በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት (እምነት ክፍል ፩)
- Category: የተለያዩ አስተንትኖዎችና አስተምህሮዎች
- Published: Thursday, 05 May 2022 15:44
- Written by Super User
- Hits: 1063
- 05 May
“በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት” (ገላ 5፡6)
የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” (ዕብ 11፡1) እያለ እምነት የተስፋ ብርኀን እና ወደ እግዚአብሔር የምንመለከትበት የነፍስ ዐይን መሆኑን ይናገራል። እግዚብሔር አምላክ በአዕምሮአችን እና በፈቃዳችን ውስጥ ብርኀኑን ያበራል፤ እምነት ተስፋ እና ፍቅር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም ሞት እና ትንሣኤ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በምሥጢረ ጥምቀት ዳግም በተወለድን ጊዜ እግዚአብሔር አብ በነፍስ ላይ የሚተነፍሳቸው የጸጋ እስትንፋሶች ናቸው። ነፍስ ከእነዚህ የጸጋ እስትንፋሶች የተነሳ ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር ቀጣይነት ባለው የአባት እና ልጅ ግንኙነት ትመላለሳለች። በእነዚህ የጸጋ ሥጦታዎች የተነሳ በነፍስ ውስጥ ቀጣይነት ያለው የተመስጦ እና እግዚአብሔርን የመናፈቅ ሕይወት ይጀምራል። የምሥጢረ ጥምቀት ጸጋ እና ሥጦታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር አብ ባለን እምነት የተፈጠርንበትን እና ለመዳን ቀን ተዋጀንበትን ጥሪ ተስፋ እያደረግን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር የምንመላለስበት ሕይወት መጀመሩ ነው።
ስለ እምነት ስንናገር እውነትን ለማግኘት የምናደርጋቸውን አእምሮአዊ ውሳኔዎች እና ምርጫዎች የሚመለከት ቁም ነገር ማለታችን ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሚገጥሙን ነገሮች ውስጥ እንደ አማኝ የምንኖረውን ተግባራዊ ሕይወት የሚመለከት እውነታ ነው። አማኝ ራሱን ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ክፍት ባደረገበት ሁኔታ ሁሉ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በስሜት እና በውጫዊ ምልክቶች ሳይሆን በፍቅር በሚሠራ እምነት (ገላ 5፡6) በተግባር ይገለጣል። ይህ በፍቅር የሚሠራ እምነት መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ነፍስ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ሕያው ምሥክር ነው። ስለዚህ የዚህ ተከታታይ ትምህርት አንኳር ነጥብ በፍቅር የሚሠራ እምነት የሚለው ቁም ነገር ነው!
እምነት መልዕልተ ባሕርያዊ በሆነ አድማስ የግዙፉን ዓለም ነባራዊ እውነታ ተሻግሮ የማይታየውን ምሥጢራዊ ነገር የሚያሰላስል የመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ነው። በዚህም መሰረት “አማኝ የሆነ ሰው” በእግዚአብሔር በማያምነው ሰው ዐይኖች ሰርክ አዲስ የማይደረስበት ምሥጢር ይሆናል።
ስለ እምነት ስንነጋገር ወይም እምነት ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ በዙርያችን ያሉትን አማኞች መመልከት ባሕርያዊ እና የመጀመርያ አካሄድ ነው። አማኝ የሚኖረውን የዕለት ተዕለት ሕይወት በመመልከት የእምነትን ቁም ነገሮች እና ባሕርያት ማስተዋል እንችላለን ነገር ግን ባሕርያዊ በሆነ ዕይታ መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነውን የእምነትን ምሥጢር ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። እምነት የሚመረመር ምሥጢር ባለመሆኑ ራሱን ለሰው ልጅ ባሕርያዊ መስፈርያ የሚሰጥ ቁም ነገር አይደለም። ስለዚህ አማኝ ከሚያሳየው ባሕርይ እና የኑሮ ዘይቤ ባሻገር ወደ መለኮታዊ የእምነት፣ የተስፋ እና የፍቅር ትርጉም መመልከት ይጠበቅብናል። ይህንን ለመገንዘብ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እንደ ቤተ ክርስትያን ያደረገልንን ቁም ነገር እና ከእርሱ በሆነ ጸጋ በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በውስጣችን የተጀመረውን የዳግም ልደት ሕይወት መመልከት ይጠበቅብናል። ይህም እግዚአብሔርን ራሱን እያሰላሰልን፣ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በኩል በእኛ ውስጥ በጥምቀት የተወለደውን የእርሱን ሕይወት ማጣጣም የምንጀምርበት የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው።
እርሱ ራሱ በሰጠን በእምነት ሥጦታ እግዚአብሔርን እየዳሰስን ፍቅሩን በሕይወታችን እንለማመዳለን። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ ተግሳጽ ልባችንን እየገራ የእምነት ሁሉ ምልዐት እና ፍጻሜ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ መልክ እናድግ ዘንድ ስለ እያንዳንዳችን በውስጣችን ይቃትታል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ በነፍሳችን ውስጥ መቃተት ወደተፈጠርንበት መልክ ምልዐት እስክንደርስ እና በእርሱ እስክናርፍ በውስጣችን የሚንቀሳቀስ መለኮታዊ ናፍቆት ነው። ይህ እምነት የአእምሮአዊ ሁናቴ እና የልብ እርግጠኝነት ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም መላውን ማንነታችንን፣ ስነ ልቦናችንን እና የእኛ የሆነውን ነገር ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነት እስኪሞላ ድረስ የሚጠቀልል ቁም ነገር ነው።
በዚህ እምነት አማካይነት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምሕረት ፊቱን የተመለከትነውን እግዚአብሔርን እናፈቅራለን። ስለዚህ በመጽሐፍ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል”(1ጴጥ 1፡8-9) ተብሎ ተጽፏል። ይህ ፍቅር እግዚአብሔር አምላክ ማን መሆኑን ሰው በከተበው ፊደል ሳይሆን እግዚአብሔር አብ ራሱ በዘላለም ቃሉ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ልሳን በልብ ላይ የሚተነፍስበት ግንኙነት ነው። በመሆኑም በተሰጠን የእምነት ሥጦታ ማንነታችንን በሙሉ በዚህ ፍቅር ፊት ለማፍሰስ እና በደረቱ ላይ ተደግፈን የልቡን ምሥጢር ለማዳመጥ (ዮሐ 21፡20) በተስፋ ዕለት ዕለት ወደ እርሱ እንናፍቃለን። እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ለዘላለም በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ወደ እግዚአብሔር የሚመልሱን የጌታ መስቀል ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህ በምሥጢረ ጥምቀት የተቀበልናቸው መለኮታዊ ሥጦታዎች ቀስ በቀስ እያደጉ የልጁን የጌታችን የኢየሱስን መልክ እስክንመስል ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ትዕግሥት ለዘላለም ለጠመረጥንበት ክብር ያዘጋጁናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌ 3፡17-21 ባለው ክፍል እንዲህ ይላል “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን”።
የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ ከጌታ ጋር ከነበረው ግንንኙነት የመነጨ የሕይወት ዘመን ትልም ነው። ከዚህም እምነቱ የተነሳ ቅድስት ሥላሴ በሁለንተናው እንዲወርሰው እና የዘላለም ከተማው አድርጎ እንዲቀድሰው ራሱን በእግዚአብሔር ምሕረት ውስጥ ይጥላል። በመሆኑም ከራሳችን ደካማ ማንነት በላይ በእኛ በሚሠራው የጌታ ኃይል እንድንታመን ያበረታናል። በሕይወት ፈተና ወቅት በእኔ ውስጥ ያለሁት እኔ ብቻ ሳልሆን ጌታ ኢየሱስ ራሱ መሆኑን እንድንመለከት እና በነገር ሁሉ ራሳችንን ለእርሱ አሳልፈን እንድንሰጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከራሱ የእምነት ጉዞ በመነሳት ግብዣውን ያቀርብልናል። ቅዱስ ጳውሎስ በሥጋው ድካም ነበረበት፣ ጎኑን እንደ ጦር እየወጋ የሚያሰቃየው ኃጢአት ነበረበት ነገር ግን በማንነቱ ውስጥ ራሱን ብቻ ሳይሆን በዚያ ከእርሱ ጋር ለመኖር ሰው መሆንን የመረጠውንን እና በደማስቆ መንገድ ከፈረሱ ላይ የጣለውን ወዳጁን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እየተመለከተ ተስፋ ባልሆነው ነገር ሁሉ ላይ ጌታን ተስፋው አድርጎ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል 4፡13) እያለ ያበረታናል። በዚህም ራሳችንን ስንመለከት በእምነት ምሥጢር አማካይነት ከእኛ ጋር ለመኖር በውስጣችን ያለውን ጌታ የምንመለከትበት እና በእርሱ ኃይል ሞት እና መውጊያን ሁሉ የምንሰብርበት ጽናት እምነት ይባላል።
አምላኬ ሆይ! አንተ የገለጽከውን፣ ቅድስት ቤተክርስትያን የምታምነውን እና የምታስተምረውን ሁሉ አምናለሁ! አሜን!
ይቀጥላል
ሴሞ