እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ (ክፍል ፩)

1.     የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ

Christ(ክፍል ፩)

ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ከሚመሰክሩ በርካታ ቁም ነገሮች መካከል ዋነኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ምስክርነት ነው፤ በመሆኑም ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለንተናዊ ማንነት እና ተልዕኮ ትርጉም ለመገንዘብ (በነገረ መለኮት ቋንቋ “ነገረ ክርስቶስ”[1] የምንለውን ጥናት ለማድረግ) የመጀመርያው ምንጭ ወደ ሆነው አዲስ ኪዳን መመልከታችን ተገቢ እና ትክክለኛ ነው። አዲስ ኪዳን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለንተናዊ ማንነት በሚሰጠው ምስክርነት ውስጥ ኢየሱስ ስላደረገልን ነገር ሳይሆን ኢየሱስ ማን መሆኑን ለመመልከት እንሞክራለን። ቀዳሚው ጥያቄ ኢየሱስ ምን አደረገ የሚለው የጌታን ግብር የሚመለክት ጥያቄ ሳይሆን ኢየሱስ ማን ነው? የሚል ሁለንተናዊ ማንነቱን የሚመለከት ጥያቄ ነው። ማንነቱን በሚገባ በተገነዘብን ቁጥር ሥራውን እና ተልእኮውን የበለጠ መገንዘብ እንችላለን።

በመሆኑም ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ማለትም ተልእኮውን ከማብራራታችን በፊት ኢየሱስ የሆነውን ማለትም ማንነቱን በሚገባ ለመተርጎም እንሞክር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከምናገኛቸው በርካታ ምስክርነቶች መካከል ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ፊሊጵስዮስ ሰዎች በላካት መልእክቱ ምእራፍ 2፡6-11 ድረስ ያለው የጥንት ቤተ ክርስትያን ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ይገኝበታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መዝሙር ውስጥ የተገለጠበት ማንነት በእጅጉ ጥልቅ የሆነ ነገረ መለኮታዊ ቁም ነገር የያዘ በመሆኑ የጌታችን የኢየሱ ክርስቶስን ማንነት በተመለከተ የምናደርገውን ጥናት በዚሁ ክፍል መጀመራችን ተገቢ እና ትክክለኛ ነው።

6 እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ 7 ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ 8 በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። 9 በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤10 ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ 11 ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

1.1.           የጥበብ መጽሐፍት ንጽጽር

ቅዱስ ጳውሎስ በነገረ ክርስቶስ ትምህርቱ የጌታን ማንነት በተመለከተ ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች በላካት መልእክቱ ያሰፈረው ምስክርነት የአዲስ ኪዳን ነገረ ክርስቶስ ትምህርት ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። በዚህ በፊልጵስዮስ ሰዎች መልእክት ውስጥ በቀረበው የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ ዙርያ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ይህንን ጥንታዊ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር በአንድ በኩል ከአይሁድ የምኩራብ መዝሙራት እና ከብሉይ ኪዳን መዝሙራት ጋር ለማገናኘት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከግሪካውያን ፍልስፍና እና ለአማልክቶቻቸው ከሚቀርቡ መዝሙራት ጋር በማዛመድ የመዝሙሩን ታሪካዊ ዳራ እና ነገረ ክርስቶሳዊ ቁም ነገር ለማለዘብ ይሞክራሉ። በርግጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዮስ ሰዎች በላካት መልእክቱ ያሰፈረው ነገረ ክርስቶሳዊ ምስክርነት ከላይ ከተጠቀሱት ታሪካዊ ምንጮች ጋር የፍሰት ተዛምዶ ቢኖረውም የመልእክቱን ነገረ ክርስቶሳዊ ቁም ነገር በሚመለከት ቅዱስ ጳውሎስ ያቀረበው ምስክርነት ፍጹም አዲስ ኪዳናዊ ነገረ ክርስቶስ ስለመሆኑ አያጠራጥርም።

በተለይ በቁጥር ፮ እና ፯ ላይ የቀረበው ሐሳብ በአንድ በኩል በሰማያት ያለ ህላዌ በሌላ በኩል ደግሞ በምድር ስለተገለጠ የዚህ ሰማያዊ ህላዌ መልክ ስለሚናገር በጥበብ መጽሐፍት ውስጥ ከቀረቡት ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይነት አለው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቁጥር ፮ እና ፯ ላይ ያቀረበው ሐሳብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ህላዌ የሚገልጽ ሲሆን፤ እንዲህ ያለው ሐሳብ በአይሁድ የጥበብ መጽሐፍት ውስጥ የተለመደ አገላለጽ ሆኖ እናገኘዋለን። ለምሳሌ መጽሐፈ ሲራክ “ጥበብ“ ከዘላለም ጀምሮ እንደነበረች፣ በዙፋንም ላይ ትቀመጥ እንደነበር፣ ወደ ዓለም እንደተላከች እንዲሁም ማደርያዋን በሰው ልጆች መካከል እንዳደረገች ይናገራል።

“ከሁሉ አስቀድሞ እኔን ከዘላለማዊነት ፈጠረ፤ ለዘላለምም እኖራለሁ” (ሲራክ 24፡9)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ውስጥ ጌታ በባርያ መልክ መገለጡ እና ራሱን ማዋረዱ፤ እንዲሁም ደግሞ በክብር ከፍ ከፍ ማለቱ በጥበብ መጽሐፍት ከተገለጠው ከእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ ባሕርይ እና ዕድል ፈንታ ጋር በንጽጽር ሊታይ ይችላል። ይህ በጥበብ መጽሐፍ የተገለጠው የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ፣ መለኮታዊ መሳርያ ሆኖ ቀርቧል። ነገር ግን እንደ አንድ ግለሰብ የራሱን እኔነት ይዞ ከመቅረብ ይልቅ በጥበብ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠበት ዐውድ ስቃይን በደስታ የሚቀበል የእግዚአብሔር ባርያ እና ቅን አገልጋይ መልክ ሆኖ ነው።

“ድኀ[2] እና ትክክለኛ የሆነውን ሰው እንጨቁን፤... ትክክለኛው ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ እርሱ ይረዳዋል፤ ከጠላቶቹም እጅ ያወጣዋል። በተንኮል እና በስቃይ እንፈትነው፣ ደግነቱን እንመርምር፣ ትዕግስቱንም እንፈትነው። አሳፋሪ ሞት እንፍረድበት፣ እግዚአብሔር ያድነዋልና ወይም እርሱ ያድነኛል ብሏልና” (ጥበብ 2፡10፣ 18-20)።

ምንም እንኳን በጥበብ መጽሐፍት ውስጥ የቀረበው የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ካሰፈረው የነገረ ክርስቶስ ትምህርት ጋር ተዛማጅ ገጽታዎች ቢኖሩትም ራሱን ከጥበብ ጋር አንድ ስላላደረገ ከዘላለም ጀምሮ ያለው ህላዌ ከዚህ አገልጋይ ማንነት ጋር አብሮ አይሄድም።

ከዚህ ባሻገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓዝዞ ያቀረበው ሐሳም ቢሆን በጥበብ መጽሐፍት ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፤ ነገር ግን የጌታ ኢየሱስ መታዘዝ በራሱ ፈቃድ እና ውሳኔ የተከናወነ ቁም ነገር በመሆኑ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ኲነት አይገኝለትም።

ምንም እንኳን በጥበብ መጽሐፍት ውስጥ የቀረቡ ልዩ ልዩ ቁም ነገሮች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ካቀረበው ነገረ ክርስቶሳዊ ቁም ነገር ጋር የሚዛመዱ አንዳንድ ፍሬዎች ቢኖራቸውም ቅሉ፤ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶሳዊ ትምህርት ከጥበብ መጽሐፍት የተቀዳ እና ተሻሽሎ የቀረበ ነው ለማለት በቂ ማስረጃ የለም። በመሆኑም የቅዱስ ጳውሎስ ነገር መለኮት አዲስ ኪዳናዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ግንዛቤ መሆኑን በጉልህ መመልከት ይቻላል። ነገር ግን እነዚህ የጥበብ መጽሐፍት መልኮች ወደ ክርስቶስ የሚጠቁሙ ከመሆናቸው ቁም ነገር የተነሳ ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ እንደ ታሪካዊ ዳራ እና ምንጭ ሊያገለግሉ እንደሚችሉ የሚካድ አይደለም።

1.2.          የነቢያት መጽሐፍት ምስክርነት

ከጥበብ መጽሐፍት ባሻገር በነቢያት መጽሐፍት ውስጥ ተመሳሳይ የሆኑ እና ከቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ ሐሳብ ጋር በእጅጉ የሚዛመዱ ቁም ነገሮች እናገኛለን። ከእነዚህ ቁም ነገሮች መካከል አንዱ እና ቀዳሚው በትንቢተ ኢሳያስ ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሔር ባርያ ነው። (ንጽ ኢሳ 42፡ 1-4፣ 49፡1-6፣ 50፡ 4-9፣ 52፡13-53፡12)

1፤ እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። 2፤ አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። 3፤ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። 4፤ በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ይበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። (ኢሳ 42፡ 1-4)

የጌታ ራስን ባዶ ማድረግ፣ ማዋረድ እና በክብር ከፍ ከፍ ማለት ስለ እግዚአብሔር ባርያ በሚዘምረው የኢሳያስ ትንቢት ውስጥ በጉልይ ይታያል። በዚህ የኢሳያስ ትንቢት ውስጥ የእግዚአብሔር ባርያ በራሱ ፈቃድ ራሱን ዝቅ እንደሚያደርግ ማስተዋል እንችላለን። ነገር ግን በትንቢተ ኢሳያስ ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሔር ባርያ ራሱን ዝቅ ማድረጉ እና ማዋረዱ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊሊጵስዮስ መልእክቱ ባሰፈረው ነገረ ክርስቶስ ውስጥ የነገረ ድኅነትን ዐውዳዊ ትርጓሜ ይዞ እንደተገለጠው ራስን ባዶ የማድረጉ ምሥጢር “ብዙዎችን ለማዳን” ስለመሆኑ የተጠቀሰ ነገር የለም። ከዚህ ባሻገር በሰብዓ ወክልኤቱ (Septuaginta) ትርጓሜ በትንቢተ ኢሳያስ ውስጥ ለተጠቀሰው የእግዚአብሔር ባርያ የተጠቀመበት የግሪክ ቃል “παῖς” (ፓይስ) የሚል ሲሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በፊሊጵስዮስ መልእክቱ የጌታን በ “ባርያ” መልክ መገለጥ ለመግለጽ የተጠቀመው የግሪክ ቃል ደግሞ “δοῦλος” (ዱሎስ) የሚለው ነው።

ከዚህ ባሻገር በኢሳያስ መጽሐፍ የተገለጠው የእግዚአብሔር ባርያ የሚለው አገባብ ክብርን የሚያመለክት ሲሆን በአዲስ ኪዳን የቅዱስ ጳውሎስ ነገር ክርስቶስ አገባብ ውስጥ ደግሞ የጌታ በባርያ መልክ መገለጥ የመጨረሻው የውርደት ምልክት ነው። በመሆኑም በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ቁም ነገሮች በአዲስ ኪዳን የቅዱስ ጳውሎስ ነገር ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ተዛማጅ የሆኑ ሐሳቦች ቢኖራቸውም ቅሉ በቀጥታ ተያያዥነት ስለመኖሩ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አናገኝም።

ሌላው በአረማይስጥ ባህል ውስጥ የምናገኘው ገላጭ “የሰው ልጅ” (kebernash) የሚለው ቃል ነው። ይህ ቃል “የሰው ልጅ የሚመስል” የሚል ትርጓሜ የሚያሰማ ሲሆን “በርናሽ” (bernash) የሚለው ቃል የሰው ልጅ ለሆነ ለማንኛውም ሰው እንደ ስም ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑ ባሻገር በሰው መልክ የተገለጠ መለኮታዊ ማንነትን ለማመልከትም ይውላል። በዚህ የአረማይክ ቋንቋ ግንዛቤ “የሰው ልጅ” (kebernash) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በመጨረሻው ዘመን የሚገለጠውን የሰው ልጆች አዳኝ ለማመልከት የሚያገለግል የፍጻሜ ዘመን ነገረ መለኮታዊ ቋንቋ ነው። ይሁን እንጂ የቅዱስ ጳውሎስ ነገር ክርስቶስ በግሪክ ቋንቋ የተሰናዳ ጽሑፍ እንደመሆኑ መጠን እና ከአረማይክ ቋንቋ ሰዋሰው የሚቀዳ ቁም ነገር የሌለው በመሆኑ በሁለቱ ቁም ነገሮች መካከል እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የገዢ ሐሳብ መመሳሰል እንጂ የወል ስምምነት የሌላቸው በመሆኑ የቅዱስ ጳውሎስን ነገረ ክርስቶስ አዲስ ኪዳናዊ ዕሳቤ ራሱን ችሎ የሚቆም እንዲሆን ያደርገዋል።

ሌላው በብሉይ ኪዳን የምናገኘው ቁም ነገር ደግሞ የእሥራኤል አምላክ ዘላለማዊ ንግሥና ነው። ይህ የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ በፊሊጵስዮስ 2፡9-11 ከቀረበው ነገረ ክርስቶሳዊ ሐሳብ ጋር ይዛመዳል። ከትንቢተ ኢሳያስ 45፡22 ጀምሮ በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁድ ስለ እሥራኤል አምላክ ኲሏዊ ንግሥና ያላቸውን ግንዛቤ ማንበብ ይቻላል።

“22፤ እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። 23፤ ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። 24፤ ስለ እኔም። በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፥ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፥ በእርሱም ላይ የተቈጡ ሁሉ ያፍራሉ። 25፤ የእስራኤልም ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፥ ይመካሉም ይባላል” (ኢሳ 45፡22) ።

በዚህ በኢሳያስ መጽሐፍ በቀረበው ዓይነት መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ ንግሥና ከስሙ ከፍ ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ ቀርቧል። የኢሳያስ መጽሐፍ ከላይ በቀረበው ክፍል “ክብር እና መንግሥት” የሚገባውን የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ እና ኲሏዊ ገዢነት ያንጸባርቃል፤ በመሆኑም እዚህ ላይ ኢሳያስ 45ን ከፊልጵስዮስ 2፡ 6-11 ካለው ክፍል ጋር በማስተያየት እንደ ታሪካዊ ዳራ ወይም ዐውድ መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን ከዐውዳዊ ዝምድና በተጨማሪ በሁለቱ ክፍሎች መካከል ቀጥተኛ የሆነ ነገረ ክርስቶሳዊ ፍሰት አለመኖሩ በግልጽ የሚታይ ነው።

1.3.          የመላእክት በእግዚአብሔር ስም መገለጥ

ከዚሁ ጎን ለጎን በብሉይ ኪዳን ውስጥ የምናገኘው የመላእክት መገለጥ (ንጽ ዘጽ 23፡0፤ ሕዝ 1፡26-28፤ ሕዝ 8፡2) በፊልጵስዮስ 2፡6 ላይ ከቀረበው መለኮታዊ ምስል ጋር በዝምድና ሊነበብ ይችላል። በብሉይ ኪዳን የተገለጠው የእግዚአብሔር መልአክ የእግዚአብሔርን ስም የሚሸከም ነበር (ንጽ ዘጸ 23፡20)።

“20፤ በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። 21፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት”

ይህ የእግዚአብሔር መልአክ በሰው ልጅ መልክ የተገለጠ እና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጊዜ ኲነት ተገድቦ እንደ ሰው የተመላለሰ ነው (ንጽ ሕዝ 8፡2፣ ሕዝ 1፡ 26-28)።

“2፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ እንደ እሳት የሚመስል አምሳያ ነበረ፤ ከወገቡም ምሳሌ ወደ ታች እሳት ነበረ፥ ከወገቡም ወደ ላይ እንደ ፀዳል ምሳሌ፥ እንደሚብለጨለጭም የወርቅ ምሳሌ ነበረ” (ሕዝ 8፡2)

ነገር ግን ይህ በብሉይ ኪዳን የተገለጠው የእግዚአብሔር መልአክ የእግዚአብሔርን ፍጹም አንድ መሆን የሚያመላክት ገላጭ አይደለም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ፊት ከሚያገለግሉት እንደ አንዱ ነው። በፊልጵስዮስ መልእክት ውስጥ የምናገኘው የጌታ መገለጥ ከዚህ መልአክ መገለጥ ጋር የሚጋራቸው ስለ ሰማያዊ መልክ መገለጥ የሚያወሱ የነገረ መለኮታዊ ቋንቋ አንድምታዎች መኖራቸውን በንጽጽር መመልከት ይቻላል። ነገር ግን በአይሁድ ነገረ መለኮታዊ ግንዛቤ የእግዚአብሔር መላእክት ቁጥር ስፍር የሌላቸው በመሆኑ ይህ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ስም ይዞ የተገለጠው መልአክ ከእነዚህ አንዱ ሲሆን በፊሊጵስዮስ መልእክት ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ አንድ እና ብቸኛ ለሰው ልጆች መዳን የተሰጠ ስም ያለው የቅድስት ሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው።

2.    የሄለንስቲክ (ግሪካዊ) እና የአሕዛብ ትርክት

2.1.          የግኖስቲክስ ቀዳሜ ሰብ

በግኖስቲክስ አስተምሕሮ ከሰው ልጆች ሁሉ በፊት የተፈጠረ “ቀዳሚው ሰው” የእግዚአብሔር መልክ ያለው የሰው ዘር አዳኝ እንደሆነ ይነገራል። ለአብነት ያህል በ3ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚነገርለት ግብረ ቶማስ (πράξεισ θωμά)[3] በዕንቁ ያጌጠውን የክብር ልብሱን እና ዙፋኑን ትቶ ከዘንዶው ጋር ለመዋጋት እና ዕንቁ ለማስመለስ ከንጉሥ ዘንድ ስለተላከው ስለ ቀዳሚው ሰው ይናገራል። በዚህ በግኖስትክስ ትምህርት ውስጥ በዓለም ታስረው የሚገኙ ነፍሳትን ነጻ ለማውጣት የሚመጣ አዳኝ አለ። ይህም አዳኝ ከክብሩ ዝቅ በማለቱ እነዚህን በእስራት የሚገኙትን ነፍሳት ነጻ ያወጣል። ተመልሶም ወደ ክብሩ በገባ ጊዜ ተልዕኮው በሰዎች ዘንድ ይረሳል።

ከዚህ በተቃራኒው በፊልጵስዮስ መልእክት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ተልዕኮ የሚረሳ ስለመሆኑ የሚገልጽ ነገር የለም፤ የማዳን ተልዕኮውን በሚመለከት የተቀመጠ አሉታዊ ገጽታም የለም። የተልዕኮው ምስጢርም ቢሆን ወደ ታች በመውረድ እና ወደ ላይ በመውጣት መካከል የሚከናውን ሳይሆን ይልቁንም ራስን ባዶ አድርጎ በባርያ መልክ በመገለጥ፣ የባርያ ሞት ተቀብሎ በመሞት እና በሞቱ ሕይወትን በመግዛት በክብር ክፍ ከፍ በማለት የተፈጸመ ተልዕኮ ነው። በመሆኑም የአግኖስቲክስ ቀዳሜ ሰብ በፊሊጵስዮስ መልእክት ከተገለጠው የጌታ ማንነት ጋር ዝምድና የለውም።

2.2.          ሰዎችን መለኮታዊ ማድረግ

በግሪካውያን ዘንድ ነገሥታት እንደ አማልክት መታየታቸው የተለመደ ነገር ነው። በግሪካውያን እምነት በዘላለማዊ አማልክት ሥር ያሉ ሁለተኛ እርከን አማልክት አሉ፤ እነዚህም በምድር ላይ ገዢ የሆኑ የሰው ልጆች ናቸው። በመሰረቱ ይህ የግሪካውያን እምነት በፊልጵስዮስ መልእክት ከተገለጠው የጌታ ማንነት ጋር በፍጹም ተቃርኖ የሚታይ ነው። በመሆኑም በዘመኑ የነበሩት ክርስትያኖች ሁሉን ቻይ የሆነ አንድ እግዚአብሔር ብቻ መኖሩን ለማመልከት በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መተማመን በሰማዕትነት ጭምር ገልጠዋል። ነገር ግን ይህ የሰው ልጆችን አማልክት የማድረግ የጥንት ግሪካውያን ባህል እና እምነት በፊልጵስዮስ ሰዎች ከተገለጠው የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነገረ መለኮታዊ ዕሳቤ የሚለይበት ዋነኛው ቁም ነገር አማልክት የሚሆኑት በጀግንነታቸው የታወቁ ታላላቅ ነገሥታት እንጂ በባርያ መልክ የተገለጠ እና ራሱን ባዶ ያደረገ ሰው ባለመሆኑ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው በግሪካውያን ዘንድ የሚመለኩት እነዚህ ሰዎች ጦረኞች እና በጦርነት ታላላቅ ጀብዱዎችን የፈጸሙ ሰዎች ናቸው።

በግሪካውያን እና በሮማውያን ባሕል ውስጥ ንግሥና እና የእግዚአብሔርነት መልክ የተያያዙ ቁም ነገሮች ናቸው። ግሪካውያን እና ሮማውያን በንጉሣቸው አዳኝነት ይመካሉ፤ ነገሥታቶቻቸው ከእግዚአብሔር ኃይል እና ሥልጣን የተሰጣቸው ልዩ ፍጡራን እንደሆኑ ያምናሉ፤ በዚህም የግሪክ እና የሮም ነገሥታት የአማልክት ልጆች እንደሆኑ ይታመናል። በመሆኑም በንጉሥ ማንነት ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ተሰውሮ የነበረው የመለኮት ባሕርይ ተገልጾ ይታያል። ነገር ግን ንጉሡ የአምላክነትን ክብር የሚጎናጸፈው የምድር ተግባሩን ጨርሶ በሞት ሲለይ ነው። ንጉሡ ከሞት በኋላ ከአማልክት እንደ አንዱ ሆኖ በግሪካውያን እና በሮማውያን ዘንድ ይመለካል። ይህ ማለት ግን የንጉሡ አምላክነት በሞቱ በኩል የተገኘ ቁም ነገር ሳይሆን አስቀድሞ በሁለተኛ እርከን አምላክ የነበረው አሁን በሞቱ ደግሞ ከአማልክት እኩል እንደ አንድ አምላክ ይመለካል ማለት ነው።

ይህ የግሪካውያን እና የሮማውያን የሰውን ልጅ ከአማልክት አንዱ ማድረግ ባሕል በፊልጵስዮስ መልእክት ውስጥ ከተገለጸው የአምላክ በሰው መልክ መገለጥ እና በምድር ላይ ተልዕኮውን ፈጽሞ ወደ ክብሩ መመለሱ ጋር ተቀራራቢ የታሪክ ፍሰት ያለው ቢሆንም በግሪካውያን እና በሮማውያን ዘንድ ንጉሥ ከአማልክት ልጆች እንደ አንዱ የሚታየው ከንግሥናው በኋላ በመሆኑ ከፊልጵስዮስ ነገረ ክርስቶስ ጋር መሰረታዊ ልዩነት አለው። በፊልጵስዮስ 2፡9 የተገለጠው የጌታ ክብር ከዘላለም ጀምሮ በአባቱ መንግሥት ያለው ክብር እንጂ በምድር ላይ በሰው ልጆች መካከል በተገለጠ ጊዜ የጀመረ አይደለም። ንጉሥነቱ ከክብሩ፤ ክብሩም ከንጉሥነቱ ተለያይቶ አያውቅም።

ይቀጥላል...

ሴሞ

[1] ነገረ ክርስቶስ ማለት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለንተናዊ ማንነት፤ ስለ ፍጹም አምላክነቱ እና ስለ ፍጹም ሰውነቱ፤ ስለ ተልእኮው እና ስለ ማዳኑ ስራ የሚያጠና አንድ የነገረ መለኮት የጥናት ዘርፍ ነው።

[2] ድኀ የሚለው ቃል እዚህ ላይ ያለው አንድምታ ቁሳዊ ጉድለትን የሚያመለክት ሳይሆን በዓለም ኢፍትሐዊነት ፊት ለፊት የእግዚአብሔርን ጽድቅ በመጠባበቅ የሚኖር ሰው ለመግለጽ የገባ ቃል ነው።

[3] በሲራይክ ቋንቋ የተጻፈው የቶማስ አዋልድ መጽሐፍ ምናልባት በ3ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንደተጻፈ ይታመናል። ይህ ግብረ ቶማስ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ የነበረውን ሕይወት ይገልጻል። በዚህ ጽሐፍ ውስጥ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 የምናገኘውን የጠፋውል ልጅ ምሳሌ የሚመስል ታሪክ እናገኛለን። በዚህም ውስጥ በእንቁ ያጌጠው ሰው ያቀረበውን ሐተታ ዋና ገፀ ባህሪው በግዛት ውስጥ ተጠብቆ ያደገ ሲሆን በመጨረሻም ከድራጎን ላይ ዕንቁ ሰርቆ የማምጣት ተልዕኮ ይዞ ወደ ምድር ይላካል። ይህን ለማድረግ ግን በመጀመሪያ ድንቅ ልብሱን አስወግዶ ወደ ዓለም መውረድ አለበት። ከትንሽ ቆይታ በኋላ መነሻውን እና ተልእኮውን ይረሳል። በድጋሚ በንጉሱ ደብዳቤ ወደ ተልዕኮው ምሥጢር ተመልሶ ተልእኮውን ፈጽሞ፣ ወደ ክብሩ እንደተመለሰ ያትታል።

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት