እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰንበት ዘብርሃን 2005 ዓ.ም.

ሰንበት ዘብርሃን 2005 ዓ.ም.

መዝሙር፡ አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሓት. . . . ።

ንባባት፡ ፍሊጲስዩስ 1፡4~11፥ 2ጴጥ 3፡8~14፥ ግ.ሓ. 26፡12~19 ሉቃስ 3፡1~6

ምስባክ፡ ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፥ እማንቱ ይምርሓኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ፥ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ። መዝ. 43፡3~4 በዛሬው ሰንበት ከሚነበበው ወንጌል ኃይለ ቃል አድርገን የምንወስደው «ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም ፤» የሚለውን ነው (ዮሐ፡ 1፡11)፡፡

Calvaryእዚህ ላይ መነሳት ከሚችሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይሆናሉ፡ «እነማን ናቸው ወገኖቹ...ይህን ያህል እምነት የተጣለባቸው? ይህ ክብር የተሰጣቸው? ምናልባት በስልጣን ከፍ ያሉ ወይም በሀብታቸው ዓለም በልዩ መዝገብ ላይ ያሰፈረቻቸው ናቸው? ምናልባት በመገናኛ ብዙኃን ቀን ከሌሊት የሚወራላቸው ይሆኑ የእርሱ ወገኖች?» መጽሐፍ ግን የክርሰቶስን ወገኖች «ታናናሽ» ብሎ ነው የሚጠራቸው፡፡ የክርስቶስ ወገኖች እርሱን በቅን እና በትሁት ልብ የሚፈልጉት ናቸው፣ ምክንያቱም በወንጌሉ መሰረት ግን የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ያለ ሁሉ እውነትም ወገን ሆኖ ክርሰቶስን የተቀበለ አልተገኘም በዘመኑ፡፡ ስለዚህ በተስፋው መሠረት ቃል የተገባለት እና የተመረጠው ሕዝብ ሳይሆን ለአሕዛብ ሆነ፣ መዝሙረኛው ዳዊት «የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ...ትዕዛዜን እንደሰሙ ይታዘዙልኛል» እንዳለው (መዝ፡ 18፡43)፡፡ የመዳኛው ቀን መምጣቱን መሲሕም በመካከሉ መቆሙን ያላወቀው፣ የተመረጠ ሕዝብ በመሆኑ ብቻ ይታበይ የነበረው ግን ዐይኑም ልቡም ታውሮ ነበርና ወገኔ ብሎ የመጣውን አምላክ ሊቀበለው አልቻለም፡፡ ክርሰቶስም ይህን የመዳኑን ጊዜ ላላወቀው ሕዝብና ከተማ አለቀሰለት (ሉቃ፡ 19፡41-44)፡፡ ልበ ትሁታን ግን አንዴ ሲያዩት፣ የአፉን ትምህርት ሲሰሙ፣ የእጁን ድንቅ ስራዎች ሲመለከቱ በአግራሞት ተሞሉ፣ ጨለማቸው በራላቸው፤ ቅ. ጳውሎስ «እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፣ የተመረጡት ግን አገኙት፣ የቀሩት ልባቸው ደነደነ» እንዳለው (ሮሜ 11፡7)፡፡

የዛሬው ወንጌል «ሁሉ በርሱ ተፈጠረ» ይላል (ዮሐ 1፡3)፡፡ ከዚህ የምንማረው ደግሞ ሁሉ በክርስቶስ ተፈጥሮ ሳለ ፍጡር ግን ከዳተኛ ሆነ፤ ፈጣሪውንም ጠንቅቆ ባለማወቁ አምላኩ በጎበኘው ጊዜ ወደ ልቡ ሳያስገባው፣ ሳይቀበለው ቀረ፣ በፈጣሪው ላይም ልቡን አሸፈተ፡፡ ነገር ግን በፍጥረታችን ደካማ፣ አንዳንዴም አስቸጋሪ ብንሆንም ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን የማይጠላ አምላክ ነውና «ወገኖቼ» ብሎ መምጣቱን አያቋርጥም፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ደግሞ በበር ቆሞ የሚያንኳኳውን እና ብርሃን የሆነውን ወደ ልቡ ማሰገባት ነው (ራዕ 3፡20)፡፡ ለእግዚአብሔር ጥሪ ጆሮውንም ልቡንም የሚዘጋ ግን ለመጥፋቱ ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ «ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» እንዲል መዝሙሩ፣ ይህን ብርሃን መጥራት፣ መጋበዝ፣ በርሱም መመላለስና መኖር ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን ወይም ማመናችን ወደዚህ ብርሃን ካላቀረበን ወይም የክርሰቶስ ወገናዊነታችንን ካላመለከተ ጎዶሎ እምነት ነው፤ የምንመላለሰውም በደመዘዘ ብርሃን ውስጥ ነው፡፡

እንግዲህ ክርስትናችን የሰንበት ወይም የዓመት በዓል ክርስትና፣ የአጋጣሚ ክርስትና እንዳይሆን ብርሃን እና የብርሃንም አባት የሆነው ክርስቶስ ጸጋውን ያብዛልን፤ የጨለማን ሥራ አስወግደን በብርሃን እንድንመላለስ የእርሱም ወገኖች እንድንሆን ያበቃን ዘንድ የአምላካችን መልካም ፍቃዱ ይሁንልን! አሜን!

አባ ዳዊት ወርቁ

የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት