እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰሙነ ሕማማት

7. ሕይወት በክርስቶስ

OIP 2ቀዳም ሥዑር በዓርብ ስቅለት ትዝታ እና በትንሳኤ ተስፋ መካከል የምትገኝ፤ በሞት እና በሕይወት መካከል ስንቆም እንደ እምነት አባታችን እንደ አብርሐም ተስፋ ባልሆነው ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ የምንማርባት ዕለት ናት። ይህቺ የተሻረችው ሰንበት የዓለምን አስተሳሰብ እና ስሌት ሁሉ የሻረች የአሸናፊነት ሰንበት ናት! በዚህች ሰንበት ኃያልነት፣ ጉልበት፣ ሥልጣን፣ ፍርድ፣ አሸናፊነት ወ.ዘ.ተ. የሚሉት ሐሳቦች ሁሉ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በሚሉ ተሰምተው በማያውቁ፣ ዛሬም ቢሆን ሲሰሙ ሰርክ አዲስ በሆኑ ቃላት ትርጉማቸው የተቀየረበት ዕለት ናት። ይህቺ ዕለት እግዚአብሔር “አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና... ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” (ኢሳ 55፡8-9) የሚለው ቃሉ እውነተኛ መሆኑን ያሳየባት ዕለት ናት!። በዚህች ዕለት ጌታችን ወደ መቃብር ሲወርድ ሞት ለዘመናት በነገሰበት ሥፍራ የሕይወት ባለቤት ገብቷልና ሞት ኃይሉን ተነጥቋል። ጌታ በመቃብር ውስጥ ሞትን ያህል ነገር “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” (1ቆሮ 15፡55) እያለ በአሸናፊነት ኃይሉ ይናገረዋል።

በሞጥ ጥላ ሥር የነበሩትን ሁሉ ወደሚያስደንቅ ብርኅን ያወጣቸው ዘንድ እርሱ እነርሱ ወደወረዱበት ጥልቅ ሊወርድ እንኳን ፈቃደኛ ሆኗልና ዛሬም እያንዳንዳችን በወረድንበት ጥልቅ ውስጥ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ የሚለው የድል አድራጊው የኢየሱስ ድምጽ ይሰማል። ይህቺ ሰንበት ክርስትና ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ተስፋ ጭምር በድል አድራጊነት የሚኖር እምነት መሆኑን የምንመሰክርባት ዕለት ናት! እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ታሪካችን ብቻ ሳይሆን ወደ ሕይወት ሁኔታዎቻችን እና ሰው መደመሆን ትርጓሜ ጥግ ሁሉ ገብቷል። እግዚአብሔር አምላክ  በአዲስ ኪዳን በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከፍትረት ሁሉ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቷል። ስለዚህ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ በልጁ በኩል ከአብ ጋር በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ያደርጋሉ። በዚህም ግንኙነት የተነሳ እያንዳንዳቸው ደግሞ የእርሱ የአካል ክፍሎች እና የቤተ ክርስትያን ልጆች ሆነው  በትውልድ መካከል የጌታን በሥጋ መገለጥ። ሕማሙን። ሞቱን እና ትንሳኤውን የሚናገሩ ሕያው ምሥክር ይሆናሉ።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው አዲስ ሕይወት የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ማንነት ሳይሆን ይልቁንም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለው እምነት እና ከእርሱ ጋር በቤተ ክርስትያን በኩል በምሥጢራት አማካይነት ባለው ኅብረት በአዲስ ማንነት ይገለጣል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስትያኖች በጻፈላቸው መልእክት እንዲህ እያለ ይህንን የአዲስ ሕይወት ማንነት እና መልክ ይገልጽልናል “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” (ገላ 2፡20)።  ኢየሱስ ክርስቶስ ለአማኞች የሚሰጠው ጸጋ ድንቅ እና ተዓምራት የማድረግ ኃይል ሳይሆን ይልቁንም ከአባቱ ጋር በልጅነት መንፈስ እንገናኝ ዘንድ አዲስ የልጅነት ጸጋ ሥጦታችን ሆኗል በኢየሱስ ልጅነት በኩል የአብ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሶች ሆኖ መወለድ ተዓምራትን ከማድረግ በላይ ሳይሆን ከተዓምራት ሁሉ በላይ ነው።

በመሰረቱ በአዲስ ኪዳን ያገኘነው ጸጋ የእግዚአብሔር የሆነ ነገር ሳይሆን ወልደ እግዚአብሔር ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የአዲስ ኪዳን የጸጋ ሥጦታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ክርስትያን በጸጋ ይኖራል ማለት በእግዚአብሔር ባሕርይ ይኖራል ማለት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ በክርስቶስ ይኖራል ማለት ነው። ይህንን እውነታ የረሱ ለመሰለው የቆሮንጦስ ክርስትያኖች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መሰረታዊ ጥያቄ ያቀርባል “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?” (2ቆሮ 13፡5)።  በታሪክ ውስጥ ሥጋ ለብሶ የተገለጠው እና በምድር ላይ የተመላለሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በቤተ ክርስትያን ምሥጢራት በኩል በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ሕያው ሆኖ ይኖራል።  እርሱ የሕልውናችን ምሥጢር  በመሆኑ ሁላችንንም ወደ ተፈጠርንበት ክብር የሚያደርሰን የክብር ተስፋ ያለው እና በውስጣችን የሚኖረው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

በክርስቶስ መኖር የፋሲካችን ትርጉም እና አክሊል ነው፤ ከፍ ብሎ የተሰቀለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ“ሰው”ነት ፍጻሜ እና ምልዓት ሆኖ ይታያል። የሰው ልጅ ቀና ብሎ ኢየሱስን በሚያይበት የሕይወቱ ክፍል ሁሉ የበለጠ “ሰው” እየሆነ ይጎለምሳል! ይህ ከፍ ብሎ የተሰቀለው ጌታ በያንዳንዱ የሰው ልጅ ውስጥ እንደ ተፈጠርንበት የሕይወት ዓላማ እና ጥሪ ራሱን አንድ አድርጎ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ይህ አዲስ የክርስቶስ ሕይወት በአማኞች ውስጥ በምሥጢረ ጥምቀት የሚጀመር ሲሆን፣ በምሥጢረ ሜሮን በመንፈስ ቅዱስ ማሕተም ለዘላለሙ ለዳነበት ኪዳን ታማኝ መሆኑ ተረጋግጦ፣ ከጌታ ጋር በአንድ ገበታ በቅዱስ ቊርባን ማዕድ እየተካፈለ አዲሱን ሕይወት በተግባር ይለማመዳል። በዚህ ጉዞው የደከመ እንደሆነ በምሥጢረ ንስሐ እየታደሰ እና የጸጋው ክብር እየተመለሰለት በክርስትያናው እየበሰለ ይጓዛል። ከዚህም ብስለት የተነሳ በምሥጢረ ክህነት እና በምሥጢረ ተክሊል የክርስቶስን አካል እየመገበ ተልዕኮውን በበለጠ ታማኝነት ይፈጽማል። ከዚህ በኋላ በምድራዊ ሕይወቱ መደምደሚያ እና በዘላለማዊ ሕይወቱ መጀመርያ ላይ አንተ ታማኝ እና ደግ አገልጋይ ና የጌታህን ደስታ ለመቀበል ግባ ተብሎ በምሥጢረ ቀንዲል በኢየሱስ ክርስቶስ የፈውስ ጸጋ  ይቀደሳል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቃብር የወረደው እያንዳንዳችንን ከመቃብራችን ይዞ ለመነሳት ነው። እርሱ ስለኛ የቀዘቀዘው እኛ እያንዳንዳችን ደግሞ በትንሳኤው እሳት በመንፈስ ቅዱስ እንድንቀጣጠል ነው። 

 

ትንሳኤውን ያሳየን

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት