እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ልደት፥ጥምቀት፥ትንሳኤ

የጌታ ሥጋ መልበስ እና የጌታ ጥምቀት ምሥጢር

Baptism fbየቤተ ክርስትያን ሊቃውንት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰላሳ ዓመት ዕድሜው በዮርዳኖስ ወንዝ እንደተጠመቀ ይናገራሉ፤ በጌታ ጥምቀት ጊዜ ሰማይ እንደተከፈተ እና እግዚአብሔር አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራል፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ ቁም ነገር በቤተ ልሔም በረት ውስጥ በመወለዱ ምሥጢር ወይም ደግሞ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የተጀመረ አይደለም። የጊዜ ሁሉ ባለቤት ዘመን ተሰፍሮለት፣ ጊዜ ተቆጥሮለት በታሪካችን ውስጥ ተገለጠ እንጂ የእርሱ ታሪክ መጀመርያ እና መጨረሻ የለውም፤ እርሱ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ” እያለ ስለራሱ እውነቱን የሚናገር ነው (ራዕ 1፡8)። ዳዊት በመዝሙሩ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” (መዝ 2፡7) እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም ጀምሮ የተወደደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የምሥራች ይናገራል።

የአሌክሳንድርያው ቅዱስ ቀለሜንጦስ በ2ኛው ክፍለ ዘመን  ስለ ጌታ የጥምቀት በዓል ለመጀመርያ ጊዜ እንደተናገረ ስራዎቹ ያሳያሉ[1]። ከዚያ ጊዜ ጅምሮ የጌታን ልደት እና የጌታን ጥምቀት ማክበር የጥንት ክርስትኖች በታላቅ መንፈሳዊነት የሚፈጽሙት ተግባር መሆኑን ማስተዋል ይቻላል። በጥንታዊቷ ቤተ ክርስትያን ከነበሩት በርካታ መንፈሳዊ ልምምዶች አንዱ ንግደት ነበር፤ በዚህም መሰረት በ4ኛው ክፍለ ዘመን የኖረችው መነኩሴ እና ነጋዲ ኤጌርያ በንግደት ማስታወሻዋ ላይ ከምዕራፍ ሰባት እስከ አስራ አንድ እንዳሰፈረችው ክርስትያኖች በቤተ ልሔም በቁስጥንጢኖስ ባዚሊካ እና በኢየሩሳሌም የጌታን ልደት ያከብሩ እንደነበር መመልከት ይቻላል።

