እምነት (ክፍል ፫)
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Monday, 23 May 2022 18:23
- Written by Super User
- Hits: 906
- 23 May
እምነት (ክፍል ፫)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነት ሲናገር በርካታ ቃላትን ይጠቀማል፤ እነዚህ በትርጓሜአቸው ዘርፈ ብዙ በሆነ መልኩ ሊታዩ የሚችሉ ሐሳቦች ሆነው ሳሉ፣ ከእነዚህ መካከል “አሚና(ህ)” (אמונה) እና “ባታህ” (בֶּטַח) የሚሉት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጉልህ ይስተዋላሉ። ከዚህ ጎን ለጎን የግሪክ ቋንቋ ስለ እምነት ሲናገር ዘርፈ ብዙ ትርጓሜ ያላቸውን ቃላት ይጠቀማል። ከእነዚህም መካከል የዕብራይስጡ “አሚና(ህ)” (אמונה) የሚለው ቃል ፒስቲስ (πιστις)፣ ፒቲስቴዮ (πιστεως) ፣ አሌቲያ (αλήθεια) ተብሎ ተተርጉሟል፤ ይህም በላቲኑ ቅጂው fides፣ credere፣ veritas ይላል፤ ይህም እምነት፣ ማመን፣ እውነት የሚል ዐውድ ይዞ ወደ አማርኛ ሊቀዳ ይችላል። ከዚሁ ጎን ለጎን “ባታህ” (בֶּטַח) የሚለው የዕብራይስጡ ቃል በግሪኩ አቻ ትርጉም ኤልፒስ (ἐλπίς)፣ ኤልፒዞ (ἐλπίζω) እና ፓይቶ (πείθω) ተብሎ በአዲስ ኪዳን ጥቅም ላይ ውሎ እናገኘዋለን፤ ይህ ቃል በላቲኑ ቅጂ spes ፣ sperare ፣ confidere ተብሎ ተተርጉሟል። ይህንኑ ወደ አማርኛ ብንመልሰው ተስፋ፣ በተስፋ መኖር፣ መታመን ወይም የተስፋ (የልብ) እርግጠኝነት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር አብረው የተገመዱ መለኮታዊ ሥጦታዎች ናቸው፤ እነዚህ በምሥጢረ ጥምቀት በነፍስ ላይ የሚዘሩ የዘላለማዊ ሕይወት ዘሮች፣ እግዚአብሔርን የምንናፍቅባቸው የነፍስ ምሥጢራዊ ኃይላት እና መንፈሳዊ ውጊያን እንደ ክርስቶስ ወታደር ባለ ክብር ለመዋጋት የምንታጠቃቸው የጌታ የኃይሉ ችሎት ማሳርያዎች ናቸው። በእነዚህ ቃላት ውስጥ የተመለከትናቸው የእምነት ትርጓሜዎች ሁለት መሠረታዊ ቁምነገሮችን በውስጣቸው ይዘዋል። እነዚህም፡-
- መታመን
- ነፍስን ወደ እግዚአብሔር ምሥጢር ከፍ ማድረግ ነው
ባሕርያዊ እምነት
እምነት በተለያዩ ዘርፎች ሊጠና የሚችል የሰው ልጅ ባሕርያዊ ሰብዓዊ አካል ነው። መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነ እምነት ሳያስፈልገኝ ባሕርያዊ በሆነ ሰብዓዊ መንገድ የማምናቸው ነገሮች አሉ። እነዚህ ባሕርያዊ በሆነ እምነት የምቀበላቸው ነገሮች ለነገሮች ያለኝን አመለካከት ጭምር የሚቀረጹ ሊሆን ይችላሉ። እነዚህም ከባሕል፣ ከቋንቋ፣ ከሰብዓዊ ግንኙነቶች እና አካባቢያዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች የሚመነጩ የጋራ መግባባት ያለባቸው መሰረታዊ ቁም ነገሮች ናቸው። እነዚህ ቁም ነገሮች ባሕርያዊ ከሆነው ነገር ባሻገር መልዕልተ ባሕርያዊ ወደሆነው መለኮታዊ ምሥጢር ለማደግ በሚፈልጉበት ወይም ወደ እውነት ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ራሱን እውነት፣ መንገድ እና ሕይወት አድርጎ ወደገለጠው አምላክ መምጣት ባልቻሉበት ሥፍራ ከባሕርያዊ ነገር በላይ የነፍስ ጥያቄ የያዘውን ቁም ነገር ለመግለጽ ጣኦታትን ያቆማሉ። በመሆኑም ወደዚህ የጣኦታት አምልኮ ላለመግባት እና የነፍስን ጥያቄ በአግባቡ ለማድመጥ እምነት ምን እንደሆነ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። እምነት በምክኒያት እየተደገፈ የሚያድግ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ነው እንጂ ከአመክንዮ ጋር ችግር ያለበት ሌላ ዓለም አይደለም።
ይህ ባሕርያዊ እምነት በምክኒያት ያልተደገፈ በሚሆንበት ሥፍራ ሁሉ ውሎ አድሮ እንደ ተራ ጉጉት ሊጠፋ እና ሊደበዝዝ የሚችል ተራ ስሜታዊነት ወደ መሆን ይወርዳል። ነፍሳችን እውነትን ለማወቅ የሚችል ዕውቀት ባለቤት ናት፤ ነገር ግን ራሱን የገለጠውን እግዚአብሔርን ለማወቅ በሰነፍንባቸው የሕይወት ክፍሎቻችን ሁሉ ነፍሳችንን ባርያ አድርጎ የሚገዛት ጣኦት ይወለዳል። እምነት ሳያስፈልገን ምክኒያታዊነት ብቻ በነገሰበት ሥፍራ ደግሞ የሰው ልጅ ሐሳብ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ሳይንስ፣ ስኬት፣ ሰውነት... ወ.ዘ.ተ. ገዢ ሐሳብ ሆኖ ይወለዳል። በዚህም እውነተኛ ምክኒያታዊነት በጎደለበት ሥፍራ ሁሉ በአንድ በኩል እግዚአብሔርን እና የእግዚአብሔርን መገለጥ የማይቀበሉ ሰዎች የሳይንስን መላ ምቶች እንደዘበት ሲቀበሉ ይታያል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነት ሲናገር እምነት “ከእግዚአብሔር ጋር መራመድ” (ዘፍ 5፡22-24፣ ዘፍ 24፡40፣ ዘፍ 48፡15) ነው ይላል። በዚህ መረዳት መሰረት ሔኖክ፣ ኖሕ፣ አብርሐም እና ይስሐቅ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ሰዎች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (እምነት ሕይወትን በአዲስ መዋቅር ማስተካከል ነው፤ አካሄዴን፣ አስተሳሰቤን፣ የእለት ተእለት ውሳኔዎቼንና ምርጫዎቼን በሙሉ ከእምነት ቱባ ሐቅ አንጻር እንደ አዲስ ማዋቀር ይጠይቃል)
በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደምናገኘው እሥራኤል በእግዚአብሔር ቃልኪዳን፣ ምሪት እና መለኮታዊ መጋቢነት እንዲጓዝ የተጠራ ሕዝብ እንደነበር መመልከት እንችላለን። እሥራኤል ለዚህ መለኮታዊ ቃልኪዳን፣ ጥበቃ እና ምሪት የሰጠው መልስ፣ እግዚአብሔርን ተከትሎ ከግብጽ የወጣበት መታዘዝ እና አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገበት ምላሽ እምነት ይባላል።
“አሚና(ህ)” (אמונה) እና “ባታህ” (בֶּטַח) የሚሉት እምነት የሚለውን አቻ ትርጉም የወሰዱት ቃላት በውስጣቸው ጽናት እና እርግጠኝነትን (ዘፍ 15፡6፣ ዘጸ 4፡15) የተሸከሙ ቃላት ናቸው። በእነዚህ ቃላት ውስጥ ከተገለጸው ጽናት እና እርግጠኝነት የተነሳ በጸሎታችን መደምደሚያ ላይ ሁሉ “አሜን” እንላለን። በመሆኑም እምነት በእውነት እና በተግባር በተገለጸ መለኮታዊ መጋቢነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን በዚህም መሠረቱ በጸና ወዳጅነት ላይ የቆመ ሕይወት ነው። ይህም እምነት ሌላውን በማንነቱ የሚቀበል፣ ለግንኙነት ክፍት የሆነ እና እያደገ የሚሄድ ቁም ነገር ነው። እምነት “ራሱን ከገለጠው አምላክ ጋር ራስን ለእርሱ አሳልፎ በመስጠት፣ መላውን የሰው ልጅ ማንነት የሚመለከት የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው (CCC 176, cf. 150)።
በመሆኑም እምነት የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር መገለጥ የሚሰጠው ምላሽ ነው። እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕይወት ነው፤ ይህም ሕይወት ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ወዳጅነት (ዮሐ 15፡15) በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ከአብ ጋር የምንገናኝበት ምሥጢር ነው። እንደ ካቶሊክ ክርስትያን ግንዛቤ እምነት፡- ራሱን በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የገለጠው አምላክ በልጁ ሰው መሆን በኩል በሰውነታችን ውስጥ በጸጋ እና በመንፈስ ቅዱስ ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕያው ሆኖ የሚኖርበት መለኮታዊ ሕይወት ነው። በእምነት ምሥጢር አማካይነት እግዚአብሔር አብ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በውስጣችን ሕያው ነው፤ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እግዚአብሔር የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” (ማቴ 22፡32) እያለ እግዚአብሔር በእምነት አማካይነት በውስጣችን ሕያው ሆኖ የሚኖርበትን ምሥጢር ይመሰክርልናል።
እምነት እንግዲያውስ መታመንን፣ እንደታመንኩበት ቁም ነገር የሕይወቴን ቅደም ተከተል ማስተካከልን እና አምልኮን ጠቅልሎ የሚይዝ ቁም ነገር ነው። የእምነታችን መሠረት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን የገለጠው አምላክ ታማኝነት ነው። ስለዚህ ከዚህ መገለጥ የተነሳ እና እግዚአብሔር ለቃልኪዳኑ ታማኝ ከመሆኑ ቁምነገር የተነሳ ሕይወቴን ከእርሱ ጋር በማዋሃድ አካሔዴን ከእግዚአብሔር ጋር አደርጋለሁ፣ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በፍቅር በሚሰራ እምነት እየተገለጠ ሕይወቴ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ለእርሱ የተቀደሰ መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል። ይህ ለእግዚአብሔር በእምነት የሚሰዋ ሕይወት በእውነት እና በመንፈስ በሚሆን አምልኮ ለዘላለም በቅድስት ሥላሴ ፊት እንደማያቋርጥ የምሥጋና መሥዋዕት ይፈስሳል።
ይህም በልባችን በመንፈስ ቅዱስ ያለን ጸጋ የበለጠ እንዲያብብ ስለሚያደርገው በትሪያችን እና በመክሊቶቻችን ፍሬአማ እንድንሆን ያደርገናል። ይህም ፍሬአማነት የሕይወት ምሥክርነት ያለበት ጌታ በወንጌል “በተራራ ላይ ያለች ከተማ” ሲል የገለጸው አይነት የእምነት ሕይወት በመሆኑ ለሌሎች በደስታ የሚቸር እና አምላክን በሕይወታቸው የሚጋብዝ ቁምነገር ነው። በዚህ የሕይወት ምሥክርነት ሰዎች ለእውነት እና እግዚአብሔርን ለማወቅ አዕምሮአቸውን እና ልባቸውን እንዲከፍቱ ይጋብዛቸዋል። ይህም የእምነታችን ራስ እና ፈጻሚ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ (ዕብ 12፡2) በኩል የእምነትን ውበት እና ምልአት እየተመለከትን ልባችንን ለበለጠ ጸጋ እንድንከፍት ዕድል ይሰጠናል። ይህ የበለጠ ጸጋ ሌላ ነገር ሳይሆን መንገድ፣እውነት እና ሕይወት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። በዚህም “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” (ገላ 2፡20) ለማለት እንደፍራለን።
ይቀጥላል...
ሴሞ