እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰሙነ ሕማማት

5. ስለ ፍቅር ራስን መካድ (kenosis)

WhatsApp Image 2022 04 22 at 101854እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረበት የመጀመርያው መገለጥ እና እግዚአብሔር ዓለምን ያዳነበት ሁለተኛው መገለጥ በቃላት ሊገለጽ በማይችል መለኮታዊ ፈቃድ እርሱ እኛን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ባፈቀረበት ፍቅር (1ዮሐ 4፡19) የተሰጠን የጸጋ ሥጦታ ነው። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በመፍጠሩ ብቻ ሳይሆን መልኩን እና ክብሩን አልብሶት እንኳን አልረካምና ጊዜው በደረሰ ጊዜ እርሱ ራሱ ሊነገር በማይችል ፍቅር ተስቦ እንደ እኛ ሰው ሆነ። እርሱ ራሱን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለሰው ልጆች ሁሉ አሳልፎ በሰጠበት መገለጥ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ስለ እኛ ሲል እኛ እስከወረድንበት የኃጢአት ጥግ ወርዶ አንድ ልጁን ስለ እያንዳንዳችን “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2ቆሮ 5፡21)። እርሱ የእኛን ኃጢአት ስለተሸከመ እኛ ደግሞ በእርሱ ጽድቅ አማካይነት በእርሱ ልጅነት በኩል ልጆች ሆነን የኃጢአት ሥርየት አግኝተናል፤ ይህ የኃጢአት ሥርየት ንጹህ በሆነ በግ በቤተ መቅደስ የተፈጸመ ሳይሆን ኃጢአት ምን እንደሆነ በማያውቀው በእርሱ ላይ ኃጢአታችን ሁሉ ተላልፎበት በጎልጎታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተፈጸመ ዘላለማዊ ቤዛ እና መሥዋዕት ነው።

እግዚአብሔር ሰው የሆነው ስለ ኃጢአት ሥርየት ብቻ ሳይሆን ስለ እያንዳንዳችን ፍቅር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ዘላለማዊው በጊዜ ውስጥ ፣ ጊዜያዊው በዘላለማዊ ውስጥ የተገለጠበት የፍቅር ሁሉ ትርጉም እና ማሰርያ ነው፤ ይህ የፍቅር ትርጓሜ ከኢየሱስ ማንነት ጋር የተሳሰረ እና ከእርሱም ማንነት ተነጥሎ ሊታይ የማይቻለው ነው። የፍቅር ትርጉም ሁሉ በጌታ መስቀል ተጠቅልሎ ይገለጻል[1]። የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ በምድር የተገለጠው በእርሱ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ በሰማያት ሥፍራ ያዘጋጅልን ዘንድ ነው (ዮሐ 14፡2)። በዚህም በጊዜ የተገደብን እና የምናልፍ የነበርን እኛ ሁላችን በእርሱ በኩል ለዘላለማዊ ሕይወት ደግሞ ታጨን፤ ስለዚህ በሰማያት የምናርፍበት ወደብ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ በልጅነት መብት የምንወርሰው ቤት አለን።

ከዘላለም ጀምሮ የማይነገር የነበረው እና የማይታወቅ የነበረው የእግዚአብሔር ፈቃድ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጧል፤ በእርሱ በኩል ከዘላለም ጀምሮ ተሰውሮ የነበረው የእግዚአብሔር ፈቃድ ተፈጽሟል። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ይህንን አዲስ ሕይወት በዕለት ተዕለት ጉዞው ይኖረው ዘንድ በምሥጢራት የታጀበ ሕይወት ሊኖር ያስፈልገዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስትያኖች ሲጽፍላቸው እንዲህ ይላል “በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤፌ 2፡7-10)።

6. በመስቀሉ ሥር

የክርስትና እምነት ታላቁ ምሥጢር ከዘላለም ጀምሮ የሚኖር አልፋ እና ኦሜጋ መጀመርያ እና መጨረሻ የሌለው አምላክ ከእመቤታችን ታሪክ ጋር ተገናኝቶ በጊዜ ቀመር መጀመርያ ተብሎ የሚጠራ ጅማሬ መውሰዱ ነው። ከጊዜ ቀመር ውጪ የሆነው እና ዘመን ሊቆጠርለት የማይቻለው የጊዜ ሁሉ ባለቤት እነሆ ዘመን ተቀጠረለት። እርሱ የማይታይ ሆኖ ሳለ የሚታይ ሆኖ መገለጡ በቤተ ክርስትያን ምሥጢራት በኩል ዛሬም በሚታዩ ምልክቶች የማይታየው የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲሰራ የጸጋ ምክኒያት ሆኗል።

ቤተ ክርስትያን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የመሆን ምሥጢር የተነሳ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ማንነት ለብሳ ሕይወቷን ሁሉ ከክርስቶስ መገለጥ ጋር በተያያዘ እየተረጎመች ወደ መስቀል በምታደርገው ጉዞ እና የጌታ መስቀል በመካከሏ ባለው ሚና የበለጠ እርሱን እየመሰለች በመስቀል ምልክት ወደ ትንሳኤው የክብር ወደብ ትደርሳለች። በዚህም ቤተ ክርስትያን የሕይወቷ እና የኅልውናዋ ምንጭ ከሆነው ከቅድስት ሥላሴ ጋር ሕብረት እያደረገች በምሥጢራት በኩል የአምላክን መገለጥ በየዕለቱ በሕይወቷ እየተመለከተች ታድጋለች። በዚህም ጉዞ ቤተ ክርስትያን በቅዱስ ጳውሎስ ቃል “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” (ገላ 2፡20) እያለች በትውልድ መካከል ሙሽራዋ የከፈለላትን የፍቅር ዋጋ ትመሰክራለች።

ይህ የቤተ ክርስትያን ምሥክርነት የኢየሱን ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ማዕከል አድርጎ የሚኖር ሕያው ምሥክርነት መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ መክፈቻ ላይ እንዲህ እያለ ያረጋግጥልናል፡- “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (ሮሜ 1፡4)። ቤተ ክርስትያን በወደዳት እና ራሱን አሳልፎ በሰጣት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላት እምነት በትውልድ መካከል ሕያው ምሥክር ሆና ትኖራለች። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ላይ ያለን እምነት የፍጥረትን ሁሉ ተስፋ እና ፍጻሜ አስተባብሮ የያዘ ነው፤ በመሆኑም ጌታ ራሱ ይህንን ተስፋ እየመሰከረ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” እያለ ያረጋግጥልናል (ዮሐ 11፡ 25-26)።

ሁሉ በእርሱ ከእርሱ እና ለእርሱ ተፈጥሮአልና (ሮሜ 11፡36) እርሱ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በምድር ላይ የቀረ ሌላ ሕይወት አልነበረም፤  ያለ እርሱ አንዳች ሊያደርግ የሚችል ማንም አልቀረም (ዮሐ 15፡4) ነገር ግን እርሱ በሞቱ የሞትን መውጊያ ሰብሮ የሞትን ድል መንሳት ሽሮታልና ዳግም በአዲስ ሕይወት ሕያዋን ሆነን ለመኖር በሞቱ ከእርሱ ጋር በሚስተባብር፣ በትንሳኤውም ከእርሱ ጋር በሚያስከብር ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በዳግም ልደት ተወልደናል። ጌታ በመስቀል ላይ በከፈለልን ዋጋ የኃጢአትን ሥርየት ብቻ ሳይሆን በቀኙ እንደተሰቀለው ፈያታይ ዛሬ ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ እንሆን ዘንድ የገነትን ደጆች የከፈተልንን ጸጋ ጭምር ነው። ይህም ሥጦታው በምሥጢራት በኩል በጸጋ ሕይወት እያደግን እና በየዕለቱ እርሱን እየተቀበልን ያለማቋረጥ የእርሱ የምንሆንበት ዘላለማዊ ጉዞ ነው። በምሥጢራት በኩል ኢየሱስን እየመሰልን እና በኢየሱስ እያደግን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ያሰበለትን የከበረ መልክ እየለበስን ወደፊት እንዘረጋለን፤ በዚህም እኛ ሳንሆን ክርስቶስ ራሱ በውስጣችን ሕያው ሆኖ ይኖራል (ገላ 2፡20)። የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወቱን በኢየሱስ መልክ ለመኖር ራሱን ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት ባደረገበት መጠን የሕይወቱን ትርጉም እና ተስፋ ማየት ይችላል። የመዳናችን ምሥጢር የመጀመርያው እና የመጨረሻው ግብ ሕይወት ያውም የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖረን ነው (ዮሐ 10፡10)።

 

ይቀጥላል

ሴሞ

[1] H.U von Balthasar: Das betrachtende Gebet. Einsiedeln, 1955, ከገጽ 177 ጀምሮ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት