም እንደሚነሣ የተነገረለት “ቅርንጫፍ” ተብሎ የተጠራው አገልጋይ ወይም መልእክተኛ ዘሩባቤል እንደሆነ ከትንቢት ቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ዘሩባቤልም ጊዜው ደርሶ በወቅቱ ኃይለኛና ብርቱ የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ድል የምትነሣው በመንፈሴ እንጂ በአንተ ብርታትና ኃይል አይደለም ብሎ አስጠንቅቆታል (ዘካ 4፡7)፡፡ ይህ ከሆነ በፊቱ እንደ ተራራ ተደቅኖ የነበረውን መሰናክል ሁሉ እንደሚወገድና ቤተ መቅደሱንም መልሶ እንደሚሠራ መላኩ በነቢዩ ዘካርያስ አማካይነት ነግሮታል (ዘካ 4፡7)፡፡ በዚህም መሠረት ዘሩባቤል ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ የቤተ መቅደስ መሠረት እንዳኖረ በእድሳትዋም በዋናነት እንደተሳተፈ ተገልጿል(ሐጌ 1፡14)፡፡ ስለዚህ ዘሩባቤል ለኢየሩሳሌም መታነጽና ቤተ መቅደስዋም በድጋሚ መሠራት ዋና ተዋናይ የነበረ መሪ ነው፡፡ ነገር ግን የዘሩባቤል ተግባርና የመጨረሻው ሁኔታ ከትንቢተ ዘካርያስ ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ዘሩባቤል ቤተ መቅደሱን መልሶ እንደሚሠራ እንዲያውም ሕንጻውን ሠርቶ እንደሚጨርስ ተገልጿል (ዘካ 4፡6-10)፤ ነገር ግን ዘሩባቤል ቤተ መቅደሱን ከጨረሰ በኋላ ወደ ባቢሎን ተመልሶ ይሂድ ወይም እዛው ኢየሩሳሌም ይኑር ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
>> ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ኢያሱና በኢያሱ ፊት ስለነበረው ከሳሹ ሰይጣን ይናገራል፤ ኢያሱን ከሳሹ ሰይጣን ማን ናቸው?
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ሊቀ ካህናቱ ባየው ራእይ ውስጥ ኢያሱ እንደ ሊቀ ካህናት ሆኖ በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ይህ ኢያሱ ከሙሴ በኋላ የእስራኤል መሪ የነበረው የነዌ ልጅ ሳይሆን ከባቢሎን ምርኮ የተመለሰው የእስራኤል ካህናት አለቃ የነበረው የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ነው፡፡ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ በኢየሩሳሌም ከዘሩባቤል ጋር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ጀምረው ብዙ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ወደ ፍጻሜ ያደረሰ የካህናት አለቃ ነበር(ዕዝ 2፡1፤ 3፡2 እና 8)፡፡ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዳግመኛ ግንባታ ባደረገው ከፍተኛ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ መልኩ ነቢዩ ዘካርያስ ልዩ ቦታና ክብር ሰጥቶት በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ እንደተገኘ ያቀርበዋል፡፡ በዚህ ራእይ ውስጥ የእግዚአብሔር መልአክ ከሳሹ ሰይጣንን ኢየሩሳሌምን የሚወድ እግዚአብሔር ይገሥጽህ! ይህ ሰው እኮ ከእሳት ውስጥ ተርፎ እንደወጣ እንጨት ነው በማለት ኢያሱ የባቢሎን ስደትና የችግር ጊዜ አልፎ ቤተ መቅደስ ያደሰና በዚህም ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ጠበቃና ተቆርቋሪ ያለው አድርጎ ያቀርበዋል(ዘካ 3፡2)፡፡ እዚህ ላይ ኢያሱን ለመክሰስ በስተቀኙ ቆሞ ስለነበረው ሰይጣን ኢያሱን ለመክሰስ በስተቀኙ ከመቆሙ ሌላ ምንም ዓይነት ተግባር ሲተገብር አይታይም፤ ስሙንም በድጋሚ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ የርሱን ማንነት በተመለከተ ምንም ዓይት ተጨማሪ የሆነ መረጃ ስለሌለ ተግባሩንም ሆነ ማንነቱን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡
ኢያሱ ኢየሩሳሌም ውስጥ በተለይም ቤተ መቅደሱ በተመለከተ ላከናወነው ተግባር በእግዚአብሔር የተቀዳጀው ትልቅ ክብር ሲገልጽ ኢያሱ ቀድሞ “ያደፈ ልብስ” ለብሶ እንደነበር ይናገርና መላኩ ግን በፊቱ ቆመው የሚያገለግሉትን “ይህን ያደፈ ልብስ አውልቁለት” ብሎ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአኩ ለኢያሱ “እነሆ በደልህን አስወግጄልሃለሁ፤ አዲስ የክብር ልብስም አለብስሃለሁ” በማለት ክብር እንደተቀዳጀ ያረጋግጥለታል(ዘካ 3፡3-4)፡፡ “ኢያሱ ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር” ይላል፤ ይህ ያደፈ ልብስ መልበሱ ምንአልባትም ባቢሎን ውስጥ በስደት በነበረበት ጊዜ ልክ እንደሌሎች ወገኖቹ በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነቱ ቀዝቅዞ በጣዖት አምልኮ ተሳትፎ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ሰይጣንም ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ኢያሱን ይከሳል፤ መልአኩ ግን ያንን ያደፈውን የቀድሞ ልብሱ ወልቆለት አዲስ የክብር ልብስ እንደሚለብስ ያረጋግጥለታል፡፡ በእርግጥም ያንን የክብር ልብስ ከመልበሱ በፊት መልአኩ “እነሆ በደልህን አስወግጄልሃለሁ” በማለት ከቀድሞ ሕይወቱ እንደተለያየ ካረጋገጠለት በኋላ ነው “አዲስ የክብር ልብስ” እንዲለብስ የተናገረው፡፡
ነገር ግን ከዚህም በላይ ክብር እንዲያገኝ ማለትም በመላእክቶቹ ፊት መግባትና መውጣት እንዲችል፣ በእግዚአብሔርና በአደባባዮቹ ላይ ያለውም ሥልጣንም የጸና እንዲሆን የእግዚአብሔርን ሕግ መፈጸምና የታዘዘውንም ሁሉ ማድረግ እንዳለበት መልአኩ በደንብ አስጠንቅቆታል(ዘካ 3፡6)፡፡ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ከብርና ከወርቅ የተሠራ ዘውድ በራሱ ላይ ተቀዳጀ፤ ወደፊት ቤተ መቅደሱ እንደገና ከሚሠራው ንጉሥ ተባብሮ መሥራትም እንዳለበት ተነገረው(ዘካ 6፡11-12)፡፡
በአጠቃላይ ነቢዩ ዘካርያስ ኢያሱ በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ትልቅ ክብር ያገኘ መሆኑን የሚገልጸው ለኢየሩሳሌምና ለቤተ መቅደስዋ መታደስ ባደረገው አስተዋጾ ምክንያት ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ነቢዩ ዘካርያስ ለኢየሩሳሌም፣ ለነዋሪዎችዋና ለቤተ መቅደሰ ትልቅ ቦታ የሰጠ ነቢይ ስለሆነ ስለእነዚህ ዳግመኛ መገንባት ተባባሪ ለሆነ በሙሉ መልካም ዋጋውን በእግዚአብሔር ፊት እንደሚያገኝ፣ በሕይወቱም የተባረኩ ጊዜያት እንደሚኖረውና ምንም ከሳሽ ወይም ተቃዋሚ ቢነሣበት እንኳ እግዚአብሔር በጥበቃው ሥር እንደሚያደርገው ለመግለጽ በማሰብ ነው ስለ ሊቀ ካህናቱ ራእይ እንዳየ የሚገልጸው፡፡
>> ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ጾም ሕዝቡን አስተምሮአል፡፡ ለመሆኑ እግዚአብሔር የሚቀበለው ትክክለኛ ጾም ምን ዓይነት ጾም ነው?
ከጥንት ጀምሮ በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው ጾም በሃይማኖት ምክንያት ያለ ምግብና ያለ መጠጥ በተለይም ከሚያሰክር መጠጥ ተከልክሎ መዋልን ያመለክታል(አስ 4፡16፤ ዳን 10፡2 እና 3)፡፡ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደጾመ እንዲሁም እስራኤላውያን እንዲጾሙ እንደታዘዙ ይታወቃል(ዘዳ 9፡9፤ ዘሌ 16፡29-31)፡፡ ጾም የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ በግል ወይም በማኅበር ሊጾም ይችላል(2 ሳ 12፡22፤ መሳ 20፡26)፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፈሪሳውያን ሰኞና ሐሙስ ይጾሙ እንደነበር ይታወቃል(ሉቃ 18፡12)፡፡ ከነቢዩ ዘካርያስ እንደምንረዳው ይህ ጾም በባቢሎን ምርኮ ጊዜና ከስደት ሕይወት መልስ በኋላ አራት የጾም ጊዜያት እንደነበሩ ነው(ዘካ 7፡3፤ 8፡18)፡፡
ባቢሎን ውስጥ ለሰባ ዓመታት ያህል በስደት በነበሩበት ጊዜ ዋናው የጾማቸው ምክንያት የነበረውም የእግዚአብሔር በረከት ይወርድ ዘንድ፣ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ ማዘናቸውን ለመግለጥና የእግዚአብሔር ምሕረትን ለማግኘት ነበር(ዘካ 7፡3)፡፡ እግዚአብሔር ግን ጾማቸው እንዳልተቀበለላቸው ነቢዩ ያስገነዝባል፤ ምክንያቱም የጾሙትና ያዘኑት እግዚአብሔርን ለማክበር ሳይሆን ለራሳቸው ብቻ ነበር(ዘካ 7፡5-6)፡፡ ከዚህ ይልቅ ነቢዩ ዘካርያስ ለምን ስደት እንደደረሰባቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ በተገለጠለት መሠረት ያብራራላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እልኸኛነት፣ እግዚአብሔርን አለማድመጥ፣ ልብን እንደ አለት ድንጋይ ማጠንከር፣ በነቢያቶች አማካኝነት የተሰጣቸውን ትእዛዛት ቸል ማለት ለስደት እንደዳረጋቸውና ከጾም ይልቅ እግዚአብሔር ታዛዥነትን እንደሚወድ ያስገነዝባል(ዘካ 7፡11-12)፡፡ በቀጣዩ ክፍል ግን ነቢዩ ዘካርያስ እንደሚናገረው አይሁዳውያን በባቢሎን የስደት ኑሮአቸው ወቅት ይተገብሩት የነበረው አራት የጾም ጊዜያት ወደፊት የተድላና የደስታ በዓል እንደሚሆኑላቸው ያበስራቸዋል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በምሕረቱ ሕዝቡን ስለጎበኘና ሊባርካቸው ስለወሰነ ነው(ዘካ 8፡15 እና 19)፡፡
>> በትንቢተ ዘካርያስ የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል (ከምዕራፍ 9 እስከ 14) ውስጥ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን አጐራባች አገራት ላይ እንደሚፈርድ ይናገራል፡፡ ለመሆኑ እንደ ነቢዩ ዘካርያስ አገላለጽ ይህ ፍርድ በምን ምክንያት የሚደርግ ነው?
በዚህ ክፍል መግቢያ ላይ ወደ ዐሥር የሚጠጉ የእስራኤል አጎራባች አገራት ተጠቅሰው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሐድራክ፣ ደማስቆ፣ ሐማት፣ ጢሮስ፣ ሲዶና፣ አስቀሎና፣ ጋዛ፣ ዔቅሮን፣ አሽዶድና በአጠቃላይ ፍልስጤማውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ከተሞች ወደፊት ከባድ ፍርድና የውርደት ጊዜ እንደሚጠብቃቸውና ከእነርሱም ከፍርድ የሚተርፉት ከአይሁዳውያን ጋር ተቀላቅለው እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡ ፍርዱም የሰበሰቡት ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌላው ሀብታቸው በሙሉ እግዚአብሔር ወስዶ ወደ ባሕር እንዲጣል ያደርገዋል፤ ሕዝቦቻቸው በሙሉ እየተሸበሩ በጭንቀትና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ተዋርደውና ተበታትነው ይኖራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ያጣሉ፤ ከተሞቻቸውም በእሳት ይጋያሉ(ዘካ 9፡1-7)፡፡ ይህን ሁሉ ፍርድና ቅጣት በእነዚህ አገራት ላይ የሚደረግበት ዋናውና ብቸኛው ምክንያት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስለጨቆኑ፣ መብታቸውንም ስለረገጡና ስላሠቃዩዋቸው መሆኑን ነቢዩ ያስገነዝባል(ዘካ 9፡8)፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገራት የእግዚአብሔርን ሕዝብ መቼ፣ እንዴት፣ ለምንና በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳሰቃዩዋቸውና በደል እንደፈጸሙባቸው ነቢዩ አይገልጽም፡፡ ብቻ እግዚአብሔር ምድሩን ለመጠበቅና ሕዝቦቹም ከሥቃያቸው ለማዳን ስለወሰነ እነዚህ ሕዝቦች ይቀጣሉ፤ በዚህም የእስራኤል ነገዶች ብቻ ሳይሆኑ የሰው ሁሉ ዐይን ወደ እግዚአብሔር የሚመለከትበት ጊዜ ይሆናል፡፡
ቀጥሎም በመጽሐፉ መጨረሻ ክፍል(ዘካ 14) ላይ የፍርድ ቀን እንደደረሰ በድጋሚ ያበስርና ይህንን የኢየሩሳሌምና የአሕዛብ መንግሥታት ላይ ስለሚደረገው የመጨረሻው የእግዚአብሔር ውሳኔ ምን እንደሚሆን ያሳውቃል፡፡ በመጀመሪያ የአሕዛብ መንግሥታት ኢየሩሳሌምን ለመበዝበዝ ተሰብስበው ይመጣሉ፤ ከተማዪቱም ትያዛለች፤ ቤቶች ይመዘበራሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከሕዝቡም እኩሌታው ተማርኮ ይሄዳል(ዘካ 14፡1-2)፡፡ ይህንን የሕዝቡን በደል የተመለከተው እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ለመውጋት ይነሣል፤ ቅዱሳኑንም አስከትሎ ወደ ሕዝቡ ይመጣል(ዘካ 14፡3 እና 5)፡፡ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይነግሣል፤ ሰዎችም አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያምናሉ፤ የእርሱንም ስም ብቻ ያመሰግናሉ(ዘካ 14፡9)፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ኢየሩሳሌም ለመውጋት በሚነሣሡ ሕዝቦች ላይ እግዚአብሔር ቀሳፊ በሽታ ያመጣባቸዋል፤ በሕይወት እያሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ አይናቸውና ምላሳቸው ይተላል(ዘካ 14፡12)፡፡ የአሕዛብ መንግሥታት ሀብት በሙሉ በይሁዳ ሰዎች ተማርኮ ይወሰዳል(ዘካ 14፡14)፡፡ ከኢየሩሳሌም አዲስ የሕይወት ውሃ ይፈልቃል፡፡ ከዚህም በላይ ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ካለው ምድር በላይ ከፍ ብላ ጸንታ ትኖራለች፤ የብዙ ሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አይደርስባትም፤ ሕዝብዋም ያለ ስጋት በሰላም ይኖራል(ዘካ 14፡11)፡፡ እርስዋን ለማጥቃት የሚነሣ ቢኖር እንኳ እራሱን ይጎዳል፤ ፈረሰኞችም ቢሆኑ እንኳ እግዚአብሔር ፈረሶቻቸውን በፍርሃት ያስጨንቃል፤ የይሁዳን ሕዝብ ግን እንደ ዐይኑ ብሌን ይጠብቃቸዋል(ዘካ 12፡3-4)፡፡
>> ነቢዩ ዘካርያስ ወደፊት ስለሚመጣው የጽዮን ንጉሥ ይናገራል፡፡ ይህ ትንቢት ዘካርያስ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የገለጸው? የጽዮን ንጉሥ ተብሎ የተነገረለትስ ማን ነው? ጽዮን ተብላ የሚነገርላት ከተማ የትኛዋ ነች?
ከቅዱስ ዳዊት ጊዜ ጀምሮ ጽዮን ለመላዋ ኢየሩሳሌም ተጨማሪ ወይም ተለዋጭ ስም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ ጽዮን ሆይ ደስ ይበልሽ! ኢየሩሳሌም ሆይ ደስ ይበልሽ! በደስታ እልል በይ በማለት የኢየሩሳሌምን ስም እያፈራረቀ ደጋግሞ በመጥራት መደሰት እንዳለባት ያበስራታል፡፡ የደስታዋም ዋና ምክንያት የሆነውም ትሑት የሆነውን የንጉሥዋ መምጣት ነው፤ ይህንንም ሲገልጽ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያይቱ ማለትም በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ በድል አድራጊነት ወደ አንቺ ስለሚመጣ ነው ይላል(ዘካ 9፡9)፡፡ ይህ ንጉሥ በድል አድራጊነት ይመጣል፤ በሕዝቦች መካከል ሰላምን ይመሠርታል፤ መንግሥቱም ከባሕር ዳርቻ እስከ ባሕር ዳርቻ ይሆናል፤ ግዛቱም ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርሳል(ዘካ 9፡10)፡፡ በዚህ ንጉሥ መምጫ ጊዜም እግዚአብሔር የጦር ሠረገላዎች ከእስራኤል አጠፋለሁ፤ ፈረሶችንም ከኢየሩሳሌም አስወግዳለሁ፤ የጦር ሜዳ ቅስቶችንም ሁሉ ይሰባበራሉ በማለት የሰላም ጊዜ እንደሚሆን ይናገራል(ዘካ 9፡10)፡፡ ነገር ግን ይህ በድል አድራጊነት ይመጣል የተባለው ንጉሥ ማንን ድል አድርጎ እንደሚመጣ፣ መቼ እንደሚመጣና ከየትኛው ወገን ወይም ቦታ እንደሚመጣ አልተገለጸም፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ እግዚአብሔር እረኞች በተባሉት የሕዝብ መሪዎች ላይ አለመደሰቱን በመግለጽ እርሱ ራሱ “መንጋዬ ለሆነው ለይሁዳ ሕዝብ እጠነቀቃለሁ” በማለት ከሕዝቡ መካከል እንደ ማእዘን ድንጋይ የሆነ ጥሩ የሆነ መሪ እንደሚያስነሣላቸው ይናገራል(ዘካ 10፡3)፡፡ በዚያን ጊዜ የይሁዳ ሕዝብም ጠላቶቻቸውን ረግጠው ከመንገድ ጭቃ ጋር እንደሚለውሱ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ስለሆነ በርትተው በመዋጋት ፈረሰኞችም ሳይቀር ድል ይነሣሉ በማለት መሪ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም በርትተው ጠላቶቻቸው ድል የሚያደርጉበት ኃይል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚቀዳጁ ያበስራል(ዘካ 10፡4-5)፡፡ ከዚህም አልፎ የዳዊት ዝርያዎች እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሆነው ሕዝቡን ይመራሉ፡፡ የኢየሩሳሌም ሕዝብም በምሕረት መንፈስና በጸሎት መንፈስ ይሞላሉ፤ እግዚአብሔርም በኢየሩሳሌም ላይ በጠላትነት የሚነሡትን የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ለመደምሰስ እንደሚነሣ ቃል ይገባል(ዘካ 12፡8-10)፡፡
በተጨማሪም የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ከኃጢአታቸውና ከጣዖት ርኩሰታቸው የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል፤ የጣዖታት ስሞች ከምድሪቱ ላይ ይወገዳል፤ ዳግመኛም የሚያስታውሳቸው አይኖርም፤ ከዚያም በኋላ ነቢይ ነኝ ብሎ የሚነሣ ቢኖር እንኳ የገዛ አባትና እናቱ በእግዚአብሔር ስም ሐሰት ስለተናገርህ ሞት ይገባሃል ብለው ይፈርዱበታል(ዘካ 13፡2)፡፡
ከትንቢተ ዘካርያስ ጠቅላላ የትምህርቱ ይዘት እንደምንረዳው በመጽሐፉ የመጀመሪያና የሁለተኛ ክፍል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳለ ነው፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ በተለያየ መልኩ እንደሚገለጽ ከላይ ለማብራራት ተሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል ዘግየት ብለው የተነገሩት የትንቢት ቃላት የያዘ ቢሆንም መጽሐፉ እንደ ትንቢት ቃልነቱ በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ለነበረ ሕዝብ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡
የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ
መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ
የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ
ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች
1. የዘካርያስ የነቢይነት ጥሪና አገልግሎት እንዲሁም የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?
ሀ)ዘካርያስ ማለት እግዚአብሔር እናስታውስ ማለት ነው፡፡ ለ)ከመጽሐፉ ይዘት በደንብ መረዳት እንደሚቻለው ትንቢተ ዘካርያስ ሁለት ክፍሎች ማለትም ከምዕራፍ 1-7 እና ከ8-14 ያሉት ነው፡፡ ሐ)በመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ውስጥ ነቢዩ ራሱን እንደ ተመታና እንደ ተነቀፈ እረኛ ሆኖ ያቀርባል፡፡ መ)የመጽሐፉ ሁለተኛው ክፍል በራእይ የተሞላ ነው፡፡ ሠ) ዘካርያስ ኢየሩሳሌምንና አካባቢዋ በደንብ እንደማያውቀው ከመጽሐፉ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡
2. ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ንስሓ ጥሪ፣ ስለ ዘሩባቤል፣ ስለ ኢያሱና ከሳሹ ሰይጣን ከተናገረው ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?
ሀ)እግዚአብሔር የቀድሞ እስራኤላውያን እንደ አካሄዳቸውና እንደ ሥራቸው አልቀጣቸውም፤ ለዘሬዎቹ ግን ሊቀጣቸው ተዘጋጅቶአል፡፡ ለ)ዘሩባቤል የቤተ መቅደሱን ሥራ ከጨረሰ በኋላ ወደ ባቢሎን ተመልሶ ሄደ፡፡ ሐ) ኢያሱ ነቢይ ሆኖ ያገለግል እንደነበር ተገልጿል፡፡ መ) ኢያሱ በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ትልቅ ክብር ያገኘ መሆኑን የሚገልጸው ለኢየሩሳሌምና ለቤተ መቅደስዋ መታደስ ባደረገው አስተዋጾ ምክንያት ነው፡፡ ሠ)ነቢዩ ዘካርያስ ለኢየሩሳሌም፣ ለነዋሪዎችዋና ለቤተ መቅደሰ ትልቅ ቦታ የሰጠ ነቢይ አልነበረም፡፡
3. ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ጾም፣ እግዚአብሔር በአጐራባች አገራት ላይ ስለሚያደርገው ፍርድና ስለ ጽዮን ንጉሥ ከተናገረው ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?
ሀ)ጾም የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ በግል ብቻ ሊጾም የሚችል ክንውን ነው፡፡ ለ)እስራኤላውያን ባቢሎን ውስጥ በስደት እያሉ የጾሙት ጾም እግዚአብሔር ተቀበለላቸው፡፡ ሐ) እግዚአብሔር የእስራኤል አጐራባች አገራት የሚቀጣበት ዋናው ምክንያት ጣዖት ስላመለኩ ነው፡፡ መ)ጽዮን ለመላዋ እስራኤል ተጨማሪ ወይም ተለዋጭ ስም ነው፡፡ ሠ) በመጨረሻም እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ በጠላትነት የሚነሡትን የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ለመደምሰስ እንደሚነሣ ቃል ይገባላቸዋል፡፡
4. ነቢዩ ዘካርያስ ካያቸው ራእዮች ውስጥ አንዱ የዐመፅ ምሳሌ ስለሆነው ሰው ይገኝበታል፡፡ ይህ የዐመፅ ምሳሌ የሆነውን በመጨረሻ ወደ ባቢሎን ተወስዶ፣ ቤተ መቅደስ ተሠርቶለት እንደሚመለክ ይናገራል፡፡ የሚመለከውም በጣዖት አምላኪዎች ነው፡፡ የዐመፅ ሰው ተብሎ በምሳሌ የተገለጸውም ናቡካዳናፆር ወይም ሌላ የባቢሎን ንጉሥ ወይም ሌላ ተሸንፎ የሚወድቅ ተቀናቃኝ ጠላት ሊሆን ይችላል፡፡ ዘካርያስ ይህንን የሚተርከው በየትኛው ራእይ ውስጥ ነው?
ሀ) በቅርጫት ውስጥ ስላለች ሴት ያየው ራእይ ነው፡፡ ለ) ጥቅል የብራና መጽሐፍ በሚለው ራእይ ነው፡፡ ሐ)ስለ መቅረዝ ባየው ራእይ ነው፡፡ መ)ስለ አራቱ ሠረገላዎች ባየው ራእይ ነው፡፡ ሠ)ስለ መለኪያ ገመድ ባየው ራዕይ ነው፡፡
5. ነቢዩ ዘካርያስ ሲናገር(ዘካ 11፡ 4-17) “የአገልግሎቴን ዋጋ ሠላሳ ብር ሰጡኝ፤ በቂ ደመወዝ ነው ብለው የሰጡኝን ሠላሳ ብር ወስጄ በቤተ መቅደሱ የገንዘብ መቀበያ ሳጥን ውስጥ ጣልሁት” ይላል፡፡ ይህ የትንቢት ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በማን ተፈጽሞ ይገኛል፡፡ ገንዘብ የተቀበለው ማን ነው? ለምን አገልግሎት ተብሎ ነው የተከፈለው? ምዕራፉና ጥቅሱ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የት ይገኛል?
6. ነቢዩ ዘካርያስ ካያቸው ራእዮች ውስጥ አንዱ ስለ ብራና መጽሐፍ የሚናገረው ነው፡፡ በተጠቀለለው መጽሐፍ ውስጥ በአንድ በኩል “ሌባ ሁሉ ከምድር ይወገዳል” ሲል በሌላ በኩል ደግሞ “በመሐላ ሐሰት የሚናገር ሁሉ ይጠፋል” የሚል ነው(ዘካ 5፡ 3-4)፡፡ ሌባና በሐሰት የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ የሚምል በሙሉ ከራሱ አልፎ ቤቱም ጭምር እንደሚፈራርስ ይናገራል(ዘካ 5፡ 4)፡፡ ጌ.ኢ.ክርስቶስ ደግሞ በሰማይም ይሁን በምድር ወይም በራስህም ቢሆን አትማል ይላል(ማቴ 5፡ 33-36)፤ ንግግራችሁ አዎ ከሆነ አዎ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን ይላል(ማቴ 5፡ 37)፡፡ ነገረ ግን በተለምዶ በንግግራችን ውስጥ አድማጫችንን ለማሳመን በማለት የቅዱሳን፣ የመላእክትና የእግዚአብሔር ስም በመጥራት የመማል አዝማምያ ይታይብናል፡፡
- ለመሆኑ ንግግርን በመሐላ ማጽናት ወይም መማል ለምን ይጠቅማል? የምንምለውስ ለምን ብለን ነው?
- በዚያ ሰዓት ማለትም በምንነጋገርበት ወቅት ባንምልስ ወይም ንግግራችን በመሐላ ባይደገፍስ ምን ሊፈጠር ይችላል?