እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

መስቀል፡- ዓለም የማይገባው ቋንቋ!

Mekel Demeraእግዚአብሔር በየዓመቱ ልዩ የሆነ ፍቅሩ የተገለጸበትን ቅዱስ መስቀል እንድናከብር ስለፈቀደ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡  ማክበር በክርስቲያኖች ዘንድ በዓል ወይም ደግሞ ዝም ብሎ ደስታ ብቻ አይደለም፣ ይልቁንም የክርስቶስ የመሆናችንን ኀላፊነት የምናድስበት እዳ ነው። በተለይም ቅዱስ መስቀልን ማክበር፣ ሰው የተገደለበትን፣ በማይገባ ጭካኔ የሞተበትን መስቀል ማክበር ደስታ ብቻ ሆኖ መቅረቱ ለአእምሮአችንም አያስኬድም። መስቀልን ማክበር እዳ ነው ያልንበትን ምክንያት ይበልጥ ይረዳን ዘንድ እንዲህ እናስብ፡- እስቲ አንድ የምንወደው ሰው የተሰቃየበትን ብሎም የተገደለበትን መሣሪያ ቤታችን ግድግዳ ላይ ወይም አንገታችን ላይ ማንጠልጠል ልማዳችን ቢሆን ምን ዓይነት ጭካኔ ሆኖ ይሰማን ይሆን! ስለዚህ መስቀልን ማክበር ማለት ከእንደዚህ ዓይነት የጭካኔ ስሜት እንዲያወጣን ተቃራኒ የሆነው የፍቅርና የምሕረት ትርጉምን መረዳት አለብን። 

መስቀልን ማክበር ምን ማለት ነው? እንደሚባለው ጠቢብ ሰው ጨረቃን ሲያሳይ ሞኙ ተመልካች የጠቢቡን እጅ በማየት ውቢቷን ጨረቃ ማየት ተስኖት በእጆቹ ተገድቦ ይቀራል፤ እናም ክቡር መስቀልን ስናከብር ከመነቫው ግልፅ ሊሆን የሚገባው ነገር በዚያ ላይ ዋጋ የከፈለልንን ክርስቶስን እና ምልክትነቱን ነው እንጂ አንዳንዶቹ ለእኛ ሊተረጉሙሉን እንደሚሞክሩት ከሚታዩት እንጨትና ብረት ባቫገር መሄድ አቅቆን በዚያው እንቆማለን ብለን አንሰጋም፤ መስቀል ስንል በቀጥታ ከክርስቶስ የሆነውን የክርስቲያንነታችንን ዋጋ ክቡርነትና ፍቅር እናከብራለን።

መስቀል ታሪክ ለዋጭ ነው፤ በብሉይ ኪዳን የሚታወቀው አዛዥ፣ መሪ፣ መዋጋት የሚያውቅ፣ ብዙዎችን የሚመራ የሆነ ዓይነት የእግዚአብሔርን ገጽታ በልዩ የፍቅር ገጽታ እንዲገለጽ ያደረገ ቅዱስ  መስቀል የእግዚአብሔር አፍቃሪ ባሕሪይ ክበረ በዓል ነው፡፡ ዛሬም ላይ የመስቀል ውጫዊው ሳይሆን ውስጣዊው ትርጉም ላይ ከገባን ታሪካችን ይለወጣል። ይህንን በዓል በደንብ ውስጣችን እንዲገባ በተለየ መልኩ የቅዱስ መስቀልን በኢየሩሳሌም የመገኘት ታሪክ  ከዚያም የዚህኑ ታሪክ ሁለተኛ ክፍል ሕይወታዊ ትርጉሙ እንደሚከተለው እናስተውል።

ታሪካዊ ትርጉሙ ብዙ ጊዜ እንደምናውቀውና እንደምንሰማው ከደመራ ክብረ በዓል ጋር የተያያዘ የመስቀል መገኘት ሲሆን ይህም  ንግሥት እሌኒ በ327 ዓ.ም የታላቁ ንጉሥ፣ የደጉ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒን አስነሣ፡፡ እርሷም አስቀድማ ከአረማዊው ንጉሥ ቁንስጣ የወለደችው ልጅዋ ክርስቲያን ከሆነላት ከቁስጥንጥንያ ወደ ኢየሩሳሌም ተሻግራ የጌታችንን ዕፀ መስቀል ልታወጣ ብፅአት ገብታ ነበር፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ሆነላት፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ቅድስቲቷ ሀገር ጉዞ አደረገች፡፡ በዚያም ይሁዳ የተባለ ሽማግሌ መምህር አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ አመለከታት፡፡ ይህ ሰው በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፡፡ ስሙም ኪራኮስ ተብሏል፡፡ ኪራኮስ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን እንደቀበሩትና ቆሻሻ መጣያ እንዳደረጉት ለእሌኒ ነገራት፡፡ እርስዋም በመጀመሪያ ዕንጨት ደምራ በዚያ ላይ ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ተመልሶ ዐረፈ፤ ጢሱ ያረፈበት ቦታም ቅዱስ መስቀሉ ነበር፡፡ ዛሬ በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንኑ ለማስታወስ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሠራዊትም ሌሊትና ቀን የጉዱፉን ኮረብታ ቆፈሩ፡፡ የቆሻሻውን ክምር ካስወገዱ በኋላ 3 መስቀሎች ተገኙ፡፡”/ከhttp://bahiran.orgየተወሰደ/አሁን የመስቀሎቹ መገኘት ትልቅ ነገር ቢሆንም አንዱ የጌታችን ሲሆን ሁለቱ መስቀሎች በጌታችን ቀኝና ግራ የተሰቀሉት የሁለቱ ሽፍቶች ነበር፤ ስለዚህም ቀጣዩ ሥራ ደግሞ የትኛው የጌታችን እንደሆነ መለየቱ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን አንዲት በጠና የታመመችና በጣም በጠና የታመመች ሴት እና አንድ የሞተን ሰው አምጥተው እያንዳንዱን መስቀል እላያቸው ላይ መጫን ጀመሩ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ይተርክልናል የሁለቱ ወንበዴዎች መስቀል ምንም ለውጥ አላመጣም የክርስቶስ መስቀል ሲጫንባቸው ግን ሴትዮዋም ተፈወሰች ሞቶ የነበረውም ተነሣ ይለናል።

ይህ ታሪክ ለሕይወታችን ምን መልእክት አለው ብለን ካሰብን፣ ሕይወት መስቀል አላት፤ የተለያየ መስቀል እንዳለ እናውቃለን  መስቀል ሁሉ አንድ አይደለም ሀብታሙም ሆነ ደሃ፤ ክርስቲያኑም ሆነ አረመኔ ሰው ነውና ሸክም አለው። ይህንን ሸክም ግን ክርስቲያናዊ ስናደርገው ማለትም ክርስቶሳዊ ትርጉም ስንሰጠው ፈውስ ነው። ይህ ከክርስቶስ ጋር የምናስተሳስረውና ስለርሱ ብለን የምንሸከመው መስቀል በሕይወታችን ሲጫንብን ከባድ ቢሆንም ውጤቱ ፈውስ ነው።  ሌላኛው ደግሞ ሸክም የሚሆንብን ሁሌም ቢሆን በማጉረምረም የሚያስኖረን፤  የማይፈውሰን የሚጫነን መስቀል ይኖራል። የሁለቱ ወንበዴዎች መስቀል በሴትዮዋና በአስከሬኑ ላይ እንደነበረው መስቀላችን ትንሽ ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል ግን እንዴት ነው የተሸከምነው በምንስ መልኩ ነው የያዝነው ብለን እናስብ።

ክርስቶሳዊ መስቀል ሃይል አለው ክርስቲያናዊ መስቀል ሸክም አይደለም ሸክም ከሆነም ውጤቱ ኃይልና ፈውስ ነው፤ በሰዎቹ ላይ ተጭኖ ፈወሳቸው አስነሣቸው። ስለዚህ ይህ ታሪካዊ ትረካ በሕይወታችን ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ታሪክ ነው ስለዚህ መስቀላችንን እናስተውል የተሸከምንበትን ትርጉም እንይ መስቀል የለኝም የሚል ሰው ውሸታም ነው እድሜያችንን እንይ ከላይ እስከ ታች የሆነ ነገር አለን። ያ ነገር ክርስቲያናዊ ሲሆን ፈውስ ነው ፈውሱ የኔ ብቻ አይደለም ለሌሎችም ነው። ታሪኩ ሲቀጥል ምን ይላል መስቀሉን ያፈላለገችው ንግሥት እሌኒ መስቀሉ በተገኘ ጊዜ  ለአገሩ ሁሉ የክርስቶስ መስቀል ፈዋሹ ተገኝቷል ተብሎ ታወጀ ስለዚህ ሰው ፈውስ ያስፈልገዋልና ተሰበሰበ። በጊዜው የነበሩት ፖትሪያሪክ በኢየሩሳሌም በከፍታ ላይ ሆነው መስቀሉ ከፍ እንዲል አደረጉ መስቀሉ ከፍ ባለ ጊዜ ሰው ተንበርክኮ ጌታ ሆይ ማረን - ኪርያ ላይሶን -  ማለት ጀመሩ።

በመስቀሉ ሥር ሊኖር የሚችል ብቸኛ ጩኸት ብቸኛ ጥሪ ይህ ነበር - ጌታ ሆይ ማረን! - ፖትሪያሪኩ መስቀሉን ከፍ ሲያደርጉ የሕዝቡ ምላሽ ምን ነበር ተንበርክበው ሰግደው ጌታ ሆይ ማረን!  ዛሬ መስቀልን ስናከብር ሌላ ትርጉም የለውም መስቀል ከፍ ይላል አሁንም የክርስቶስ በዓል አይደለም የኔ እና የእናንተ በዓል ነው ምላሻችንን በዚህች ቅጽበበት እንስጥ።

 ቅዱስ አባታችን ቤኔዲክቶስ መስቀልን ሲገልጹት የሃይማኖታችን ጭማቂ እምነታችንን በሙሉ ጨምቆ የያዘ ምልክት ነው፤ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸበት ነው ስለዚህ ይህ ፍቅር  ከሞት በላይ ሞትን የሚሻገር ፍቅር ነውና ከኃጢያታችንና ከደካማነታችን በላይ የሚሄድ ፍቅር ነውና ተወዳዳሪ ሊኖረው አይችልም። በዘመናችን በተለይ ከሞት የበለጠ ፍቅር ከየት እናገኛለን? ከኃጢአት ከደካማነት የበለጠ ፍቅር ፊት እንገኛለን። ደካማነታችንን ኃጢአታችንን መዝነን መስቀልን የቀለለ ሚዛን መስጠት አንችልም። ቅዱስ አባታችን ከኃጢአትና ከደካማነታችን የበለጠ ፍቅር በክርስቶስ መስቀል አለ ይላሉ፤ ስለዚህ ትልቅ መጽናናት ነው በዚህ መልኩ ብቻ የመስቀል በዓል ለኛ ደስታ ሊሆንልን ይችላል።

በዓለ መስቀል የምግብ በዓል አይደለም በቱሪስት በዓል አይደለም ወዘተ የደስታ በዓል ሊሆን የሚችለው ከኔ ደካማነት ከኔ ኃጢአት በላይ የበረታ መስቀል ፊት ነኝ ማለት ስንችል ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሃሳብ ቅዱስ አጉስጢኖስ “ከኃጢአትህ ትድን ዘንድ የተሰቀለውን ክርስቶስ ተመልከት” ይለናል። መስቀለ ያ ነው! ባዶ መስቀልን እንኳ ስንመለከት እንጨት፣ ብረት ወይም ወርቅም አይደለም መስቀል ስንል አጭር ቃል ነው፡- የተሰቀለ ክርስቶስ! የተሰቀለውን ክርስቶስ ተመልከት ከዛም በኃጢአትህ ትነጻለህ።

መስቀል በኑሯችን አለ፤ ሥጋዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ አእምሯዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ… ወዘተ እያልን ማተት ይቻላል። የሆነ ሆኖ ግን በሕይወታችን ሸክም አለ፣ ሸክሙን ግን ወይ ትርጉም ያለው እናድርገው ወይም ደግሞ ምንም ውጤት የሌለው! በሕይወታችን ሁሉም በእጃችን ነው። በተለይም መስቀል ከትልቁ የዘመናችን በሽታ ከእኔነት በሽታ ሊፈውሰን ዝግጁ ነው። አንድ ሰው ለራሱ ከተስማማው ምን አገባኝ የሚል ዓይነት አባዜ የሥልጣኔ አንዱ ክፍል ሆኗል። “ይመችህ” “ይመችሽ” ሌላው ሁሉ የፈለገውን ይሁን! የሚል ነገር እየተለመደ ነው። ወንጌል ምን ይላል “ዓለምን ሁሉ ብታተርፍና ነፍስህን ግን ካላተረፍክ ምን ዋጋ አለው”! ሁሉ ቢሆንልህ ቢመችህ ምን ዋጋ አለው? ታዲያ ይመችህ በሚል ዙሪያ መስቀል ምን ትርጉም አለው፤ በዚህ መልኩ መስቀል ሞኝነት ነው ጳውሎስ መልእክቱ ላይ እንዳለው የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው ይላል።

አንዳንድ ሰለጠኑ በሚባሉ አገሮች ማለትም ለሕይወት ሳይሆን ለሞት ዋጋ በሰጡ ስልጣኔዎች ውስጥ የተጀመረ ነገር አለ፡- ራስህን ማጥፋት ከፈለክ እኛ ጋ አንተ አትድከም፤ አትንጠልጠል እኛ እናግዝሃለን - ለመግደል ማለት ነው። በቃ ተስፋ ከቆረጥክና መኖር ካንገፈገፈህ እኛ ጋ ና ይመችህ! በቀላሉ እንድትሞት እናፋጥንልሃለን። ስለዚህ መስቀል ፈውስ ነው ስንል ከእንደዚህ ዓይነት ትልቅም ሆነ እለታዊ ጥቃቅን ሥር ነቀል የግላዊነት ጥቅምና ርካታ ፍለጋ በሽታ የሚፈውስ ነው። ስለዚህ ነው መስቀልን አባታችን ቤኔዲክቶስ ዓለም የማይገባው ቋንቋ ነው የሚሉት። መስቀልን ስናከብር የፍቅርና የምሕረት መልእክቱን ለራሳችን ቀምሰን ለሌሎች በማሳለፍ እንኑረው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት