እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰንበት ዘዳግማይ ትንሣኤ

ሰንበት ዘዳግማይ ትንሣኤ

 532200posterl

መዝሙር፡-  ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሰይ ምድር

ንባባት፡- 1 ቆሮ 15፡ 1-19፣ 1ዮሐ 1፡1-10፣ ሐሥ 23፡1-9

ወንጌል፡- ዮሐ 20፡19-31

ስብከት፡- ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም ወከመ ኃያል ውኅዳገ ወይን፥ወቀተለ ጸሮ በድኅሬሁእግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ” (መዝ 7865-66)

ከትንሣኤ በኋላ ያለው የመጀመርያው እሑድ ዳግማይ ትንሣኤ እየተባለ ይጠራል፤ በላቲን ሥርዐተ አምልኮ ቀመር መሠረት ደግሞ ይህ ሰንበት የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት እየተባለም ይጠራል። ሁለቱም በዮሐንስ ወንጌል 20፡19-31 ባለው የጌታን ትንሣኤ እና ሐዋርያት የተቀበሉትን የዕርቅ ምሥጢር ተልዕኮ በሚተርከው ክፍል ውስጥ ተስማምተው ይታያሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በተዘጋ አዳራሽ በሐዋርያቱ መካከል ተገኝቶ ትንሳኤውን ሲገልጥላቸው እና ቁስሎቹን ሲያሳያቸው እንመለከታለን፤ እነዚህ የጌታ ቁስሎች የትንሣኤው ምልክት እንደሆኑ ሁሉ የመለኮታዊ ምሕረት ምሥክሮችም ናቸው። በጌታ ቁስሎች የተነሳ ተፈውሰናልና ፈውስ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ በመለኮታዊ ምሕረት የሚከናወን ዳግማይ ትንሳኤ ነው። መለኮታዊ ምሕረት ኃጢአተኛውን የሚያጸድቅ፣ ዘማዊውን ድንግል የሚያደርግ የጸጋ አክሊል ነው፤ ይህ የጸጋ አክሊል ትንሣኤያችን ባጌጠበት የእሾህ አክሊል የተገኘ በመሆኑ የትንሣኤ ፍሬ መለኮታዊ ምሕረት ነው። በመሆኑም ጌታ ትንሣኤውን ከገለጠ በኋላ ለሐዋርያቱ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” (ዮሐ 20፡22-23) እያለ የዕርቅ ምሥጢር እና የመለኮታዊ ምሕረት አገልጋዮች አድርጎ ሐዋርያቱን ሲልካቸው እንመለከታለን።

የዳግማይ ትንሣኤ ሰንበት የእግዚአብሔርን የምሕረት ፊት የተመለከትንበት ሰንበት ነው፤ በዚህ ሰንበት ከአይሁድ ቤተ መቅደስ መጋረጃው ጀርባ ምን እንዳለ በመደነቅ ሳይሆን በጦር ተወግቶ በተከፈተው የጌታ ልብ በኩል የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ምሕረት የምናሰላስልበት እና “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም” (መዝ 34፡8) ለሚለው የመዝመረኛው ዳዊት ግብዣ ተግባራዊ ምላሽ የምንሰጥበት ሰንበት ነው። የጌታን ቸርነት ለመቅመስ ራስን ወደ ጌታ ልብ ማስጠጋት እና በደረቱ ላይ ተደግፎ የልቡን ምሥጢር ማድመጥ ይጠይቃል (ዮሐ 21፡20)። በጌታ ልብ ላይ ተደግፎ የእርሱን ምሥጢር ማድመጥ የሕይወት ራዕይ ይሰጣል፤ ራዕይ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚገራን መለኮታዊ ግብረገብ ነው። የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ “ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው” (ምሳ 29፡18) እያለ ራዕይ የሕይወትን ፈልግ የሚያሰምር መለኮታዊ ጥበብ መሆኑን ያስረዳል። መለኮታዊ ምሕረት ያጣነውን ራዕይ የሚመልስልን ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ በድንግዝግዝ ከመራመድ እና ከደቦ ማንነት ነጻ አውጥቶ በተስተካከለ መንገድ ላይ የሕይወትን መስመር እንደ አዲስ እንድናሰምር የሚያስችለን የትንሳኤ ቁርጠኝነት ነው።

ይህ ሰንበት መለኮታዊ ምሕረት ለእያንዳንዳችን የተከፈተ የጸጋ ምንጭ መሆኑን የምናስብበት እና ምሕረትን ለመቀበል ልባችንን ክፍት የምናደርግበት ሰንበት ነው። ነገር ግን መለኮታዊ ምሕረት የተቀበለ ሰው እንደ ቶማስ አይነት መንታ ማንነት ሊኖረው እንዴት ይቻላል? ነቢዩ ኤልያስ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ” (1ነገ 18፡21) ሲል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የምናመልከውን እንድንመርጥ ያቀረበው ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተገቢ ጥያቄ ነው!  

ይህ አንካሳ ማንነት በትንሣኤ ብርኀን እንዲረታ ጌታ እጆቼን እና እግሮቼን ተመልከቱ እያለ ወደ መዳናችን ምሥጢር ይጠቁመናል። ዳግማይ ትንሣኤ የጌታን ቁስሎች እንደ አዲስ የምንመለከትበት የጸጋ ብርኀን ነው! በዚህ የጸጋ ብርኀን መመልከት “እኛ እና እነሱ” ከሚል የተንሸዋረረ ዕይታ ነጻ የሚያወጣ የመንፈስ ቅዱስ መነጽር ነው። በዚህ የመንፈስ ቅዱስ ኩል ካልተኳልን አጥርተን መመልከት አንችልም። አጥርተን መመልከት የማንችልበት የተንሸዋረረ ዕይታ የተዛባ የፍርድ ሚዛን፣ ፍትሐዊነት የጎደለው የዕዳ መዝገብ እና በሰው ቁስል እንጨት የሚሰድ ፍርድ የሞላበት ጥራዝ ነጠቅ አማኝነት የሚጋብዝ የፍርሃት ዋሻ እስር ቤት ነው።

ዳግማይ ትንሣኤ ከከንቱ ፍርሃት ነጻ ወጥተን በራሳችን ዕይታ ሳይሆን በክርስቶስ ቁስል በተፈወሰ ዕይታ የምንመላለስበት የአዲስ ኪዳን ማንነት ነው። ጌታ በሐዋርያቱ መካከል ተገኝቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” ሲላቸው በልባቸው የሞላውን ፍርሃት አውጥቶ የእርሱ በሆነ ነጻነት እንዲነጋገሩ አዲስ ዐውድ ሰጥቷቸዋል። ይህ የጌታ ዐውድ ከምንም ነገር በፊት በ “ሰላም”ታ የሚጀምር የጋራ ጉዞ ነው። የጌታን ቁስሎች ለማየት እና በእነርሱ ለመማረክ የመጀመርያው ቁም ነገር በሚፈርድ ዕይታ ሳይሆን “በሚያስተውል የልብ ሰላም” መሞላት ነው። ስለዚህ ጌታ ወደ ቁስሉ እንዲመለከቱ እና በተደረገላቸው ምሕረት እርስ በእርስ በአዲስ ዐውድ እንዲተያዩ ከመጋበዙ በፊት “ሰላም”ታ ያቀርባል። ሰላምታ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ልብን መክፈት፣ እንደገና ማመን እና ኃላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። ቅድስት እማሆይ ትሬዛ ማንኛውም የሰላም ሥራ ከፈገግታ ይጀምራል ማለታቸው ይህንን የጌታን የትንሣኤ “ሰላም”ታ ከመረዳት የሚመነጭ ቁም ነገር ነው።

ጌታ ይህንን ሰላም መቀበል እና በዚህ ሰላም መሞላት እንድንችል ብሎም ይህንን ሰላም ማስተጋባት እንድንችል የሚያበረታንን መለኮታዊ ጉልበት በእያንዳንዳችን ላይ እየተነፈሰ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” (ዮሐ 20፡22) ይላል። ዘላቂ ሰላም በጠረጴዛ ዙርያ በፖለቲካ ድርድር የሚገኝ የሰው ልጆች የጋራ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው። ሰላም በክርስቶስ የታረቀ አማኝ የአዲስ ኪዳን ማንነት ነው። ሰላም አዲስ ኪዳናዊ ማንነት ነው እንጂ እንደ አዲስ የምንደርስበት የጋራ ስምምነት አይደለም። ስለዚህ ይህንን ማንነት እንላበስ ዘንድ ዛሬም ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ራሳችንን ክፍት እንድናደርግ እንጋበዛለን።

ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” (1ዮሐ 1፡5) እያለ የትንሣኤው ብርኀን በመካከላችን መገለጡን ይናገራል። እግዚአብሔር ብርኀን ከሆነ በእግዚአብሔር የሚያምን በብርኀን ይመላለሳል፤ በብርኀን የሚመላለስ ከእውነት ጋር እንጂ ከአመጻ ጋር ኅብረት የለውም። በእግዚአብሔር አምናለሁ የሚል አመጻን ግን በልቡ የሸሸገ ሰው “በኖራ የተለሰነ ግድግዳ” (ሐሥ 23፡5) ሆኖ ይታያል። ነገር ግን ልብን እና ኩላሊትን በሚመረምር አምላክ ላይ መዘባበት አይቻልምና በእርሱ ዘንድ የተሰወረ የማይገለጥ፤ የተሸሸገ የማይታወቅ አንዳችም ነገር የለም (ማቴ 10፡26)። ስለዚህ አማኝ እንደ ቶማስ በሁለት ሐሳብ ከማነከስ ሕይወት በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን የሚያርፍ፤ በእምነት እንጂ በማየት የማይመላለስ አዲስ የትንሣኤ ፍጥረት ነው፤ መንፈስ ቅዱስን የሚቀበል እና ለመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ በእምነት የሚታዘዝ አማኝ ሁሉ ዳግማይ ትንሣኤን የሚያከብር ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ በክርስቶስ የሆነ አዲስ ፍጥረት እና ሰርክ ዳግማይ ትንሣኤ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ” (1ቆሮ 15፡1) እያለ ትኩረታችንን ወደ ወንጌል አስኳል እንድንመልስ ዐደራ ይለናል። ወንጌል እስከ ዓለም ዳርቻ ይሰበክ ዘንድ የተሰጠን ተልዕኮ ከጌታ በሐዋርያት ትምህርት፣ በቤተ ክርስትያን በኩል  የተቀበልነው፣ ኲሏዊ ተልዕኮ ያለው፣ ወደ መዳን የሚያደርስ፣ ወደ እውነት እና ወደ ጽድቅ የሚመራ የምሥራች ነው። ይህ የምሥራች ከሌላ ነገር ጋር እንዳይቀየጥ “መንፈስን ሁሉ መርምሩ” (1ዮሐ 4፡1) የሚለውን የሐዋርያውን ማሳሰቢያ የቅኝታችን ሁሉ መስፈርት በማድረግ ዛሬም በትንሣኤ የሰላም መልእክት የምናምን፣ የትንሣኤውን “ሰላም”ታ ለፍጥረት ሁሉ የምናደርስ የአዲስ ኪዳን አምባሳደሮች መሆናችንን አጥብቀን እንድንይዝ ጌታ ይጋብዘናል። ኢየሱስ በመስቀሉ “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” (ዘፍ 4፡9) የሚለውን የቃኤልን ምላሽ እኔ ለወንድሜ ራሴን አሳልፌ እሰጣለሁ (ዮሐ 15፡13) በሚል አዲስ ኪዳናዊ መልስ ሽሮታልና አዎ! እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ! ዳግማይ ትንሳኤ ስለ ጌታ ሕማም፣ ሞት እና ትንሣኤ በፍቅር እየመሰከርኩ በጌታ “ሰላም”ታ የምመላለስበት አዲስ ማንነት ነው። ዛሬም በዚህ ማንነት በቀልን ሁሉ አሸንፈን በጌታ “ሰላም”ታ የሕይወትን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እናደርስ ዘንድ የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤውን ጸጋ ይስጠን!

መልካም የዳግማይ ትንሣኤ እና የመለኮታዊ ምሕረት በዓል!

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት