በሥጋ ልጇ ከመሆኑ በፊት የእምነቷ ልጅ ነው!
- Category: በሰንበት ወንጌል ላይ አስተንትኖ
- Published: Friday, 01 February 2013 11:22
- Written by Super User
- Hits: 3812
- 01 Feb
(ማቴ 2፡1-12) የማርያም የእምነቷ ኀይል ኢየሱስ ከእርሷ እንዲጸነስና እንዲወለድ አደረገ፤ ስለዚህም በሥጋ ልጇ ከመሆኑ በፊት የእምነቷ ልጅ (ፍሬ) ነው፤ ሐዋርያት የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት እንኳን እንዳልነበራቸው ኢየሱስ ተናግሯል፤ እሷ ግን እምነቷ ሙሉ ስለሆነ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ እንዲወለድና ዓለምን እንዲያድን አደረገ፡፡ እሷ በእምነቷና በጸሎቷ ሰዎች በእግዚአብሔር መንግስት እንዲወለዱ የምታደርገው የቤተክርስቲያን አርአያ ናት፡፡ እሷ በእምነቷ ኃይል የኢየሱስ ክርስቶስ እናት በመሆኗ ምክንያት የኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑ ሁሉ በእምነት እናት ትሆናለች፡፡ ሙሉ በሙሉም ለእግዚአብሔር መገዛትን የክርስቶስ የሆኑ ሁሉ የሚማሩት ከእርሷ ነው፣ እሷ ከተዘለለች እምነታችን መሠረት እንደሌለው ቤት ይሆናል፡፡
ስለዚህ የጌታ ልደት በመጀመሪያ ደረጃ የማርያምን እምነት ሲያመለክት ቀጥሎ የቅዱስ ዮሴፍንና የእረኞችን እምነት ያመለክታል፤ የጥምቀቱ (አሰተርእዮ) ግልጸት የአይሁድን ንገሥ ለማክበር ከምዕራብ ወደ ምስራቅ የመጡትን የሰብአ ሰገልን እምነት ይገልጻል፡፡ ማርያም የተስፋውን ቃል በእምነት ሲጠባበቅ የኖረውን የእስራኤልን ሕዝብ ቅሪት ስትወክል ሰብአ ሰገል ደግሞ ሰላምን፣ እውነትን፣ ፍትሕንና ነፃነትን የሚፈልጉ ሕዝቦቸን፣ ሃይማኖቶቸን፣ ባህሎችንና ሥልጣኔዎችን ይወክላሉ፡፡{jathumbnail off}
ማርያም ለአበው በተገለጸው እግዚአብሔር የሚያምነውንና የሚያውቀውን ሕዝብ ስትወክል እምነቷም በእምነት አባታችን የሆነውን የአብርሃምን እምነት ይመስላል፡፡በአብርሃም አዲስ የተስፋ ዘመን ጀመረ፤በማርያም እምነት ደግሞ ያ ተስፋ እውን ሆኖ አዲስ የደኅንነት ዘመን ጀመረ፡፡ በዚህም ምክንያት የእምነቷ ፍሬ የሆነው የክርሰቶ ብርሃን ቅን ልቦና ላላቸው ሁሉ የተፈጥሮ ምልክትም (ከዋክብት) ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንዲገባቸው ያደርግና ወደ እውነት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል፤(ሰብአሰገልን ኮከብ እንደመራቸው)፡፡ የዚህ ንባብ መልእክት፤ እንደ ሰብአ ሰገል ቅን ልቦና ያላቸውና ለእውነት ክፍት የሆኑ ሁሉ እግዚአብሔርን በኢየሱስ አማካይነት ሊያውቁትና ከሱ ጋር አንድ ቤተሰብ መሆን እንደሚችሉ ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ የሆናችሁ ሁሉ ለእውነት በቅንነት የምንገዛና እውነትን በቅንነት የምንፈልግ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ዙሪያችንን ከበው ያሉ ነገሮች ሁሉ በክርሰቶስ ብርሃን አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱን ናቸው፤ የእውነትም ፀሐይ በርቶልናልና፤ መድረሻችንም አንድያ ነው እሱም ሁላችን በኢየሱስ ትስብእት /ሰው መሆን/ አንድ ሆነን በእግዚአብሔር ቤት አንድ ቤተሰብ መሆን ነው፡፡ ይትባረክ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ አሜን፡፡
አባ ወልደ ትንሣኤ ባለወልድ - ሲታዊ