እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ (ክፍል ፪)

የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ

(ክፍል ፪)

Christእስካሁን ድረስ በክፍል ፩  የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ (ክፍል ፩) ያየናቸው ንጽጽሮች ከቋንቋ ዐውዳዊ አግባብ እና ከታሪክ ፍሰት ተመሳሳይነት ባለፈ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዮስ መልእክቱ ካቀረበው ነገረ ክርስቶስ ጋር የውርስ ዝምድና እንደሌላቸው ተመልክተናል። ራሱን ባዶ ማድረጉ፣ ራሱን ማዋረዱ፣ በመስቀል ሞት መክበሩ፣ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት በሰው ሥጋ መገለጡ እና ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም መልበሱ በየትኛውም ዘመን ውስጥ ከተገለጡ ታሪካዊ ክስተቶ እና ንግርቶች ሁሉ በላይ ነው። ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ ከሁሉ በላይ ስለ እግዚአብሔር መገለጥ የሚናገር የግልጠት ምስክርነት ነው። ይህ ምስክርነት በዘመኑ በነበረው የቋንቋ እና የማሕበረሰባዊ ሁለንተናዊ ዐውድ ውስጥ የክርስትናን ማዕከላዊ ቁም ነገር ለጊዜው ምልክቶች ምላሽ በሚሰጥ ሁኔታ ይተርካል። ዛሬም ቢሆን ለዘመናችን ማኅበረሰባዊ ሁለንተናዊ ዐውድ ተስማሚ በሆነ ነገር ግን የክርስቶስን ግልጠት በማይሸራርፍ ጤናማ ቋንቋ የክርስቶስን መገለጥ ምሥጢር ለማብሰር ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ባለ ዐደራ ናት።

ቅዱስ ጳውሎስ በፊሊጵስዮስ መልእክቱ ያቀረበው ነገረ ክርስቶስ ይህንን የክርስቶስን የመገለጥ ምሥጢር ለዘመኑ አእምሮ በሚረዳ ቋንቋ እና አቀራረብ ከእውነቱ ሳይዛነፍ ለትውልድ የእግዚአብሔርን በሰው ልጆች መካከል መገለጥ ይመሰክራል። በዚህም ምስክርነቱ ውስጥ የክርስቶስን ዘላለማዊ ኅላዌ፣ የክርስቶስን አምላክነት እና ሥጋ ለብሶ የመገለጡን የትሥጉት ምሥጢር መልእክቱ ለተጻፈበት ዐውድ በሚረዳ የቋንቋ እና የነገረ መለኮት አግባብ በግልጽ ያሳያል። እንደ ክርስቶስ መገለጥ አይነት መልክ ያላቸው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሚነገሩት ትርክቶች በተመሳሳይ መልኩ የተገለጡ በርካታ ሰዎችን ሲያመላክቱ ቅዱስ ጳውሎስ በተቃራኒው የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ሰው የመሆን ምሥጢር በሰማይ እና በምድር ከምድርም በታች አንድ እና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተከናወነ የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን ይመሰክራል።

2.3   የፊሊጵስዮስ መልእክት የተሰናዳበት መቼት

ይህ የፊሊጵስዮስ መልእክት በሮማውያን የግዛት እና የጣኦት አምልኮ ዘመን የተጻፈ ነው። ነገር ግን የአይሁድ ባሕል እና አስተሳሰብ እንደሚንጸባረቅበትም ማስተዋል ይቻላል። በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለግሪካውያን እና ለአይሁዳውያን አማኞች እንደጻፈው መመልከት እንችላለን። ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ እጅግ ጥንታዊ የአዲስ ኪዳን ነገረ ክርስቶስ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ኅላዌ ምሥጢር አይነተኛ ምስክር ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ያጠናቀረበት ስፍራ በአንጾኪያ አልያም በደማስቆ እንደሆነ ይታመናል። የፊሊጵስዮስ ሰዎች የዚህ የቅዱስ ጳውሎስ ነገረ ክርስቶስ ተደራሲያን ሆነው በቅዱስ ጳውሎስ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አማካኝነት ምናልባትም በፊሊጵስዮስ ያለችው ቤተ ክርስትያን በተተከለችበት ዘመን ማለትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ 49 ዓ.ም. ገደማ ከዚህ ክርስቶሳዊ መዝሙር ጋር ሊተዋወቁ ችለዋል።

2.4  የመዝሙሩ ፋይዳ (Sitz im Leben)

ይህ መዝሙር ለክርስቶስ የቀረበ ውዳሴ እና የእምነት ምስክርነት ነው። ለአንድ አምላክ ኅላዌ እና ለማዳን ሥራው ክብር በቤተ ክርስትያን ጉባዔ መካከል በሥርዐተ አምልኮ ዐውድ የተዘመረ መወድስ ነው። በመሆኑም በእግዚአብሔር ፊት የቀረበ የአምልኮ አኮቴት ነው። ከዚህ ባሻገር የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚዘክር እና የክርስቶስን ትሥጉት ምሥጢር የሚመሰክር የእምነት ምላሽ ነው። በመሆኑም በዚህ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ውስጥ የአንድ አማኝ መሰረታዊ የእምነት ቀኖና ተገልጦ ይታያል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን አንድ አማኝ እምነቱ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የነፍስ መታመን ምስክር የሆነ መዝሙር ነው።

2.5   የመዝሙሩ አወቃቀር

ይህ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር በሁለት ክፍሎች እና በሦስት አንጓዎች ተሰናድቶ የቀረበ መዝሙር ነው፤ የመጀመርያው ክፍል በሁለት አንጓዎች የተዋቀረ ሆኖ ቁጥር ስድስት እና የቁጥር ሰባትን የመጀመርያ ፍሬ ነገር ያካትታል፤ ይህም የጌታን በእግዚአብሔር መልክ የመኖር ዘላለማዊ ኅላዌ እና በትሥጉት ምሥጢር የባርያን መልክ ይዞ መገለጡን የሚያወሳ ክፍል ነው፤ ሁለተኛው አንጓ ደግሞ በቁጥር ስምንት ላይ ያለው ራሱን ባዶ አድርጎ በሰው መልክ መገለጥ እና እስከ ሞት ድረስ ለዚያውም እስከ መስቀል ሞት ድረስ የታዘዘበትን ምሥጢር የሚያወሳ ክፍል ነው። የዚህ ክርስቶሳዊ መዝሙር ሁለተኛ ክፍል ደግሞ አንድ አንጓ ብቻ ያለው ሲሆን፤ እርሱም ከቁጥር 9 – 11 ድረስ ያለውን ኃይለ-ቃል የሚጠቀልል ነው። ይህም ጌታ ከክብር ሁሉ በሚበልጥ ክብር ከፍ ከፍ ማለቱን፣ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም መውሰዱን እና በሰማይ እና በምድር ሁሉ ገዢ መሆኑን የሚያትት ክፍል ነው።

እነዚህ ሁለት ክፍሎች ራሳቸውን የቻሉ ሲሆኑ በግሪኩ ቅጂ ከቁጥር 6–8 ያለው ክፍል ከቁጥር 9 ጀምሮ ካለው ክፍል ጋር “δίο” (ዲዮ) በሚለው አያያዝ ቃል ተገናኝተዋል፤ ይህም በሁለቱ ክፍሎች መካከል የሐሳብ ፍሰት ለውጥ መኖሩን የሚያመላክት ቁም ነገር ሲሆን በዚህም በመጀመርያው ክፍል የተከናወነው ቁም ነገር በሁለተኛው ክፍል ለተገለጠው ክብር ቅድመ ሁኔታ እንደነበር ያመለክታል። ከዚህ ባሻገር “δίο” በሚለው የቅደም ተከተል አያያዥ ሰዋሰዋዊ አገባብ መሰረት በቀደመው እና በሁለተኛው ክፍል መካከል የሐሳብ ፍሰት ብቻ ሳይሆን የገቢር ለውጥ መኖሩንም የሚያመላክት ቁም ነገር አለው። በዚህም በመጀመርያው ክፍል ከቀረበው ከወልደ እግዚአብሔር ማንነት ባሻገር በሁለተኛው ክፍል የገቢር ባለቤት እግዚአብሔር አብ ራሱ መሆኑን ማስተዋል እንችላለን። የዚህ መዝሙር ሰዋሰው በንጽጽር፣ ባልተጠበቁ አስደናቂ ውሳኔዎች እና በገዢ ሐሳብ ድግግሞች የተሞላ ከመሆኑም ባሻገር በግሪኩ ቅጂ በርካታ የ “Aorist-Forme” አንድ ድርጊት ለአንድ ጊዜ ብቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መከናወኑን የሚያመለክት ሰዋሰዋዊ ይዘት ያለቸው አገባቦች በእጅጉ ይስተዋሉበታል።

2.6  ስነ ጽሑፋዊ ሂስ እና የመዝሙሩ ደራሲ ማንነት ጥያቄ

የፊሊጵስዮስ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ጸሐፊ ቅዱስ ጳውሎስ ይሁን ወይም ደግሞ መዝሙሩ ከቅዱስ ጳውሎስ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በፊት ቀድሞ የነበረ ይሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድ በእጅጉ አነጋጋሪ ቁም ነገር ነው። በፊሊጵስዮስ መልእክት 2፡6–11 ያለው ክፍል ራሱን ችሎ የሚቆም እና መክፈቻም ሆነ መዝጊያ ያለው ወጥ አስኳል በመሆኑ የጳውሎስን ደብዳቤዎች አይነት ይዘት አይታይበትም። በመሆኑም ያለማንገራገር የጳውሎስ መልእክት ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስደፍር አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ መዝሙሩ ከጳውሎስ የቀደመ ስለመሆኑ ውኃ የሚያነሳ ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም።

2.7   የመዝሙሩ ሰፊ ዐውድ

ሰፊው ዐውድ የፊሊጵስዮስ መልእክት ሲሆን ፊሊጵስያ ከሜቄዶንያ በስተምሥራቅ የምትገኝ በተሰሎንቄ አውራጃ የነበረች ጥንታዊ ከተማ ናት። ከተማዋ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ 168 ዓ.ዓ. ጀምሮ ለረጅም ዘመን በሮማውያን ቅኝ ግዛት ሥር የነበረች ስትሆን የፊልጵስያ ቤተ ክርስትያን ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ ጳውሎስ ከስልዋኖስ እና ከጤሞቴዎስ ጋር ወደ ተሰሎንቄ ባደረገው ሁለተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዘመን የተተከለች ቤተክርስትያን ናት። መዝሙሩ በፊልጵስዮስ በቤተ ክርስትያን መካከል ጥቅም ላይ የዋለበት ዘመን ከጌታ ልደት በኋላ በ54 ዓ.ም. አካባቢ እንደሆነ ይታመናል። መዝሙሩ ከቅዱስ ጳውሎስ ሥራዎች አንዱ ነው በሚለው መረዳት መዝሙሩ የተጻፈበት ስፍራ ጳውሎስ በእሥር ላይ የነበረበት ኤፌሶን ውስጥ እንደሆነ ሊቃውንት ይስማሙበታል።

2.8  የመዝሙሩ ንዑስ ዐውድ

በፊሊጵስዮስ 1፡27– 2፡4 ድረስ ያለው ክፍል ስለ አንድነት እና በወንጌል በተቃኘ ማንነት በክርስቶስ ኢየሱስ ስለመኖር የሚያትት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን በተጋድሎ ስለመኖር እና ተግባራዊ ክርስትያናዊ ኑሮ ስለመምራት ይናገራል። ፊሊጵስዮስ 2፡5 በቀጥታ ወደ ፊሊጵስዮስ መዝሙር ይጋብዘናል፤ በተለይም በዚህ ክፍል የቀረበውን የክርስቶስ አብነት እንድንከተል እንበረታታለን። ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትያኖች ይህንን የክርስቶስን አብነት እንዲከተሉ ከመከረ በኋላ በተለይ በምዕራፍ 2፡12-18 ድረስ የፊሊጵስያ ክርስትያኖች መዳን ያስጨንቀው እንደነበር መመልከት እንችላለን። በዚህ ክፍል የቀረቡት ሐሳቦች በፊሊጵስያ ይኖሩ የነበሩትን ክርስትያኖች ሕይወት ያማከለ እና ለእነርሱ ሁኔታ ታስቦ የተዘጋጀ ስብከተ ወንጌል መሆኑን ከይዘቱ መረዳት ይቻላል። ከእነዚህ በተቃራኒ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል የራሱን ገዢ ሐሳብ ይዞ የተገለጠው የነገረ ክርስቶስ መዝሙር በጊዜ ውስጥ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተከናወነ የእግዚአብሔር መገለጥን የሚዳስስ ረቂቅ ነገረ መለኮታዊ ጭብጥ ሆኖ በፊሊጵስዮስ መልእክት ውስጥ ቀርቧል።

2.9  የቅዱስ ጳውሎስ ቀለማት

በዚህ የፊሊጵስዮስ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ውስጥ ለቅዱስ ጳውሎስ ቋንቋ እና ነገረ መለኮታዊ ዕይታ እንግዳ የሆኑ አንዳንድ ነጥቦችንም ማስተዋል ይቻላል። በዚህም በፊልጵስዮስ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ውስጥ የሚስተዋሉ አንዳንድ ቃላት በተቀሩት የጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉት የሰዋሰው አገባብ እና የቃላት ምርጫ የሚለዩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከዚህ ባሻገር በቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የምናገኘው የመዳን ጥያቄ በዚህ በፊልጵስዮስ ነገረ ክርስቶሳዊ መዝሙር ውስጥ አይስተዋልም። በተጨማሪም ይህንን መዝሙር እንደ መግቢያ ሆኖ የሚያስተዋውቅ ወይም ደግሞ ለመዝሙሩ የሚገባውን ዐውድ የሚሰጥ ሌላ ማብራርያ አናገኝም።

በመሆኑም ይህ የፊልጵስዮስ መዝሙር በይዘቱ በጥንት ክርስትያኖች ዘንድ የታወቀ በመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መዝሙሩ ማብራራት ሳይጠበቅበት በቀጥታ በጽሑፉ ውስጥ እንዳካተተው ይታመናል። በመሆኑም የዚህ የፊልጵስዮስ መዝሙር ከባዕድ ትርክት ጋር ያልተቀየጠ ይልቁንም በጥንት ክርስትያኖች ዘንድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የታመነ ከቅዱስ ጳውሎስ ስብከተ ወንጌል እና መዝሙሩ ከሚገኝበት ከፊልጵስዮስ መልእክት አስቀድሞ በቤተ ክርስትያን መካከል ይዘመር የነበረ መዝሙር ነው።

በ ፊል 2፡8 መዝጊያ ላይ “ለመስቀል ሞት” እንኳን ታዛዥ ሆነ የሚለው ሐሳብ በመዝሙሩ ዋና ቅጂ ውስጥ የማይገኝ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ መዝሙሩን በፊልጵስዮስ መልእክት ውስጥ ባካተተበት ወቅት እንደጨመረው ይታመናል፤ የጌታ መስቀል ለቅዱስ ጳውሎስ ነገረ መለኮታዊ እሳቤ እና ዕይታ የተለመደ ነገረ መለኮታዊ መረዳት ነው። በዚህም የመዝሙሩ የመጀመርያው ክፍል በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ይደመድማል፤ በመሆኑም በሕማሙ፣ በሞቱ፣ እና በትንሳኤው በኩል ወደ ክብሩ ዙፋን ከፍ ከፍ እንዳለ ለሚናገረው ለሁለተኛው የመዝሙሩ ክፍል ጥሩ መንደርደርያ እና ማሰርያ ያገኛል።

የፊልጵስዮስ መዝሙር በመሰረቱ በጥንት ክርስትያኖች ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የአምልኮ ኃይል በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር አብ የቀረበ ምሥጋና ነው፤ በመሆኑም መዝሙሩ ከሁሉ አስቀድሞ በዚህ ተቀዳሚ ዐውድ ውስጥ ሆኖ ሊታይ ይገባዋል። ይህም ማለት መዝሙሩ ነገረ መለኮታዊ ማብራርያ ወይም ነገረ ክርስቶሳዊ ጥናት የሚቀርብበት ሳይንሳዊ ግብዓት አይደለም። ይልቁንም በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ ለኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበ ሥርዐተ አምልኳዊ ውዳሴ ነው። ይህ ለኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበ የጥንታዊቷ ቤተ ክርስትያን ውዳሴ በውስጡ እጅግ በርካታ ነገረ መለኮታዊ ቁም ነገሮችን የያዘ በመሆኑ እነዚህን ቁም ነገሮች ማየቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ባለ ረቂቅ ጥበብ ስለ ክርስቶስ እንደሚመሰክር ለማስተዋል ዕድል ይሰጠናል። በመሆኑም በክፍል ሦስት ጽሑፋችን የዚህን መዝሙር ነገረ መለኮታዊ እና ነገረ ክርስቶሳዊ ቁም ነገሮች እንዳሣለን።

ይቀጥላል

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት