ት/ርት ፴፬ - የትንቢተ ሚልክያስ ጥናት
- Category: የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
- Published: Wednesday, 18 November 2015 05:32
- Written by Super User
- Hits: 10903
- 18 Nov
ክፍል ሦስት (ትምህርት ሠላሳ አራት)
የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ሚልክያስ
ነቢዩ ሚልክያስ ተወልዶ ያደገውና ለነቢይነት የተጠራው፣ የአገልግሎት ተግባሩን ያከናወነው መቼና የት ነው?
ሚልክያስ ማለት “መልእክተኛዬ” ወይም “የእኔ መልአክ” እንደማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ሚልክያስ የነቢዩ ስም እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ እንደነዚህ ሊቃውንት አገላለጽ ሚልክያስ በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጸውና ወደፊት ይመጣል የተባለው መልእክተኛ ነው እንጂ በእንደዚህ ዓይነት ስም ማለትም “የእኔ መልአክ” በማለት አንድ አይሁዳዊ ቤተሰብ ልጁን ይሰይማል ብሎ ማመን ያስቸግራል(ሚል 3፡1)፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በወቅቱ ከነበረው የአይሁዳውያን ባህል፣ ሃይማኖትና የአኗኗር ሁኔታ መነሻ በማድረግ ወደዚህ መደምደሚያ ይድረሱ እንጂ የነቢዩ ስም ማን ሊሆን እንደሚችል ምንም ዓይነት አስተያየት አይሰጡም፡፡ መጽሐፉ ስለ ሚልክያስ የግልም ሆነ ቤተሰባዊ ሕይወቱ ወይም ከየትኛው ወገንና ከየትኛው ቤተሰብ እንደሆነ ምንም ዓይነት መረጃ ስለማይሰጥ ይህ ነው ብሎ በተጨባጭ ሁኔታ ስለ ሕይወቱ መናገር ያዳግታል፡፡
ሚልክያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ምዕተ ዓመት(520-515) ኢየሩሳሌም ውስጥ እንደኖረና የነቢይነት ተግባሩን እንዳከናወነ ከመጽሐፉ እንረዳለን፡፡ በዚህ ወቅት የቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ግንባታ ተጠናቅቆ የነበረ ሲሆን ካህናቶች አገልግሎታቸው ማከናወን የጀመሩበት ሕዝቡም ኑሮውን በተረጋጋና በተደራጀ ሁኔታ ይኖር የነበረበት ወቅት ነው(ሚል 1፡10፤3፡1)፡፡ ነገር ግን ካህናቶችም ሆኑ በወቅቱ የነበረው ሕዝብ ፍቅሩ የቀዘቀዘ፣ የአምልኮ ሕይወቱም የተዳከመና የተሰላች፣ በማኅበራዊ ሕይወትም ግዴለሽነት የበዛበት ወቅት ነበር፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ ከሕዝቡ መካከል ባዕዳን ሴቶች እያገቡ ኑሮአቸውን በዘፈቀደ የሚመሩ አይሁዳውን እንደነበሩ ከመልእክቱ እንረዳለን፡፡
ነቢዩ ሚልክያስም ይህንን መነሻ በማድረግ ሕዝቡ ለቃል ኪዳኑ ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ የነቢይነት መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡ በመልእክቱም ሕዝቡ እግዚአብሔርን በታማኝነት ስላላመለኩ፣ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ስለጣሱና ከባዕዳን ሴቶች ጋር ስለተጋቡ እንዲሁም ፍትሕን ስላጐደሉ ይህንን መረን የወጣና የተበላሸ አካሄዳቸውን ትተው ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ማደስ እንዳለባቸው ነቢዩ ይናገራቸዋል፡፡
የትንቢተ ሚልክያስ ጥንቅር፣ ይዘትና ትኩረት ምን ይመስላል? እንዴት ይገለጻል?
ትንቢተ ሚልክያስ ከዐሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት አንዱና ከነቢያት መጻሕፍትም መጨረሻው ነው፡፡ መጽሐፉ በአራት አጫጭር ምዕራፎች የተጠናቀረ ሲሆን መልእክቱም ግልጽ ሆኖ አድማጮቹን በቀጥታ የሚናገርና ወደ ለውጥ ጐዳና የሚጋብዝ መጽሐፍ ነው፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ በእርግጥ በአጻጻፉና መልእክት በማስተላለፍ ሂደቱ ከሌሎች ነቢያቶች ለየት ይላል፡፡ ይህንንም የምንረዳው የሚጠቀምባቸው መልእክት ማስተላለፊያ መንገዶችን በማየት ነው፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ ውስጥ ለየት ያሉ ስድስት የሚያህሉ ውይይቶች ማለትም እግዚአብሔርን ወክሎ በሚናገረው በነቢዩ እና በሕዝቡ መካከል የተደረጉ ሙግቶች ተካትተዋል፡፡ እነዚህም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር በተመለከተ የተደረገ ሙግትና(ሚል 1፡2-5) ለእግዚአብሔር ስለሚገባው ክብር(ሚል 1፡6-2፡9) በቅድሚያ ይጠቀሳሉ፡፡ ቀጥሎም ታማኝነትን በተመለከተ(2፡10-16)፣ የፍትሕ አምላክ ወይም እግዚአብሔር ስለሚተገብረው ፍትሕ ጉዳይ(ሚል 2፡17-3፡5)፣ ስለ ንስሓ ወይም ወደ እግዚአብሔር ስለመመለስ(ሚል 3፡ 6-12) እና እግዚአብሔርን ስለመፈታተን ናቸው(ሚል 3፡13-21)፡፡
ይህንን ዓይነት አቀራረብ ነቢዩ ሚልክያስ ከሌሎች ነቢያት ለየት የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ማስተላለፍ የፈለገውን መልእክት ግልጽ በሆነና የአድማጩን ትኩረት በሚስብ መልኩ ማቅረቡን የትንቢት ቃሉ በአድማጩ ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በላይ ይህ አቀራረቡ በወቅቱ የነበሩትን ችግሮች እየዳሰሰ ወይም ሕዝቡ ማስተካከል የነበረበትን ነገሮች እየጠቀሰና በማስረጃ እያስደገፈ በሚገባ ለማስተላለፍ የተጠቀመበት መንገድ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ በተለያየ መልኩ እግዚአብሔር አፍቃሪ አባት(ሚል1፡2)፣ እግዚአብሔር የሁሉም ገዥ ጌታ(ሚል1፡6)፣ እግዚአብሔር ፈጣሪና የእስራኤል አባት(ሚል 2፡10) እንደሆነ አበክሮ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ፣ እግዚአብሔር የማይለወጥና ቅን አምላክ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚጠላና የሚቀጣ አምላክ መሆኑን እየደጋገመ በማረጋገጥ ይገልጻል፡፡
በተለይም ስለ ፍቅር፣ ፈሪሓ እግዚአብሔርና ታማኝነት በተመለከተ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይናገራል፤ እነዚህ ሀሳቦች ደግሞ በኦሪት ዘዳግም ውስጥ በልዩ ትኩረት በተደጋጋሚ የተገለጹ ስለሆኑ ጸሐፊው ከኦሪት ዘዳግም ጋር ቀረቤታ የነበረውና አጻጻፉም ተመሳሳይነት እንዳለው ሊቃውንቶች ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ነቢዩ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚወድና ቃል ኪዳኑንም እንደሚጠብቅ ይገልጻል፤ ነገር ግን ይህ አምላክ እንዲከበርና ሕዝቡም ታማኝ ሆኖ እንዲኖር እንደሚፈልግ ያረጋግጣል፡፡ ሕዝቡ ቃል ኪዳናቸው ጥሰዋል፤ ኢፍትሐዊ ሆነዋል፤ በእግዚአብሔርም ላይ የድፍረት ቃል ተናግረዋልና እንዲጸጸቱና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ የማይመለሱ ከሆነ ግን እግዚአብሔር ምድሪትዋን ይረግማል፤ ይፈርድባታልም፡፡
መጽሐፉ ኢየሩሳሌም ውስጥ ከ520 እስከ 515 ዓ.ዓ አካባቢ እንደተጻፈ ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንንም የምንረዳው አብዛኛው መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ውይይቶችም ሆነ ግሣጼዎች እንዲሁም አስተምህሮቶች ኢየሩሳሌም ውስጥ የቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የነበረውን የአኗኗር ሁኔታ ተመርኩዘው የተገለጹ በመሆናቸው ነው፡፡ ጸሐፊው ወይም ነቢዩ ለሌዋውያኖች ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚናገር ምንአልባት ራሱ ከሌዋውያን ወገን የሆነ ወይም ከሌዋውያን ጋር ልዩ ቅርበት ያለው ሊሆን እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡
ነቢዩ ሚልክያስ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስላለበት ክብር በስፋት ይናገራል፡፡ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስላለበት ክብር ማለት ምን ማለት ነው?
እንደ ነቢዩ ሚልክያስ አገላለጽ እግዚአብሔር ከምንም በላይ አፍቃሪ አባት ነው(ሚል 1፡2)፡፡ ይህ አፍቃሪ አባት ሁሌም መከበርና ቅድሚያ እንዲሰጠው ይገባል፡፡ ልጅ አባቱን፣ አገልጋይም አሳዳሪ ጌታውን እንደሚያከብር ሁሉ የሁሉም ጌታ የሆነውን እግዚአብሔር አምላክ መከበር አለበት(ሚል1፡ 6)፡፡ ይህንን በተመለከተ እግዚአብሔር ራሱ በነቢዩ አማካኝነት እነሆ እኔ አባታችሁ ነኝ፤ ታድያ ለምን አታከብሩኝም? ጌታችሁም ነኝ፤ ለምንስ ክብር አትሰጡኝም? እናንተ እኮ እኔን ንቃችኋል በማለት ይናገራል(ሚል 1፡6)፡፡ በእርግጥ በዚህ ወቅት ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ተገቢውን መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የረከሰ የእንጀራ መሥዋዕት፣ እንዲሁም የታወረውን፣ የታመመውን፣ አንካሳ የሆነውንና የተሰረቀውን እንስሳ ለመሥዋዕት በማቅረብ መሠዊያውን አርክሰው ነበር(ሚል 1፡7-8)፡፡ ሕዝቡ ይህንን ድርጊታቸው በደንብ እንዲረዱት እግዚአብሔር ይህን የመሰለ እንስሳ ለአለቃችሁ ገጸ በረከት አድርጋችሁ ብታቀርቡለት ደስ ብሎት የሚቀበላችሁና የሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን? በማለት የድርጊታቸው አስጸያፊነት የበለጠ እንዲረዱት ከዕለታዊ ሕይወታቸው ጋር እያመዛዘነ ያስገነዝባቸዋል(ሚል1፡8)፡፡
ከአይሁዳውያን ውጪ የሆኑት ባዕዳን ሕዝቦች እንኳ ዕጣን እያጠኑ ንጹሕ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤ አይሁዳውያን ግን አስነዋሪ መሥዋዕት በማቅረብ መሠዊያውን ንቀው በማቃለል ከማርከሳቸውም አልፎ እግዚአብሔር የሚያዝንበትን ነገር አድርገዋልና መታረምና አካሄዳቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው ነቢዩ ያስጠነቅቃቸዋል(ሚል11-12)፡፡ ይህንን ማስጠንቀቂያ ተረድቶ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ሳይሰጥ እንደ ቀድሞ አደራረጉ በእልኸኝነት ማለትም የረከሰ መሥዋዕቱን በድፍረት ወደ መሠዊያው ለሚያቀርበው ወዮለት በማለት ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ ይህም ከመንጋው መካከል ለእኔ ንጹሕ እንስሳ እያለው ነውረኛ እንስሳ መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብልኝ አታላይ ሰው የተረገመ ይሁን፤ ምክንያቱም እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ የተፈራ ነው በማለት የበለጠ የስጠነቅቃቸዋል(ሚል1፡14)፡፡ ይህንን የጥሪ ቃል ሰምተው፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር በልቦናቸው አድሮ፣ ለእርሱ በመታዘዝ የሚገባውን መሥዋዕት በክብር የሚያቀርቡ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላቸዋል፤ ፈውስንም ይሰጣቸዋል፤ ነፃ ወጥተውም ከማሰሪያው ተለቆ በደስታ እንደሚብዋርቅ እንቦሳ ይሆናሉ በማለት ያረጋግጥላቸዋል(ሚል 4፡2) ፡፡
ለእግዚአብሔር መሰጠት ስለሚገባው ክብር ተጓድሎ የነበረው በሕዝቡ ብቻ ነበር ወይንስ በሌሎችም ዘንድ የነበረ ችግር ነው?
ይህ ለእግዚአብሔር የሚገባው ክብር አለመስጠት በሕዝቡ ላይ ብቻ የታየ ችግር ሳይሆን በካህናቶችም ጭምር ስለሆነ ነቢዩ ካህናቶችን ለየት ባለ መልኩ እየገሠጸ ያስጠነቅቃቸዋል(ሚል 2፡1-9)፡፡ ካህናት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ስለሆኑ ፈቃዱን ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ(ሚል 2፡7)፡፡ ካህናቶች የእግዚአብሔር እውነተኛውን መንገድ ማሳየትና ቀናውን ነገር ማስተማር ይጠበቅባቸዋል(ሚል 2፡6)፡፡ ካህናቶች ሁሉንም እኩል በመመልከት ማስተማር፣ እግዚአብሔርን በመፍራት በሥራቸው ስሙን ማክበር፣ ትእዛዙን ከልብ መገንዘብና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሕዝቡ የሚያሳውቁ መሆን አለባቸው(ሚል 2፡2-7)፡፡ ይህ መሆኑ ቀርቶ ከእውነተኛው መንገድ ፈቀቅ ቢሉ፣ በትምህርታቸው ሰዎችን ቢያሳስቱ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ቢያጣምሙና ለእግዚአብሔር መታዘዛቸውን ቢተዉ ይዋረዳሉ፡፡
በተጨማሪም በትምህርታቸው በሰዎች መካከል ቢያዳሉና ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ቢያፈርሱ እነርሱን በእስራኤል ሕዝብ ፊት የተናቁና የተዋረዱ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ በረከታቸውንም ወደ እርግማን ይለውጣል፤ ለመሥዋዕት ያቀረቡትንም አይቀበልላቸውም፤ ልጆቻቸውንም ይቀጣል(ሚል 2፡2፤2፡8-9)፡፡ ስለዚህ ካህናቶች በተለይም የሌዊ ዝርያዎች የተሰጣቸውን ቃል ኪዳን የጸና እንዲሆንና ሕይወትንና ሰላምን አግኝተው መኖር እንዲችሉ እግዚአብሔርን በመፍራትና በማክበር ተግባራቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ነቢዩ ሚልክያስ ያገለገለው የእስራኤል ሕዝብ ከባቢሎን የስደትና የመከራ ኑሮ ተመልሰው አገራቸው ውስጥ ዳግመኛ ኑሮአቸውን በመሠረቱበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ አሰቃቂ ከሆነው ከስደት ኑሮ በኋላ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸው እምነት ምን ይመስል ነበር?
አይሁዳውያን ከባቢሎን የስደት ኑሮ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ መሬቶቻቸውን አርሰው፣ ንብረት አፍርተው፣ ቤተ መቅደሱንም በድጋሚ ገንብተው ኑሮአቸውን በአዲስ መልክ የጀመሩበት ወቅት ነበር ነቢዩ ሚልክያስ ሕዝቡን በእግዚአብሔር አለመታመናቸው የነገራቸው፡፡ በእርግጥም በዚህ ወቅት ሕዝቡ እምነቱ ላይ የቀዘቀዘበት ብቻ ሳይሆን ከእምነቱና ከሥነ ምግባራዊ ሕይወት ውጭ የሆኑና እግዚአብሔርን ያሳዘኑ ድርጊቶች ሲያከናውኑ ነበር፡፡ ከእነዚህም ተግባራት ውስጥ ቤተ መቅደስን ማርከስ፣ ለቅሶና ዋይታ በበዛበት እንባ የእግዚአብሔርን መሠዊያ መሸፈን ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ወንዶች የገቡትን ቃል ኪዳን በማፍረስ የሕግ ሚስቶቻቸውን በመፍታት የባዕድ አገር ጣዖት አምላኪ የሆኑ ሴቶችን ማግባትና ታማኝነታቸውን ማጉደል እንዲሁም ሌሎችም ይጠቀሳሉ(ሚል 2፡10-11፤ 2፡14-16)፡፡ ነቢዩ ሕዝቡን ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር መነሻ ጥያቄ የሚያደርገው እርስ በርሳችን የተለዋወጥነውን ቃል ኪዳን ስለምን እናፈርሳለን? እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር የገባውንስ ቃል ኪዳን ስለምን እንንቃለን? የሚለውን በቃል ኪዳን ዙሪያ የተደረገውን ስምምነትን ነው(ሚል 2፡10)፡፡ የይሁዳ ሕዝብ ግን ይህንን የገቡትን ቃል ኪዳን በማፍረስ በመላው አገሪቱ ውስጥ አስጸያፊ የሆነውን ርኩሰት አድርገዋል፤ እግዚአብሔርንም የሚወድደውንም ቤተ መቅደስ አርክሰውታል፤ ወንዶቹም የባዕድ አገር ጣዖት አምላኪ የሆኑ ሴቶችን አገቡ(ሚል 2፡11)፡፡ እግዚአብሔር ለወንዶችና ለሴቶች የአንድነት መንፈስ ሰጥቶ አንድ አድርጓቸው የነበረው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሆኑ ልጆችን እንዲወልዱና ከሚስቶቻቸው ጋር በታማኝነት እንዲኖሩ ነበር፤ ሕዝቡ ግን የገቡትን ቃል ኪዳን መጣስና በእግዚአብሔር የነበራቸው አመኔታ ስላጐደሉ ነቢዩ በማስጠንቀቅ ይናገራቸዋል፡፡
ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ባልና ሚስት የትዳር ሕይወትና መፋታትን በተመለከተ የሚናገረው ምንድን ነው?
በትንቢተ ሚልክያስ አማካይነት እግዚአብሔርም እኔ የባልና ሚስት መፋታት ጠላሁ መሥዋዕታችሁም አልመለከትም፤ በደስታም አልቀበልም ይላል(ሚል2፡14 እና 16)፡፡ ከዚህም በላይ ለሚስቶቻችሁ ታማኞች ለመሆን የገባችሁላቸውን ቃል ኪዳን ላለማፍረስ ልዩ ጥንቃቄ አድርጉ በማለት ያስጠነቅቃቸዋል (ሚል 2፡16)፡፡ በተጨማሪም ይህንን የጥሪ ቃል ሰምተው በቸልተኝነት የሚጓዙትን ይረግማል፤ ማኅበረሰቡ ገለልተኛ እንዲያደርጋቸውና እግዚአብሔርም ቁጣውን እንዲያወርድባቸው ይናገራል፡፡ ይህንንም ሲናገር ይህን የሚያደርገውን ሁሉ ከእስራኤል ሕዝብ ማኅበር እግዚአብሔር ያስወግደው! ሕዝባችን ለሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚያቀርበው መሥዋዕት ተሳታፊ ሳይሆን እንደወጣ ይቅር! ይላል(ሚል 2፡12)፡፡
እግዚአብሔር እኔ የባልና ሚስት መፋታት ጠላሁ ይላል(ሚል 2፡16)፡፡ ፍቺ ወይም የባልና የሚስት መፋታት እግዚአብሔር እንደሚጠላና የእርሱ ፈቃድ እንዳልሆነ ነቢዩ ሚልክያስ በግልጽ ተናግሮታል፡፡ በእርግጥ ከጥንት ጀምሮ በእስራኤላውያን ዘንድ ፍቺ የተለመደ ነበር፡፡ ለዚህም በኦሪት መጻሕፍት ግልጽ በሆነ ሁኔታ አንድ ሰው አንዲት ሴት አጭቶ ካገባ በኋላ ዘግየት ብሎ እርስዋን የማይወድበትን ነገር በማግኘቱ ይጠላት ይሆናል፤ ስለዚህም የተፈታችበትን ምክንያት የሚገልጥ የፍች ደብዳቤ ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ያባርራታል፤ እንደገናም ሌላ ባል ታገባ ይሆናል፤ ሁለተኛውም ባል ስለሚጠላት የተፈታችበትን ምክንያት የሚገልጥ የፍች ደብዳቤ ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ያባርራታል፤ ወይም ሁለተኛ ባልዋ ይሞት ይሆናል፤ በሁለቱም መንገድ ቢሆን ያ የመጀመሪያ ባልዋ እንደገና ሊያገባት አይፈቀድለትም የሚሉ መመሪያዎች ተሰጥተው ነበር(ዘዳ 24፡1-4)፡፡ ጌታችን ኢሱስ ክርስቶስ ግን ሙሴ ሚስቶቻችሁ እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ ልባችሁ ደንድኖ አስቸጋሪዎች በመሆናችሁ ምክንያት ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ግን እንዲህ አልነበረም በማለት ፍቺ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን ግልጽ በሆነ መንገድ ተናግሮታል(ማቴ 19፡8)፡፡
ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ጋብቻ ከሰባቱ ምስጢራት እንደ አንዱ በመውሰድ የተክሊልን ምስጢር ታስተምራለች፡፡ ቃል ኪዳን ልክ ክርስቶስና ለቤተ ክርስቲያን ያለው ፍቅር፣ ጥበቃና አንድነት ጸኑ እንደሆነ ሁሉ ወንድና ሴት በተክሊል ምስጢር አንድ ይሆናሉ(ኤፌ 5፡ 21-33)፡፡ አንድነታቸውም በመንበረ ታቦት ፊት ለእግዚአብሔር ቃላቸውን በመሐላ በመስጠት ይገልጻሉ፡፡ ይህም ቃል ኪዳን ሁለቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ጸንቶ ይኖራል፤ ሁለቱም በሕይወት እስካሉ ድረስ በምንም መልኩ አይፈርስም፡፡ ከሁለት አንዱ በሞት ቢለይ ግን ቃል ኪዳኑ መልኩን ሊለውጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም ምስጢረ ተክሊል በሕይወት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ከምንቀበላቸው ምስጢራት ማለት ከምስጢረ ጥምቀትና ከምሥጢረ ክህነት ጋር ይመደባል፡፡
ነቢዩ ሚልክያስ ለእግዚአብሔር መከፈል ስላለበት ዐሥራት በተመለከተ ለሕዝቡ ምን ዓይነት ትምህርት ያስተላልፋል?
ዐሥራት ማለት አንድ ዐሥረኛ ማለት ሲሆን ከጥንት ጀምሮ ከማንኛውም ገቢ ለሃይማኖት መሪ ወይም ለመንግሥት ይሰጥ የነበረ ድርሻ ነው፡፡ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ ዐሥራት እንደሰጠውና ያዕቆብም ለእግዚአብሔር ዐሥራት ለመክፈል እንደተሳለ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንረዳለን(ዘፍ 14፡20፤ 28፡22)፡፡ በጥንት ዘመን ሌዋውያን ካህናት እንዲጠቀሙበት ምድር ከምታፈራው ሁሉ ከከብትም ጭምር ዐሥራት እንዲሰጥ ተነግሯል(ዘኁ 18፡21-22 ዘሌ 27፡30-33)፡፡ በተጨማሪም ዐሥራት የሚከፈልበት ጊዜ እንደተወሰነና ዐሥራትም ሲከፈል እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚባርክ ተገልጿል(ዘዳ 26፡13-15)፡፡ በቀድሞ ጊዜ ፈሪሳውያን ከቅመማ ቅመም እንኳ ሳይቀር ለእግዚአብሔር የሚገባ ዐሥራት ይከፍሉ እንደነበር ከአዲስ ኪዳን እንረዳለን(ማቴ 23፡23)፡፡
በነቢዩ ሚልክያስ ጊዜ የነበረው ሕዝበ እግዚአብሔር ግን ዐሥራት የመክፈሉ ተገቢነት ቢያምንም አከፋፈሉ ላይ የራሱ የሆነ ችግር እንደነበረውና ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ አተገባበሩን እንዲያስተካክል ጥሪውን ያሰማል፡፡ በዚህ ዙሪያ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሲወቅስ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ ሕጌንም አልጠበቃችሁም፤ ይልቅስ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ ይላቸዋል(ሚል 3፡7)፡፡ የመመለሻው መንገድ ምን እንደሆነ ሲያብራራላቸው በቅድሚያ የሚያሳስባቸው ዐሥራት አሳጣጣቸው ነው፡፡ በእርግጥ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ዐሥራት አለመክፈላቸው እግዚአብሔርን እንደ ማታለልና እንደ ሌብነት ስለተቈጠረባቸው ይህንን ድርጊታቸው እንዲያርሙ የዐሥራቱንና የመባውን ገቢ በመውሰድ ትሰርቁኛላችሁ፤ እናንተ የእስራኤል ሕዝብ ዐሥራቴንና መባዬን በመስረቃችሁ የተረገማችሁ ሆናችኋል፡፡ ይልቅስ በቤተ መቅደሴ ሢሣይ ይበዛ ዘንድ ዐሥራቴን በሙሉ ወደ ጐተራ አግቡ ይላቸዋል(ሚል 3፡8-9)፡፡
ተገቢውን ዐሥራት ለእግዚአብሔር አለመስጠት በራስ ላይ እርግማንን ማምጣት ወይም በእግዚአብሔር እንደ መረገም እንደሚቆጠር ነቢዩ ደጋግሞ ያስገነዝባል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ተገቢውን ዐሥራት በትእዛዙ መሠረት ለእግዚአብሔር መክፈል ብዙ በረከት እንደሚያስገኝ ሲገልጽ በቤተ መቅደሴ ሢሣይ ይበዛ ዘንድ ዐሥራቴን በሙሉ ወደ ጐተራ አግቡ፤ እናንተ ይህን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሰማይን መስኮቶች ከፍቼ መልካም የሆነውን በረከት ሁሉ አብዝቼ ባልሰጣችሁ በዚህ ልትፈትኑኝ ትችላላችሁ፡፡ እህላችሁ በተባይ እንዲጠፋ አላደርግም፤ የወይናችሁ ተክል ዘወትር ያፈራል፤ ፍሬውም አለጊዜው አይረግፍም ይላቸዋል(ሚል 3፡10-11)፡፡ ከዚህም በላይ ምድራቸው ለኑሮ የተመቻቸ እንድትሆን ሕዝብዋም በበረከት እንዲሞላ ወቅቱን ጠብቀው ለእግዚአብሔር የሚገባውን ዐሥራት ወደ ቤተ መቅደሱ ማምጣት ይኖርባቸዋል(ሚል 3፡12)፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ነቢዩ ሲያስተምር እግዚአብሔርን በመፍራት የሚያገለግሉትና የሚጠበቅባቸውን ተግባር የሚወጡ ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያከብራቸውና ስማቸውንም በሰማይ መዝገቡ እንደሚጽፍላቸው ያረጋግጥላቸዋል(ሚል 3፡16)፡፡
እነዚህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሰዎች የተለዩና ለዘላለሙ የእግዚአብሔር ሆነው ይኖራሉ፤ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግላቸዋል፤ ትዕቢተኞችና ክፉ አድራጊዎች ግን ክፉ ነገር ይደርስባቸዋል(ሚል 3፡18)፤ እንደ ገለባ በእሳት ይጋያሉ፤ ተቃጥለውም ይጠፋሉ(ሚል 4፡1)፡፡ የጌታ ቀን ሲደርስ ለታዛዦች ሁሉ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላቸዋል፤ ፈውስንም ይሰጣቸዋል፤ ነፃ ወጥተውም እየተደሰቱ ይኖራሉ ፤ በእግራቸውም ትቢያ ሥር ዐመፀኞችን ይረጋግጣሉ(ሚል 4፡2-3)፡፡
ነቢዩ ሚልክያስ ወደፊት ስለሚመጣው የእግዚአብሔር መልእክተኛ ይተነብያል፤ ይህ የእግዚአብሔር መልእክተኛ የተባለው ማን ነው? እንደ ነቢዩ ሚልክያስ አገላለጽ በምን ዓይነት መልኩ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል?
ሕዝበ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ጉዞ ውስጥ መሪዎቻቸው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ በሆነ መንገድ ሲጓዙ፣ የውጭ ጠላቶች ሲያስጨንቁዋቸውና በአጠቃላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲያድርባቸው ከሰዎች ዘንድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ተመርጦ፣ ሕዝቡን በቀና መንገድ የሚመራና በፍትሕ የሚያስተዳድር መሪ ይመጣልናል ብለው ይጠብቁ እንደነበር አስቀድመን አይተናል፡፡ በነቢዩ ሚልክያስ ጊዜም ሕዝቡ በተመሳሳይ መልኩ በወቅቱ በነበሩት መሪዎች ደስተኛ ስላልነበር እንዲሁም ሰዎች በኑሮአቸው አዝነውና ተክዘው ተስፋቸው በተሟጠጠ ሁኔታ ላይ ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነቢዩ ይህንን ጊዜ ማብቂያው መዳረሱንና እግዚአብሔር በቅንነት የሚፈርድበት ቀን መቃረቡን የእግዚአብሔር መልእክተኛ መምጫው መዳረሱን በማብሰር ይናገራል(ሚል 3፡1-5)፡፡
ይህ መልእክተኛ በፊት ይመጣሉ ተብለው በሌሎች ነቢያቶች ከተነገረላቸው መልእክተኞች ለየት የሚያደርገው እርሱ ከመምጣቱ በፊት መንገዱን እንዲያዘጋጅ፣ ጥርጊያው እንዲያቀና እንዲሁም አዋጅ እንዲነግር አስቀድሞ ሌላ መልእክተኛ እንደሚመጣ መገለጹን ነው(ሚል 3፡1)፡፡ ቀጥሎም ሕዝቡ በናፍቆት ይጠብቁት የነበረው ጌታ ወደ ቤተ መቅደስ በፍጥት ይመጣል፡፡ ይህ መልእክተኛ ብረት እንደሚያቀልጥ አንጥረኛ እሳት እጅግ በጣም ብርቱ፣ ፈራጅና እውነተኛ መስካሪ እንደሚሆን ነቢዩ ለሕዝቡ አስቀድሞ ያሳውቃል፤ በዚህም ምክንያት እርሱ በተገለጠ ጊዜ በፊቱ ጸንቶ መቆም የሚችል አይኖርም(ሚል 3፡2)፡፡ ይህ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውና ከእርሱ በፊት መንገዱን እንዲያዘጋጅ የሚመጣው መልእክተኛ ማንነት ባይገለጽም “ታላቅና አስፈሪ የሆነው የጌታ ቀን” ከመምጣቱ በፊት ግን እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን ወደ ሕዝቡ እንደሚልክ ነቢዩ ሚልክያስ በግልጽ ይናገራል(ሚል 4፡5)፡፡ ኤልያስም እግዚአብሔር ምድሪቱን እንዳያጠፋ ተለያይተው የነበሩትን አባቶችና ልጆች ልብ ለልብ እንዲቀራረቡ ያደርጋቸዋል(ሚል 4፡6)፡፡
ይህ የሚመጣው መልእክተኛ በቶሎ ሥራውን ይጀምራል፤ የሚያከናውናቸው ብዙ ተግባራት ስለሚኖሩም ወዲያውኑ የሚጠበቅበትን ተግባር ወደ ማከናወን ተግባር ይገባል፡፡ ከተግባራቶቹም የመጀመሪያው የሚሆነው ቃል ኪዳኑን ማወጅ ነው(ሚል 3፡1)፡፡ ቀጥሎም እንደ ፈራጅ በመቀመጥ ሕዝቡንና ካህናቶቹን ያጠራል፤ በመጨረሻም በአስማተኞችና በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚመሰክሩና የሠራተኛውን ደመወዝ አታልለው በሚያስቀሩ አሠሪዎች፣ ባል የሌላትን መበለትና ድኻ አደጉን በሚያስጨንቁ፣ የስደተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙና እግዚአብሔርን በማይፈሩ ወገኖች ላይ ይመሰክርባቸዋል(ሚል 5፡5)፡፡ ከዚህ የማጥራት ሥራ በኋላ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝቦችም ሁሉ ቀድሞ ያደርጉት በነበረው ዓይነት የሚያቀርቡለት መሥዋዕት ሁሉ ጌታ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ይሆናል(ሚል 3፡4)፡፡
በአዲስ ኪዳን ታሪክ እንደሚታወቀው ጌ.ኢ.ክን ቀድሞ በመምጣት መንገዱን ሲያዘጋጅ የነበረው መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ እንደ ነቢዩ ሚልክያስ አገላለጽ ግን ኤልያስ አስቀድሞ ይመጣል፡፡ ጌ.ኢ.ክ ሲያስተምር መጥምቁ ዮሐንስን እርሱ እነሆ እፊት እፊትህ እየሄደ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ በፊት እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ያ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እነሆ ይህ ዮሐንስ ነው፤ በምድር ላይ ከተወለዱት ሰዎች ሁሉ ከአጥማቂው ዮሐንስ የሚበልጥ ከቶ የለም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉ ያነሰው ይበልጠዋል በማለት እየመሰከረ ኤልያስ ተብሎ የተነገረለት ለመጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ያረጋግጣል(ማቴ11፡ 11-14)፡፡
የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ
መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ
የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ
ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች
1. የነቢዩ ሚልክያስ የነቢይነት አገልግሎት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት በተመለከተ ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?
ሀ)ሚልክያስ የተወለደው ከነቢያት ቤተሰብ ሲሆን የኖረውም ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው፡፡ ለ) ሚልክያስ ለሌዋውያኖች ለየት ያለ ትኩረት ስለሚሰጥ ምንአልባት ራሱ ከሌዋውያን ወገን ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ሐ)የትንቢተ ሚልክያስ መልእክት ለአንባቢውም ሆነ ለአድማጩ ብዙም ግልጽ የሆነ አይደለም፡፡ መ)ትንቢተ ሚልክያስ በወቅቱ የነበሩትን ችግሮች የዳሰሰ አይደለም፡፡ ሠ)መጽሐፉ ባቢሎን ውስጥ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡
2. ነቢዩ ሚልክያስ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስለሚገባው ክብርና ከስደት ተመላሹ ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ ስለነበረው እምነት በተመለከተ ከተናገረው ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?
ሀ)በወቅቱ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ተገቢ የሆነውን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር፡፡ ለ)ካህናቶች ለእግዚአብሔር የሚገባውን ተገቢውን ክብር ይሰጡ ነበር፡፡ ሐ)ከስደት ኑሮ በኋላ ሕዝቡ የገቡትን ቃል ኪዳን ጠብቀው እግዚአብሔርን እያከበሩ ይኖሩ ነበር፡፡ መ)ከአይሁዳውያን ውጪ የሆኑት ባዕዳን ሕዝቦች ዕጣን እያጠኑ ንጹሕ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር፡፡ ሠ)ከስደት ኑሮ በኋላ ሕዝቡ እምነቱ በርትቶ በሥነ ምግባራዊ ሕይወት ይኖር ነበር፡፡
3. ነቢዩ ሚልክያስ ስለ ትዳር ሕይወት፣ ስለ ዐሥራት አከፋፈልና ወደፊት ይመጣል ተብሎ ስለሚጠበቀው መልእክተኛ ከተናገረው ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?
ሀ)ከጥንት ጀምሮ በእስራኤላውያን ዘንድ ፍቺ አይታወቅም ነበር፡፡ ለ)ዐሥራት ማለት አንድ ዐሥረኛ ማለት ሰው፤ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ዐሥራት ሰጠው፡፡ ሐ)ታላቅና አስፈሪ የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር ሙሴን ወደ ሕዝቡ ይልካል፡፡ መ)ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው መልእክተኛ ሲመጣ ሥራውን ቀስ ብሎ ይጀምራል፡፡ ሠ)ዐሥራት አለመክፈል እግዚአብሔርን እንደ ማታለልና እንደ ሌብነት ይቈጠራል፡፡
4. ነቢዩ ሚልክያስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እርሱም አዳመጣቸው፤ የተናገሩትንም ሁሉ ሰማ፤ እርሱን በመፍራት የሚያከብሩት ሁሉ እንዳይረሱ…..” ይልና…“እርሱን በመፍራት የሚያከብሩት ሁሉ እንዳይረሱ” ምን አደረገላቸው?(ይህንን ለመመለስ አራቱንም ምዕራፎች ማንበብ ያስፈልጋል)
ሀ) በእርሱ ፊት ስማቸው በመዝገብ ተጽፎአል፡፡ ለ) በረከት የተሞላበት ሕይወት ይወርሳሉ፡፡ ሐ) ጠላቶቻቸውን ድል ያደርጋሉ፡፡ መ) የእርሻና የከብት መንጋ በረከት ይቀዳጃሉ፡፡ ሠ) አገራቸው በመላእክት ተጠብቆአል፡፡
5. እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ አማካይነት ለእርሱ ስለሚገባው ዐሥራት ይናገራል፡፡ ዐሥራታቸው በሚገባ ለሚከፍሉት ሕዝቦች እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግላቸው ቃል ይገባላቸዋል?(ይህ ጥያቄ መመለስ ያለበት ትንቢተ ሚልክያስ ውስጥ የሚገኘውን በማንበብ ነው)፡፡
-
-
-
-
6. እግዚአብሔር የሕዝቡን መሥዋዕትም ሆነ ጸሎት እንደማይሰማ በነቢዩ ሚልክያስ አማካይነት ይናገራል፡፡ የዚህ ዋና ምክንያት የሆነውም ብዙዎቹ የቃል ኪዳን ሚስቶቻቸው ስለፈቱና ቃል ኪዳናቸውን ስላፈረሱ ነው(ሚል 2፡ 13-16)፡፡ አንዲያው ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “በቃል ኪዳን ባገባችኋቸው ሚስቶቻችሁ ላይ ተንኰል በመሥራት ታማኝነታችሁን አጓድላችኋል፤ ታድያ እግዚአብሔር እናንተና ሚስቶቻችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ እንዲኖራችሁ አድርጎ አልነበረምን?” ይላል(ሚል 2፡ 14-15)፡፡
ወንድና ሴት ተዋውቀው፣ ተፈቃቅደው፣ ተፋቅረው፣ ትዳር ለመመሥረት ተስማምተው፣ አስፈላጊውን የጤና ምርመራ አድርገው፣ የጋብቻ የዝግጅት ትምህርት ተምረው፣ በመንበረ ታቦት ፊት ቃል ኪዳናቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በመሐላ ካጸኑ በኋላ መፋታት ወይም መለያየት ተገቢ ነውን? ምላሹ አዎን ወይም አይደለም ከሆነ የምላሻችን ምክንያቶች መዘርዘር አለባቸው፡፡