እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰባቱ መንፈሶች (ኢሳ 11፡1-3)

ሰባቱ መንፈሶች (ኢሳ 11፡1-3)

7ቱ የመንፈስትንቢተ ኢሳያስ 11፡1-3 ከእሴይ ዘር ስለሚያቆጠቁጠው አዲስ ግንድ ይናገራል፡፡ ከዳዊት ቤት ሰለሚነሳው አዲስ ሕይወት፣ ስለተቀባው ንጉሥ፣ ሰለ መሲሑ በትንቢት መንፈስ ሲናገር፣ መሲሑ በሰባት መንፈሶች የከበረ ስለመሆኑ ይመሰክራል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ የእውቀትና የጥበብ መንፈስ፣ እግዚአብሔርንም የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል›› ስለዚህ የእሴይ ልጅ እና የዳዊት ዘር የሆነው መሲሑ በሰባቱ መንፈሶች የከበረ ነው፡፡ እነዚህ ሰባቱን መንፈሶች የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ አለ፡፡ ብሉይ ኪዳን ስለእነዚህ ሰባቱ መንፈሶች ጠለቅ ያለ ማበራርያ ይሰጠናል፡፡

1ኛ. የጥበብ መንፈስ (በዕብራይስጥ Hokma) ነገሥታት ፍርድ የሚሰጡበት፣ የፍርድን ውኃ ልክ ሳይዛነፍ የሚጠብቁበት፣ ደኃ ሳይበደል ፍርድ ሳይጓደል የሚያስተዳድሩበት መንፈስ እንደሆነ ብሉይ ኪዳን ንጉሥ ሰሎሞንን ምሥክር አድርጎ በ1ኛ ነገ 3 ይናገራል፡፡ የጥበብ መንፈስ ነገሥታት ክፉውንና ደጉን የሚለዩበት መንፈስ ነው፡፡ የጥበብ መንፈስ የእግዚአብሔር ማደርያ የሆነውን ድንኳንና በውስጡ የሚገኙትን ነገሮች እንደ እግዚአብሔር ዓላማ ያበጁ ዘንድ ለባለሙያዎች እንደተሰጠ ዘጸ 31፡ 3 ላይ እናነባለን፡፡ የህ የጥበብ መንፈስ መለኮታዊ ሐሳብን ተረድተው በሰው ተግባር በሥራ ላይ ያውሉት ዝንድ ለሥራ ለተጠሩት የተሰጠ መንፈስ ነው፡፡ የጥበብ መንፈስ የማስተዳደር፣ የራስን ሕይወት ፈር የማስያዝ ኃይል ያለበት የሚገራ፣ ነገሮች በሕይወታችን በመለኮታዊ ተዋረድ ልኬት ባላቸው ቅደም ተከተል የሚያዋቅር ሥርዐትና ጨዋነት ነው፡፡ የጥበብ መንፈስ የሕይወት ለዛ እና ውበት የሚጠበቅበትና የሚያንጸባቅበት መንፈስ ነው፤ ጥበብ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ሕይወት ሥርዐት የሚሰጥ መንፈስ ነው፡፡ 

2ኛ. የማስተዋል መንፈስ (በዕብራይስጥ binah) ራዕይ የሚሰጥ እና ራዕይ የሚመረምር መንፈስ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ እና ምክር የምናዳምጥበትና ልብ የምንልበት ኃይል ነው፤ (መዝ 119፡ 34፣73፣100፣125) የማስተዋል መንፈስ የእግዚአብሔርን መገለጥ ሥውር ምሥጢር የምናስላስልበትና መለኮታዊ ኃብታትን የምናጣጥምበት መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕግ ምሥጢር ቀንና ሌሊት በማሰላሰል የዕለት ተዕለት ገጠመኛችንን የምንተረጉምበት፣ የእግዚአብሔርን ሕላዊ የምንገነዘብበት የልብ ኃብት ነው፡፡ በዕለት ተዕለት ገጠመኞቻችን ልብ ውስጥ ዘልቀን እንድንገባ፣ የተሰወረውን እንድንመረምር፣ ያልተነገረውን እንድናዳምጥ የሚያስችለን መንፈስ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳያስ ሰባቱ መንፈሶች በዘረዘረበት ቅደም ተከተል እንዳደረገው፣ ማስተዋልና ጥበብን አያይዘን ስንመለከት ሁለቱ መንፈሶች እርግጠኛነትን፣ ለእውነት መጨከንን፣ አርዶ መውጣትን የምንደፍባቸው ኃይላት ሆኖ ይታያሉ፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በጥበብ እና በማስተዋል ስጦታቸው መለየት ላለብን ነገር ሁሉ ያስጨክኑናል፡፡

3ኛ. የምክር መንፈስ (በዕብራይስጥ esah) ነው፡፡ የምክር መንፈስ አንድን ነገረ በተገቢው መልኩ ለማከናወን ተገቢና ትክክለኛ የሆነውን መንገድ የምንመርጥበት የነፍስ ኃይል ነው፡፡ ተዋቂው የግሪክ ፈላስፋ አርሰቶትል Nicomachian ethics በተባለው ስራው ሲጽፍ ‹‹ሁሉም ሰው መበሳጨት፣ መቆጣት ይችላል ይህም ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ከትክክለኛው ሰው ጋር፣ በትክክለኛው ሰአት፣ በትክክለኛው አላማ፣ በትክክለኛው መንገድ፣ በትክክለኛው መጠን መቆጣት የሁሉም ሰው ችሎታ አይደለም፤ ይህም ቀላል አይደልም›› ይላል፡፡ የምክር መንፈስ የመስከን፣ የእርጋታ፣ የመመለስ እና የማረፍ መንፈስ ነው፡፡ ይህንን የሚያውቅ፣ የእግዚአብሔርን መንፈሰ ምክር የሚያቃልል እና በፈረሶች ኃይል የሚታመን ንጉሥ ሞኝ እንደሆነ ኢሳ 29፡ 15፣30፡1 ማየት ይቻላል፡፡ ምክራቸውን ጥፈልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር የሚሰወሩ፣ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀና? ለሚሉ ወየውላቸው! ‹‹(ኢሳ 29፡ 15) ጥበብ እና ምክር የተሳሰሩ ናቸው፣ ጥበብን የሚሻ ያዳምጣል ምክር ጥበበኛ ያደርጋል፣ ጥበብም ለምክር ልብና አዕምሮን ይከፍታል፡፡ ምክር ከጽናት ጋር የሚያያዝ ነው፤ ንጉሥ በጦር ሜዳ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርግ እና ከውሳኔውም ወደ ኋላ እንዳይሸሽ በመለኮታዊ ምክር በጠላቱ ላይ ብርቱ የሆናል፡፡

4ኛ. የጽናት መንፈስ (የኃይል) (Heb. geburah) ይህ መንፈስ ነገርን ሁሉ በእውነት ሚዛን ልክ መዝነን በፍትህ የምንፈርድበትን የሞራል ልዕልና የሚሰጠን መንፈስ ነው! ስለዚህ ኢሳያስ በትንቢቱ ሲመሰክር በምዕራፍ 28፡6 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹በፍርድ ወንበር ላይ የሚቀመጥ የፍርድ መንፈስ፣ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱ ኃይል ይሆናል››፡፡ የጽናት መንፈስ ታላላቅ ፈተናዎችን የምንታገስበት፣ እስከ ሰማዕትነት የምንታመንበት መንፈስ ነው፡፡ ለምሳሌ በትንቢተ ኢሳያስ 3፡25 እንደምናነበው የጸናት መንፈስ በሌለበት ስፍራ ሁሉ ጎልማሶች በሰይፍ፣ ኃያላንም በውጊያ ይወድቃሉ፡፡ ኢሳያስ ይህንን በጦርነት መልኩ መናገሩ የመንፈሳዊ ውጊያ እና የተጋድሎን አስፈላጊነት ያሳያል፡፡ ያለተጋድሎ በመንፈሳዊ ሕይወት ከጌታ ጋር አንዲትም እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ ማለት አይቻልም! ስለዚህ ኢሳያስ ምክር እና ጽናትን ጎን ለጎን አያይዞ ያሳየናል፡፡ በጸሎት መውጣት፣ በእግዚአብሔር ድምጽ መውጣት የሚያጸና ኃይል መሆኑን ይመሰክራል፡፡

5ና የእውቀት መንፈስ (በዕብራይስጥ da'at elohim) እግዜርን የማወቅ መንፈስ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ሕግ ወደ ነፍስ ዳርቸዎች ሁሉ የምናደርስበት፣ እግዜርን የምናሰላስልበት፣ መለኮታዊ ምስጢራትን የምናጣጥምበት ኃይል ነው፡፡ ዳዊት ስለዚህ ሲናገር ‹‹ጻድቅ በእግዜር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉን በቀንና በሌሊት ያስበዋል›› (መዝ 1፡2) ይህም የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል እና ሕይወትን በዚህ መንገድ ለመቀየስ የሚያግዝ መንፈስ ነው፡፡ ኢሳያስ በትንቢቱ 11፡9 ‹‹ውሃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዜርን በማወቅ ትሞላለች›› ይላል፡፡ የእውቀት መንፈስ የእግዜርን ፍቃድ ማወቅ እና እንደ እግዜር ፍቃድ መኖር የሚሰጡን መንፈስ ነው!

6ኛ. እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ (በዕብራይስጥ yirat) ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔርን ማወቅ፣ መውደድ፣ ትእዛዙን መፈጸም፣ እግዜርን የማክበር መንፈስ ነው፡፡ ይህም ስርዐተ አምልኮን ለእግዜር የሚገባውን ክብር በሚሰጥ መልኩ በስጋና በነፍስ መፈጸምን፣ ለፍጥረት ሁሉ እንደ እግዜር ያለ ጥንቃቄን ይመለከታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስገባ ብቻ ሳይሆን በሁለተናየ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስነቴን የሚስተካከል አካላዊ እና መንፈሳዊ ቁመና መላበስ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ኢሳያስ በትንቢቱ 29፡13 እንዳለው ‹‹ይህ ሕዝብ በአፉ ወደኔ ይቀርባል እና በከንፈሮቹ ያከብረኛልና፣ ልቡ ከኔ የራቀ ነው›› የሚለው ይሆንብናል፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት አማኙን ሰነፍ አማኝ እንዳይሆን የሚረዳው ኃይል ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት በሁሉ ነገር እግዚአብሔርን ማምለክ ነው፤ እግዜርን መፍራት በንጹ አምልኮ በሁሉ ነገር ለእረሱ ብቻ መገዛት ነው፡፡ እግዜርን መፍራት ለነፍስ እና ለሥጋ በልባቸው በአርአያው እና በአምሳሉ ለፈጠራቸው ለእርሱ መጠንቀቅ ነው!

ኢሳ 11፡3 ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ደስታውን ያያል! መንፈስ ቅዱስ ያስተምራል፣ በእግዚአብሔር መንገድ ያራምደናል፤ በእግዚአብሔር አላማ ውስጥ ደግሞ ደስታው ነው! ስለዚህ ደስታ በእግዚአብሔር እንኖር ዘንድ እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በምስጢረ ጥምቀት ተቀብለናል፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ልብና አዕምሮ ወደ እግዚአብሔር ይመልሳል፣ ፈላጎቶቼን እየገራ በጨዋነት ያሳድገኛል፡፡ አሜን!

7ኛ - የየዋህነት መንፈስ - ይህ ስጦታ ከእምነት የሆነው የፍትሐዊነት አቋማችንን ሙሉ ያደርግልናል፤ እግዚአብሔርንም እንደ አባታችን የምናውቅበትን ፍቅር ይሞላናል። የዋህነት ስለ እግዚአብሔር ብለን ሰዎችንና ነገሮች ለማፍቅርና ለማክብር ያበቃናል። የየዋህነት ስጦታ በየዋህነት የምናደርጋቸውን የሃይማኖት ልማዶችና አምልኮ ደስታን ወደ ተሞላ የእግዚአብሔር አገልግሎት ይቀይርልናል።

እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ አምላክ በምስጢረ ጥምቀት አዲስ ልደት የሰጠኸን ኃጢያታችን ከኛ ያስወገድህን እና በደምህ አጥበህ ያለ እንከን በፊትህ ያቀረብከን ጌታ ኢየሱስ ሆይ የመጸናናት እና የመጽናትን መንፈስ፣ መካሪ እና ጠበቃችን የሆነ መንፈስ፣ የጥበብ እና የማስተዋል መንፈስ፣ የእውቀት እና እግዜርን የመፍራት መንፈስ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ መስቀል አትመህ የለየኸን ጌታ ሆይ መንፈስህን ላክ፣ የምድርህንም ገጽ አድስ! አሜን!    

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት