እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ፍቅር (ክፍል ፩)

R

ፍቅር (1ቆሮ 13)

መለኮታዊ ፍቅር የእግዚአብሔር የጸጋ ሥጦታ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ” (1ዮሐ 4፡7)  እያለ ስለ ፍቅር ይመሰክራል። የእግዚአብሔር ፍቅር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር በኩል ራሱን ለእኛ አሳልፎ ሰጥቷል፤ ይህንን መለኮታዊ ፍቅር ከመስቀሉ ላይ ተቀብለን በዚህ አይነት ራስን አሳልፎ የመስጠት ፍቅር ሌሎችን እንወድበት ዘንድ በሁሉ ፊት ግልጽ ሆኖ የሚታይ የተሰቀለ ምሳሌ አለን። እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ በእርሱ ፍጹም ሐሳብ እያንዳንዳችንን በሚያውቅበት የክብር ፍጻሜ ማንነታችን ውስጥ በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በልባችን ያፈሰሰው ፍቅር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በጦር በተከፈተ ልብ ውስጥ ተገልጦ ታይቷል። በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በታጠበ ንጹህ ልጅነት የእግዚአብሔር አብ ልጅ ሆኖ መንፈሱን በሰውነቱ የሚጠብቅ ቤተ መቅደስ ለመሆን በውኃ እና በመንፈስ ቅዱስ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን የተወለደ ሁሉ በዚህ የፍቅር ሥጦታ አማካይነት ማፍቀር እና ፍቅርን መቀበል የሚችል ወደ ክርስቶስ ምልዓት የሚያድግ ዘር ሆኗል። ነገር ግን ለዚህ መልዕልተ ባሕርያዊ ፍቅር ራሳችንን መክፈት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ መልዕተ ባሕርያዊ ፍቅር ምንድነው? ይህ መለኮታዊ ፍቅር ልባችንን የሚለውጠው እንዴት ነው? የፍቅር ተስፋ በምርኮ በተያዘባቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ መለኮታዊ ፍቅር እንደ አዲስ ይቀጣጠል ዘንድ በምን መልኩ ልንደግፋቸው እንችላለን?

መለኮታዊ ፍቅር ለሰው ልጅ ባሕርያዊ ከሆነው ፍቅር ከፍ ያለ መልዕልተ ባሕርያዊ የእግዚአብሔር መገለጥ ቋንቋ ነው። ይህ የመለኮታዊ ፍቅር ቋንቋ እግዚአብሔር አምላክ ፊቱን ወደ እኛ የመለሰበት እና ወደ እኛ  ዘንበል ብሎ ከእኛ ጋር በመረዳታችን ልክ፣ ውሱንነታችንን በሚያከብር ቋንቋ እና ምሳሌ አስቀድሞ በእምነት አባቶታችን በነብያት በኩል ከእኛ ጋር የተነጋገረበት “ቃል”፣ ጊዜው በደረሰ ጊዜ እንቀበለው ዘንድ ለፍጥረታችን በሚስማማ፣ ሰውነታችንን በሚያከብር እና በሚቀድስ መገለጥ እያንዳንዳችንን ከዘላለም ጀምሮ እጹብ ድንቅ አድርጎ በፈጠረብት “ቃል” በአንድ ልጁ ቤጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ ለብሶ፣ ጸጋን እና እውነትን ተሞልቶ በመካከላችን ተገልጧል።

የግሪክ ቋንቋ ስለ ፍቅር ሲጽፍ የሚጠቀምባቸው በርካታ ስሞች ያሉት ሲሆን አዲስ ኪዳን ስለ ፍቅር ሲናገር በስፋት የሚጠቀመው ቃል αγάπη አጋፔ የሚለው ነው። ይህ አጋፔ የሚለው ቃል ነጻ ፈቃድን የሚመለከት፣ በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ ያልተመሰረተ፣ ሳይሰፍር የሚሰጥ፣ ከነጻነት የሚመነጭ ሥጦታ ነው። በዚህም ፍቅር የሚገባውን ሰጥቶ አይረካም፤ ይልቁንም እርሱ ራሱ በነፍሱ ከፈሰሰው በላይ ደግሞ በሌላው ላይ ያለ መጠን ከጸጋ ሥጦታ ያካፍላል። ጌታ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እያለ ሲናገር አዲስ ኪዳን የሚጠቀመው ቃል ይኸው αγάπη አጋፔ የሚለው ቃል ሲሆን ይህም ጠላትን መውደድ ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን እንደማይመለስልን እያወቅን ዋጋችንን በሰማያት መዝገብ ላይ ለመጻፍ ለእግዚአብሔር ፈቅደን የምናበድረው ገንዘብ ሙሆኑን ማሳያ ነው።

αγάπη አጋፔ የልብ ቅንነት ያለበት ለመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ስፍራ ያለው በጎ ፈቃድ ነው። αγάπη አጋፔ ስሜት ላይ ያተኮረ እና በስሜት የሚዘወር ቁም ነገር ሳይሆን ከመስቀል ሥር የሚነሳ ወደ መስቀል ምሥጢር እያደገ የሚሄድ መሥዋዕትነትን እና ራስን አሳልፎ መስጠትን  በራስ ላይ እንደሚሳል የክርስቶስ ኢየሱስ የጸጋ ሙላት መልክ የሚቀበል፣ መመዘኛዎቹን ሁሉ በጌታ ኢየሱስ ሕማም፣ ሞት እና ትንሳኤ ላይ ያደረገ ምሥጢር ነው። αγάπη አጋፔ ከእግዚአብሔር የጸጋ በጎነት በነጻ የተቀበልነው፣ ከዚህም የተነሳ በእግዚአብሔር ፊት ባላጸጋ የሚያደርገን የልብ ኃብት እና የነፍስ ጌጥ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር በምሥጋና የሚመለስ የፍቅር ልውውጥ ነው።

 

ነገር ግን እናፈቅራለን ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ አስቀድመን የፍቅርን አጠቃላይ ግንዛቤ መመልከት ያስፈልገናል። ሰዎች ፍቅርን በተለያዩ መንገዶች ይረዱታል፤ ነገር ግን ስለ ፍቅር ስናወራ እግዚአብሔር በጸጋው ኃይል በውስጣችን ስለሚያንቀሳቅሰው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ማለትም እግዚአብሔር ማፍቀራችንን ስለሚገራበት እና መልክ ስለሚሰጥበት እንቅስቃሴ እየተነጋገርን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ዛሬ በአብዛኛው ሰፍኖ የሚገኘው የብዙኅን ግንዛቤ ፍቅርን በአንድ በኩል ከተለያዩ የሕይወት ልምዶች እና ከስሜት ጋር ብቻ አያይዞ የሚመለከት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ፍቅር የሌላውን ሰው ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ ድርጊት ተደርጎ ይወሰዳል፤ ከዚህም ባሻገር በሦስተኛ ደረጃ ከመጀመርያው በተቃራኒ ስለተወደደው ሰው ሲባል ነገሮችን መተው፣ ከተወሰኑ የሕይወት ልምዶች መታቀብ እና ከተወሰኑ ስሜቶች መከልከል እንደ ፍቅር ተደርጎ ይወሰዳል። በርግጥ እነዚህ ሦስቱም ቁም ነገሮች ከፍቅር ባሕርይ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን በእነዚህ ውስጥ የፍቅርን ምንነት ማየት እንችላለን ወይ? የሚለው ጥያቄ ልናስብበት የሚገባ መሰረታዊ ቁም ነገር ነው። በዚህ ጥናታችን ውስጥ የምናስብበት ገዢ ሐሳብ ይህ የፍቅር “ምንነትን” የሚጠይቀው አስተውሎት ነው።

  1. ፍቅር በሕይወት ጣዕም የሚለካ ቁም ነገር ተደርጎ ይታያል።

ማፍቀር ከተለያዩ የሰው ልጅ ፍላጎቶች እና ስሜቶች ጋር ብቻ ተያይዞ ትርጓሜው በዚሁ ዐውድ ውስጥ እየታየ ከደስታ፣ ከእርካታ፣ ከስኬት፣ ቅጽበታዊ ከሆነ ፍላጎት እና እርካታ ጋር ተመሳስሎ ይተረጎማል። በዚህም የፍቅር ትርጓሜ የፍቅር ተልዕኮ በዚህ የሕይወት ልምድ ውስጥ እያለፉ የሚገኙትን ሰዎች ደስተኛ ማድረግ ነው፤ ከጥልቅ፣ መሰረታዊ እና ዘላቂ የሕይወት መርሐ ግብሮች ይልቅ የሕልም ዓለም የሚወደድበት፣ ቅጽበታዊነት እና ሕይወትን አልጋ በአልጋ አድርጎ የሚመለከት፣ ከኃላፊነት ይልቅ ደስታን የሚያስቀድም የኑሮ ዘይቤ ገዢ ሐሳብ ሆኖ ይሰፍናል። የግሪኩ αγάπη አጋፔ የሚለው የፍቅር ግንዛቤ ይህንን አይነቱን ግንኙነት ፍቅር ብሎ አይጠራውም። ፍቅር የግዴታ ከቅጽበታዊ ደስታ፣ ከእርካታ፣ ከታይታ ጋር መቆራኘት አይጠበቅበትም፤ ፍቅር ስሜት ሳይሆን የሕይወት መንገድ ምርጫ እና ውሳኔ ነው። ፍቅር ልክ እንደ መንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ የሚኖ‘ር፣ እያደገ የሚሄድ፣ የሚነጻ፣ በእውነት እና በጽድቅ እየተገረዘ የሚጠራ ሂደት ነው እንጂ በአንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት የክብር ደመና ምልዓት አይደለም። እግዚአብሔር በእውነት እና በመንፈስ ወደሚገለጥ እምነት ሲመራን መንፈስ ቅዱስ ዕለት ተዕለት በነፍሳችን ውስጥ በሚያደርገው ስብዕናችንን በሚያከብር እና የብስለት ደረጃችንን በሚያገናዝብ መልኩ እንደመሆኑ መጠን የፍቅር ጉዞ እንዲሁ ነው። ትልልቅ መንፈሳዊ መገለጦችን በሕይወታችን ነባራዊ እውነታ ውስጥ ተገልጠው አለመመልከታችን የእግዚአብሔርን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንደማይጥለው እንዲሁ የስሜት ጡዘት አለመኖር የፍቅርን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ሊጥለው አይገባም።

  1. ፍቅር በድርጊቶች የተሞላ ቁም ነገር ነው።

ፍቅር ማለት በዘላቂ ለውጥ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በሚተርፍ ተግባር መመላለስ ነው። በዚህ አይነት ፍቅር ለሥራ የሚያነሳሳን እና መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ጥበብ ለሌሎች ደግሞ እንኖር ዘንድ የምንበረታበት ተስፋ ነው። የሚያፈቅር ሰው ሥራ ፈት የሚሆንበት ጊዜ የለውም፤ ፍቅር የሙሉ ጊዜ ሥራ እንደመሆኑ መጠን ሥራ ፈትነት የፍቅር ጠላት ነው። ነገር ግን ይህ ራስን አሳልፎ የመስጠት እና የመሥዋዕትነት ሕይወት ለራስ ስም እና ዝና የሚደረግ ሥውር ራስን የማምለክ ኃጢአት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሌሎች ሰዎች መልካም ሥራ መሥራቴን የማሳይባቸው መገልገያዎች እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እና የተከፈለላቸውን የመዳን ደም ዋጋ በራሴ ሚዛን እንዳልመዝን ኢየሱስ የከፈለላቸውን ዋጋ ዘወትር የተግባሬ ሁሉ መሪ እና ሚዛን ማድረግ ይገባኛል።

  1. ፍቅር ራስን መካድ ይጠይቃል።

ይህ ከመጀመሪያው መረዳት ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ነው። እዚህ ላይ ከፍላጎታችን እና ከሌሎች ሰዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ከሚሰጠን ደስታ ሩቅ መሆንን የሚጠቀልል ቁም ነገር ነው። በመሆኑም በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደርግ ሰዎችን በሚሰጡት ጥቅም እና በሚያስገኙለት እርካታ ሳይመዝን ሰው ሆነው በመፈጥራቸው ቁም ነገር ብቻ ተመስርቶ  ለማፍቀር የሚደረግ ጥረት የሚታይበት ዐውድ ነው። በዚህ ውስጥ ከማንም ጋር የተለየ የሚባል ወዳጅነት የሌለበት ሕይወት ሲሆን ራስንም ቢሆን በጤናማ ደረጃ ብቻ ለመውደድ የሚሞክር የፍቅር ግንዛቤ ነው።  ይህ አይነቱ የፍቅር ግንዛቤ ላይ ላዩን ሲታይ መንፈሳዊ ይምሰል እንጂ በጥልቅ ፍርሃት የተሞላ ጤናማ ያልሆነ ግለወጥነት የሚዘውረው ስሜት ነው። በመሆኑም ከእግዚአብሔር ጋር ባለው የግል ግንኙነት ላይ በእጅጉ የሚያተኩር የሚመስል፣ ነገር ግን ውጫዊ እና ዓለማዊ ሆነው የሚታዩትን ገጽታዎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚሸሽ በመሆኑ ለሌሎች ፍላጎቶች ደንታ ቢስ የሚሆን የፍቅር ዝንባሌ ነው። ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን በቀጣይ በተከታታይ በሚወጡት ጽሑፎች የበለጠ እነዚህን ሐሳቦች እያሳደግን አብረን እንጓዛለን።

 

ሴሞ

ተመሳሳይ ርእሶች

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት