ሰንበት ዘገብር ኄር
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Sunday, 03 April 2022 10:40
- Written by Super User
- Hits: 967
- 03 Apr
ሰንበት ዘገብር ኄር
ንባባት፡- 2ጢሞ 2፡ 1-15፣ 1ጴጥ 5፡ 1-11፣ ሐዋ 1፡6-8
መዝሙር፡- መኑ ውእቱ ገብር ኄር
ስብከት፡- “ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፥ ወሕግከኒ በማከለ ከርስየ ዜኖኩ ጽድቀከ በማሕበር ዐቢይ። አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ።”
ወንጌል፡- ማቴ 25፡14-31
እግዚአብሔር አምላክ ከዘላለም ጀምሮ ለፍጥረቱ ሁሉ ካለው በጎ ዓላማ የተነሳ ፍጥረትን መሸለም፣ ፍጥረትን ማክበር እና ፍጥረትን ሁሉ በሥጦታዎቹ ማበልጸግ ያውቅበታል። ዳዊት በመዝሙሩ ይህንን አምላክ ፍጥረቱን የኳለበትን ውበት እያወደሰ “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ” (መዝ 65፡9) በሚል መዝሙር ያመሰግናል። ትልቅ መከራ የደረሰበት እና መከራውን ሁሉ እንደ ምሥጋና ምክንያት የታገሰው ጻዲቁ ኢዮብ በበኩሉ “ አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል፤ ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?” (ኢዮ 12፡7-10) እያለ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥጦታ እና ቸርነቱን እንደሚያውቅ ይመሰክራል። እግዚአብሔር ፍጥረትን በጸጋ ሲሸፍን ፍጥረት የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ግርማ እና ባለጠግነት ከማንጸባረቅ ባለፈ ይልቁንም የተፈጠረበትን ውበት እየመሰለ ያድጋል። ስለዚህ የእግዚአብሔር የጸጋ ሥጦታ ለግለሰባዊ ልዕልና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የሚቸር በረከት ነው። የሰው ልጅ መሰረታዊ ማንነት እና ጥሪ ሌላ ነገር ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ “በረከት” መሆን ነውና እግዚአብሔር ሥጦታውን ሲሰጥ “ለበረከት ሁን!” እያለ ይባርካል (ዘፍ 12፡2)።
በዛሬው ወንጌል ጌታ ስለተሰጠን መክሊት፣ ጸጋ ወይም በረከት ሲያስተምር አንድ ወደ ሩቅ ሀገር የሚሄድ ሰው ለአገልጋዮቹ እንደ በጎ ፈቃዱ ልዩ ልዩ መጠን ያለውን ሥጦታ እንደሰጣቸው ይናገራል። ይህ “ወደ ሩቅ ሀገር የሚሄድ ሰው” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው፤ እርሱ ለሁላችን ቃል በገባው መሰረት ሥፍራ ሊያዘጋጅልን (ዮሐ 14፡1-3) ወደ አባቱ ቀኝ ይወጣልና “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ” (ኤፌ 4፡8) ተብሎ እንደተጻፈው ስለራሱ በምሳሌ ይናገራል። እርሱ በአባቱ ቀኝ ስለሆነ በዚያ እኛ ሁላችን ደግሞ መጻተኞች ሳይሆን ይልቁንም ከቅዱሳን ጋር ባለአገሮች (ኤፌ 2፡19) ሆነን እንድንገለጥ አስቀድሞ በምድር ለሰማያዊ ሕይወት የሚያዘጋጁን የጸጋ ሥጦታዎች ሰጥቶናል። የዛሬው ሰንበት ከዚህ በመነሳት “ዘገብር ኄር” ወይም የመልካም አገልጋይ ሰንበት እየተባለ ይጠራል።
መልካም አገልጋይ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ የዚህ ሰንበት አንኳር ነጥብ ነው። ስለ መልካም አገልጋይ ስናስብ ወደ አእምሮአችን የሚመጡት ነገሮች፣ አጋጣሚዎች እና ሰዎች እነማን ናቸው? መልካም አገልጋይነት የእያንዳንዱ ግለሰብ የአፈጻጸም ውጤታማነት የሚመስልባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፤ ምናልባት በመንግሥት እና በዜጎች፣ በጳጳሳት እና በካህናቶቻቸው፣ በካህናት እና በምዕመናን፣ በወጣቶች እና በቆሞሳት ወይም ደግሞ በመንፈሳዊ ማሕበራት እና ከእነርሱ ጋር አብረው በሚሰሩ አገልጋዮች ወ.ዘ.ተ. መካከል የሚስተዋሉ አለመግባባቶች ሁሉ ምንጭ የመልካም አገልጋይ ትርጓሜ መዛባት ወይም የመልካም አገልጋይነት መልክ መጠውለግ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ሐቅ ነው። ዛሬ ስለ መልካም አገልጋይነት የማንሰማበት ወይም መልካም አገልጋዮች እንድንሆን የማንጋበዝበት የሕይወት ክፍል የለም። ከመንግሥት ሥልጠናዎች እስከ ጾም ጸሎት የሚያዝባቸው ሱባዔዎች ድረስ ዋነኛው አጀንዳ “መልካም አገልጋይነት” ነው። የመንግስት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች ሁሉ የጋራ ችግር ተደርጎ የሚቀርበውም ይህ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ታዲያ ይህ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስትያን ፈተና የሆነባት ጥያቄ እንዴት በአግባቡ ሊመለስ ይችላል? አንድን አገልጋይ መልካም አገልጋይ የሚያደርጉት ቁምነገሮች የትኞቹ ናቸው?
ጌታ በዛሬው ወንጌል ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ሊሆን የሚችል የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል። የጌታን ምክር ተከትለን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አስቀድመን አንዳንድ ቁምነገሮችን ማስተዋል ይገባናል። በመጀመርያ የሰጪውን ልግሥና መመልከት ያስፈልጋል። ጌታ በዛሬው ወንጌል ስለ መልካም አገልጋይ ሲናገር አስቀድሞ ስለሰጪው ይናገራል፤ ይህም የመልካም አገልጋይነት የመጀመርያው ቁልፍ ነው። መልካም አገልጋይ ለሰጪው ሥጦታ የሚታመን ነው፤ ስለዚህ መልካም አገልጋይ የሚያገለግልበት ጸጋ በታማኝነት የተሰጠው፣ የታመነበት ሥጦታ መሆኑን ይገነዘባል። ይህ ግንዛቤ ለእግዚአብሔር ሥፍራ የሚሰጥ፣ የሥጦታው ምንጭ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን የሚታመን በመሆኑ በልብ ትህትና የታጀበ አገልግሎት ነው። በመሆኑም ለእግዚአብሔር በሚሆን ሥፍራ ሰው ቆሞ እንዳይገኝ እና የአምላክን ክብር በሚመኝ ግለኝነት እንዳንጠመድ ጌታ አስቀድሞ ስለ ሥጦታው ባለቤት ይናገራል። እግዚአብሔር የነገር ሁሉ ባለቤት በሆነባት ነፍስ የፍጥረት ተዋረድ መዛነፍ የለም፣ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ቀዳሚ በሆነበት ሕይወት የሰው ልጅ ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር በአንድ ድምጽ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” (ዮሐ 3፡30) በሚል የሕይወት መርህ ይገለጣል።
ስለ አገልግሎት ስናስብ መርሳት የሌለብን ዋነኛው ቁም ነገር የመጀመርያው እና የመጨረሻው አገልጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ነው። ይህንን የሚታመን አገልግሎት፣ የአገልግሎቱ አቅጣጫ፣ ሚዛን እና ወኃ ልክ አገልጋዩ በዘርፉ ያለው ዕውቀት እና ልምድ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ያገለገለበት ግብረግብ የመልካም አገልጋይነት መምርያ እና መለኪያ መስፈርታችን ነው። እርሱ ስለ አገልግሎቱ ሲናገር “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማቴ 20፡28) በማለት አገልግሎት በነፍስ ዋጋ ልክ መታመንን የሚጠይቅ መሥዋዕትነት ያለበት መሆኑን በግልጽ ያስረዳል። በመሆኑም መልካም አገልጋይ ለተጠራበት የሕይወት ዘርፍ እና አገልግሎት የሚያበረክተው ነገር ጊዜውን፣ ጉልበቱ፣ ዕውቀቱንና ችሎታዎቹን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ሁሉን አንድ አድርጎ የያዘውን ነፍሱን ጭምር ነው።
መልካም አገልጋይነት ከዘላለም ሕይወት ጥያቄ ጋር የተቆራኘ ተልዕኮ ነው። የመልካም አገልጋይነት የምሥክር ወረቀት እና የክብር ሽልማት በመስቀል ላይ በነፍሱ እስኪታመን ድረስ ባገለገልን በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነው። ስለዚህ መልካም አገልጋይ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምክር ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደሚቀርብ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮ 10፡31)። በመሆኑም የመልካም አገልጋይ የመጀመርያው መስፈርት የሥጦታውን ባለቤት መታመን እና ሥጦታው ከእኔ ግለሰባዊ በጎነት እና ቅድስና የተገኘ የምሥክር ወረቀት ወይም የዕውቅና ሽልማት ሳይሆን፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር አባታዊ ልብ የፈለቀ እና ከበጎ ፈቃዱ የተነሳ በጸጋ የሆነልኝ በረከት መሆኑን በተግባር አምኖ መቀበል ነው። በዚህም የአገልግሎቱ መስፈርት የእኔ ግለሰባዊ ግንዛቤ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን እስከ መስጠት በመስቀሉ ላይ የከፈለው ዋጋ ነው፤ ከዚህ ዋጋ በላይ ልመካበት የምችልበት ሌላ ዋጋ፣ ከዚህ አገልግሎት በላይ የሆነ ሌላ መሰረታዊ አገልግሎት በሰማይም በምድርም የለም።
ጌታ በመቀጠል “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠ” (ማቴ 25፡15) እያለ ስጦታዎቹ በተለያየ መጠን እንደተሰጡ ይናገራል። እነዚህ ሥጦታዎች እንደ በጎ ፈቃዱ አሳብ እንገለጥባቸው ዘንድ የተሰጡን የእግዚአብሔር ጸጋ መልኮች ናቸው። እንግዲህ እነዚህ የጸጋ መልኮች ሥጦታዎች ናቸው እንጂ የወዛችን ፍሬ ወይንም የጽድቃችን ደመወዝ አይደሉም። በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህ ነጥብ በሚገባ እንዲገባን “አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?” (1ቆሮ 4፡7) እያለ ለእያንዳንዳችን መሰረታዊ ጥያቄውን ያቀርባል። ይህ የጸጋ ሥጦታ ለእያንዳንዳችን የተሰጠበት መስፈርት ምን እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስትያኖች ሲናገር ጸጋ እንደ ክርስቶስ ሥጦታ መጠን እንደተሰጠ ያስተምራል (ኤፌ 4፡7)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ እንደወደደ የጸጋ ሥጦታዎቹን ሰጥቷል ስንል የእያንዳንዳችንን አቅም፣ ዝንባሌ እና ችሎታ በሚያከብር የአባት መጋቢነት እንደየመጠናችን አስተናግዶናል ማለታችን ነው። ጌታ በጥሪው እና በስጦታው ፍትሐዊ ነው!
በዛሬው ወንጌል ጌታ “ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ” እንደተሰጠው ይናገራል፤ እነዚህ መክሊቶች በተለያየ መጠን መሰጠታቸው እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለውን የተለያየ የሕይወት ጥሪ የሚያመላክት ነው። ጌታ እነዚህን መክሊቶች እና እያንዳንዳቸው ያስገኙትን ትርፍ አመስግኖ ሲቀበል እንመለከታለን፤ ይህም በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች እና በጥሪዎቻችን ፍሬ ባፈራንበት ሥፍራ ሁሉ የጌታ ምሥጋና እና ዘላለማዊ ሹመት ከእኛ ጋር መሆኑን ያመለክታል። አምስት የተሰጠው እና አንድ የተሰጠው በተሰጣቸው ነገር ጌታን ታምነው መረባቸውን እንዲጥሉ እንጂ በግለሰባዊ ችሎታዎቻቸው ብቻ እንዲንቀሳቀሱ አልተጠየቁም፤ ጌታ ጥሪውን ሲያቀርብ ውሱንነታችንን፣ የእምነታችንን ትንሽነት እና ሰብዓዊ ማንነታችንን ሁሉ ባገናዘበ መልኩ ሊቀርበን እና ሊያነጋግረን ይወዳል። ይህም በተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ እና የሕይወት ጥሪ ያልሆንነውን ነገር ሆነን እንድንገኝ ወይም በየቀኑ የበለጠ የሥራ መሳርያ እና ያነሰ “ሰው”ነት እየሆንን እንድንሄድ የሚያስገድደን ሳይሆን ይልቁንም በተቀበልነው ነገር ፍሬ ለማፍራት ታማኞች እንድንሆን የሚጠይቅ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤” (2ቆሮ 3፡5) እያለ በእኛ በኩል እልፎ የሚሰራውን የጌታን ጸጋ እንድንታመን ያሳስበናል። ጌታ በዚህ በእኛ ትንሽ እምነት ውስጥ አልፎ ዛሬም የሚያነጋግራት ፣ የሚፈውሳት፣ ከታሰረችበት ሰንሰለት የሚፈታት እና ከተጠመደችበት ቀንበር ሰብሮ በአምላክ ልጆች አርነት የሚያወጣት ነፍስ አለች። የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ስለ እኔ ግለሰባዊ እና መንፈሳዊ ብልጽግና የሚሰጡ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ተቀዳሚ ዓላማ ለቤተ ክርስትያን ሕንጸት ነው። የጸጋ ሥጦታዎቻችን ለቤተ ክርስትያን ሕንጸት የተሰጡን እንደሆነ ቤተ ክርስትያን በሁሉ ነገር ለትታነጽ ይገባታልና የእያንዳንዳችን መክሊት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። እንደ አለመታደ ሆኖ ስለ አገልግሎት ወይም ስለ መልካም አገልጋይነት ስናስብ ወደ አእምሮአችን የሚመጡት የአገልግሎት ዘርፎች እና ግለሰቦች ብዙውን ጊዜ ጥቂቶች እና ተመሳሳይ ናቸው። ይህም በቤተ ክርስትያን እና በግል ሕይወታችን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን ልምምድ የሳሳ እንደሆነ የሚያመላክት ቁም ነገር ነው።
የዝማሬ አገልግሎታችን፣ የእግዚአብሔር ቃል የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችን ፣ የፍቅር ሥራዎች፣ ሥርዐተ አምልኳዊ ማንነቶች፣ የጥሪ ቅስቀሳዎች እናክብካቤ፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት ዕድገት ወዘተ የማይስተዋልባት ቤተ ክርስትያን የሆንነው ለምንድነው? እግዚአብሔር ዛሬ ሰዎችን በስጦታዎች እና በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መባረክ አቁሟልን? ወይስ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ መተንፈሱን ትቷልን? በየቁምስናችን ስለ አገልግሎት ስናስብ ቀድመው ከፊት የመኢሰለፉት ሰዎች የሚታወቁ ለምን ሆኑ? አዳዲስ ፊት ለማየት ያልቻልነው ለምንድነው? በየቤተ ክርስትያን ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎች እና የጸሎት መርሐ ግብሮች ላይ የምናያቸው ሰዎች የሚታወቁ፣ ከዓመታት በፊት ጀምሮ የሚታዩ፣ ከዓመት ወደ ዓመት ያንኑ ተመሳሳይ ሐሳብ የሚሰጡ አይደሉምን? ታድያ ይህ ሁሉ ከየት የመጣ ነው? እንደ ሐገር የምንታዘበው አካሄድ ከቤተ ክርስትያን ሕይወት እጅግም የተለየ አይደለም። አዲስ የሚመስሉን ነገር ግን ከዘመናት ጀምሮ የነበሩ ገዢ ሐሳቦች ዛሬም በመካከላችን አሉ። ማዳመጥ ስላቆምን ትናንት እንዴት እንደዚህ ይባላል ላልንበት ንግግር ዛሬ ቆመን እናጨበጭባለን። ትናንት የሰው ልጆች ሞት በትንንሽ ቁጥር ስለተለማመድን ዛሬ የእርስ በእርስ ጦርነት ባለበት ሥፍራ ምንም እንዳልተፈጠረ እንመላለሳለን፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ በክርስትያኖች መካከል እንዲህ ያለውን ነገር ከታዘበ በኋላ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ 3፡1) እያለ ይጠይቃል።
ምናልባት ዛሬ መጠየቅ የሚገባን መሰረታዊ ጥያቄ ይህ ነው። በጥሪያችን እንዳንታመን፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎቻችን እንዳንገለጥ፣ ለክብር እና ለዘላለማዊነት ተፈጥረን ስናበቃ ራሳችንን ከአንበጣ ጋር ማወዳደር፣ ኢየሱስ የአገልጋይ ልብሱን በአጭር ታጥቆ በሚያገለግልበት በሰማያዊ ገበታ የክብር እንግዶች ሆነን ተጋብዘን ሳለ የአሳማ ምግብ ለመብላት መጎምጀት ከየት የመጣ ነገር ነው? ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል” (2ጴጥ 2፡ 20-22) ሁኔታችንን ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል።
በዛሬው ወንጌል ጌታ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተ ክርስትያን ብሎም እንደ ሀገር ስለ መክሊቶቻችንን እንድናስብ ብቻ ሳይሆን መክሊቶቻችን በዋጋ የተገዙ ትርፍ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን እንድናስብ ይጋብዘናል። በዋጋ የተገዛን ነገር ያለ ዋጋ መቅበር የሚያስከትለውን ነገር ጌታ ሲናገር ወደ ጨለማ መውረድ እያለ ይገልጸዋል። ዛሬ የቆምንበት ሥፍራ ምናልባትም ከዚያ ጨለማ ሩቅ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ጌታ ለሊቀ ሐዋርያት ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገው ዛሬም በዚህ በመልካም አገልጋይ ሰንበት “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ” (ሉቃ 5፡4) እያለ እንደ አዲስ እንድንጀምር ይጋብዘናል። መልካም አገልጋይ በራሱ መንገድ እና ችሎታ ብቻ ሳይሆን በጌታው መንገድ እና ችሎታ ተማምኖ ተስፋ የሌለው በሚመስለው ነገር ላይ መረቡን ለመጣል ወደ ጥልቁ ፈቀቅ የሚል ነው።
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ ብለህ መረቡን ጣል ለሚለው የጌታ ግብዣ መልስ ሲሰጥ “አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ” (ሉቃ 5፡5) ይላል። ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት የመልካም አገልጋይነት ሁሉ መሪ ቃል ነው። መልካም አገልጋይ በጌታው ቃል እና እምነት እንጂ በራሱ ጉልበት እና ችሎታ ብቻ አይወጣም። ምናልባትም እንደ ሀገር ለዜጎች ሕይወት የሚበጁ እና የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን ለመዘርጋት፣ እንደ ቤተ ክርስትያን በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ሁሉ ለመገለጥን እና ለሰው ዘር በሙሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ የማውረስን ተልዕኮ እንደሚገባት ለመወጣት፣ እንደ ግለሰብ በተሰጠን የጸጋ ሥጦታ በታማኝነት የክርስቶስን አካል እንድናገልግል እና ፍጥረትን ሁሉ እየቀደስን ለተፈጠረበት ክብር እናዘጋጀው ዘንድ የሚረዳን ቁም ነገር “በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ!” የሚለው የሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ አይነት የእምነት መታዘዝ ነው። በዚህ የእምነት መታዘዝ መልካም አገልጋይ የሆነ ሁሉ ራሱን፣ ባልንጀራውን እና የክርስቶስን አካል ሁሉ ይመግባል፤ “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን! (1ጴጥ 4፡10-11)። ከዚህ የእምነት መታዘዝ የተነሳ በመጨረሻው ቀን “መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!” የሚለውን የጌታ ምሥጋና ለመቀበል የተገባን እንሆናለን።
ሴሞ