የጌታችን ምድራዊ ሕይወት እና ተግባር ሁሉ ከመዳናችን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ቁም ነገር አለው። በጌታ ሕይወት ውስጥ የተገለጠው እያንዳንዱ ቁም ነገር የሰው ልጆችን የሕይወት አድማስ የሚዳስስ እና ከዘላለም ጀምሮ ለተፈጠሩበት ዓላማ የሚቀድስ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። በመሆኑም በጌታ ሕይወት እያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ የእያንዳንዳችን ሕይወት እና የተፈጠርንበት የክብር ዓላማ ፍንትው ብሎ ይታያል። ቅዱስ አውጉስጢኖስ ይህንን ሁኔታ ሲያብራራ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት፣ ወደ መታን ዓለም መውረድ፣ ትንሳኤ፣ በክብር ወደ ሰማይ መውጣት እና በዘላለም ዙፋኑ በአብ ቀኝ የመቀመጡ ምሥጢር ሁሉ ከእኛ ሕይወት ጉዞ እና ከፍጻሜያችን ክብር ጋር በእጅጉ በመቆራኘቱ በእርሱ ሕይወት መሰወር ምሥጢር ውስጥ እያንዳንዳችን ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ክብር በመንፈስ ቅዱስ ከብረናል”[2] ይላል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በእነዚህ ምሥጢራት የተሞላ ነው፤ በመሰረቱ ወንጌል ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የቀረበ ትረካ ሳይሆን የወንጌል አስኳል እና ፍጻሜ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው።  ይህ ወንጌል በተለይም በሥርዐተ አምልኮ ውስጥ ሥጋ ለብሶ ይገለጣል፤ ሊጡርጊያ “ቃል ሥጋ ለብሶ እውነት እና ጸጋን ተመልቶ” በመካከላችን ሕያው የሚሆንበት  የትስብዕቱ ምሥጢር የማያቋርጥ መገለጥ ነው፤ በመሆኑም በቤተ ክርስትያን የምናከብራቸው በዓላት እና አጽዋማት በሙሉ በየዕለቱ ከጌታ ሕይወት ጋር ሕብረት በሚያደርግ ክርስትያናዊ እና ክርስቶሳዊ ኑሮ ለመመላለስ ዕድል ይሰጡናል።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በአብ የነበረው የማዳን ተልዕኮ በጎ ፈቃድ ተገልጧል፤ በመሆኑም የጌታን ጥምቀት ስናከብር የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በሕይወታችን እንመሰክራለን፤ እርሱ ከዘላለም ጀምሮ በልቡ የነበረውን “ለእናንተ የማስባትን ሐሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜ እና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም ሐሳብ ነው” (ኤር 29፡11) እያለ የተናገራትን ተስፋ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ገልጦልናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስያስ ክርስትያኖች በላከው መልእክቱ ይህንን መገለጥ እንዲህ እያለ ይመሰክራል፤ “ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው” (ቆላ 1፡25-27)። ይህ የእምነት ምሥጢር በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ነው።

የእግዚአብሔር ምሥጢር ስለ እምነት የተገለጠ ረቂቅ እውቀት ሳይሆን፣ ይልቁንም የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ ምሥጢር ሁሉን የፈጠረበት ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው (ቆላ 2፡2)። ይህ “ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር” (ኤፌ 3፡9) አሁን በቤተክርስትያን መካከል ተገልጧል፤ በመሆኑም ቤተ ክርስትያን የእግዚአብሔር ምሥጢር መገለጥ ናት። እርሷ “ቃል ሥጋ” በመሆኑ ምሥጢር በመካከላችን የእግዚአብሔር ሕልውና ምሥክር ሆና ትታያለች፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የቤተ ክርስትያን ምሥጢር እንዲህ ይገልጸዋል “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ” (ኤፌ 3፡10)። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በዚህ የእግዚአብሔር የዘላለም ሐሳብ ውስጥ የተካተተ ስለነበር ጊዜው በደረሰ ጊዜ (ገላ 4፡4) እንደ እግዚአብሔር የማዳን ሥራ ተልዕኮ በጎ ፈቃድ ሥጋ ለብሶ ተገለጠ።

የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በታሪካችን ውስጥ ይፈጸማል፤ ይህ የማዳን ሥራ በ“ቃል” ብቻ የተነገረ የምሥራች ሳይሆን ይልቁንም በቃል እና በሥራ የተገለጠ እውነታ ነው። ይህ በቃል እና በሥራ የተገለጠው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ከጊዜ ጋር የጀመረ፣ ጅማሬ እና ፍጻሜ ያለው ሳይሆን ይልቁንም ከጊዜ እና ከፍጥረት አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮ የነበረ (ንጽ ቆላ 1፡26፣ ኤፌ 1፡5-11፣ ኤፌ 3፡11) ሁሉ የተመሰረተበት የፍቅር ምሥጢር ነው።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እና ጥምቀት በውስጣቸው በተሸከሙት ይዘትም ይሁን በአከባበራቸው፣ በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ የተሳሰሩ “ቃል ሥጋ” የመሆኑ ምሥጢር ተመጋጋቢ ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ተልዕኮ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ቁም ነገር ነው፤ በመሆኑም ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ በመጥምቁ ዮሐንስ አንደበት አድርጎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ተራው እስከሚደርስ ድረስ ከኃጢአተኞች ጋር ተሰልፎ ይጠብቅ እንደነበር ይመሰክራል (ዮሐ 1፡26)። ጌታ በልደቱ የተካፈለውን ሥጋ የግርዘት ሥርዐትን ፈጽሞ ከሕግ ቀንበር አርነት ካወጣው በኋላ በዮርዳኖስ በተካፈለው ጥምቀት ደግሞ ለቤተ መቅደስነት ክብር የተገባ አድርጎ ሲቀድሰው እንመለከታለን። በርግጥ በዮርዳኖስ የተቀበለው ጥምቀት በመስቀል ላይ የሚቀበለው እና እኛም በመሥዋዕተ ቅዳሴ የምንፈጽመው የደሙ ጥምቀት ምሥጢር ነው። በዚህም በልደቱ በኩል ፍጥረት ሁሉ እንደ አዲስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደተወለደ እንደዚሁ፣ በደሙ የተነሳ ፍጥረት ሁሉ እንደ አዲስ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስነት ክብር ተቀድሷል (ሮሜ 5፡8-9)። እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የቤተ ክርስትያን በዓላት ስላለፈ ታሪክ የሚዘግቡ የጥንት ታሪክ መዘክሮች ሳይሆኑ፣ ይልቁንም የእግዚአብሔርን የማዳን ምሥጢር በአሁናዊ ሁኔታችን ውስጥ የሚያስተጋቡ እና ወደ ተቀበልነው የጸጋ ሙላት እንድንቀርብ የሚጋብዙን የጸጋ አጋጣሚዎች ናቸው።

የልደት እና የጥምቀት በዓላት የሚተነብዩት የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ በኩል ተፈጽሞ ይታያል፤ በመሆኑም የልደት እና የጥምቀትን በዓል ስናከብር በመሰረቱ የምናከብረው ቁም ነገር በቀራኒዮ የተፈጸመውን የጌታችን እና የመድኃኒታችንን ቤዛነት ነው። በመሆኑም እነዚህ ሦስቱ ማለትም ልደት፣ ጥምቀት እና ትንሳኤ ስለ እያንዳንዳችን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መግባት በአንዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የተገለጡ የእግዚአብሔር ፍቅር እውነተኛነት የቃልኪዳን ማኅተሞች ናቸው።  በመሆኑም ከጥምቀቱ በኋላ በቀጥታ የምናከብረው የቃና ዘገሊላ በዓል “ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ ያምኑ ዘንድ” በማመናቸውም ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ጌታ ክብሩን በመካከላቸው ሲገልጥ እንመለከተዋለን (ዮሐ 2፡11)።

እያንዳንዱ የቤተ ክርስትያን ሥርዐተ አምልኳዊ ሕይወት ወደ ኋላ የሚመለከት፣ ልናነሳው የሚገባንን የእምነት ምሥጢር ወደ አእምሮአችን ከፍ የሚያደርግ ቁም ነገር ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም የቤተ ክርስትያን ሥርዐተ አምልኳዊ ሕይወት “የመዳን ቀን ዛሬ ነው! ሰዓቱም አሁን ነው!” ተብሎ እንደተጻፈ እንዲሁ የእግዚአብሔር ማዳን በእያንዳንዳችን የሕይወት ዛሬ እና አሁን ውስጥ እንዲፈጸም ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት የሚያደርገን የጸጋ ሕይወት መገለጥ ነው። በዚህ አይነት የክብር ተስፋ ያለውን ክርስቶስ ኢየሱስን እያከበርን በምሥጢረ ጥምቀት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ የእግዚአብሔር አብ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ሆነን ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በተወለድንበት የጸጋ ልጅነት ወደ ትንሳኤው ተስፋ እየተመለከትን ዳግም እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን እና ትንሳኤውን እንናገራለን።

ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መገለጥ የሚመሰክሩት የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች ይህ “ምሥጢር” በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮ ይኖር እንደነበር ይናገራሉ፣ በመሆኑም ሐዋርያቱ እና ደቀ መዛሙርቱ ሳይቀሩ ስለዚህ ምሥጢር ቀስ በቀስ ወደ እውቀት ሙላት ለመድረስ ይመላለሱ እንደነበር ከቅዱሳት መጽሐፍት ማስተዋል እንችላለን። በዚህም ሐዋርያቱ ቀስ በቀስ የጌታን ማንነት እየተረዱ በመምጣታቸው “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ማቴ 16፡16) የሚለው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምሥክርነት ስለ ጌታችን ማንነት መገለጥ የተሰጠ ከፍተኛው የሐዋርያት የእምነት ቃል ሆኖ ይነበባል።

የጌታ ሥጋ ለብሶ መገለጥ ምድርን እና ሞላዋን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ቀድሷታል። የሁሉ ነገር ፈጣሪ፣ ነገር ሁሉ የተፈጠረበት ምሥጢር፣ የሚታየው እና የማይታየው ሁሉ በልክ፣ በመጠን እና በመለኮታዊ ውበት የተሞሸረበት ጥበብ እና ሁሉ ነገር በሰመረ ተግባቦት ተያይዞ የጸናበት ምሥጢር (παντοκράτωρ) የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረትን ሁሉ በመስቀሉ አጥርቶ ባዘጋጀው የሕይወት ብራና ላይ በደሙ ቀለም እንደ አዲስ ጽፎታል። እርሱ ሰው ሆኖ በመገለጡ ምሥጢር መለኮታዊ ብርኀኑን እና ክብሩን ሁሉ በከኛ በተካፈለው ሰውነት ውስጥ ሰውሮ እኛ ልናየው በምንችለው ሰብዓዊ መልክ ቀርቦናል።  አይተነው በሕይወት እንኖር ዘንድ፣ ማየታችን ለሕይወት እንዲሆንልን እንደ ምስኪን ሕጻን በበረት እስከሚተኛ ድረስ ስለ መዳናችን ትሑት ሆናል። እርሱ ትሑት ሆኖ በምድር በመመላለሱ ምሥጢር በኩል እኛ ደግሞ በአባቱ መንግሥት እንደ ተወደዱ ልጆች የምንመላለስበትን ከዘላለም ጀምሮ የእርሱ ብቻ የነበረውን የልጅነት መብቱን አካፍሎናል።

የጌታ ጥምቀት ምሥጢር የቅድስት ሥላሴ መገለጥ የታየበት፣ ቅድስት ሥላሴ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን በመካከላችን የገለጠበት የሥላሴ ብርኀን በዓል ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዮሐንስ መጥምቅ በበረሃ የሚሰብከው የእግዚአብሔር መንግሥት መቅረብ በዐይኑ ፊት ሲፈጸም ተመልክቷል። የቀደመችው ርግብ የተስፋ መልእክት ይዛ በውኃ መካከል ወደ ነበረው ወደ ኖኅ እንደመጣች እና የአዲስ ዘመን የምስራች እንዳበሰረች፣  በኢየሱስ ላይ ያረፈችው ርግብ እንዲሁ የአዲስ ዘመን ብሥራት ምሥክር ሆና ትታያለች። በዚህም ኢየሱስ ወደ ውኃው በመግባቱ እግዚአብሔር ውኆችን እና የምድር ምንጮችን ሁሉ ቀድሷል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት እንድንካፈል በቅድስት ሥላሴ ስም በሚሆን በምሥጢረ ጥምቀት አዲስ ፍጥረት እንሆን ዘንድ ዓለም ሁሉ ለዚህ ዓላማ በክርስቶስ ቤዛነት በኩል ተቀድሷል[3]

ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በጸሎት መጽሐፍት ውስጥ የጌታን ጥምቀት የሚያሳዩ ስእላዊ መግለጫዊች ክርስቶስ የጎልማሳ ተክለ ሰውነት ተላብሶ በዮሐንስ ፊት ለጥምቀት ተዘጋጅቶ ይታያል። ኢየሱስ ፍጹም ሰው የመሆኑ ምሥጢር በለበሰው ተክለ ሰውነት እና በኃጢአተኞች መካከል በመሰለፉ በኩል ግልጽ ሆኖ እየታየ ሁላችንም በእርሱ በኩል ወደ ሕይወት ውኃ መጋበዛችንን እንድናሰላስል ያሳስበናል። ኢየሱስ በውኃ መካከል በመቆሙ፣ ወደ ውኃው በመስጠሙ እና ከጥልቁ የባሕር ውኃ ዳግም ወደ ሕይወት በመውጣቱ ምሥጢር በኩል ማንም በዚህ ውኃ መካከል የሚያልፍ ሁሉ በእምነት ምሥጢር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ሱታፌ አለውና ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርኀን ተሸጋግሯል፤ ስለዚህም ኢሳያስ በትንቢቱ አስቀድሞ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርኀን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርኀን ወጣላቸው” (ኢሳ 9፡2) እያለ ይመሰክራል።

በዮርዳኖስ ባሕር የተፈጸመው የጌታ ጥምቀት ነገር መለኮታዊ አንድምታ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ሁሉ የሚጠቀልል ቁም ነገር ነው፤ ኢየሱስ ራቁቱን በወኃ መካከል መቆሙ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊል 2፡7) እያለ የተናገረውን ኢየሱስ ከኃጢአት በስተቀር በሁሉ ነገር እንደኛ ይሆን ዘንድ የታዘዘበትን ትሕትና ያሳየናል። በዚህም በእርሱ ራቁትነት አዳም ያጣውን የጸጋ ካባ ደግሞ ይለብስ ዘንድ መብት አለው፤ ይህ የጽድቅ ካባ ሌላ ነገር ሳይሆን እርሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ የሰውን ልጅ በመለኮታዊ ክብር አልብሶ ለተፈጠረበት መልክ በሚሆን ውበት አድሶታል፤ በመሆኑም ምድር እንደ ቀደመው ዘመን እሾህ እና አሜኬላ ሳይሆን፣ ይልቁንም ኢሳያስ አስቀድሞ እንደተነበየው “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል” (ኢሳ 35፡1)፤ በመሆኑም የዮርዳኖስ ብቻ ሳይሆን የምድር ውኆች ሁሉ የሕይወት ምንጭ ሆነዋል።

ዳዊት በመዝሙሩ ፍጥረት ኢየሱስን ያወቀበትን መረዳት ሲዘምር “አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ” (መዝ 77፡16) እያለ በፈጣሪነቱ ኃይል ይደነቃል። ዳዊት ዝማሬውን ቀጥሎ ፍጥረት የመለኮታዊ ክብሩን መገለጥ ሊቋቋመው እንደማይችል እየመሰከረ የዮርዳኖስን ባሕር ይጠይቃል “ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ... አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል? (መዝ 114፡ 3-5)። ኢየሱስ ወደ ውኃው በመግባቱ በውኃው ላይ የነበሩ አማልክት እና መናፍስት ሁሉ ኃይላቸውን ተነትቀው ፍትጥት ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ተቀድሷል። ዮርዳኖስ ይህንን መለኮታዊ እሳት መሸከም ስለማይችል ወደ ኋላው ያፈገፍጋል፤ ንጹሕ ነገር ለማጠብ ግብሩ አልነበረምና ፣ ኃጢአት ያልነካውን ከኃጢአት ለማንጻት የማይቻል ነውና ዮርዳኖስ ወደ ኋላው አፈግፍጓል (መዝ 114፡3)፤ ነገር ግን ኢየሱስ ወደ ውኃው ስለገባ፣ ውኃው በመንፈስ ቅዱስ ስለተነካ እና ስለተቀደሰ ከዚህ በኋላ የኃጢአትን እሾህ ሁሉ አቃጥሎ ያስወግድ ዘንድ እሳታዊ ኃይል ተሞልቷል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በበኩሉ የዮርዳኖስን ባሕር ሁኔታ ሲያብራራልን እንዲህ ይላል፡-

“ማዕበሉ ተቀልብሷልና ዮርዳኖስ በተለመደው ዑደት ይፈስ ዘንድ አልተቻለውም፤ ውኃው መለኮትን መሸከም አይቻለውምና፣ ዮርዳንስ ፈጣሪውን ሊያጥብ ግብሩ አይደለም፤ ውኃው አይነ ስውሩን እንጂ መለኮታዊውን ብርኀን ለመሸከም አቅም የለውም፤  እግዚአብሔር በእሳት እና በብርኀን ራሱን ገልጧልና መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዷል። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ውኃው በገባ ጊዜ ዮርዳኖስ የሚነድ ውኃ ሆናልና”[4]

ኢየሱስ የማይጠልቅ የጽድቅ ጸሐይ ነውና ራሱን በእሳት እና በብርኀን ይገልጣል፤ ዓለም ከዚህ ከማይጠፋው ብርኀን የተነሳ በብርኀን የተሞላች ትሆናለች። ጥንታውያኑ የጸሐይ እና የጨረቃ አማልክት “ሄሊዮስ” እና “ሴሌኔ” ተሽረዋል። ጸሐይ እና ጨረቃ ብርኀናቸውን ሳይቆጥቡ በኢየሱስ ክብር ተሞልተው ያበራሉ (የብርኀናቸው ኃይል ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ መጨለማቸውን ልብ በል።)፣ ከዋክብትም የእግዚአብሔርን ክብር እያንጸባረቁ ወደ ጽድቅ ጸሐይ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እስክንደርስ ድረስ ይመሩናል።

 የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የሚደመደመው ዮሐንስ ስለ እርሱ ማንነት በሚሰጠው ምሥክርነት ነው። ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየጠቆመ “የዓለም ኃጢአት የሚያጠፋ የእግዚአብሔር በግ እነሆ!” (ዮሐ 1፡29፣36) ይለዋል። በዚህ የዮሐንስ ምሥክርነት ውስጥ እንደምንመለከተው የጥምቀት በዓል በተመሳሳይ ጊዜ ወደ መስቀል የሚጠቁም የጌታ መሥዋዕት የሚታይበት መገለጥ ነው። በጥምቀት አማካይነት በዚህ ምሥጢር ውስጥ ስለተካፈልን የጥምቀት በዓል እያንዳንዳችን የጥምቀት ቃልኪዳኖቻችንን የምናድስበት፣ እንዲሁም ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለንና” (2ኛ ቆሮ 4፡10)። ጥምቀት ለእግዚአብሔር ክብር ከክርስቶስ ጋር የተሰወረውን መንፈሳዊ ሕይወታችንን መልሰን ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት በዓል ነው። የቀደመው አዳም በኤደን መካከል ዕርቃኑን እንደነበረ እንዲሁ አዲሱ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ በዮርዳኖስ፣ በኋላም በቀራኒዮ መስቀል ላይ ዕርቃኑን መታየቱ አዳምን በሁለንተናው መቀቡሉን እና አዳምም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አዲሱን ማንነቱን መላበሱን ለመመልከት ያስችለናል።

አማኝ ይህንን ምሥጢር ተቀብሎ በንቃት ሊጠብቀው ይገባል፤ የመኃልየ መኃልዬ ሙሽራ ይህንን ንቃት ስታስተምረን “እኔ ተኝቻለሁ ልቤ ግን ነቅቷል” (መኃ 5፡2) ትላለች። ማመናችን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በንቁ ልብ በሚመላለስ ሕይወት ሊገለጥ ይገባዋል። በፍቅር ንቁ ሆነን እንድንጠብቅ አምስቱ ብልህ ልጃገረዶች በቂ ዘይት እንድንይዝ ይመክሩናል። የጌታ መምጣት በድንገት የሚሆን የመለኮት መገለጥ በመሆኑ አማኝ ዘወትር ተዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት በመጠባበቅ በንቁ ልብ በዚህ ዓለም መመላለስ ይኖርበታል። ኢሳያስ የመሲሁን መምጣት ሲናገር “አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፤ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም” (ኢሳ 42፡2) እያለ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚገለጥ ምልክት ይሰጠናል። በመሆኑም “በንቃት መጠበቅ” የአማኝ ሕይወት መሰረታዊ ቁም ነገር ነው።

“ቃል ሥጋ ሆነ” የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ምሥክርነት የብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የፍጥረት ሁሉ ምልዓት እና የተስፋ ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ከአብርሐም ጋር የገባው ቃልኪዳን ፍጻሜውን የሚያገኘው ኢየሱስ “ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ 14፡3) በማለት  ለሐዋርያቱ  የገባላቸው ቃል ሲፈጸም ነው።

የአሌክሳደርያው ቅዱስ ቀለሜንጦስ ስለዚህ ክርስትያናዊ ተስፋ ሲናገር “ክርስትያን አሁን በሆነው መልካም ነገር ይደሰታል፤ ነገር ግን ከዚህኛው ባሻገር በተፈጸመ ተስፋ፣ እንደሚገለጥ እርግጠኛ በሆነበት የወደፊቱ ክብር የበለጠ ሐሴት ያደርጋል። ይህ ተስፋ የሌለ እስኪመስል ድረስ ከአማኙ የተሰወረ ምሥጢር አይደለም፤ ይልቁንም አማኝ በልቦናው እነዚህ ነገሮች መኖራቸውን አውቆ በተፋ እየተመለከተ ይጠባበቃቸዋል”[5]። በምሥጢራት በኩል በሚገኘው ጸጋ የአማኝ ሕይወት ዕለት በዕለት እያደገ በተመሳሳይ እነዚህ ምሥጢራት የያዙትን የተስፋ ፍጻሜ ወደፊት ይመለከታል።

እነዚህ ምሥጢራት የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ሰርክ ተግባራዊ ስለሚያደርጉ በተመሳሳይ ጊዜ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የሚጠቀልለውን ቁም ነገር ሁሉ በተስፋ ይዘዋል። በመሆኑም በመሥዋዕተ ቅዳሴ ቅዱስ ቊርባን ሲፈተት ሥጋ የለበሰው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት በመካከላችን “ትናንትናም ዛሬም ለዘላለምም ያው ሆኖ” ይገለጣል። በዚህም እያንዳንዱ አማኝ በዚህ የቊርባን መሥዋዕት በኩል ሕይወቱን ወደ ጌታ መምጣት አቅጣጫ እንዲያሲዝ ጥሪ ቀርቦለታል።

መልካም በዓለ ጥምቀት!

ሴሞ

[1] Stromateis 1,21 (PG 8, 888) ይህንን ማስፈንጠርያ በመጠቀም የአሌክሳንደርያው ቅዱስ ቀለሜንጦስን ጽሑፎች ማንበብ ይቻላል፡- Clement of Alexandria: Stromata, Book 1 (earlychristianwritings.com)

[2] Augustinus, Ench. N. 14 c. 53 (PL 40, 257 ጀምሮ)

[3] የአንጾኪያው ቅዱስ ኢግናጢዮስ ስብከቶች (PG 5, 660)

[4] የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጽሑፎች (PG 6, 685)

[5] ቅዱስ ቀለሜንጦስ Stromateis VII 47, 4 Clement of Alexandria: Stromata, Book 7 (earlychristianwritings.com)

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት