እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ደብረ ታቦር

ደብረ ታቦር

2S1LlNbበወንጌል ውስጥ ከምናገኛቸው በርካታ ቁም ነገሮች መካከል አንዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር መልኩ ተለውጦ እንደ ጸሐይ የማንጸባረቁ እውነታ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ነው። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17፡1-19 የምናገኘው ክፍል ይህንን የጌታን ክብር መገለጥ ዘርዘር ባለ መልኩ ይተርካል። ይህ የወንጌላዊው ማቴዎስ ትረካ የወንጌሉ እምብርት ነው፤ በአንድ በኩል እስከዚህ ድረስ የነበረው የኢየሱስ አገልግሎት መደምደሚያ ሲሆን፤ ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ላይ “አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በማለት የገለጸው ምሥክርነት ከሰው ሳይሆን ከራሱ ከአብ ማረጋገጫ የሚያገኝበት የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ከታቦር ተራራ ሲወርድ የሕማሙ መጀመርያ ይሆናል፤ ስለዚህ የጌታ መልክ መለወጥ እና የጌታ ክብር መገለጥን የሚተርከው የዚህ ወንጌል ክፍል የወንጌል የምሥራች አንኳር ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዮርዳኖስ ጥምቀት በኋላ ሰማይ ሲከፈት እና እግዚአብሔር አብ ሲናገር የምንመለከተውም በዚህ ክፍል ውስጥ ብቻ ነው፤ ከዚህም ባሻገር የኢየሱስ ቅድመ ምሥል የነበሩት ሙሴ እና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ እና ተስፋ ያደረጉት ዘመን መድረሱን በክብር ሲመለከቱ እናያለን።

በዚህ የወንጌል ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ በደብረ ታቦር ተራራ የተገለጠውን ምሥጢር በውል ሊረዱት ባለመቻላቸው በፍርሃት ተውጠው እንደነበር ወንጌል ይናገራል። ከድቅድቅ ጨለማ ይልቅ የሚያስደንቅ የታቦር ብርኀን የሚያስፈራ ግርማ አለው። በእርግጥ የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካልሆነ በስተቀር የእግዚአብሔርን መገለጥ እንደሚገባው ሊተረጉመው አይችልም። በመሆኑም የእግዚአብሔርን መገለጥ ለመረዳት እና በተገለጠበት መለኮታዊ ዐውድ እንደሚገባው ለመተርጎም የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስትያኖች በጻፈላቸው መልዕክቱ “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” (ሮሜ 8፡26) እያለ መንፈስ ቅዱስ ወደዚህ ምሥጢር ከፍ እንደሚያደርገን ይናገራል። በታቦት ተራራ ይህ ከእግዚአብሔር መገለጥ ቀጥሎ የሚከናወነው ሁለተኛ መገለጥ ሰማይ ተከፍቶ በዮርዳኖስ የሰማነው የአብ ድምጽ ስለ ልጁ ይመሰክራል። የእግዚአብሔርን መገለጥ እንረዳው ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በእያንዳንዳችን ነፍስ ሊገለጥ ያስፈልጋል፤ የምሥጢረ ጥምቀት እና የምሥጢረ ሜሮን ዐብይ ተልዕኮ ይህ ነው።

እግዚአብሔር አብ ለስምኦን ጴጥሮስ በፊሊጶስ ቂሳርያ የገለጠለትን የወልድን ማንነት በታቦር ተራራ ላይ በዮሐስን እና በያዕቆብ ምሥክርነት ሲያጸናው እንመለከታለን። ይህም በአንድ በኩል የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን ታማኝነት ሲያጸናልን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳን በሰመረ ተግባቦት የሚነበቡ በትውልድ መካከል የእግዚአብሔር መገለጥ ምሥክሮች መሆናቸውን ማሳያ ነው፤ ይህ በታቦር ተራራ ላይ የሚነገረው እግዚአብሔር ለሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ ውስጥ የተናገረው፣ ለነብያትም የዘላለም ዕቅዱን የገለጸላቸው፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት አንድ እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይህ አስቀድሞ ከሙሴ ጋር፣ ቀጥሎም ከነብያት ጋር የተነጋገረው አምላክ፤ ጊዜው በደረሰ ጊዜ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእኛ ደግሞ የተናገረን አምላክ፣ ከዘላለም ጀምሮ ተሰውሮ የነበረዉን መለኮታዊ ምሥጢር በአንድ ልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በደብረ ታቦር ገለጠልን፤ ይህም ምሥጢር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” (ማቴ 17፡5) የሚል ነው።

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ብርኀን ስለተደነቀ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” እያለ ሁኔታው እንዴት ውብ እጅግ እንደሆነ በዐይነ ኅሊናችን ያስቃኘናል። ከዚህም ባሻገር ቅዱስ ጴጥሮስ ሦስት ድንኳኖችን ለመስራት እና የእግዚአብሔር መገለጥ የታቦር ብርኀን ባለበት ለመቆየት ያለውን ፍላጎት ለጌታ ሲያቀርብለት ይታያል። ቅዱስ ጴጥሮስ ሊሰራ የወደደው ድንኳን ተራ ጊዜያዊ መጠለያ ሳይሆን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እና የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ውስጥ ለመቆየት የሰራው የመገናኛውን ድንኳን ማለቱ ነበር። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ሰው እና እግዚአብሔር የሚገናኙበት መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በሚመለከት ለጢሞቴዎስ በጻፈለት የመጀመርያይቱ መልዕክቱ “ አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (1ጢሞ 2፡5) እያለ ይመሰክራል። ስለዚህ ሰው እና እግዚአብሔር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመንፈስ እና በእውነት ይገናኙ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍ ብሎ በተሰራ ድንኳን ውስጥ ሳይሆን ከፍ ብሎ በሚታይ መስቀል ላይ ስለሁላችን ኃጢአት ቤዛ ይሆን ዘንድ ከፍ ብሎ መሰቀል ነበረበት።

ከሰማያት የተሰማው “እርሱን ስሙት!” የሚለው ድምጽ በብሉይ ኪዳን በኦሪት ዘዳግም 18፡15 ላይ ሙሴ ለእሥራኤላውያን የተናገረውን ትንቢት ያስታውሰናል። “የእግዚአብሔርን ድምጽ ከሰማሁኝ እሞታለሁ” ብሎ የሚናገር ትውልድ የእግዚአብሔርን ድምጽ የሚያደምጥበት ዘመን ይመጣል። እግዚአብሔር አምላክ በምሕረት ፊቱ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሊያነጋግረን ሰው ሆኖ የሚገለጥበት ዘመን አሁን ተፈጽሟል። ይህ የእግዚአብሔር ድምጽ ዘላለማዊ አርምሞውን አልፎ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እግዚአብሔር ስለሁሉም፣ ለሁሉም፣ በሁሉም ላይ የተናገረው ድምጽ በታቦር ብርኀን ተገልጦ ይታያል። ስለዚህ ዛሬ የምንሰማውን በመፈለግ ግራ እንዳንጋባ እግዚአብሔር አብ ራሱ ስለ ልጁ ምሥክር ሆኖ እርሱን ስሙት ይለናል። እርሱን በመስማት ውስጥ የብሉይ ኪዳን ናፍቆት እና የአዲስ ኪዳን ፍጻሜ በፊታችን ግልጽ ሆኖ ይታያል። ጌታ ወደ ታቦር ተራራ መውጣቱ ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሰን የሙሴን ወደ ተራራ መውጣት እና የእግዚአብሔርን ክብር ማየት እንድናስታውስ ያደርገናል። የሙሴ ፊት በተራራው ላይ ከእግዚአብሔር ክብር የተነሳ እንደ ጸሐይ እንዳበራ እንዲሁ የጌታ ፊት ከክብሩ የተነሳ እንደ ጸሐይ ሲያበራ እንመለከተዋለን። ሙሴ በእግዚአብሔር ክብር እንዳበራው ሳይሆን ጌታ በመለኮታዊ ክብሩ ለዓለም ሁሉ የሚያበራ የጽድቅ ጸሐይ ሆኖ በታቦር ላይ ተገልጧል።

በኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 24 ተጽፎ እንደምናነበው ሙሴ በተራራው ላይ የእግዚአብሔርን ክብር ተመልክቶ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ሊያደርግ የወደደውን የደም ቃልኪዳን በሚገባ ለመፈጸም የኮርማውን ደም በሕዝብ ሁሉ ላይ እንደረጨው እንዲሁ ለሕዝብ ሁሉ መድኃኒት የሚሆነውን ደም ከማፍሰሱ እና ፍጥረትን ሁሉ በደሙ ከመቀደሱ በፊት ኢየሱስ በተራራ ላይ ቆሞ እንመለከተዋለን። የዓለምን ኃጢአት የሚያጠፋው ንጹህ ደም አሁን ሊሰዋ ቀርቧልና ተራራው የክብር ምልክት እንደሆነ ሁሉ በሌላ በኩል የሰው ልጅ ለእያንዳንዳችን ቤዛ ይሆን ዘንድ ከፍ ብሎ የሚሰቀልበት የአዲስ ኪዳን የመጀመርያው መንበረ ታቦት ነው።

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በታቦር ተራራ ላይ ያየውን የጌታን ክብር ዘወትር ከፊታችን አስቀድመን እንድንመላለስ በዚያ የነበረውን ነገር ሲመሰክርልን እንዲህ ይላል፡-

16 የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። 17 ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ 18 እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን። 19 ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ። 20 ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ 21 ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።

ቅዱስ ጴጥሮስ ክብሩን አይተናል፤ ድምጹን ሰምተናል! እያለ በምሥክርነቱ የሚያረጋግጥልን ጌታ ዛሬም በእያንዳንዱ መንበረ ታቦት ላይ  በክብሩ ይገለጣል፤ ዛሬም ድምጹን ያሰማናል፤ ዛሬም የጌታን ድምጽ በሚገባ እንድናደምጠው እና እንድንተገብረው ሊረዳን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን በማይነገር መቃተት ይጠብቀናል። የደብረ ታቦር በዓል የክብር ፍጻሜያችን የታየበት በዓል ነው፤ ነገር ግን ወደዚህ የክብር ፍጻሜ ለመድረስ በመስቀል ምሥጢር በኩል ከጌታ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ጋር ሱታፌ ሊኖረን ይገባል። ይህንን ታስተምረን ዘንድ “እናቱ በመስቀሉ ስር ቆማ” እያንዳንዳችንን ወደዚህ ምሥጢር ትጋብዘናለች። ከእርሷ ጋር በጌታ መስቀል በኩል ወደ ክብሩ ብርኀን ወደ ታቦር እንወጣ ዘንድ የፍልሰታ ለማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን!

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት