ሰንበት ዘኒቆዲሞስ
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Wednesday, 13 April 2022 22:54
- Written by Super User
- Hits: 1056
- 13 Apr
ሰንበት ዘኒቆዲሞስ
መዝሙር፡- ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ …
ንባባት፡- ሮሜ 7፡ 1-18 ፣ 1ዮሐ 4፡18-21 ፣ ሐ.ሥ 5፡34-42
ወንጌል ፡- ዮሐ 3፡14-21
በዚህ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከሚባል የእሥራኤል የሕግ መምህር ጋር ሲወያይ እንመለከተዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢተኛ ሰው ወደ ጥፋት ያመራል፤ ትሑት ሰው ግን ክብርን ይጎናጸፋል“ (ምሳ 18፤12) እያለ ያስተምራል። ይህ ሐሳብ ቀድመን ወዳነበብነው የወንጌል ክፍል ይመልሰናል። ኒቆዲሞስ ታላቅ የእሥራኤል የሕግ መምህር ቢሆንም የማያውቀውን ለመጠየቅ፣ በውስጡ የጨለመበትን ነገር ወደ ኢየሱስ ለማቅረብ በሌሊት ጥያቄውን ይዞ መጣ፡፡ ኒቆዲሞስ በትዕቢት ተሞልቶ “እኔ የእሥራኤል የሕግ መምህር ነኝ! የተሻለ ግንዛቤ፣ የተሸለ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ዕውቀት አለኝ” በማለት አልታበየም። ነገር ግን በትሕትና፣ በጽሞና ዝቅ በማለት ወደ ኢየሱስ መጣ። ስለ ኢየሱስ እና ስለ ኒቆዲሞስ የሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በርካታ ቁምነገሮችን የሚያስተምረን ታሪክ ነው። ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ የመጣበት ሁኔታ፣ ማንነቱ፣ የጠየቀው ጥያቄ ወዘተ እያንዳንዳችን በእርሱ ቦታ እራሳችንን እንድናስቀምጥ ይጋብዘናል።
1ኛ ኒቆዲሞስ ታዋቂ የህግ መምህር መሆኑ
ኒቆዲሞስ የአይሁድ ሸንጎ አባል በመሆኑ ከነበረው ኃላፊነት፣ ሥልጣን፣ ዝና የተነሳ ወደ ኢየሱስ መምጣት ቀላል አልነበረም። ዛሬም እኛ ልክ እንደ ኒቆዲሞስ በሰዎች ፊት እንከን የሌለብን፣ የተመሰገንን ታዋቂ ክርስትያኖች፣ እገሌ ቁምስና ሲባል ስማችን አብሮ የሚነሳ ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን ከሰዎች አልፎ በኢየሱስ ዘንድ እንዴት ነው ያለነው? ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ምን ይመስላል? ታዋቂ ሰው መሆን፣ ዝነኛ ካቶሊክ ክርስትያን መሆን፣ በሰዎች ዘንድ ስማችን ከፍ ያለ መሆኑ አያድንም። ኒቆዲሞስ ዝነኛ፣ የተከበረ፣ ዐዋቂ ሆኖ ሳለ ወደ ጌታ መጣ። ገና እንደ ጀማሪ ተማሪ በጌታ እግሮች ሥር ተቀመጠ። ይህ የኒቆዲሞስ ትህትና ሰማያትን የሚከፍት ቁልፍ ነው።
2ኛ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ
ኒቆዲሞስ ከኢየሱስ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ጥልቅ ውይይት ለማድረግ በሌሊት ወደ ጌታ መምጣቱ ጌታን የማነጋገር ጥማቱን ጥልቀት ያሳየናል። ልቡን በኢየሱስ ፊት አውጥቶ ለመናዘዝ መጣ። የክብር ልብሱን ለብሶ ሰዎች የከበረ ሰላምታ እየሰጡ እንደሚያሞግሱት መምህር ሳይሆን፤ የህይወት ቃል ለመስማት እንደሚፈልግ ተማሪ መጣ። በዚያች ምሽት ኢየሱስ ሁሉን ይገልጥለት ዘንድ መጣ። ያዕቆብ ከብርቱው ሰው ጋር ሲታገል አድሮ “ካልባረከኝ እልለቅህም” (ዘፍ 32፡26) እንዳለው ሁሉ ኒቆዲሞስም ውስጣዊ የህይወት ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ ኢየሱስን የሚለቀው አይመስልም።
እኛም ዛሬ ከኢየሱስ ጋር ጥልቅ ውይይት የምናደርግበት፣ የእርሱን ምላሽ የምንሰማበት ጊዜ ያስፈልገናል። ከኢየሱስ ጋር መገናኘት፣ በተለይ በቅዱስ ቊርባን ከሚገኘው ኢየሱስ በጥልቅ መወያየት፣ ልባችን ከፍተን ማሳየት፣ በውስጣችን በጥያቄ ተሞልተው የተዘጉ በሮችን በኢየሱስ ፊት መክፈት፣ አለማወቃችን ሳያሳፍረን፣ ዝናችን አንቆ ሳያስቀረን፣ ዛሬ ታይቶ ነገ የማይደገመው የሰዎች ከንቱ ውዳሴ ሳያታልለን በኢየሱስ ፊት በትህትና መቅረብ ያስፈልጋል። ጥያቄዎቻችንን ይዘን በዚህ በዐብይ ጾም ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ጥልቅ ውይይት ልናደርግ ያስፈልጋል።
3ኛ ኢየሱስ መልስ ይሰጣል፤ የቋንቋ ለውጥ ያደርጋል
ኒቆዲሞስ ለጥያቄው መልስ አግኝቷል። ማብራርያ የሚያስፈልገውን ነገር ጠይቆ ተብራርቶለታል። ይህ እንዴት ይሆናል? ብሎ የተደነቀበት ነገር እንዴት እንደሚከናወን ተነግሮታል። ስለዚህ በእርግጠኝነት እንደ አመጣጡ በከንቱ አልተመለሰም ማንነቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተለውጧል።
አብዛኛውን ጊዜ እኛም እንደኒቆዲሞስ መለከታዊውን ነገር አናስተውልም። ለእራሳችን ጥያቄዎች ራሳችን መልስ እየሰጠን እንጓዛለን። የእራሳችን ድምጽ ብቻ ይሰማል። በራሳችን መልስ እንዳንጠፋ ያሰጋል። ስለዚህ የቋንቋ ለውጥ ያስፈልገናል። ከምድራዊ ቋንቋ ባሻገር መለኮታዊ ድምጽ፣ መለኮታዊ ቋንቋ ሲገባን ህይወታችን በዚያ ደረጃ ይለወጣል፣ የኢየሱስ ድምጽ፣ የእውነት ድምጽ ሲመጣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይለውጠናል። ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስ ልብ የእኛም ልብ በሩ ወለል ብሎ መከፈት አለበት። ሰማያዊውን ቋንቋ ለማድመጥ መዘጋጀት አለብን። በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ይህንን መለኮታዊ ድምጽ በትጋት መፈለግ፣ እርሱም ሲናገር በአግባቡ ማድመጥ እንችል ዘንድ ምድራዊውን እውቀት፣ ሁካታ መልስ ሁሉ ጸጥ ለማሰኘት እንበርታ።
4ኛ ዳግም መወለድ ያስፈልጋል
ይህ በሰማያዊ ቋንቋ የቀረበልን ጥሪ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማርቆስ ወንጌል መግቢያ ላይ በመጥምቁ ዮሐንስ አፍ “በዘመኑዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግስት ቀርባለች፣ ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” (ማር 1፡14-15) እያለ ጥሪውን እና ግብዣውን ያቀርባል። ዳግም መወለድ በላባችን፣ በእውቀታችን፣ በኑሮ ደረጃችን የምናገኘው ነገር ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ በእግዚአብሔር የተሰጠ ሥጦታ ነው። በእግዚአብሔር ጥሪና ምርጫ የሚከናወን በእርሱ መሪነት የሚፈጸም መንፈሳዊ ልደት ነው። ይህ ሰማያዊ ተግባር በዓለማዊ ቋንቋ ሊገለጽ አይችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ልጁን ጌታችን ኢየሱስን ወደመምሰል ይገነባናል። የዕብራውያን መልእክት ይህንን ያረጋግጥልናል “በኢየሱስ ክርስቶ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፣ ፍቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ” (ዕብ 13፡21)።
ዳግም መወለድ የልብ ለውጥ፤ ዳግም መወለድ ወደ እግዚአብሔር በሙሉ ልብ መመለስ ነው። ሰው ራሱን አውቆ ራሱን ማሸነፍ ከቻለ በዓለም ደስተኛ ሆኖ በሰላም መኖር ይችላል፤ ዳግም መወለድ ማለት ትህትና ለብሶ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛት ነው። ትሁት ሰው መታወክንና መጨነቅን አያውቅም፤ ከራሱ ያልተገራ ፍቅር ነፃ የወጣ ስለሆነ በእግዚአብሔር በመታመን ተስፋ ያደርጋል። ትሁት ሰው “እኔ! እኔ!” የሚለውን ተውላጠ ስም አይጠቀምበትም። ትሁት አይቆጣም፣ አያኮርፍም፣ ክብሬ ተነካ ብሎ ለውጊያ አይነሳም፤ ምክኒያቱም በፈቃዱ ራሱን ከክርስቶስ ህማም ጋር ለማስተሳሰር ወስኗል። ትሁት በሚያገኘው ክብር አይመካም፤ በልቡ ግን ማን መሆኑን ያውቃል። ዳግም መወለድ ይህን መሰል ትህትና መልበስ ነው።
ኒቆዲሞስ ምዕመን፤ የሃይማኖት አባት እና የፖለቲካ መሪ
ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ ሲመጣ እንደማንኛውም አይሁዳዊ በኢየሱስ ሥራ እና ትምህርት ተማረኮ ነበር። ይህ ይህንንም በውይይታቸው መጀመሪያ ላይ በግልጽ ይናገራል ”መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሲያደርግ የሚችል የለምና” (ዮሐ 3፡2)። ኒቆዲሞስ እንደ አንድ አማኝ በኢየሱስ በመማረኩ የራሱ ዕውቀት፣ ዝና፣ ታዋቂነት ሳይገድበው ወደ ኢየሱስ መጥቷል “እኔ ብሆን ከእርሱ የተሸለ አድርጌ አስተምር ነበር!” በማለት በትዕቢት በገዛ ራሱ ኃይል አልተመካም። ይልቁንም የእርሱን ሥራ ተመልክቶ በዚያ ውስጥ እግዚአብሔር መገለጡን ስላስተዋለ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ ውይይት ጀመረ። ለነፍሱ ስለሚጠቅመው ነገር ይወያይ ነበር እንጂ ለክርክር፣ ለክስ፣ እኔ እበልጣለሁ ብሎ ለመሟገት አልመጣም። ኒቆዲሞስ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በተጠቀሰባቸው ሦስት ሥፍራዎች (ዮሐ 3፣7፣19) እውነትን የሚፈልግ፣ ከእውነት ጋር የሚወግን እና እውነትን እስከመጨረሻው የሚከተላት መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ በእነዚህ ክፍሎች ኒቆዲሞስን ሲታስተዋውቀን አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው እያለ ይገልጸዋል፤ ይህም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር የነበረው ግንኙነት በሕይወቱ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ለመሆኑ ማሳያ ነው።
በዚህ በዐብይ ጾም ጊዜ በክርስትያናዊ ሕይወታችን ትሕትናን በመለማመድ ኢየሱስን ማን እንደምንለው በሥራችን መግለጥ አለብን። በተለይ ለመሪዎች (የሃይማኖትም ይሁን የፖለቲካ) መጸለይ አለብን። እንደ መሪ በጥበብና በማስተዋል እንዲያስተዳድሩ የሚያስችላቸው እውቀታቸው ፣ ትምህርታቸው፣ የሚገኙበት የሥልጣን እርከን ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ በሀገራችን እንዲሰፍን የእያንዳንዳችን ጸሎት ወሳኝ ነው። የጸሎት ሰዎች ሆነን ሁሉን ነገር በጸሎት እንድንታገል ኒቆዲሞስ ያስታውሰናል።
ከኒቆዲሞስ ታሪክ ምን እንማራለን?
ከኢየሱስ ጋር ለብቻችን የምናሳልፈው የጸሎት፣ የጽሞና፣ የአስተንትኖ ጊዜ የብርሀን ጸጋ የምናገኝበት ጊዜ ነው። እርሱ የተፈጥሯችንና የህይወታችን ምንጭ በመሆኑ እውነተኛውን መልካችንን የምናገኘው ከኢየሱስ ጋር ልብ ለልብ የምንገናኝበት ጊዜ ሲኖረን ነው። ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ሁሉ ሁላችንም ውስጣዊ ጥያቄ አለን፣ ጥልቅ ፍላጎት አለን፣ ሸክም ሆኖ የሚያስጨንቀን ቀንበር አለን፣ ባርያ አድርጎ የሚገዛን ኃጢአት አለ። ይህንን ይዘን እንቅረብ። ኢየሱስ ልባችንን ስለሚፈለግ “እናንተ ሸክም የከበዳችሁ ወደ እኔ ኑ! እኔም አሳርሃችኋለሁ” ይላል (ማቴ 11፡28)። በምሥጢረ ንስሐ እየታደስን እንድንለወጥ ኢየሱስ በምሥጢረ ቊርባን ሆኖ የእያንዳንዳችንን መመለስ፣ የእያንዳንዳችንን መምጣት ይጠባበቃል። ወደ ኢየሱስ መጥተን አዲስ ህይወት አግኝተን በዳግም ልደት ታድሰን፣ በሰማያዊ ድምጽ ተሞልተን እንድንጓዝ ወደ ኢየሱስ እንቅረብ።
ሴሞ